Saturday, August 31, 2013

የኛ ነገር፡ ከኔ ማዕዘን፡- በብርሀኑ ተበሳጨሁ፤ በሰማያዊ ተጽናናሁ፡ በአንድነት ደግሞ ተስፋ አደረግሁ (ከተ/ሚካኤል አበበ)

የኛ ነገር፡ ከኔ ማዕዘን፡ ክፍል 13
በብርሀኑ ተበሳጨሁ፤ በሰማያዊ ተጽናናሁ፡ በአንድነት ደግሞ ተስፋ አደረግሁ

ከተክለ ሚካኤል አበበ

1-      ይህ ጽሁፍ ዓላማው አድናቆት፡ ትችትና ግብዣ ነው። የአንድነት ምሽት በቶሮንቶ ግብዣ። ከአድናቆትና ከግብዣው በፊት ስለፖለቲካ መሪዎችና ስለፖለቲካ ተንታኞች አትቶ፤ የብርሀኑ ነጋን (ዲባቶ) አቀራረብ ይተቻል። የሰማያዊ ፓርቲን ርምጃ ያደንቃል። የአንድነት ዘመቻን ስለማገዝ ያሳስባል። እንደው ተገጣጥሞ ነው እንጂ፤ አንዱን ለማሞገስ ሌላው መኮሰስም መከሰስም የለበትም። ግን አንዳንዴ ደግሞ፤ በጊዜ ያልተተቸ፤ ይለመዳል። አጉል ልማድ ይሆናል። ሁሉንም ለያይቶ ለመጻፍ ደግሞ፤ ጊዜ የለም። ስለዚህ ባንድ ወንጭፍ ሶስት ወፍ ነው ለመማረክ የምጥረው። ከሀተታ ልጀምር።
የፖለቲካ ተንታኝና የፖለቲካ መሪ
2-      የፖለቲካ መሪ ከፖለቲካ ተንታኝ መለየት አለበት። የፖለቲካ መሪ የፖለቲካ ተንታኝ ሲሆን፤ የጋዜጠኞችንና የፖለቲካ ተንታኞችን/የምሁራንን ስራ ይጋፋል። ያ ብቻም አይደለም። መምራት አቅቶት፤ ወይም መምራት ጠፍቶት፡ በአካልና በስም የፖለቲካ መሪነቱን ወንበር ተቆናጦ፤ በግብር ግን የፖለቲካ ተንታኝነትን ቦታ ይዞ፤ የፖለቲካ መሪነትን ስራ በፖለቲካ ትንታኔ ሊያካክስ ይሞክራል። ያም ብቻ አይደለም፡ የፖለቲካ መሪነት ሚናን ከፖለቲካ ተንታኝ ጋር ያደባለቀ መሪ፤ የያዘውን የፖለቲካ መሪነት ሀላፊነት ከተንታኝነት ሲለሚቀይጠው፤ ትንታኔው ንጹህ አይሆንም። ስለዚህ የፖለቲካ ትንታኔውን መቀበል ይከብዳል። ባይከብድም ትንታኔው ጎዶሎና ወደሁዋላ የሚጎትት፤ ወይንም ወደፊት የማያራምድ ይሆናል። ወይም ትንታኔው ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የሚደረግ ጥልቅ ያልሆነ ትንታኔ ይሆናል።
3-      ለምሳሌ ብርሀኑ ነጋ ባለፈው የኢሳት ስብሰባ ላይ ያቀረበውን የንግግሩን ገጽ 16 መጨረሻና ገጽ 17 መጀመሪያ ብንመለከት ሀሳቡ ጥልቅ ወይም ሀቀኛ አለመሆኑን በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል። http://www.zehabesha.com/amharic/archives/6563 ለዚህም ነው ምሁር ፖለቲከኛ መሆንን ከመረጠ፤ ምሁርነቱን ቀንሶ መሪነቱን እንዲያጠብቅ ግድ ነው የምንለው። ኦባማን ውሰዱ። ኦባማ ሲመረጥ ምሁር ነበር። ከአራት አመት በሁዋላ ግን ምሁርነቱ እየቀነሰ፤ ወደቡሽነት እየተጠጋ መጥቷል። የኦባማ የሶሪያ አቋም፤ ከቡሽ የኢራቅ አቋም ብዙ አይለይም። አሳድን እንበለው ወይም እንብላው እያለ ነው። ኢሳት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ብርሀኑ ነጋ (ዲባቶ) ያንን መለየት ነው የተሳነው። በፖለቲካ መሪነት መጥቶ (በግንቦት ሰባት ሊቀመንበርነት) የፖለቲካ መሪነቱን ግን ትቶ፤ ምሁር ለመሆን ሞከረ። ተንታኝ። የፖለቲካ ተንታኝ በመሆን የጋዜጠኞችንና የምሁራንን ስራ መሻማት ብቻ ሳይሆን፤ ሁለቱንም ሳይሆን ቀረ። በዚህ ረገድ ጃዋር ይሻላል። እንደተንታኝ በደንብ ይተነትን ነበር። የተንታኝነቱን ሚና ትቶ ባለፈው ሰሞን የራሱን የፖለቲካ አቋም ሲያንጸባርቅም፤ ብዙ ሰዎችን ቢያበሳጭም፤ እቅጩን ነው ያስቀመጠው። ብሬ አድበሰበሰው። በእስር ላይ የሚገኙትም ይሁኑ በነሱ የተተኩትን ከነሱም የቀደሙትን ሙስሊሞች አካሄድና እንቅስቃሴ የሚጠራጠሩ ካሉ፤ ጥርጣሬያቸው በወያኔ ፕሮፓጋንዳ ነው የተፈጠረው ለማለት ይከብዳል። በወያኔ ፕሮፓጋንዳ የማይበገሩም ከተጠራጣሪዎቹ ተርታ ውስጥ አሉበትና።
4-      የዲባቶ ብርሀኑ ነጋ ያልጠራ ትንታኔ የመነጨው፤ ፖለቲካዊ መሪ መሆንና ፖለቲካዊ ምሁር/ተንታኝ መሆንን አጣምሮ ለመሄድ ከመሞከር ነው። የፖለቲካ ተንታኝ የምለው፤ በፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ በአድራጊ-ፈጣሪነት ሳይሳተፍ ወይም መሳተፍ ሳይጠበቅበት፤ የአንድን ፖለቲካዊ ስብስብ/ማህበረሰብእ ፖለቲካዊ ሁኔታ እየቃኝ፤ ከአካባቢያዊና አለማቀፋዊ ሁነቶች ጋር እያጣቀሰ፡ የሁነቶቹን ምክንያት የሚያብራራ፤ ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችን የሚጠቁም፤ አደጋዎችን የሚተነብይ፡ ተመልካችና ተናጋሪ ማለት ነው። የፖለቲካ መሪ የፖለቲካ ተንታኝ ሲሆን፤ አደናጋሪ ነው የሚሆነው። የፖለቲካ መሪዎች የፖለቲካ ተንታኝ መሆን የለባቸውም እያልኩ አይደለም። እኔ የምለው፤ አንደኛ ፖለቲካ መሪዎች የፖለቲካ ትንታኔ ችሎታቸው የሚገለጸው በፖለቲካዊ አመራራቸው በሚወስዱት ፖለቲካዊ እርምጃ ውስጥ መሆን አለበት ነው። ሁለተኛ፡ ፖለቲካን መተንተን የፖለቲካ መሪዎች ዋና የአደባባይ ስራ መሆን የለበትም ነው። እዚያው ድርጅታቸው ውስጥ እንደፍጥርጥራቸው። ይፋዊ ፖለቲካዊ ስራቸው ግን፤ መምራት እንጂ መተንተን አይደለም። አቶ መለስ ከሞቱ በሁዋላ ብቻ ያለውን ሁኔታ እንኳን ብንለመከት ግን፤ የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ብርሀኑ ነጋ፤ ከሲሳይ አጌና ጋር ያደረጋቸውን ቃለምልልሶች ወይንም ያለፈው ሰሞንን የኢሳት መድረክ ጨምሮ፤ በቀረበባቸው መድረኮች ላይ የሚናገራቸወን ስንለመከት አድራጊ የፖለቲካ መሪ ሳይሆን፤ ተንታኝ ጋዜጠኛ ወይንም እዚህ አገር እንደሚሉት ጠቢብ ምስክር ለመሆን ነው የጣረው።
5-      ያ ብቻም አይደለም፤ አሁን በእመ-ብርሀን፤ ሰላሳ ድርጅቶች የኢትዮጵያን እጣፈንታ ከህዝብ ጋር ሊመክሩ በተሰበሰቡበት መድረክ ላይ ለመነሻ የሚሆን የአስር ደቂቃ ንግግር አድርጎ የተቀረውን ሰዓት ለህዝብ ውይይት መተው እንጂ፤ የ55 ደቂቃ ድርሳን ማንበብ ምን የሚፈይደው ነገር አለ? ብርሀኑ ነጋ ባለፉት ሶስት ወራት በኢሳትም ይሁን በተለያዩ መድረኮች ያገኘውን እድልና ሰዓት ስንመለከተው ደግሞ የንግግሩ መርዘም ስህተትነትና አበሳጭነት ይጎላል። ያ ብቻም አይደለም፤ ሶስት ሺህ ምናምን አመት፤ መጀመሪያ በጸሀዩም በጨረቃውም በማምለክ፤ ከዚያ ብሉይን በመቀበል፤ ከዚያ ክርስትናን፤ ከዚያ እስልምናን፤ ከዚያ ካቶሊክን፤ ከዚያ ፕሮቴስታነንስዝምን፤ በመቀበልና በማቻቻል ለኖረች አገር፤ የሊበራሊዝምና ዴሞክራሲ መፍትሄ ለሀይማኖት ነጻነት የሚል የአንድ ሰዓት ስብከት ያስፈልጋታል? ቢቀርብንስ?
6-      በዚህ ኢሳት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ፤ ግንቦት ሰባትን ወክሎ ንግግር ካቀረበው ብርሀኑ ነጋ ይልቅ፤ የሽግግር ምክርቤቱ እጥር ምጥን ባለች ባለአራት ገጽ ወረቀቱ፤ የተሻሉ የሽግግር ሀሳቦችን አቅርቧል። http://etntc.org/ENTC/wp/wp-content/uploads/ESAT-Presentation-0818.pdf። እነሱ የሚመኟት ኢትዮጵያ ምን መምሰል እንዳለበት፤ ሽግግሩ ምን እንደሚመስል፤ የሽግግር ሰነድ የሚያረቅ ኮሚቴ ስለማዋቀራቸው፤ አለማቀፍና አገርአቀፍ የእምቢተኝነት ቡድን ስለማቋቀም፤ ድርጅታቸው ምን እየሰራ እንደሆነ ተናግሯል። ከሽግግር ምክርቤቱ አራት አመት ቀደም ብሎ የተቋቋመው ግንቦት ሰባት ግን ጥምረት ከተቋቋመ ከሶስት አመት በሁዋላ፤ የከማል ገልቹ ኦነግ ከተመለሰ ከሁለት አመት በሁዋላ፤ ገና ስለድርጅቶች አንድነት፤ በጋራ ትግል ወያኔን ስለማስወገድ አጣዳፊነት ይሰብካል። የዛሬ አመት፡ የዛሬ ሁለት አመት፡ የዛሬ ሶስት አመት ከነበርንበት ብዙም ፈቀቅ አላልንም።
7-      ኢሳት ይሄንን ስብሰባ ማዘጋጀቱ ይደነቃል። ይሁን እንጂ፤ የኢሳት አስተዳዳር የሆነው ወዳጄ ነአምን ዘለቀ የዛሬ አመት አካባቢ እንዲህ ያለው ተመሳሳይ ስብሰባ ሲዘጋጅ፤ (ያኔ ስብሰባው የተዘጋጀው በኢሳት ሳይሆን በግንቦት ሰባትና በነኑሮ ደደፎ (ዲባቶ)/ከማል ገልቹ ኦነግ ነበር)፤ እባክህን መሪዎቹ ንግግር ያሳጥሩና ለሰዉ እንዲተነፍስ ግዜ ይስጡት ብዬ አሳስቤው ነበር። ነአምን አንዳንዴ አይሰማም። ወይም ቢሰማም አያደምጥም። እነሆ፤ ባመቱ፤ ሌላ ውድ መድረክ ባከነ። የብርሀኑ ነጋ ጽሁፍ፤ የመጀመሪያው አስራሶስት ገጽ ለዚያ መድረክ አስፈላጊ አልነበረም። ነገር መቁረጥና ማሰጠር፤ እንዲሁም መድረክ ላይና ምድር ላይ የምናቀርበውን መምረጥ አለብን። ያለበለዚያ ትክክለኛና ውጤታማ ሚናችንን መለየት አለብን።
ተስፋ፡ አድናቆትና፤ ግብዣ
8-      መቼም ተቃጥላችሁ አትሙቱ ያለን ፈጣሪ መጽናኛ አያሳጣንም፤ በግንቦት ሰባት ሊቀመንበር አቀራረብ ብንበሳችም፤ አላህ የሚያጽናናን አላሳጣንም። የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ እኛ በምናደርገው ነገር ምንም ቀስቀስ በማይልበት፤ ፖለቲካዊ አየሩ ጸጥ ረጭ ባለበት ሁኔታ ነው፤ የዛሬ ሶስት ወር አካባቢ፤ ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ የተሳካ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ አደረገ። ላለፉት ስምንት አመታት ሰልፍ አይታ ለማታውቀው አዲስ አበባ ሀያ መቶም የሁን ሀያ ሺህ ሰው ያስወጣ ሰልፍ ተከሰተ። ያ ያጽናናል። እነሆ ያኔ በያዙት ቀጠሮ መሰረት፤ ሁለተኛው የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ በመጪው እሁድ ይቀጥላል። መቼም ብዙዎቻችን ፈሪዎችና ሸሺዎች በሆንበት ሁኔታ፤ ጥቂት ዠግኖች አልጠፉምና፤ የሰማያዊ ፓርቲዎች ድፍረትና ቁርጠኝነት የሚያስደንቅ ነው። የህወሀት ኢህአዴግ መንግስት ባለስልጣናት፤ በአዲስ አበባ መስተዳድር በኩል ሰልፉ ህገወጥ ነው ቢሉም፤ የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች ግን ሰልፉ ህጋዊ ነው፤ እንገፋበታለንም እያሉ ነው። የመጪው እሁድ ትልቅ ተጋድሎ ዋዜማ ላይ ነን።
9-      እንዲህ ያለውን ትእይነት ቆሞ መመልከት ብቻ ግን ነውር ነው። መቼም አንዴ ሸሸተን ወጥተናል፤ በወጣንበትም ቢሆን ግን፤ የምንችለውን እንኳን በማድረግ ተዋናይ መሆንም አለብን። የኛ የተቀናቃኙ/ተፎካካሪው/ተቃዋሚው ጎራ፤ በተለይ በውጪ የምንኖረው ተቃዋሚዎች ትልቁ ችግር፤ ማድረግ የምንችለውን እንኳን ማድረግ አለመቻላችን ነው። በሰላማዊም ይሁን ደማዊ መንገድ፤ በአመጽም ይሁን በጸሎት ለሚታገሉት ስንቅና ትጥቅ ማቀበል። ስንቅና ትጥቅ ላለማቀበል ብዙ ምክንያት መደርደር ይቻላል። ምንም ምክንያት ግን አጥጋቢ አይሆንም። ቅዳሜና እሁድ የዱለትና የቁርጥ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን ጉዳይ እያብራራ የሚተነትነው፤ የምእራባዊያንን ሴራ የሚመሰጥረው ወዳጄ፤ የኢሳት ዝግጅትን የ20 ብር ትኬት ስሰጠው ፊቱን እንዳጨፈገገው መሆን የለብንም። ለሰማያዊ ፓርቲ ሁለተኛ ሰልፍ መሳካት እንጸልያለን። በጸሎት ብቻ አናበቃም። በግብርም እንከተላለን።
10-   መቼም በየከተማው ብዙ የማይደክማቸው ሰዎች አሉ። እነሆ በመጪው ቅዳሜ ማታ፤ በዚህ በኛ ከተማ ትንሽ ተንፈስ እንላለን። ተሰብስበን ኢህአዴግን ከመዘልዘል ባሻገር፡ የትግሉ በረከት እንጥፍጣፊ ይደርሰን ዘንድ የአንድነት ምሽት ያዘጋጁ አሉ። “የአእላፋት ድምጽ ለነጻነት” የተሰኘውን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ዘመቻ በመደገፍ እዚህ ቶሮንቶ ከተማ፤ እንደፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር፤ ቅዳሜ ኦገስት 31 ማታ ከ6ሰኣት ጀምሮ’፤ 2050 ዳንፎርዝ ጎዳና በሂሩት ሬስቶራንት የቤተሰብ አዳራሽ የእራት ምሽት ተዘጋጅቷል። በሰሀን $ 50 ብቻ። ለጥንዶች $ 60። ለኔቢጤው ደሀ ደግሞ $ 30 ብቻ። ገቢው፤ ከወጪ ምላሽ ለአንድነት ፓርቲ የሚሄድ ነው።
11-   እነሆ፤ በአካል ከግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሀይል ጋር ላንዘምት እንችላለን። በአካል ከሰማያዊ ፓርቲም ጋር አንሰለፍ ይሆናል። ከአንድነት የነጻነት ድምጾች ጋር ለመጮህ ግን አይሳነንም።ለሚጮሁት ጉልበት፤ ለሚሰለፉት ብርታት፤ ለሚዘምቱትም ጽናት ልንለግስ እንችላለን። በያለንበት አካባቢ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች እንርዳ። እዚህ ቶሮንቶ ያለን፤ ቅዳሜ ሂሩት ሬስቶራንት ብቅ እንበል። ቅዳሜ እንኩዋን፤ ላሊበላና ብሉናይል፤ ዞብልና ራንዴቩ ይቅሩብን። ቅዳሜ ማታ፤ ሂሩት ጋር እንገናኝ።
እኛው ነን። ከቶሮንቶ። ነሀሴ፡ 2005/2013።

No comments:

Post a Comment