ነሃሴ 18 ቀን 2005
ሰሞኑን
ከኢትዮጵያ ህዝብ ጆሮ የገባው የሰማያዊ ፓርቲና የ‘33ቱ’ ፓርቲዎች የውዝግብ ዜና የተስፋ ጭላንጭል የተፈጠረለትን
የዋህ ህዝብ እጅግ ቅር ያሰኘና ያሳዘነ እንደሆነ ከራሳችን የተጎዳ ስሜት በመነሳት ስለተረዳን፤ ‘የተቃዋሚ
ድርጅቶቻችን ይማሩበት ዘንድ’ በሚል የየዋህ መንገድ ይህችን ኣጭር መልዕክት ለማስተላለፍ ተገደድን።
በሃገራችን
የፖለቲካ ታሪክ ድርጅቶች በሰለጠነ መንገድ ልዩነታቸውን በውይይት መፍታት ሲችሉ አልያም በልዩነታቸው ተቻችለው
ሲጓዙ ሰምተን አናውቅም። ተቃዋሚ ድርጅቶቻችን በጋራ ለነፃነት ከመታገል ይልቅ እርስ በእርስ ከመናቆር ጀምሮ
እስከመጠላለፍ ሲደርሱ ማየት የተለመደ ሆኗል። ይህ የድርጅቶች የእርስ በእርስ ግጭት የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነትና
ፍትህን እየናፈቀ እንዲኖርና ገዢዎች በማናለብኝነት ያሻቸውን እየፈጸሙ፤ ህዝብም ሰባዊነቱን ተገፎ፣ አንገቱን ደፍቶ፣
እንዲኖር ከማድረግ ሌላ ምንም ፋይዳ እንዳላስገኘ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያውቃል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘው
ድርጅቶች መጠላለፉን ትተው በጋራ የሚሰሩበትንና በመቻቻል የሚኖሩበትን ጊዜ ብቻ ነው። እዚህ ላይ ተቃዋሚ
ድርጅቶቻችን ሊረዱት የሚገባው፤ እነርሱ እርስ በእርስ ሲጠላለፉ፤ ስንቱ ንጹህ ዜጋ በማያውቀው ሃጥያት በዘረኛው
የወያኔ መንግስት እየተደበደበ፣ እየተገደለ፣ እየተሳቀቀ፣ በገዛ ሃገሩ እያለው እንደሌለው በረሃብና በእርዛት እያለቀ
እንደሚገኝ፣ ሳይወድ በግዱ በቁጭት ባዶ ተስፋን እያለመ እንደሚኖር ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን
በምናያቸው የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች በሚያደርጉት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ያልተደሰተ ፍትህ ናፋቂ ኢትዮጵያዊ
ይኖራል ብለን መገመት እጅግ ከባድ ነው። እኛም እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ስንመኘው ለነበረው የትግል አቅጣጫን
ስላመላከተን በቅርበት ከመከታተል ጀምሮ እስከ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን የምንችለውን ሁሉ ልናበረክት ቃል በመግባት
እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። ይህ የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በዚሁ ከቀጠለ የምንናፍቀውን ዲሞክራሲ፣
የምንመኘውን ነፃነትና፣ የምናልመውን የህዝብ የበላይነት ከማየት የሚያግደን አንዳችም ምክንያት አይኖርም። ስለሆነም
ድርጅቶቻችን ሊወደሱና ተግባራቸውም እሰየሁ ሊባልና ሊበረታታ ይገባል እንላለን።
ምንም እንኳን እያንዳንዱ
የፖለቲካ ድርጅት በትግሉ ዙሪያ መሳተፍ የራሱ የሆነ አስተዋፅዎ ቢኖረውም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሌላውን ለመጥለፍና
ትግሉን ለማሰናከል ቅርብ የሆኑ ተቃዋሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልፅ ነው። አበው እንዳሉት “እውነቱን ተናግሮ
የመሸበት ማደር” ይበጃልና፣ ህገመንግስቱ የሚፈቅድለትን መብት በመጠቀም በዘረኛው የወያኔ መንግስት የተጫነብንን
አመታት ያስቆጠረውን የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ እገዳን በመስበር ፍርሃታችንን መሰባበር የቻለውን የሰማያዊ ፓርቲ
አመራርና አባላትን ልናመሰግን እንወዳለን። በዚህ ኣጋጣሚ ለሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባላት ነፃነት በትግል እንጂ
በልመና አይገኝምና በርቱ እያልን፤ ለሌሎች የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን የዲሞክራሲን የመናገርና የመፃፍ ነፃነት
ምን ማለት እንደሆነና እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው ቀድመው ማወቅ ይገባቸዋል ብለን እናምናለን።ይህ ካልሆነ ግን
የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ ስርዓት ለይቶ እንደማያያቸው እናምናለን። የኢትዮጵያ ህዝብ እውነትን የመለየት ችሎታውም፣
ብቃቱም፣ ልምዱም እንዳለው ሁላችንም ልንረዳ ይገባል። ስለሆነም ተቃዋሚ ድርጅቶቻችን የዲሞክራሲን ምንነት ለማወቅና ስ
ህተታቸውን ለማስተካከል ቢሞክሩ እጅግ የተሻለ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሌላ ዲክታተር የሚያስተናግድበት ጫንቃና
ጀርባ ከእንግዲህ የለውም።ስለዚህ ከምቾትና ከፍርሃት ዞናቸው በመውጣትና በመተባበር ህዝብ ለነፃነቱ የሚያደርገውን
ትግል ሊቀላቀሉ ይገባል። ይህ ካልሆነ ደግሞ ቢያንስ በመሬት ላይ ጥሩእየሰሩና እየሞከሩ የሚገኙትን ለመጥለፍና
ትግሉን ለማፈን ከመሞከር ቢታቀቡ እጅግ መልካም ነው ስንል ምክራችንን እንለግሳለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
ስምንቶቹ
ስምንቶቹ
No comments:
Post a Comment