የሴት ልጅ ግርዛት በተለያዩ 28 ሃገራት ተግባራዊ እንደሚሆን ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነዉ። አሁን አሁን ግን በሰዎች ከሀገር ወደሀገር መዟዟር ምክንያት ቀድሞ በማይታወቅበት አካባቢ ሁሉ እየተዳረሰ መሆኑ እየተነገረ ነዉ።
አዉሮጳ ዉስጥ በልማድም ሆነ በባህል ያልነበረዉ ይህ ድርጊት ዛሬ የበርካቶች ስጋት ከሆነ ሰነባበተ። መረጃዎች
እንደሚያመለክቱ አዉሮጳ ዉስጥ በየዓመቱ 180,000 ታዳጊ ሴቶች ለግርዛት ይጋለጣሉ። ይህን ጎጂ ልማድ ለመግታት
የሚንቀሳቀሱ ተቋማትም የአዉሮጳ ኅብረት የተጠናከረ ርምጃ እንዲወስድ ግፊት እያደረጉ ነዉ። አዉሮጳ ዉስጥ ስዊድን
ናት በመጀመሪያ ሴት ልጆች ግርዛት እንዳይፈጸምባቸዉ በህግ የደነገገች አገር። ለዚህ ዉሳኔ ስቶክሆልም ያበቃት የራሷ
ተወላጆች አዲስ ልማድ ጀምረዉባት ሳይሆን እዚያ የሚገኙ በተለይም የሶማሊያ ዜጎች ልጆቻቸዉን ለእረፍት ወደሀገራቸዉ
በመዉሰድ እዚያ የማይታወቀዉን ድርጊት ፈጽመዉ ሲመልሷቸዉ ግራ ቢገባት እንጂ። ኔዘርላንድ ዉስጥ ወደ19ዓመታት ያሳለፉት ወ/ት ሃይማኖት በላይ ወደዚህ
በስደት መጥተዉ በቆዩባቸዉ ዓመታት ከመጀመሪያ አንስቶ በበጎ ፈቃደኝነት በተለያዩ ማኅበራት ዉስጥ ሲያገለግሉ
መኖራቸዉን ይናገራሉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2008ዓ,ም በመሠረቱት ጎበዝ በተሰኘዉ ተቋም አማካኝነትም የባህል ልዉዉጥና
ማኅበራዊ እንዲሁም ጤና ነክ ጉዳዮችን የሚመለከቱ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ።
ጎበዝ የተሰኘዉ ተቋም በተለይ የሴቶችን ጤንነት በሚመለከት የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም የበኩሉን ጥረት
እንደሚያደርግ ነዉ የተረዳነዉ። ወ/ት ሃይማኖት ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቀረት የተነሳሱበት አጋጣሚ
የተከሰተዉ እዚሁ ባህር ተሻግረዉ በሚኖሩበት ወቅት ነዉ፤
ያኔም ይላሉ ወ/ት ሃይማኖት ያኔም ይህ በአካልና በስነልቡና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ልማዳዊ
ድርጊት መቆም አለበት የሚል ሃሳብ ዉስጣቸዉ ገባ። በተለያዩ የኔዘርላንድ ከተሞች ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት
ለማስቀረት የሚንቀሳቀሱ የሀገሬዉ ተወላጆች ነበሩና የወ/ት ሃይማኖትን ዉስጣዊ ዝግጅት የሚደግፍ መንገድ ተከፈተ፤
ሶስት ሚሊዮን ታዳጊ ሴት ልጆችና ሴቶች ግርዛት የሚፈጸምባቸዉ ሲሆን በየቀኑ ወደ8,000 ያህል የዚህ
ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባ መሆናቸዉን መረጃዎች ያመለክታሉ። ወ/ት ሃይማኖት እንደሚሉት ግን ድርጅታቸዉ መረጃዉን
የሚያካፍላቸዉ ኢትዮጵያዉያን ወገኖች ግርዛት ስለሚያደርሰዉ ችግር የሚያዉቁ ዓይነት አይመስሉም፤ ያ
ማለት ግን ይላሉ ወ/ት ሃይማኖት ልጆቻቸዉን ያስገርዛሉ ማለት ዓይደለም፤ እንደዉ ትኩረት አልሰጡትም ማለት እንጂ።
የኔዘርላንድ መንግስት ግን መረጃ ማዳረሱንና ለቤተሰቦችም ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ገፍቶበታል፤
በነገራችን ላይ በዚህ አገልግሎት ከሚሳተፉ ሶስቱ የኔዘርላንድ ዜጎች ናቸዉ። አንዱ ደግሞ ከደችና
ኢትዮጵያዊ ወላጆች የተገኘ መሆኑን ገልጸዉልኛል። ወ/ት ሃይማኖት በላይ በቅርቡ በሚኖሩበት አካባቢ በማኅበረሰቡ
መካከል ላደረጉት አስተዋጽኦ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፤
የዓለም የጤና ድርጅት የሴት ልጅ ግርዛት ከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ዉጨኛዉን የሴትን የመዋለጃ አካል
ያለምንም የህክምና ምክንያት የሚያሳጣ ርምጃ መሆኑን ይገልጻል። የሚያስከትለዉ ስቃይም በወቅቱ ሲፈጸም ብቻ ሳይሆን
ለአንዳንዶች የእድሜ ልክ መሆኑንም የደረሰባቸዉን በእማኝነት የሚጠቅሱ መረጃዎች ሞልተዋል። አዉሮጳ ዉስጥ በስደተኛዉ
ኅብረተሰብ መካከል ድርጊቱ እንዲቆም የሚታገሉት ወገኖች ጎጂዉ ልማዳዊ ድርጊት የሴቶችና ወንዶችን ጾታዊ እኩልነት
ሚዛን ከሚያሳጡ ነገሮች አንዱ ነዉ ይሉታል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለጤና አደገኛ መሆኑ ከፍተኛ
ትኩረት ተሰጥቶት ልማዳዊዉን ድርጊት ለማስቆም እንቅስቃሴ ከተጀመረ ከአስር ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።
ሸዋዬ ለገሠ
ሂሩት መለሰ
dw.de
No comments:
Post a Comment