Wednesday, August 21, 2013

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ ያካሄዱት ክርክር በጉጉት እየተጠበቀ ነው · ኢቲቪ ክርክሩን መቼ እንደሚያስተላልፍ አልገለፀም

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ
ያካሄዱት ክርክር በጉጉት እየተጠበቀ ነው
·        ኢቲቪ ክርክሩን መቼ እንደሚያስተላልፍ አልገለፀም
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ ኢህአዴግና አራቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ ለሦስት ሰዓታት ያደረጉት ክርክር በጉጉት እየተጠበቀ ሲሆን፤ ኢቴቪ ክርክሩን መቼ እንደሚያስተላልፍ ግልፅ አለማድረጉ በተከራካሪ ፓርቲዎች በኩል ቅሬታ አስነስቷል። 
በክርክሩ ላይ የተሳተፉት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መድረክ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ እና ኢዴፓ ፓርቲዎች ሲሆኑ ኢህአዴግ በሁለት ተወካዮቹ በኩል ቀርቦ በክርክሩ ተሳትፏል። 
በክርክሩ ወቅት ኢህአዴግን በመወከል የቀረቡት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማልና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስና የፐብሊሲቲ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ጌታቸው ረዳ ሲሆኑ፤ ከአንድነት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ከሰማያዊ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል፣ ከመድረክ አቶ በቀለ ነጋ እና ከኢዴፓ አቶ ሙሼ ሰሙ ናቸው። 
በክርክሩ ወቅት አራቱ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም በማራመዳቸው ሚዛን መድፋታቸውን በክርክሩ ላይ የተሳተፉት አቶ ሐብታሙ አያሌውና አቶ ሙሼ ሰሙ ተናግረዋል። 
በሕጉ ላይ አንቀፅ በአንቀፅ ለማወያየት ፍላጎት ቢኖርም በቅዳሜው ዕለት ክርክር ላይ ከሕጉ መሠረታዊ ጭብጦች ባለፈ ፖለቲካዊ ጎኑ ማመዘኑን ተከራካሪዎቹ ተናግረዋል።  በቀጣይ በአወዛጋቢው የፀረ-ሽብር ሕግ ላይ አንቀፅ በአንቀፅ ለመወያየት ቀጠሮ መያዙንም አመልክተዋል። 
ሕጉ ከወጣ ከአራት አመት በኋላ በተካሄደው በዚህ ክርክር ላይ በገዢው ፓርቲ ተከራካሪዎች በኩል ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያ የፀረ-ሽብር ሕግ እንደማያስፈልጋት አድርገው ለማቅረብ የሞከሩ ሲሆን፤ በተቃዋሚዎች በኩል ሕጉ ከወጣ በኋላ የሀገሪቱ ሕዝቦች የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ጥሷል።  ዜጎችም ሕጉ ከወጣ በኋላ በፍርሃት ድባብ ውስጥ እንዲሆኑና ጋዜጠኞችና የፖለቲካ አመራሮች መታሰራቸውን በመጥቀስ ተከራክረዋል። 
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ክርክሩን ቢቀርፅም በፕሮግራም መደራረብ እስካሁን አለማስተላለፉ ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልፀዋል።  የፕሮግራም መደራረቡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት ጋር የተያያዘ እንደሆነም ተጠቅሷል።¾  
አንድነት በኦሮምያ ከተሞች ሊዘምት ነው
በዘሪሁን ሙሉጌታ
የአንድነት ለዴሞክራሲ ለፍትህና ፓርቲ (አንድነት) ለሦስት ወራት የጀመረውን የሕዝብ ንቅናቄ በመቀጠል በቀጣዩ ሳምንት በኦሮምያ ከተሞች ውስጥ ዘመቻውን እንደሚቀጥል አስታወቀ። 
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊና የብሔራዊ ም/ቤት አባል አቶ ሐብታሙ አያሌው ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ፓርቲው በኦሮምያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በባሌ ዞን ባሌ ከተማና በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ከተማ ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። በሦስቱም ከተሞች በተመሳሳይ ቀን ነሐሴ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ሰልፉ ይካሄዳል። 
ፓርቲው በመንግስት የአስተዳደር አካላት እየደረሰበት ያለውን ተፅዕኖ ተሸክሞ ንቅናቄውን ከማቆም መቀጠል መርጧል ያሉት አቶ ሐብታሙ፤ መንግስት በፓርቲው ላይ የተቀነባበረ ወንጀል እየፈፀመ ነው ብለዋል።  እንደምሳሌ ፓርቲው ያስፈረመው የፀረ-ሽብር ሕግን የመቃወሚያ ሰነድ ፖሊስ ከሚያስፈርሙ አባላቱ ነጥቋል አባላቱም በእስር እየተጉላሉ ነው ብለዋል። 
ፓርቲው ንቅናቄውን ከጀመረ በኋላ እየደረሱበት ያሉትን ተፅዕኖዎች የሚያመለክት ዝርዝር መረጃ ለብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ማቅረቡን፣ ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ለሀገሪቱ ጠ/ሚ ጭምር ደብዳቤ ለመፃፍ መገደዱን ገልፀዋል።  በክልልም ለየክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ለፀጥታው ዘርፍ ኃላፊዎች ለማስረዳት መሞከሩንና ችግሩ ግን ፓርቲው እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ወቅት የማደናቀፍ ተግባሩ እየተፈፀመ ነው ብለዋል። 
ፓርቲው የጀመረው የሦስት ወራት ሕዝባዊ ንቅናቄ በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄድ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠናቀቅ መግለፁ ይታወሳል።¾ 
በቀጣዩ ወር ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞች
ሌላ ዙር የቤት ምዝገባ ሊካሄድ ነው
በፀጋው መላኩ
የአዲስ አበባ ከተማን የመኖሪያ ቤት እጥረት በዋነኝነት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለማቃለል ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ምዝገባ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በመስከረም ወርም 2006 ዓ.ም ሌላ ዙር የቤት ምዝገባ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።
የ2005 በጀት ዓመት የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት የእቅድ አፈፃፀምን አስመልክተው ባለፈው ቅዳሜ መግለጫ የሰጡት የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በመስከረም ወር ተጨማሪ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎች ምዝገባ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል። ምዝገባው በመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ በሥራ ላይ ያሉ ሰራተኞችን ተጠቃሚ የሚያድርግ ነው። የቤቱ አይነት 40/60 ሲሆን በሰራተኞቹ ስም ሙሉ ክፍያውን እንዲፈፅም የሚደረገው ሰራተኞቹ የሚሰሩበት የልማት ድርጅት ነው። የልማት ድርጅቶች በእያንዳንዱ ተመዝጋቢ ስም መቶ ፐርሰንት የቤቱን ዋጋ መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን ሰራተኛው በአንፃሩ ከሚሰራበት የልማት ድርጅት ጋር በሚፈጽመው ውል መሰረት በወር የሚከፍለውን የገንዘብ መጠን በተመለከተና በሌሎች ዝርዝር ግዴታዎችና መብቶችን ለይቶ እንዲያውቅ ይደረጋል።
እንደ አቶ መኩሪያ ገለፃ የልማት ድርጅቶቹ ከሰራተኞቻቸው ጋር ይገባሉ ተብሎ ከሚጠበቁት ውሎች መካከል በልማት ድርጅቶቹ አማካኝነት የቤት ልማት ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡ ሰራተኞች የአገልግሎት ጊዜ ነው። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ አንድ የልማት ድርጅት በሰራተኞቹ ስም የቤት ልማት ገንዘብን መቶ ፐርሰንት ክፍያን ሲፈፅም አሰሪና ሰራተኛው በሚገቡት ውል መሰረት ሰራተኛው መሥሪያቤቱን ለተወሰኑ ዓመታት ለቆ ሳይሄድ የማገልገል ግዴታ ይጠቅበታል።
ይሁንና አንደ ሰራተኛ ቤቱን ተረክቦ ከገባው ውል ውጪ የቤት ባለቤት ያደረገውን የልማት ድርጅት ለቆ ቢሄድ ግለሰቡ በየወሩ የከፈለው ገንዘብ እንደኪራይ ተቆጥሮ ቤቱን እንዲለቅ የሚደረግ መሆኑን አቶ መኩሪያ አመልክተዋል። መመሪያው እየተዘጋጀ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ከመስከረም 15 እስከ መስከረም 30 ቀን 2006 ባሉት ቀናት ምዝገባውን ለማከናወን ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጨምረው አመልክተዋል። የመንግስት የልማት ድርጅቶች በመንግስት ይዞታ ስር ሆነው በትርፍ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ንግድ ባንክና የመሳሰሉት ድርጅቶች ናቸው።¾
ኢህአዴግ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ድርጅታዊ ስራ እንዲሰራ ማስገደዱን ተቃወሞ ቀረበበት
በዘሪሁን ሙሉጌታ
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንዳንድ ሰራተኞች የኢህአዴግ የ2006 እቅድ መስሪያ ቤቱ ካለበት መደበኛ ስራ ውጪ የገዢውን ፓርቲ ድርጅታዊ ስራ በልዩ ሁኔታ እንዲያስፈፅም ማስገደዱን ተቃወሙ።
የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አብዛኛዎቹ ሰራተኞች ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በ2006 ዓ.ም ድርጅታዊ ስራን ትኩረት ሰጥተው እንዲተገብሩ መድረጉ ሰራተኛው ያለፍላጎቱ የመንግስትንና የድርጅትን ስራ ቀይጦ እንዲሰራ የሚያስገድድ ነው ብለዋል። ለዝግጅት ክፍላችን ቅሬታ ያቀረቡት እነዚሁ ሰራተኞች እቅዱን ያለፍላጎታቸው እንዲተገብሩ፤ ካልሆነም የደመወዝ እድገትም ሆነ የደረጃ እድገት የሚያገኙበት ዕድል ዝግ የሚያደርግ ነው ብለዋል። አሰራሩም ሆነ እቅዱ የመንግስት ሰራተኞች የሚተዳደሩበትን የሲቪል ሰርቪስ ህግ የጣሰ እንደሆነም ገልጸዋል።
ሚኒስትር መስሪያቤቱ በሐምሌ ወር 2005 ዓ.ም “የዝግጅት ምዕራፍ ዝክረ ተግባር” በሚል ባለ ስምንት ገፅ እቅድ ላይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የድርጅት ስራ ማጠናከር ተገቢ መሆኑን አመልክቷል። በእቅዱ ሰነድ ላይ እንደተገለፀው፡-
“ከዚህ ቀደም በነበሩን የሴክተራችን እንቅስቃሴዎች የድርጅት እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚታይ ያልነበረ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ በጀት ዘመን ይህ አካሄድ መቀጠል አይኖርበትም። ሴክተራችን የሚመራው መሪ ድርጅታችን ባስቀመጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም የነዚህ ተግባራት ተፈፃሚነት ዕውን የሚሆነው ልዩ ልዩ ዘርፎቻችን በውስጣቸው ያለውን የድርጅት እንቅስቃሴ ማጠናከር ሲችሉና አባላትም የሴክተሩን ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማስፈፀም ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ሲችሉ ነው። በዚህ በጀት ዘመን በሴክተራችን ይህን ማረጋገጥ ካልተቻለ መሪው ድርጅት በተቋማችን ውስጥ ያለው የመሪነት ሚና እና ውጤታማነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ሆኗል። በመሆኑም በዝግጅት ምዕራፍ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ተግባራት ማከናወን እንደ ወሳኝ አቅጣጫ ሊወሰድና ወደ ተግባር ሊለወጥ ይገባል” ሲል ሰነዱ አመልክቷል።
በተጨማሪም የወረዳ አደረጃጀቱን እንደገና ፈትሾ ማጠናከር፣ በተዋረድ የመሰረታዊ ድርጅትና የህዋስ አደረጃጀቶችን ፈትሾ ማጠናከር፣ በሴክተራችን የድርጅት ዘርፍ የሚታዩ የአቅም ክፍተቶችን በጥንቃቄ በጥናት መለየት፣ ክፍተትን ማዕከል ያደረገ የአቅም ግንባታ ስልጠና ዝግጅት ማከናወን፣ በየደረጃው ለሚገኙ አመራርና የመሪ ድርጅት አባላት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት፣ የድርጅት ዘርፍ የጠራ ዕቅድ ማዘጋጀት፣ ዕቅዱን ማዕከል በማድረግ ለእያንዳንዱ አመራርና አባላት በተዘረዘረ እቅድ የተደገፈ ግልፅ ተልዕኮ መስጠት፣ የአባልነት መለኪያው በዋነኝነት በዘርፉ እቅድ ሁሉም ምዕራፎች ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ መገኘት መሆኑን ማስረፅ፣ ተግባራዊ ማድረግና የክትትልና ድጋፍ አግባብ ዘርግቶ ሂደቱን መከታተልና መደገፍና የመሳሰሉ ተግባራት ናቸው” ሲል ይኸው ሰነድ አመልክቷል።¾ 
እውነቱ ብላታ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ተሾሙ
በዘሪሁን ሙሉጌታ
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር የነበሩት አቶ እውነቱ ብላታ ደበላ ከያዙት ኃላፊነት ተነስተው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ተሾሙ።
አቶ እውነቱ የተሾሙት ቦታ አቶ በከር ሻሌ በአሁኑ ወቅት የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት የያዙት ቦታ ሲሆን አቶ በከር ከዚህ ኃላፊነታቸው ተነስተው የአዳማ ከንቲባ ሆነው ከተሾሙ በኋላም ከዘጠኝ ወራት በላይ ቦታው ክፍት ሆኖ መቆየቱ ታውቋል።
አቶ እውነቱ ብላታ ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል የፍትህና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የሰሩ ሲሆን በኋላም በፌዴራል ጉዳዮች ጽ/ቤት በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ተሹመው ለአንድ ዓመት ሲሰሩ ቆይተዋል።
አቶ እውነቱ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በተያያዘ ጠንከር አስተያየት በመስጠትና ከሚዲያ ጋር ባላቸው ቅርበት ይታወቃሉ።¾ 
ለካንሰር ሕሙማን መርጃ የሚውል የገቢ
ማሰባሰቢያ ሊካሄድ ነው
በአሸናፊ ደምሴ
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የካንሰር በሽታዎች ለተጠቁና በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተኝተው ህክምናቸውን ለሚከታተሉ ከ36 በላይ ለሚደርሱ ህሙማን መርጃ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ የኪነ-ጥበብ ምሽት ከመጪው እሁድ ነሐሴ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ ሊካሄድ መታቀዱን በኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ማቲዎስ ወንዱ እና የፕሮግራሙ ሃሳብ አመንጪ የሆነችው የሚስ አዲስ 125ኛ የቁንጅና ውድድር ሁለተኛ አሸናፊዋ ወይዘሪት ሜቲ ታምሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ፕሮግራሙ የሚካሄደው ቦሌ ዲኤች ገዳ ታወር ላይ በሚገኘው “ማማስ ኪችን” መሆኑን ያስታወቁት አዘጋጆቹ፤ ከፕሮግራሙ የሚገኘው ገቢም ሙሉ በሙሉ ህሙማኑን ለመርዳት ከማገልገሉም በተጨማሪ ካንሰርን በተመለከተ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና የመከላከል እንቅስቃሴ ይውላል ተብሏል። በኢትዮጵያ በስፋት የሚታዩት የካንሰር አይነቶች የጡት ካንሰር፣ የማህፀን ካንሰር፣ የደም ካንሰርና የአጥንት ካንሰር መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ማቲዮስ ወንዱ፤ እነዚህም የካንሰር አይነቶች በአብዛኛው በሴቶችና በህጻናት ላይ ይታያሉ ብለዋል። ከነዚህም ውስጥ በሀገራችን የጡት ካንሰር ሁለተኛው ገዳይ በሽታ መሆኑን ተነግሯል።
የካንሰር ህሙማንን ለመርዳት በሚደረገው በዚህ የምሽት ፕሮግራም ላይ የፋሽን ዲዛይኖች ትርኢት፣ የግጥምና የሙዚቃ ስራዎችን ጨምሮ ካንሰርን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች እንደሚከናወኑ ለማወቅ ተችሏል። በእለቱ ቦሌ ላይ በሚጀምረው ፕሮግራም የመዝናኛና የእራት ግብዣውን ጨምሮ አንድ ታዳሚ 219 ብር የመግቢያ ዋጋ በመክፈል የወገን ደራሽነቱን ማሳየት እንደሚኖርበት ያስታወሱ ሲሆን፤ ዝግጅቱም ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ እኩለሌሊት ስድስት ሰዓት እንደሚዘልቅ ተነግሯል።
ፕሮግራሙ ቢጂ አይ. እና ክለብ ኤች ቱ ኦ የስፖንሰሮች ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን፤ በፕሮግራሙ ላይም ታዋቂውን የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ይልማ ገ/አብ እና ልጁን ኤልሻዳይ ይልማን ጨምሮ ታደለ በቀለ፣ ደመቀች መንግስቱ፣ ጀማል ማህመድ ያደምቁታል ተብሎ ይጠበቃል። በምሽቱ የሚቀርቡትን የአልባሳት ዲዛይኖችንም ከውጪ የመጡ ወጣት ዲዛይነሮች ስራዎቻቸውን የሚያሳዩበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በፕሮግራሙ ላይ ከአራት መቶ በላይ እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት አዘጋጆቹ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከሚገኙት አራት ካንሰር ተኮር ግብረሰናይ ድርጅቶች አንዱ ከሆነው ከኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ጋር በመተባበር ይህን መሰሉ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በየወሩ እንዲካሄዱ ሁኔታዎችን ያመቻቸው የሚስ አዲስ አበባ 125ኛ ዓመት አሸናፊዋ ሚስ ሜቱ ታምሩ፤ ሁለተኛ ደረጃን አግኝታ ባጠናቀቀችበት ወቅት የገባችውን ቃል ለማክበር ስትል ይህንን በጎ አላማ ማከናወኗን ለጋዜጠኞች ተናግራለች።¾ 
ኢትዮጵያዊቷን አሰቃይታ የገደለች አሰሪ
በ3 ዓመት እስራት ተቀጣች
በመስከረም አያሌው
ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛዋን ለረጅም ጊዜ አሰቃይታ ለሞት የዳረገች የአቡዳቢ አሰሪ በሶስት ዓመት እስራት ተቀጣች።
ብሉምበርግ ከአቡዳቢ እንደዘገበው አሰሪዋ ኢትዮጵያዊቷን በየእለቱ የፈላ ውሃ ላይዋ ላይ በመድፋት፣ በፀጉር ማድረቂያ የኤሌክትሪክ መሣሪያ በመደብደብ እና አይኗ ውስጥ በርበሬ በመጨመር ስታሰቃያት ቆይታለች። ኢትዮጵያዊቷ ወደዚች አሰሪዋ ቤት ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ አይነቱ ስቃይ ውስጥ የነበረች ሲሆን በስቃዩ ብዛትም ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል። አሰሪዋም ባለፈው የካቲት በቁጥጥር ስር ውላለች።
ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የሀገሪቱ ፖሊስም አሰሪዋ ጥፋተኛ ናት ሲል ባለፈው ነሐሴ አንድ በሶስት ዓመት እስራት እንድትቀጣ ወስኗል። አሰሪዋ ሰብዓዊነት እና ርህራሄ በጎደለው መልኩ ኢትዮጵያዊቷ ላይ በየእለቱ ለፈፀመችው ስቃይም ሆን ብላ መሆኑን ከስነልቦና ባለሞያዎች የተገኘው ውጤት ያመለክታል ብሏል። የስነ ልቦና ባለሞያዎች ሪፖርትም አሰሪዋ ጤነኛ እና የምታደርገውን ነገር የምታውቅ ሴት መሆኗን አረጋግጠዋል።
ህይወቷ ያለፈው ኢትዮጵያዊት ቤተሰቦችም አሰሪዋ ላይ የሞት ቅጣት እንዲፈረድ እና 200ሺ ድሪሃም የደም ካሳም እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል።
በተያያዘ ዜና አንድ ኢትዮጵያዊ በካሮሊና በባለቤታቸው እና በሁለት ወንድ ልጆቻቸው ላይ በፋስ እና በቢላዋ ጉዳት ማድረሳቸውን ደብልዩ ቢ ቲቪ ዘግቧል። አቶ ምሩጽ ሃይሉ የተባሉት የ57 ዓመቱ የካሮሊና ነዋሪ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ምሽት ላይ ባለቤታቸውን እና ሁለት ታዳጊ ወንድ ልጆቻቸው ላይ ፋስ እና ቢላዋ ተጠቅመው ጉዳት አድርሰው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ምሽት ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ ከአንድ የተረበሸ የ16 ዓመት ልጅ በደረሳቸው የስልክ ጥሪ ወደ አቶ ምሩፅ ቤት ያመሩት ፖሊሶች ጊቢው ውስጥ ሲደርሱ የ15 ዓመት እድሜ ያለው ልጅ በረንዳ ላይ ወድቆ እንዲሁም የልጁ እናት መኝታ ቤት ውስጥ ተዘርራ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ፖሊስ አቶ ምሩፅን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ በግቢው ውስጥ ባደረገው ፍለጋ አንድ የስጋ ቤት ቢላዋ እና ሌላ የስጋ ቢላዋ ከአልኮል ጠርሙስ ጋር ቆሻሻ ውስጥ ተጥሎ ተገኘቷል።
ጉዳቱ የደረሰባት የልጆቹ እናት ሁኔታው አሳሳቢ በመሆኑ እርዳታ እየተደረገላት ሲሆን የ16 ዓመቱ ታዳጊ ልጅም በካሮሊናስ የህክምና ማእከል ቀዶ ህክምና ሊደረግለት በዝግጅት ላይ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።
አቶ ምሩፅ ድርጊቱን የፈፀሙበት ምክንያት እስከ አሁን ድረስ ያልታወቀ ቢሆንም፤ ግለሰቡ ሆን ብሎ ለመግደል በማሰብ በመሳሪያ መዋጋትን ጨምሮ የተለያዩ ስድስት አይነት ክሶች እንደተመሰረቱባቸው ተገልጿል። ጉዳያቸው በፍ/ቤት እንዲታይ ባለፈው ማክሰኞ ተቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ጉዳያቸውን ሊያስረዳላቸው የሚችል አስተርጓሚ በማስፈለጉ ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቷል።¾
የድምፃዊ እዮብ መኮንን የቀብር ሥነ-ሥርዓት
 ዛሬ ይፈፀማል
በአሸናፊ ደምሴ
በሬጌ የሙዚቃ ስልት አጨዋወቱ በበርካቶች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈው ድምጻዊ እዮብ መኮንን ባሳለፍነው ቅዳሜ ለህክምና በሄደበት ኬኒያ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ አጋ-ካሃን የተሰኘ ሆስፒታል ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ ትናንት ማምሻውን ወደሀገሩ የተመለሰው አስክሬኑ፤ ዛሬ ከቀኑ በ9ሰዓት በቅዱስ ስላሴ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ እንደሚፈፀም ምንጮች አስታወቁ።
“እንደቃል” በተሰኘው ብቸኛና የመጀመሪያ አልበሙ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፎ የነበረው ድምፃዊ እዮብ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የእህቱን ልጅ ትምህርት ቤት አስመዝግቦ ከተመለሰ በኋላ የግቢውን በር በማንኳኳት ላይ ሳለ ራሱን ስቶ መውደቁ የታወቀ ሲሆን፤ ህመሙም የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (stroke) መሆኑ ታውቋል።
ከድንገተኛ አደጋው በኋላ ራሱን ስቷል። በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የህክምና እርዳታውን ሲያገኝ የቆየው ድምፃዊው፤ ለተሻለ የህክምና እርዳታ ወደኬኒያ፤ ናይሮቢ አምቡላንስ ባለው የግል አውሮፕላን ቅዳሜ ምሽት ከሀገሩ የወጣው እዮብ ጤናውን ይዞ መመለስ ሳይችል ቀርቷል።
በኬኒያ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች የወጣቱን ድምጻዊ ህይወት ለመታደግ የተቻላቸውን የጣሩ ቢሆንም፤ ድምጻዊ እዮብ መኮንን ግን በተወለደ በ38 ዓመቱ እሁድ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት 3፡45 አካባቢ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
ድምጻዊው ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ሲሆን፤”እንደቃል” በተሰኘው ተወዳጅ አልበሙ በተጨማሪም በቅርቡ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅ የሙዚቃ ስራውን ከ70 በመቶ በላይ አጠናቆ እንደነበር ምንጮች ይጠቁማሉ። የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ለድምፀዊው ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና አድናቂዎች ሁሉ መፅናናትን ይመኛል።¾
ሰማያዊ ፓርቲ  ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳላደርግ
አዳራሽ ተከለከልኩ አለ
*    “ግጭት አፈታት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ የውይይት ሃሳብ ያቀርባሉ
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የመብራት ኃይል አዳራሽና በምኒልክ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሾች ውስጥ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ቢያቅድም ማድረግ አለመቻሉን ፓርቲው አስታወቀ።
የፓርቲው የህግ ጉዳይ ኃላፊ ወጣት ይድነቃቸው ከበደ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፀው ፓርቲው በመጪው እሁድ በመብራት ኃይል አዳራሽና በምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሽ ጥያቄ አቅርቦ የአዳራሾቹ ባለቤቶች ፓርቲው ስብሰባ ለማካሄድ ከአዲስ አበባ አስተዳደር የፈቃድ ደብዳቤ እንዲያመጣ ሲጠይቁ የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ ለአዳራሽ የከፈላችሁበትን ደረሰኝ አምጡ በማለቱ ቢሮክራሲያዊ በሆነ መንገድ አዳራሾቹን መከልከሉን ተናግረዋል።
“ወደ አዳራሾቹ ባለቤት ሄደን ክፍያ ልንፈፅም ስንል ፈቃድ አምጡ ይሉናል። ከአዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ ፈቃድ ስንጠይቅ የተዋዋላችሁበትን ደረሰኝ አምጡ በማለት አጉላልተውናል” ያለው ወጣት ይድነቃቸው በግል የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሆኑትን አቶ አባተ ስጦታውን ቢያናግሩም ፈቃዱ ሊሳካ አልቻለም ብሏል።
በተያያዘ ፓርቲው ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የእውቅና ደብዳቤ ማስገባቱንና ሰልፉን ሊያደምቁ የሚችሉ ልዩ ልዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያካሄዱ መሆኑን ከወጣት ይድነቃቸው ገለፃ መረዳት ተችሏል።
በሌላ በኩል ፓርቲው ቀበና በሚገኘው ጽ/ቤቱ በየሳምንቱ እሁድ ምሁራንን እየጋበዘ የሚያደርገውን ውይይት በመቀጠል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑትን ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬን በመጋበዝ “የግጭት አፈታት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በቀጣይ እሁድ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ፓርቲው ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ አመልክተዋል።
ዶ/ር በቃሉ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆኑ በሳይኮሎጂና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሁለት ማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በትምህርት (Education) የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በቋንቋና ስነልቦና የፒኤች ዲግሪ አላቸው። ከአስር ዓመት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማስተማር ላይ ይገኛሉ።¾
(ምንጭ፡-ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 415 ረቡዕ ነሐሴ 15/2005)

No comments:

Post a Comment