Wednesday, August 21, 2013

የመለስ ነፍስም በቀጥታ ከሲኦል ወደ አዲስ አበባ ገባች::

የመለስ ነፍስም በቀጥታ ከሲኦል ወደ አዲስ አበባ ገባች::

መለስ ከሞተ ዓመት ሊሞላዉ ነው አይደል? ይገርማል እኮ አምና ይህን ጊዜ መለስ ታመመ ፣ መለስ ሞተ ተብሎ ሲወራ አቶ በረከት ብቅ እያሉ ምንም አልሆነም በቅርቡ ይመጣል እያለ ሲያታለለን ፣ በእኛ እና “ባለራዩን መሪያችንም” ሲያላግጥ ነበር … ወይ ግሩም! እስኪ ዛሬ ደግሞ እኛም በተራችን በ “ባለ ራዕዩ መሪያችን” ትንሽ እናላግጥ::
አቶ መለስ ነፍሳቸው ከስጋቸው ብትለይም ወዳጃቸዉም ጠላታቸዉም በሆነ ባልሆነው ስማቸዉን እየጠራ እረፍት ስለነሳቸው ለሁሉም ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ስለፈለጉ ለአንድ አፍታ ነፍሳቸው ምድርን ትጎበኝ ዘንድ እንዲፈቅድላት ፈጣሪን ከሲኦል በደብዳቤ ፈቃድ ጠየቁት ፤መቸም ሰው የገደለ እና ያስገደለ ሰው ገነት እንደማይገባ ሁላችሁም ታዉቃላችሁ ብዬ ነዉ ከሲኦል ያልኩት:: የለመኑትን የማይነሳ ፈጣሪም “ ወደቀደመ ክፉ ስራህ እንዳትመለስ” የምትለዉን አምላካዊ ቃል ነግሮ ለነፍሳቸው ፈቃድ ሰጣት::
የመለስ ነፍስም በቀጥታ ከሲኦል ወደ አዲስ አበባ ገባች:: ነፍሳቸው አዲስ አበባ እንደገባችም በሕይወት ዘመናቸው አይተዉት በማያውቁት መልኩ በየቀበሌው የሃዘን ድንኩአን ተጥሏል፣ ፎቶአቸዉ በየቦታዉ ተሰቅሏል ፤ ከፎቶአቸዉ ስርም “ ባለራዩ መሪያችን” የሚል ፅሁፍ አዩና ድርጅታቸው ኢህአዴግ እሳቸው ቢሞቱም ስም ለማዉጣት እንዳልሰነፈ ስለተረዱ ትንሽ ፈገግ አሉ:: በመቀጠልም ነፍሳቸው ወደ አንዱ የቀበሌ የሃዘን ድንኩአን በመግባት ሰው ምን እንደሚል ለመስማት ወሰነች:: በድንኩአኑ ዉስጥ የተሰበሰቡት ሁሉ የቀበሌዉን ሊቀመንበር “ አይዞህ ባገር የመጣ ነው” እያሉ ሲያፅናኑት ነፍሳቸው አይታ ትንሽ ግራ ተጋባች፤ ከተወሰኑ ደቂቃወች በሁአላ ሊቀመንበሩ ስልክ ስለተደወለለት ከድንኩአኑ ወጥቶ ስለሄደ በድንኩአኑ የተሰበሰቡት ሰወች እርስ በእርስ በነፃነት ማዉራት ጀመሩ:: ምንም እንኩአን በሳቸው ሞት ያዘኑ ሰወች ቢኖሩም በድንኩአኑ ዉስጥ የተሰበሰበዉ አብዛኛዉ ሰው እንዲህ እያለ ሲያማርራቸዉ ነፍሳቸዉ ሰማች “ ይህ የተረገመ ሰዉዬ ቁሞም ሙቶም ያስለቅሰናል አይደል” ፤ ነፍሳቸውም እጅግ ተበሳጨች እና እንደዚህ የሚሉትን ሰወች “እጣት ለመቁረጥ” ፈለገች ግን “ወደቀደመ ኃጢያትህ አትመለስ” የምትለዉ የአምላካቸዉን ትእዛዝ አስታወሰችና ዝም አለች::
ከዚህ ቀጥሎ ነፍሳቸው በቴሌቪዥን ምን እንደሚባል ለማወቅ ስለፈለገች ሰተት ብላ ኢቲቪ የተከፈተበት አንድ መዝናኛ ቦታ ገባች:: እጣታቸዉን ቀስረው መቼ እንደተነሱት ትዝ ያላላት ፎቶ ከጋዜጠኛዉ ጀርባ ተሰቅሏል:: የሃዘን ጥቁር ልብስ የለበሱ የተለያዩ ሰወች በሳቸው ሞት የተሰማቸዉን ሃዘን ይገልፃሉ፣ ሁሉንም በጥሞና ስትከታተል የነበረችዉ ነፍሳቸው የጎዳና ተዳዳሪወች “እኛ እሳቸዉን አምነነ ነው ጎዳና የወጣነው ከእንግዲህ ማን ይጠብቀናል” ሲሉ ስለሰማች በጣም ተከዘች:: ቀጥሎ በሠራዊት ፍቅሬ የሚመራዉ የአርቲስቶች ቡድን የሃዘን መግለጫ ሲያስተላልፍ ነፍሳቸው ሰራዊትን አየችና ተበሳጨች ፣ “አይ አጅሬ በኔ ሞትም ቢዝነስ ይሰራል አይደል” ይገርማል እኮ ብላ ተናዳ ሳትጨርስ ትግስት ወይሶ እንባዋን ሞከ ሞክ እያደረገች “እሳቸው እኮ ምን ልበልህ አንዳንዴ ቀበቶአቸው ተፈትቶ ታየዋለህ ፣ ሌላ ጊዜ ፀጉራቸው ተንጨብሮ ሳያበጥሩት ታያቸውለህ … እሕ ሕ ሕ ሕ” ስትል ነፍሳቸዉ ስለሰማች በጣም ተገርማ “ መለስ የሚንጨባረር ፀጉር ለመሆኑ ነበራቸው እንዴ? ቀበቶየንስ መቼ ነው ያየችዉ ?” ብላ እራሷን ጠየቀች፣ በኢቲቪም በጣም ተናደደች:: በተለይ በማስታወቂያ ሚንስተሩ በበረከት ስምዖን ላይ እንዲህ ተናገረች “ ይሄ የማይረባ ቢያንስ ስለፀጉሬና ቀበቶዬ የተባለዉን እንኩአን ምናለ ቆርጠዉ እንዲያወጡት ቢያስደርግ” ፤ ገና ሙቷል ተብሎ እንዲህ በለመደ ዉሸታም ቴሌቪዥን ጣቢያዉ የሀገር መሳቂያ ያድርገኝ! ብላ “ድሮስ ከ ኢቲቪ ምን ይጠበቃል” ልትል ስትል ኢቲቪን እራሳቸው መለስ ዉሸት እንዳስተማሩት ስላወቀች ተፀፀተች ::
በመቀጠልም ነፍሳቸው ስለሳቸው በጋዜጣ ምን እንደሚባል ለማወቅ ስለፈለገች ጋዜጣ ገዝታ ማንበብ ቀጠለች:: ገቢያ ላይ ያገኘችዉ በመንግስት የሚታተሙትን ጋዜጦች ብቻ ነበር ፤ ሌላዉ ቀርቶ እሳቸው በሕይወት እያሉ እንድምትታተም ያውቁአት የነበሩት “ፍትህ” ጋዜጣ መዘጋቷን ሰወች ሲያወሩ ሰማች:: የመንግስት ጋዜጦች ላይ ከኢቲቪ የተለየ ነገር ማግኘት ስላልቻለች በጣም ተናደደች ፤ መለስ የግል ጋዜጦችን በጅምላ የዘጉበትንም ቀን እረገመች ::
በጋዜጣዉ ብዙም ያልረካችዉ ነፍስ ከመረጃ መረብ (ኢንተርኔት) የተሻለ ነገር አይጠፋም ብላ አንድ ኮምፒተር ላይ ተጣደች:: በሕይወት እያሉ አዘዉትረው የሚጎበኙትን “አይጋ ፎረም” እና “ትግራይ ኦን ላይን” ላይ ሰላሳቸው ሞት የፃፉትን ስታነብ ከቆየች በሁአላ ከስር ስለአባይ ግድብ የተፃፈ ነገር አየች:: “ትግራይ ኦን ላይን” ላይ የሳቸው ደጋፊወች ግድቡ ሲጠናቀቅ “ መለስ ግድብ” መባል አለበት ብለዉ የፃፉትን አይታ ትንሽ ደስ አላት:: ነገር ግን ከስር ለግድቡ ማሰሪያ ገንዘብ ለመሰብሰብ በአዉሮፓ እና በአሜሪካ የተጠሩ ስብሰባወች “በአሸባርወችና ፀረ ልማቶች ” ሴራ ተበተኑ የሚል ዜና ስላየች እንደገና ተበሳጨች:: ቀጥሎም የተቃዋሚወችን ድህረ ገፅ ማየት ስትጀምር “ አቶ መለስ ባለማችን ሁለተኛዉ ሃብታም ጠቅላይ ሚኒስቴር ነበሩ” የሚል ዜና አየች በዝርዝሩም ይህ ገንዘብ ለአባይ ግድብ ከሚያስፈልገው ጠቅላላ መጠን ሶስት አራተኛዉን መሸፈን ይችላል ማለት ነው ይላል፤ ነፍሳቸው በጣም ስለተበሳጨች ለእናንተ እልክስ ይህን ገንዘብ ለግድቡ አዋጥቸው በሞትኩ ኑሮና ግድቡም አልቆ በስሜ በተሰየመ ብላ ጮኽች ::
ነፍሳቸው ከኢንተርኔት ላይ ከመነሳቷ በፊት ሚስጥራዊ የፌስ ቡክ አካዉንታቸዉን ከፈተች:: ፌስ ቡክ ላይ ቀደም ሲል በየመንገዱ ተሰቅለዉ ያየቻቸዉን ፎቶወች ደጋፊወቻችዉ ግድግዳቸው ላይ ለጥፈው “ባለራዕዩ መሪያችን” እያሉ ስያሞካሹአቸው አይታ ፈገግ ከማለቷ አንዱ የማይወዳቸው ልክ ሲኦል ዉስጥ ባየቻቸው እና ጧት ማታ በሚገርፏት ሰይጣናት አምሳያ የሳቸዉን ፎቶ “ቫምፓየር” አስመስሎ የፌስ ቡክ ግድግዳዉ ላይ ለጥፎ ስላየች እጅግ በጣም ተበሳጨች ፤ ከሁሉም ያበሳጫት ደግሞ ያ ምስል ብዙ “ላይክ” ማግኘቱ ነበር፤ “ይህንስ እንኩአን ጣቱን አንገቱንም ብቆርጠው አልረካ” አለችና ለራሷ ተናገረች::
ነፍሳቸው ምድርን ተሰናብታ ወደሲኦል ከመመለሷ በፊት እጅግ ይወዱት የነበረዉን የደህንነት መስሪያ ቤቱን መጎብኘት ፈለገች እና እሳቸዉ እና የቅርብ ሰወች በሚያውቁት ሚስጥራዊ የበር መክፈቻ ቁጥር በሩን ከፍታ ገባች:: እሳቸው ከሞቱ በሁአላ መስሪያ ቤቱ የሰበሰባቸውን መርጃወች ሰታሥስ እሳቸዉ በሌሉበት በቅርቡ ባህርዳር የተካሄደውን የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ የሚያሳይ ቪዲዮ አገኘች:: በጉባዔው ላይ የፎቶአቸው ቁጥር ከተሰብሳቢዉ ሳይበልጥ እንደማይቀር ስታስተዉል በኢህአዴግ አፈረች ፤ በዛ ላይ እሳቸዉን የተኩት ሰዉዬ አሁንም አሁንም “ባለራዩ መሪያችን” ሲል ስትሰማ እንደለመደችዉ “ የሞኝ ዘፈን ሁልግዜ አበባዬ” ብላ ተረተችበት:: ማጠቃለያ ላይ ባለቤታቸው አዜብ “ በዚህ ዓለም ላይ በ 4000 ብር ደሞዝ ሀገር የሚመራ መለስ ብቻ ነበር”ስትል ነፍሳቸዉ ሰማችና አይይ ይ “ዉሸት ለኔም አልጠቀመ እንዴት በጋህነም እሳት እንደምቃጠል ብታይ አትዋሽም ነበር” ብላ አዘነች፤ ሀዘኗን ሳትጨርስ ቀጥሎ ባየችዉ ቪዲዮ በጣም ደነገጠች:: ቪድዮዉ ሰማያዊ ፓርቲ የጠራዉ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር:: ሕዝብ ተሰብስቦ ተቃዉሞዉን ያሰማል ፣ ሁኔታው ከምንም በላይ አስቆጣት እና እንዲህ አለች “ ገና ከሞትኩ ዓመት እንኩአን ሳይሞላኝ አዳሜ ተሰብስቦ ቀዩን መስመር ተላለፈ?”፤ “እነዚህ ጣቶች የሚቆርጣቸው አጡ ማለት ነው?” “መንጋ አሸባሪ!”:: ይህን ብላ ወደመቃብሯ ስታመራ መንፈሷ በጣም ስለታወከ እንዲህ አለች “ ይህን ሁሉ ጉድ የሚያሳዩኝ ከዚህ ጨርቅ ህዝብ ማህል አዲስ አበባ ስለቀበሩኝ ነው እንጅ ይህን ጊዜ ወርቁ ሕዝቤ በሚኖርበት ቦታ ቢቀብሩኝ ኑሮ በሰላም አንቀላፋ ነበር”::
Mstewal Dessalew
source..freedom4ethiopian

No comments:

Post a Comment