Friday, August 30, 2013

የህይወት ዋጋ ያስከፈለው ትንሽዬ ሰነድ “የተገንጣዮችና የሲ.አይ.ኤ. ግንኙነት”

ርዕስ፡- “የተገንጣዮችና የሲ.አይ.ኤ. ግንኙነት”
ጸሓፊ ተስፋሚካኤል ጆርጆ
——-
በዚህ አነስተኛ ጽሁፍ የማወጋችሁ ስለአንድ አስገራሚ ሰነድ ነው፡፡ ሰነዱ የያዘው ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሰነዱ ጸሐፊም አስገራሚና አሳዛኝ ታሪክ አለው፡፡ ይህ ሰው “ኦሮማይ” በተሰኘው የበዓሉ ግርማ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት ዋና ዋና ገጸ-ባህሪዎች አንዱ ነው። በዚህ ሰነድ የምታነቡትንም ታሪክ በኦሮማይ ውስጥ በትንሹ ታገኙታላችሁ፡፡ ጸሓፊው በዚህ ሰነድ የህይወት ዋጋ ከፍሎበታል። ታሪኩን በአጭሩ እነሆ!
——-
አቶ ተስፋሚካኤል ጆርጆ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን በደቡብ ምስራቅ ኤርትራ የሚገኘው የደቀምሐረ ወረዳ ገዥ ነበሩ። ሻዕቢያ (EPLF) ከጀብሀ (ELF) ተገንጥሎ የትጥቅ አመጽ የጀመረውም በዚህ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው የዓላ በረሃ ነው። በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኤርትራ ገዥ የነበሩት ልዑል ራስ አስራተ ካሳ እነዚህ የሻዕቢያ ተገንጣዮች በሰላም እጃቸውን ሰጥተው ወደ ህብረተሰቡ እንዲመለሱ ለማግባባት እንዲያመቻቸው ሶስት አባላት የነበሩት የሰላም ኮሚቴ ያቋቁማሉ። ተስፋሚካኤል ጆርጆም የኮሚቴው አባል ሆነው ይሰየማሉ።
ኮሚቴው በታቀደው መሰረት ሻዕቢያን አግባብቶ የመመለስ ተግባሩን ጀመረ። ነገር ግን እቅዱ መልኩን ቀየረና ሻዕቢያን ከሲ.አይ.ኤ ጋር ያቆራኘ ሆነና አረፈው። ይህ ቁርኝት እንዴት ተከሰተ? ከዚያ በኋላ ምን ተከተለ? መጨረሻውስ ምን ሆነ? በዘመኑ የድራማው ተሳታፊ የነበሩት አቶ ተስፋሚካኤል ጆርጆ ዝርዝሩን በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ይነግሩናል። ስለዚህ ታሪኩን ረጋ ብላችሁ አንብቡት። 
ከላይ እንደገለጽኩት አቶ ተስፋሚካኤል በዓሉ ግርማ በጻፈው “ኦሮማይ” ውስጥ ካሉት ዋና ዋና ገጻ ባህሪያት አንዱ ናቸው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የተወከሉት “ስዕላይ ባራኺ” በሚባለው ዝነኛ ገጸ-ባህሪ ነው። ይሁንና በዓሉ ኦሮማይን ሲጽፍ የአቶ ተስፋሚካኤልን እውነተኛ ታሪክ በእጅጉ ለዋውጦታል። በቅርብ ጊዜ ስለኦሮማይ ገጸ ባህሪያት ስጽፍ ያየኝ Yosef Berhe የሚባል ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ከሰጠኝ መረጃ ለማወቅ እንደቻልኩት በኦሮማይ ውስጥ ያለው የ“ስዕላይ ባራኺ” ገቢር በሁለት ግለሰቦች ታሪክ የተመሰረተ ነው፡፡ “ስዕላይ ባራኺ” ወደ ሳህል በረሃ ከመውጣቱ በፊት የነበረውን ህይወቱን የሚያትተው ክፍል የአቶ ተስፋሚካኤል ጆርጆ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ “ስዕላይ ባራኺ” በሰሃል በረሃና ከዚያም በአስመራ የነበረውን ህይወቱን (በዓሉ ግርማ የዐይን ምስክር ሆኖ የተመለከተው) የሚያወሳው ክፍል “ተክላይ አደን” (ተክላይ ገብረ ማሪያም) በሚባል የሻዕቢያ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
***** ***** *****
አቶ ተስፋሚካኤል ይህንን ጽሁፍ ያቀረቡት በዘመነ ቀይ ኮከብ በተካሄደው የምጽዋ ሲምፖዚየም ላይ ነው (በዓሉም በ“ኦሮማይ” ውስጥ “ስዕላይ ባራኺ” ጽሁፉን በሲምፖዚየሙ ላይ ማቅረቡን ገልጿል)። ይሁንና ይህ ጽሁፍ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሊሆን የቻለውና ታሪካዊ ጠቀሜታው ጎልቶ የወጣው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት (የባድመ ጦርነት) በፈነዳበት ማግስት በኢትኦጵ መጽሔት ላይ ሐምሌ 1991 በታተመበት ጊዜ ነው፡፡ 
አቶ ተስፋሚካኤል ጆርጆ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የሚተርኩት ታሪክ የነበራቸው ተሳትፎ ጦስ ሆኖባቸው እስከ ሀይለስላሴ መንግሥት ፍጻሜ ድረስ በእስር ላይ ቆዩ፡፡ ከእስር ሲፈቱ የሻዕቢያ አዳኞች ለግድያ እንደሚፈልጓቸው በማወቃቸው ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ጀብሃ ገቡ፡፡ እስከ 1972 መጀመሪያ ድረስ ከጀብሃ ጋር ከቆዩ በኋላ ጀብሃ በሀይለኛ ሁኔታ በሻዕቢያ ሲመታ እንደገና ህይወታቸው ለአደጋ ተጋለጠ፡፡ በዚህን ጊዜም ወደ ሱዳን ተሰደዱና ካርቱም ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እጃቸውን ሰጡ፡፡ የደርግ መንግስትም አስፈላጊ ሰው መሆናቸውን በመረዳቱ ወደ አዲስ አበባ አስመጣቸው፡፡ ከዚያም ይህንን ታሪክ ለመንግሥት ባለስልጣናት ተናገሩ፡፡ ከላይ እንደተገለጸውም ባለስልጣናቱ ታሪኩን በጽሑፍ ጽፈው በቀይ ኮከብ ዘመቻ ዘመን በተካሄደው የምጽዋ ሲምፖዚየም ላይ እንዲያቀርቡት ስላደፋፈሯቸው እርሳቸውም ይህንኑ አደረጉ፡፡ 
አቶ ተስፋሚካኤል እስከ ደርግ መውደቂያ ድረስ በአዲስ አበባ ኖሩ። በ1984 መጨረሻ ገደማ ግን እርሳቸውን ሲያሳድዱ የነበሩት የሻዕቢያ ኮማንዶዎች ከሳር ቤት ዝቅ ብሎ ባለው የቫቲካን ኤምባሲ አካባቢ ወደቤታቸው በመግባት ላይ እያሉ ገደሏቸው። ጽሁፋቸው ግን አልሞተም። ዛሬም አስገራሚውን ታሪክ ይናገራል። 
ይህንን አስገራሚ ሰነድ ከሚከተለው የኢንተርኔት ገጽ በቀጥታ ዳውንሎድ አድርጉትና እዩት፡፡ የዛሬ 40 ዓመት ግድም የነበረውን የኤርትራ ምስቅልቅልና የአፍሪቃ ቀንድ የጂኦፖለቲካ ሁኔታ በደንብ ትማሩበታላችሁ፡፡ ለሁሉም ጋሽ ስብሐት እንዳለው ሰነዱን “እነሆ በረከት” ብያለሁ። መልካም ንባብ!
freedom4ethiopian

No comments:

Post a Comment