Tuesday, August 27, 2013

የግብጹ ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ውድቀት እና የናይል ፖለቲካ


በሚኪያስ በቀለ    
እንደመነሻ፤ የግብጽ አብዮቶች
ግብጽን ለሠላሳ ዓመታት ያስተዳደራት የሁስኒሙባረክ መንግሥት ወዳጆቹን በሙስና አበለፀገ፣   የኑሮ ውድነትን ከማየትበቀር መፍትሔ ማምጣት አቃተው፡፡ በቱንዚያ የሕዝቡን ሥልጣን ያዩት የግብጽ ሕዝቦች በቃን እንዲሉ ምክንያት ሆናቸው፡፡ ሠላሳ ዓመታትተንደላቀው ሀገሪቷን ያስተዳደሯት፤ ሙባረክን ጨምሮ የተለያዩ ኃላፊዎች ዕጣ ፈንታቸው በሰልፉ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን በማስገደልእና በፈፀሙት ሰፊ የሙስና ተግባር ችሎት መቆም ሆነ፡፡ በመቀጠል የወታደራዊ መንግሥት ግብጽን ያስተዳድር ጀመር፡፡ አሰተዳደሩንበሲቪል ለመቀየር ሀገራዊ ምርጫ ተሰናዳ፡፡
በሙርሲ የሚመራውና በሙስሊም ወንድማማቾችየተመሠረተው የነጻነት እና ፍትሕ ፓርቲ (Freedom and Justice Party) አባላት 47.1 በመቶ በሆነ ጠባብ አብላጫድምጽ ግብጽን ለማስተዳደር ምክር ቤቱን ተቀላቀሉ፡፡ ሙሐመድ ሙርሲም 51.7 በመቶ ድምጽ አግኝተው የሃገሪቷ ጠቅላይ ገዥ ሆኑ፡፡ነገር ግን ፕሬዘዳንት ሙርሲ የሥልጣን መንበራቸውን ከያዙ በኋላ ውሳኔያቸው በፍርድ ቤት ሳይቀር አይተችም የሚል መመሪያ አወጡ፡፡የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ቁልቁል ለቀቁት፡፡ ሕዝቡ የሙባረክ አስተዳደር በምን ጣዕሙ ይል ጀመር፡፡ የታህሪር አደባባይ በአዲሱ ፕሬዘዳንትላይ ተቃውሞ በሚያቀርቡ ግብጻዊያን በድጋሚ ተሞላች፡፡ እራሳቸው የሾሙዋቸው የወታደሪያዊ ኃላፊዎች ሙርሲ ለሃገሪቷ መፍትሄ ማምጣትአይችሉም አሉ፡፡ አደባባይ የወጡትን ሰዎች ፍላጎት እንዲያሟሉ እና ውጥረቱን እንዲያረግቡ የ48 ሰዓት ገደብ አውጡላቸው፡፡ ሙርሲአሻፈረኝ አሉ፡፡ በጭብጨባ በተሾሙ በዓመታቸው በወታደሩ ጉልበት እና በሕዝቡ ጩኸት ከመንበራቸው ተነሱ፡፡ የሙርሲ ደጋፊዎችም ዲሞክራሲለእስላም አይሠራምን? ብለው ጠየቁ፡፡ የመረጥናቸው ፕሬዘዳንት በመፈንቅለ መንግሥት ነው የተነሱትና ወደ ሥልጣናቸው ይመለሱ በሚልአመጻቸውን አቀጣጠሉ፡፡ ፖሊስ እና ወታደሩ በከፈቱት ተኩስ 54 የሙርሲ ደጋፊዎች ሐምሌ 2 ቀን ተገደሉ፡፡ አንዳንዶች በመሣሪያምሳይቀር እንዋጋለን ብለው ሲያስተጋቡ ተደመጡ፡፡
በናይል ጉዳይ ተጠመዶ የከረመው የግብጽመገናኛ ብዙሃን ለአዲሱ አብዮት ቦታውን ለቀቀ፡፡ የወታደራዊው ተቋም በድጋሚ አዲስ የሽግግር መንግስት አቋቋመ፡፡ የሽግግር መንግሥቱጊዜያዊ ፕሬዘዳንት ከፀደቀ 7 ወር ያስቆጠረውን ሕገ መንግሥት እንዲያሻሽሉ 10 የሕግ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ እንዲዋቀር መመሪያአወጡ፡፡ ግብጽም እንዲሁ በሁለት ዓመት ሁለት አብዮቶችን አስተናገደች፡፡

የናይልፖለቲካ፤ የሙርሲ አካሄድ
መሐመድ ሙርሲ ጊዜ መለወጡን ግምት ውስጥሳይከቱ፣ ኢትዮጵያ ‘ግድብ በራሴ ወጪ አሠራለሁ’ ማለቷን ሳያጤኑ፣ በፊት ከነበሩት የግብጽ አስተዳደሮች ባልተለየ የራስጌ ተፋሰስሀገሮች በናይል ላይ ምንም ፕሮጀክት መሥራት አይችሉም፣ ናይል የግብጽ ብቻ ነው የሚል አመለካከት ሲያራምዱ ተስተውለዋል፡፡ የኢትዮጵያመንግሥት የሕዳሴውን ግድብ ለመገንባት ውኃውን 500 ሜትር ማስቀየሱን ካሳወቀበት ጊዜ ተከትሎ በፕሬዘዳንታዊ ቤተመንግሥታቸው የፖለቲካፓርቲ ተወካዮችን ሰብስበው ኦነግ እና ኦጋዴንን ከመርዳት፣ ግብጽ መሳሪያ እየገዛች ነው የሚል የውሸት መረጃ እስከመልቀቅ እና ሁሉምአማራጭ ክፍት ነው እስከሚል አሳፋሪ ውይይት በቀጥታ የቴሊቪዥን ስርጭት አሳዩ፡፡ ‘የናይልን አንድ ጠብታ ውኃ ሳይቀር እንጠብቃለን’ብለው ስብሰባውን ሲዘጉ ተስተዋሉ፡፡ ‘ናይል ከቀነሰ አማራጫችን ደማችን ነው’ ብለው ከበፊት ፕሬዘዳንቶች ባልተለየ የጦርነት ታንቡርአስጋቡ፡፡ የግብጽ አርበኝነታቸውን ለማሳየት ‘የግብጽ ሕዝብ አንድ መሆን አለበት’ በማለት የውስጥ ተቃውሟቸውን ለማብረድ ሞክሩ፡፡ብዙም ባያዛልቃቸውም፡፡
ሙርሲ የተሳሳቱት ኢትዮጵያ ከበፊቱ በተሻለመረጋጋቷ እና ለግንባታው ከሀገር ውስጥ ወጪዎች መጠቀሟ ግብጽ ግንባታውን ለማስቆም የሚያስችላትን አጋጣሚ ማጥበቡን ነው፡፡ የኢሕአዴግንመንግሥት ለማናጋትም ሆነ የግድቡን ወጪ ማስከልከል እንደ በፊቱ ቀላል እንዳልሆነ ዘነጉት፡፡ የተፋሰስ ሀገራቱ የጋራ ተጠቃሚነትንየሚያበረታታ የሕግ ማዕቀፍ በመፈረም መተባበራቸውን ከወረቀት የዘለለ ትርጉም አይኖረውም የሚል አቋም አራመዱ፡፡ የውኃ ጦርነት በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚያስተች እና የማያዋጣ ተግባር መሆኑን ከግምት ሳይከቱ ማስፈራራት ተያያዙ፡፡ በተቃራኒው የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንአስመልክቶ የወሰደው እርምጃ የተረጋጋና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያበረታታ ሆኖ መቀጠሉ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትንእንድታገኝ እና በትክክለኛው አቅጣጫ እንደተራመደች አስመሰከረ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብእንዳታስፈጽም ከግብጽ ሊደርስባት የሚችለው ብቸኛ ጥቃት ለውስጥ ተቃዋሚዎች እና ለሽምቅ ተዋጊዎች መርዳት ይመስለኛል፡፡ የጠላቴጠላት ወዳጄ ነው የተለመደ የውጊያ ስልት ነው፡፡ ሕውኀት ከግብጽ ባገኘው እርዳታ ደርግ በአባይ ላይ ያስጀመረውን ግድብ መምታቱየቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥ ያሉትን እንደ ኦጋዴን እና ግንቦት 7 ያሉ ታጣቂዎችን አሸባሪ ከማለትከልማት ተጠቃሚ በማድረግ ለጥያቂያቸው ምላሽ መስጠት ይኖርበታል፡፡ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጥያቄ በአግባቡበመመልስ አንድ ኢትዮጵያን መመሥረት ከግብጽ ጥቃት ለመዳን ያለው ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ አባይን ስንገድብ የዜጎችን ሰብኣዊ መብትጥሰት አብሮ መገደብ ያስፈልጋል፡፡ ለግድቡ የሚሰበሰቡትን ገንዘቦችበግልጽነት የተለያዩ የኅብረተሰቡን ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ ኦዲት መደረግ እና ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ፕሮጀክትነቱ መረጋገጥአለበት፡፡
የሕዳሴው ግድብ በዋነኛነት ለኃይል ማመንጫጥቅም ታስቦ የተረቀቀ ነው፡፡ ከሦስቱ (ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን) ተፋሰስ ሃገሮች ሁለት፣ ሁለት እና አራት ገለልተኛ ባለሙያዎችንያሳተፈው ኮሚቴም ያቀረበው ሪፖርት ከሞላ ጎደል ግድቡ በግብጽ እና ሱዳን ላይ ወሳኝ ጉዳት እንደማያደርስ ነው፡፡ ተጨማሪ ጥናትእንደሚያስፈልግ በመግለጽ፡፡ ስለዚህ የግብጽ አስተዳደር እንደ ሱዳን ከግድቡ ያለውን ተጠቃሚነት (ከጎርፍ አደጋዎች፣ ከደለል፣ እናከርካሽ የኃይል አቅርቦት) ለማስጠበቅ ፖሊሲውን ቀስ በቀስ በማስተካከል የግድቡን ግንባታ መቀበል ብቻ ሳይሆን በባለሙያዊ እርዳታምመተባበር ይገባዋል፡፡

የምዕራብያውያንወደ ግብጽ መመለስ
 ገማል አብዱልናስርን ተከትለው የፕሬዝዳንትነቱንቦታ የተቀናጁት አንዋር ሳዳት ግብጽ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግጭት በካምፕ ዴቪድ ስምምነት ቋጩት፡፡ ወራሻቸው ሁስኒ ሙባረክም ከአውራሻቸውበተሻለ ከእስራኤል ጋር ፍቅራቸውን ጨመሩ፡፡ የእስራኤል ቀኝ እጅ አሜሪካም ከግብጽ ጋር ያላትን ወዳጅነት ጨመረች፡፡ መሣሪያ እስከአፍንጫዋ አስታጠቀቻት፡፡ ቢሊዮን ዶላሮችን በሰበብ አስባቡ ታቀብላት ጀመር፡፡ ነገር ግን እስራኤልና ግብጽ ታሪካዊ ጠላት ናቸውናፍቅራቸው ከመንግሥታት አልፎ ሕዝቡ ውስጥ መስረጽ አቃተው፡፡ በተቃራኒው የኢትዮ-ኤርትራ ጠብ በመንግሥታቱ መሃል ብቻ እንደሆነው፡፡እንግዲህ ይህ ቀዝቃዛ ፍቅር ባለበት የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ወደ ሥልጣን መጣ፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ከእስራኤል ጋር የነበረውን የካምፕዴቪድ ስምምነት ካለው ነባራዊ ፖለቲካአንጻር ቢቀበለውም፤ የእስላማዊ አስተዳደርን የሚደግፍ ሕገ መንግሥት ለመመሥረት ያለውን ፍላጎት ግልጽ አደረገ፡፡ ይህም ለአሜሪካበተለይም ለእስራኤል ስጋት የሚያሳድር ኩነት ሆነ፡፡ አሜሪካ ከሙስሊም ወንድማማቾች ይልቅ የዘመናት ወዳጇ የሆነውን የግብጽ ጦርመርጣለች፡፡ የሙርሲን ውድቀት መፈንቅለ መንግሥት ለማለት ድምጽ አንሷታል፡፡ ምክንያቱም አባባሉ በዓመት ለግብጽ የምትሰጠውን የ1.5ቢሊዮን ዶላር እርዳት እንድታቆም ሕጓ ያስገድዳታል፡፡ ፖለቲከኞቿ እንደ በፊቱ አቋማቸውን ማስቀመጥ ከብዷቸዋል፡፡ ዝምታቸው በሙርሲውድቀት እጃቸው አለበት ከሚል እስከ እስላማዊ ዲሞክራሲ በምዕራብያውያን ዘንድ አይፈቀድም ወደ ሚል ድማዳሜ እወሰደ ነው፡፡
በግብጽ ውስጥ ከእስራኤል እና/ወይም ከምዕራብያውያንጋር ተቃርኖ ያለው አስተዳደር መመሥረቱ ኢትዮጵያ በናይል ላይ ለሚሠሩ ፕሮጀክቶች በዓለም ባንክ እና በመሳሰሉት ተመካኝቶ ገንዘብእንድታገኝ መንገድ ይከፍታል፡፡ ግብጽን ለመቅጣት የናይል ወንዝ ፍሰትን ከመቀነስ ሌላ ወሳኝ አማራጭ የለም፡፡ የበፊት ተሞክሮዎችይህንን ይመሰክራሉ፡፡ ሦስት ቀደምት ተሞክሮችን እንመልከት፡፡ ግብጽ በእንግሊዝ ቀኝ ግዢ ስር በነበረችበት እ.ኢ.አ. በ1924ዓ.ም ላይ የግብጽ ወታደር ጠቅላይ ገዢ እና የሱዳን አስተዳዳሪ የነበሩት ሰሊስ ስታክ በካይሮ አደባባይ መገደላቸውን ተከትሎ የእንግሊዝመንግሥት እንደ ቅጣት በሱዳን የጎዚራ እስኪም ለተሰኘውን ትልቅ የጥጥ እርሻ የሚረዳ እ.ኢ.አ. በ1925 ዓ.ም የተጠናቀቀ የሲናግድብ ለማሠራት ምክንያት ሁኗቸዋል፡፡
የግብጹ ገማል አብዱልናስር ለአስዋን ግድብማስገንቢያ እ.ኢ.አ በ1953 ዓ.ም ከአሜሪካ የተገባላቸው ቃል በሦስት ዓመቱ በመሰረዙ ከሩስያ ለመበደር በወሰኑት መሠረት እ.ኢ.አበ1964 ዓ.ም አሜሪካ ለቀዝቃዛው ጦርነት ምላሽ በኢትዮጵያ ውስጥ በናይል ላይ ሊሠሩ የሚችሉ የኃይል ማመንጫ እና የመስኖ ፕሮጀክቶችንእንዲጠኑ አድርጋለች፡፡ የሕዳሴው ግድብም የዚህ ጥናት አንዱ ውጤት ነው፡፡ ጉልበት ከመጠቀሟ በፊት እንግሊዝ የስዊዝ ቦይን የግብጽንብረት ለማድረግ የተነሱትን ገማል አቡዱልናስር ሐሳብ ለማስለወጥ በኡጋንዳ የኦይን ፎል ግድብ ለመሥራት ዋነኛ ምክንያቷ እንደነበርይገለጻል፡፡
እስራኤል እና አሜሪካ በተለየ እንዲሁምምዕራብያውያን ባጠቃላይ የሕዳሴውን ግድብ እና ሌላ የአባይ ፕሮጀክቶችን ከግብጽ ጋር እንደ መደራደሪያነት ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡
የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ በዚህ ጊዜከሥልጣን መባረር ብቻ አይደለም፣ ሙርሲ በቁም እስር ላይ ሲሆኑ ለሌሎች አመራሮቹ የእስር ፍቃድ አቃቢ ሕግ ከፍ/ቤት እንዳወጣ ሰምተናል፡፡በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ አንድም የወንድማማቾች ፓርቲ አባል አልተሳተፈም፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ከግብጽ ፖለቲካ በድጋሚእየራቁ ይመስላል፡፡ በሚቀጥለው ምርጫም እስላማዊ ፓርቲ ካልተሳተፈ፤ የምዕራብያውያን ድጋፍ ያለው አስተዳደር እንደሚመጣ አመላካችነው፡፡ የግብጽ ወታደራዊ ተቋም ከአሜሪካ ጋር ካለው የከረመ ወዳጅነት እና የሽግግር መንግሥቱ ባለሙያዎችና ሊበራሎችን ማካተቱ ለዚህትንበያ እንደ ምክንያት ተጠቃሽ ነው፡፡ በአንዋር ሳዳት እና በሁስኒ ሙባረክ አስተዳደር ጊዜ እንደነበረው ግብጽ በሰሜን ምስራቅአፍሪካ የአሜሪካ ዋነኛ ወዳጅ መሆኗ ከቀጠለ ኢትዮጵያ የናይል ፕሮጀክቶቹን በራሷ ወጪ ማሠራቷን ትቀጥላለች፡፡ በተቃራኒው በግብጽየእስራኤልን ጠብ አጫሪ ድርጊት በመቃወም አሻፈረኝ የሚል አስተዳደር ከመጣ ቦንድ ከመግዛት የሚያስጥለን አጋጣሚ ሊመጣ ይችላል፡፡እስራኤልም ከግብጽ ጋር ያላትን ቀዝቃዝ ሠላም አመካኝታ በዓለም ላይ የታወቀችበትን በአግባቡ መስኖ የመጠቀም ልምድ ኢትዮጵያን ጨምሮለራስጌ ሀገራት ማስተማሩዋን ትቀጥላለች፡፡

የግብጽአለመረጋጋት በናይል ፖለቲካ ላይ የሚኖረው እንድምታ
ግብጽ የናይልን ውኃ ለዘመናት እንግሊዝበሰጠቻት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በመመራት በበላይነት ስትጠቀም እና ስታስተዳድር ቆይታለች፡፡ የብቻ የመጠቀም መብቷን እ.ኢ.አበ1959 ዓ.ም ሙሉ የናይል ፍሰትን ለሁለት የተከፋፈሉበትን ስምምነት በመጥቀስ ስታሰፍፅም ቆየች፡፡ የራስጌ ሀገራት ውኃውን እንዳይጠቀሙለፕሮጀክቶች የሚሰጡ እርዳታዎችን በማስከልከል፣ እርስ በርስ ጦርነቶችን በመደገፍ እና የጦርነት ዛቻዎችን በመለፈፍ የናይልን ሙሉተፋሰስ ሳይነካ ከታች ሆና ስትቀበል ኖረች፡፡ አሁን ጊዜው ተለወጠ፤ የተፋሰስ ሀገሮቹ የተረጋጋ መንግሥት ኖራቸው፣ ኢትዮጵያ በራሴወጪ ትልቅ የኃይል ማመንጫ እገነባለሁ አለች፣ ሁሉን ያሳተፈ የተፋሰስ ውኃ የሕግ ማዕቀፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስድስት የተፋሰስ ሀገሮችተፈረመ፡፡
የግብጽ አለመረጋጋት ምን ያህል ዘላቂነው? ክብደቱስ ምን ያክል ነው? የሚለው ጥያቄ የዓለም አቀፍ ተንታኞችን የሚያነጋግር ጉዳይ ሆኗል፡፡ በሕዝቡ ድምፅ ሥልጣን ላይየወጡት መሐመድ ሙርሲ በመፈንቅለ መንግሥት ነው የተነሱት በሚል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ተቃውሟቸውንቀጥለዋል፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች ደጋፊዎች ‘ዲሞክራሲያችንን ሊቀለብስ የሚሞክረውን በመሳሪያ ሳይቀር እንዋጋለን’ ሲሉ እየተደመጡነው፡፡ ሁለተኛው ትልቅ እስላማዊ ፓርቲ-ኑር ፓርቲ- የወታደራዊ አማራጮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጿል፡፡ የሙርሲ የደኅንነት አማካሪ የነበሩት ኢሳም ኤል ሀዳድ ‘መፈንቅለ መንግሥቱ ለዓለም ግልጽየሆነ መልዕክት ነው፤ ዲሞክራሲ ለእስላም አይሆንም’ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከሞላ ጎደል የግብጽ አለመረጋጋት በቀላሉ መፍትሄአይገኝለትም የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች ትንሽ አይደሉም፡፡ አዲሱ የሽግግር መንግሥት ከሁለቱ ትልልቅ እስላማዊ ፓርቲዎች – ከሙስሊምወንድማማቾችም እና ከኑር ፓርቲ – አንድ አባል ሳያሳትፍ 34 አባላትን ይዞ ተዋቅሯል፡፡ የግብጽ ዕጣ ፈንታ እርስ በእርስ ጦርነትነው የሚሉ ትንበያዎችም ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው፡፡
የግብጽ አለመረጋጋት በናይል ፖለቲካ ላይየሚኖረውን እንድምታ ከሁለት አቅጣጫ ማየት ይቻላል፡፡ በናይል ላይ የሚደራደረው የሽግግር መንግሥት ከሚኖረው አቋም እና ግብጽ ለዘመናትስታስኬደው የነበረውን ለብቻ የመጠቀም እና የማስተዳደር አካሄድ ከማስፈጸም አኳያ፡፡
የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ በኢትዮጵያናበግብጽ ተደጋጋሚ ድርድሮች ያስፈልጋሉ፡፡ በናይል ተፋሰስ ጊዜያዊ ድርጅት የውኃ ሚኒስቴሮች ስብሰባ በዓመት አንዴ ተፋሰሱ ለጋራተጠቃሚነትን ወደ ፊት የሚራመዱበትን አጋጣሚ ለማጎልበት ምክክር ያደርጋሉ፡፡ በእነዚህ ድርድሮች የሽግግር መንግስቱ በውስጥ ፖለቲካከመጠመዱ እና በሕዝቡ የተወከለ ባለመሆኑ የግብጽን አቋም በግልጽ ማስቀመጥ ያዳግተዋል፡፡ የውኃ ጦርነት ከቃላት ባያልፍም ግብጽበወታደራዊ አስተሳሰብ እንደመተዳደሩዋ የውስጡን ተቃውሞ ለማርገብ ጦርነት ወደ አማራጭ የሚመጣበት አጋጣሚም ጠባብ ቢሆንም የለምለማለት አይቻልም፡፡
ግብጽ እኔ ብቻ የሚለውን የውኃ መጠቀምአካሄድ የምታስፈፅመው በዋናነት ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ፖለቲካዋ እንዳትረጋጋ ተቃዋሚዎችን በመርዳት፣ ለፕሮጀክት የሚሰጡ ገንዘቦችንበማስከልከል እና እ.ኢ.አ በግንቦት 2011 ዓ.ም ለፊርማ ክፍት የሆነውን፤ በ6 ተፋሰሶች ተፈርሞ በኢትዮጵያ በቅርቡ የፀደቀውንየሕግ ማዕቀፍ እንዳይፀድቅ ተፋሰሱን በመደለል ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ሰዓት እራሷ ሳትረጋጋ የኢትዮጵያን አስተዳደር ማተራመስአስቸጋሪ ነው፡፡ ሁሉን አቀፍ የውኃ ስምምነቱ የተፋሰስ ሀገራቱ እንዳያፀድቁ መደለልም የተረጋጋ አስተዳደር ይፈልጋል፡፡
የፊተኞች ወደ ኋላ እንዲሉ ግብጽ በራስጌሀገራት እርስ በርስ ጦርነት እና መተራመስ ስትጠቀም እንደነበረው የራስጌ ሀገራት በግብጽ ትርምስ የሚጠቀሙበት ጊዜ የደረሰ ይመስላል፡፡
—–
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው mikiyaslaw@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡
 ምንጭ http://revolutionfordemocracy.com/2013/08/26/53-24/

No comments:

Post a Comment