Wednesday, August 28, 2013

በአዕምሮ ሁከት የተለከፈችው እህት በጅዳ! በትዞራለች… ትዞራለች… ሲደክማት ታርፈና አሁንም ትዞራለች!

ነቢዩ ሲራክ
አንድ ወዳጀ መሃመድያ ተብሎ በሚጠራው የጅዳ ከፍል ከኢትዮጵያ አለም አቀፍ ትምህር ቤት አካባቢ ይህችን በፎቶው ላይ የምታዩዋትን እህት አግኝቶ ሊያነጋግራት ቢሞክርም ፈቃደኛ አልነበረችም። ከየት ነው የመጣሽ ? ስትባል” ከመቀለ ” ከማለት ባለፈ ስሟንና የሆነችውን አትናገርም ። ብዙ ሊያግባባት ሞክሮ ያልተሳካለት ይህ ወዳጀ ይህች እህት ያደፈና የተቀደደ ጥቁር “አባያ” ለብሳና መናኛ ነጠላ ጫማ የተጫማችው እህት የአዕምሮ ሁከት እንዳለባት የተረዳው ብዙ ለማነጋገር ሞክሮ በሰጠችው አንዳንድ ምላሽ እንደሆነ ገልጾልኛል! ልጁን ትምህርት ቤት ሊያስመዘግብ በሔደበት አጋጣሚ በጠራራው ሜዳ ስትንከራተት በማየቱና ምንም መርዳት ባለመቻሉ ያዘነው ወዳጀን መረጃ ይዠ የጅዳን ቆንስል ሃላፊዎች ስልክ በመደዎል ይህችን እህት በመጠለያው አምጥተው ሌላው ቢቀር ካሉት የአዕምሮ በሽተኞች ጋር ቀላቅለው ከመኪና እና ከመሳሰሉት አደጋዎች አንዳትጋለጥ ይሰበስቧት ዘንድ ለማሳወቅ ያደረግኩት ሙከራ አልተሳካም!Ethiopian in Saudi Arabia
አንድ ሌላ ወዳጀ ከትናነት በስቲያ የዚህችን እህት አሁን ድረስ በአካባቢው መኖርና ዝም ብላ እንደምትዞር ነገረኝና ወዳለችበት አካባቢ ሔጀ በአካል ለማነጋገር ሞክሬ ነበር ። በጠራራው ጸሃይ የውሃ ፕላስቲክ ባንድ እጇ በሌላ እጇ ፊስታል አንጠልጥላ እየሳቀች እና እየተኮሳተረች ክው ክው እያለች የምትራመደው እህት አገኘኋት። ብዙ ከተከትልኳት በኋላ አረፍ ስትል ጠብቄ አማርኛ ትችያለሸ ? አልኳት “ግደፈኒ” አለችኝ ፊቷን ዘወር እያደረገች! ለማግባባትና ለማቅረብ ሞከርኩ ፣ ልታሰቀርበኝ አልቻለችም! ብዙ ተከተልኳት! … ትዞራለች …ትዞራለች …ሲደክማት ታርፈና አሁንም ትዞራለች ! በቃ ! እንዲህ ሆናለች …
ዛሬም እዚያው አካባቢ እየዞረች እንደምትገኝ ወደ ትምህርት ቤት ለጉዳዩ የሔደ ወንድም አግኝቷት በስልክ ገልጾልኛል። ስትንከራተት አይቶ ሊረዳት የፈለገው ይህ ወንድም እሱም ሆነ ያየውን የዚህች እህት አበሳ ያሳያቸው የትምህርት ቤቱ ሴት ኢትዮጵያውያን መምህራን ተከትለው ሊያነጋግሯትና ሊረዷት ቢፈልጉም ፈቃደኛ ባለመሆኗ ምንም ማድረግ እንዳልቻለ እያዘን ካነሳው ፎቶ ጭምር ልኮልኛል! ዛሬም ይህን መረጃ ለማቀበል ወደ ጅዳ ቆንስል ሃላፊ ወደ ቆንስል ጀኔራል ዘነበ ከበደ እና ቆንስል ሙንትሃ ስልክ ደውየ የነበረ ቢሆንም ሊመልሱልኝ ግን አልቻሉም! ይህ በእንዲህ እንዳለ በተፈናቃይ ሰራተኞች ዙሪያ ጥናት ለማድረግ በአንባሳደር ውብሸት የተመራ ቡድን ዛሬም በጅዳ ከቆንስል ሃላፊዎች ጋር በመምከር ላይ መሆኑን ታውቋል።
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ

 ምንጭ https://ecadforum.com/Amharic/archives/9569/

No comments:

Post a Comment