Wednesday, August 7, 2013

የኪስማዮ ዕጣ ፈንታ

የኪስማዮ ዕጣ ፈንታ

በደቡብ ሶማልያ የምትገኘው የኪስማዮ ከተማ አስተዳደር ለሶማልያ ማዕከላዊዉ መንግሥት እንዲሰጥ ሀሳብ ቀረበ። ይህንን ሀሳብ ያቀረቡት በሳምንቱ መጨረሻ በዩጋንዳ መዲና ካምፓላ የአንድ ቀን ምክክር ያካሄዱት ያካባቢ ሀገራት መሪዎች ናቸው። ይህ የቀረበው ሀሳብ በተግባር ሊተረጎም መቻል አለመቻሉ የሚመለከታቸውን ወገኖች ብዙ እያነጋገረ ነው።

ጦራቸውን በሶማልያ ለተሰማራው የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል፣ በምሕፃሩ ለአሚሶም ያዋጡ አፍሪቃውያት ሀገራት መሪዎች ከስብሰባው በኋላ ባወጡት መግለጫ ኪስማዮ፣ አየር ማረፊያው እና ወደቡ ጭምር በማዕከላዩ መንግሥት አስተዳደር ስር መግባት እንደሚኖርበት አሳስበዋል። ኪስማዩ በወቅቱ የኬንያ ጦር ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት አሸባብን ከከተማይቱ ለማስወጣት ዘመቻ ባካሄደበት ጊዜ ድጋፍ በሰጠው እና በአህመድ ማዶቤ በሚመራው የራስካምቦኒ ብርጌድ በተባለው ቡድን አስተዳደር ስር ትገኛለች። ማዶቤ በኪስማዮ ከማዕከላዊዉ መንግሥት ጋ ግንኙነት የሌለው ያካባቢ መስተዳድር ነው ያቋቋሙት። አሚሶም ላካባቢዎቹ ጦር አዋጪ ሀገራት በካምፓላ ባካሄደው ስብሰባ ማብቂያ ላይ የወጣው የመሪዎቹ መግለጫ ተግባራዊ ማድረጉ ግን ቀላል እንደማይሆን፣ ከዚያ በፊት ሁለቱ ወገኖች መግባባት ላይ ሊደርሱ እንደሚገባ ነው ፕሪቶርያ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ አንድሩስ አታ አሳሞአ የገለጹት።

«በመጀመሪያ በማዕከላዩ መንግሥት እና ባካባቢው አስተዳደር መካከል ሰላም ይወርድ ዘንድ አንዳንድ ጉዳዮች ማስተካከል ይኖርባቸዋል። አስተዳደሩ በማዶቤ መያዙን ማዕከላዊዉ መንግሥት ያልደገፈበት ምክንያት ከከተማይቱ፣ በተለይም ከአየር ማረፊያው እና ከወደቡ በሚገኘው ገቢ የተነሳ ነው። ስለዚህ ይህ ወሳኝ ገቢ በማዕከላዊዉ መንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲዲውል ከማዶቤ ያካባቢ አስተዳደር ጋ የሆነ ስምምነት መደረስ ይኖርበታል። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት የሀገሪቱን ሀብት ክፍፍል በተመለከተ በጊዚያዊ ሕገ መንግሥት ላይ የሰፈረው አንቀጽ ግልጽነት ይጎድለዋል። ማዕከላዊዉ መንግሥት ለሕዝቡ አስፈላጊውን ያቀርብ ዘንድ ከገቢው መካከል የተወሰነውን መቆጣጠር ይኖርበታል። »
የመሪዎቹ መግለጫ በተለይ የራስካምቦኒን ቡድን ይደግፋል በሚል ወቀሳ በተሰነዘረበት በኬንያ ጦር ላይ ግፊት አሳርፎበታል።
ምክንያቱም መሪዎቹ በከተማይቱ ከኬንያውያኑ በተሻለ ገለልተኛ የሆነ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል፣ /አሚሶም ኃይል / እንዲሰማራም በተጨማሪ ጠይቀዋል። አታ አሳሞአ የኪስማዮን አየር ማረፊያን እና ወደብ በወታደራዊ ርምጃ ለማዛወር የሚደረግ ሙከራ የተሳሳተ ሆኖ ነው የሚያዩት። እንደ አታ አሳሞአ አስተያየት፣ የወደብ ከተማዋን ለማዕከላዊዉ መንግሥት ለማዛወሩ ጥረት ከድርድር በስተቀር ሌላ የተሻለ አማራጭ አይኖርም።
«ይህንን ጉዳይ በጦር ኃይሉ ርምጃ ለመፍታት የሚደረግ ሙከራ ሁኔታዎችን አባብሶ በኪስማዮ ውጥረቱን ይበልጡን ያካርራል። የአሸባብን የመጠናከርንም ዕድል ያሰፋል። መንግሥት ሌላ አማራጭ መፍትሔ ማፈላለግ እንጂ ወታደራዊውን ርምጃ መውሰድ አይገባውም።»

አርያም ተክሌ
ሸዋዬ ለገሠ

source...dw.de

No comments:

Post a Comment