በፀረ-ሽብር አዋጁ ፓርቲዎች
ሊከራከሩ ነው
-
ኢህአዴግ፣ መድረክ፣ አንድነት፣
ሰማያዊ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ከፀደቀ አራት ዓመታት በላይ በማወዛገብ ላይ ያለው
የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ላይ ፓርቲዎች በመጪው ቅዳሜ ክርክር ሊያደርጉ ነው። የክርክር መድረኩን ያዘጋጀው
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ነው።
ተቋሙ በፀረ-ሽብር አዋጁ ላይ እንዲከራከሩ ገዢውን ፓርቲ
ጨምሮ መድረክ አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ጋብዟል። መኢአድ ግን ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ በክርክር
መድረኩ አለመጋበዙን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አበባው መሐሪ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል። ባለፈው አርብ የኢትዮጵያ ሬዲዮና
ቴሌቭዥን ድርጅት ፓርቲዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ክርክር መድረክ እንዲመጡ በደብዳቤ ጥያቄ ቢያቀርብም፤ አንድነት ፓርቲ በቂ
ጊዜ ይሰጠን በማለቱ ትናንት ይደረጋል የተባለው ክርክር ወደ ቅዳሜ እንዲተላለፍ መደረጉን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ ተናግረዋል።
መድረክ በክርክር መድረኩ ለመሳተፍ ተወካይ መመደቡን
የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንዳሻው የገለፁ ሲሆን፤ እስካሁን በክርክር መድረኮች ተጋብዞ የማያውቀው ሰማያዊ ፓርቲ
በክርክር መድረኩ ተጋብዟል። ፓርቲውም በሊቀመንበሩ በኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እንደሚወከል ታውቋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ
ከማል ከፓርቲዎቹ ጋር ስለሚደረገው ክርክር ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው “ክርክርና ድርድር የተለያየ ነው። መንግስትም ሆነ
ኢህአዴግ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ለመከራከር ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ አያውቅም። በዚህ መነሻ ጣቢያው በራሱ ተነሳሽነት ወቅታዊና
አንገብጋቢ ጉዳዮችን በመለየት የማወያየት ተግባሩን እየተወጣ ነው” ብለዋል።
በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ የሚካሄደውን ክርክርን ተከትሎ
“መንግስት የፀረ-ሽብር አዋጁን ሊያሻሽል ነው” እየተባለ የሚነገረውን አስተያየት ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አቶ ሽመልስ
አስተባብለዋል።¾
በታላቁ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥ
የሠራተኞች ተሳትፎ ከባለሃብቶች
በልጧል
§ መንግስት ዲያስፖራውንና ባለሃብቱን በማንቀሳቀስ ረገድ ባሳየው ድክመት ተተቸ
§ አርሶአደሩንና አርብቶአደሩን ለማሳተፍ የታዘው ዕቅድ ዘንድሮ አልተሳካም
በፍሬው አበበ
የታላቁ
የኢትዮጽያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ባለሃብቱና እና በውጪ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ) ይልቅ
የመንግስት ሠራተኞችና አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የገቡትን ቃል በትክክል መወጣታቸው ተጠቆመ።
የታላቁ የኢትዮጽያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ
አስተባባሪ በብሔራዊ ምክርቤት ሐምሌ 26 ቀን 2005 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል ባካሄደው አራተኛ መደበኛ ጉባዔ በተለይ
ባለሃብቶች ለግድቡ ግንባታ ቃል ከገቡት ገንዘብ ውስጥ እስካሁን መስጠት የቻሉት 40 በመቶውን ብቻ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በጠቅላላው 10.2 ቢሊየን ብር በላይ
ሕዝቡ ለማዋጣት ቃል መግባቱን ሆኖም ከዚህ ብር ውስጥ መሰብሰብ የተቻለው 5.2 ቢሊየን ብር ብቻ መሆኑን የቀረበው ሪፖርት
ያሳያል። ከመንግስት ሠራተኞች ይሰበሰባል ተብሎ ከታሰበው 1.8 ቢሊየን ብር ውስጥ 1.6 ቢሊየን (89 በመቶ) መሰብሰብ
የተቻለ ሲሆን በአንጻሩ ከባለሃብቶች ቃል ከተገባው ገንዘብ ማለትም 2.8 ቢሊየን ብር ውስጥ 1.1 ቢሊየን ብር ገደማ (40
በመቶ) ያህሉ ብቻ ሊሰበሰብ ችሏል። ለዚህ ምክንያቱ ባለሃብቶቹ የኢንቨስትመንት ስራዎቻቸውን በማስቀደማቸው እንደሆነ በሪፖርቱ
ቢጠቅስም በምክርቤቱ ስብሰባ ላይ የተገኙ አንድ ባለሃብት ግን አብዛኛው ባለሃብት በባንክ ብድር የሚንቀሳቀስ መሆኑን በመጥቀስ
“አጽሙ ብቻ ነው፤ የቀረው” ሲሉ ባለሃብቱ ጋር ያለውን ተጨባጭ ችግር ለማሳየት መሞከራቸውን አንድ ስብሰባውን የተከታተለ
ምንጫችን ለሰንደቅ ገልጾአል።
በተጨማሪም በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን
በቦንድ ግዥ ለማሳተፍ የተደረገው ጥረት አመርቂ አለመሆኑ በውይይት ወቅት የተነሳ መሆኑን ምንጫችን ጠቅሶ በተለይ መንግሥት ባለሃብቱንና
ዲያስፖራውን አሳምኖ በማንቀሳቀስ ረገድ ድክመት ማሳየቱን በግልጽ መነሳቱን፣ ይህን ችግር ለመቅረፍም የምክርቤቱ አባላትና ታዋቂ
ግለሰቦች እንዲሁም የመንግስት አካላት ያሉበት የልዑካን ቡድን ወደተለያዩ አገራት በመጓዝ የማግባባት ስራ የሚያከናውንበት ሁኔታ
እንዲመቻች ጠይቀዋል።
ይህም ሆኖ ሪፖርቱ ዲያስፖራውን ለማሳመን የተደረጉ
የመንግስት ጥረቶችን ይዘረዝራል። “በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ
የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት በገቡት ቃል መሰረት የቦንድ ግዥውን ለማስፈፀም በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ሚሲዮኖቻችን ሰፋ
ያለ እንቅስቃሴ አካሂደዋል። እንቅስቃሴው በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካና በአውስትራሊያ የሚገኙ ዜጎችን
በማወያየትና በማግባባት እንዲሁም አደራጅቶ በማንቀሳቀስ ሲፈፀም የቆየ ሲሆን፤ ስራው ገና በጅምር ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።
እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ መጠነኛ የቦንድ ሽያጭ በውጭ ምንዛሪ የተካሄደ ሲሆን ስራውን ለማስፋፋትና ይበልጥ ውጤታማ
ለማድረግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖቻችን በተደራጀ አኳኋን በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው።
በውጭ የሚካሄደው የቦንድ ሽያጭ በየአገሩ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚታየውን የኢኮኖሚ ቀውስና ሌሎች ማነቆዎችን በማለፍ
ብቻ የሚሳካ ሲሆን፤ ሽያጩን ለማጠናከር እና አስፈላጊው ውጤት እንዲገኝ ለማስቻል የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ጋር በመሆን ስራውን የሚጠይቀውን ወቅታዊ ክትትል በማድረግ እንዲሁም የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ቀምሮ በማስፋት እንዲተገበሩ
የሚያደርግ ይሆናል።”
ከቦንድ ሽያጭ አኳያ ሌላው ትኩረት የተሰጠው ለከተማ
ነዋሪዎች፣ ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ተሳትፎ ነበር። በዚህ መሰረት ከከተሞች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ
ወገኖች እንደሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ሁሉ በአንድ በኩል በግድቡ ግንባታ እንዲሳተፉ ለማድረግ በሌላ በኩል በዚያው የቁጠባ
ባህላቸውን ለመገንባት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መካሄዳቸውን ሪፖርቱ ያትታል።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ
ምርቶቻቸው የተሻለ የገበያ ዋጋ የሚያገኙበትን እና መንግስት የሚሰጣቸውን ልዩ ልዩ ድጋፎች ታሳቢ በማድረግ አርሶ አደሩና
አርብቶ አደሩ ባሳለፍነው ዓመት ሰፋ ያለ የቦንድ ግዥ እንዲያከናውኑ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ አርሶ አደሩ ለእርሻ ስራዎቹ
የሚውሉ የተለያዩ ግብአቶች መግዣ እጅ በእጅ እየከፈለ ተጠቃሚ መሆን መቻሉ እና ለመደበኛ ቁጠባ የቅድሚያ ፍላጎት በማሳየቱ
እንዲሁም በየደረጃው ያለው የፖለቲካ አመራር በተለያዩ ወቅታዊ ተግባራት በመጠመዱ በአርሶ አደሩ እና በአርብቶ አደሩ አካባቢ
ያለው የቦንድ ስራ የሚጠበቀውን ያህል ትኩረት ባለመስጠቱ ምክንያት ዕቅዱ ትርጉም ባለው ደረጃ በተግባር ላይ ሳይውል ቀርቷል።
በአርብቶ አደሩ አካባቢም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሁኔታ ስለነበር በሁለቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቦንድ ግዥን ለማስፋፋት
የሚከናወነው ስራ በቀጣይ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትንና በየደረጃው ያሉትን የሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ም/ቤት መዋቅሮችን
በመጠቀም የቦንድ ሽያጭ ትኩረት ተሰጥቶት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚደረግ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይ የመንግስት ሰራተኛው እና
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ግዥ ያሳዩት ተሳትፎ የላቀ ሲሆን ይህ የሕዝቡ ተሳትፎ ከዚህ ቀደም ታይቶ
የማይታወቅ እና ለብሔራዊ መግባባትም ሆነ የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ግንባታ አጠናክሮ ከማስቀጠል አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ
ይኖረዋል ተብሎ እንደሚታመን ተመልክቷል።
ቃል በገቡት መሰረት ክፍያቸውን መቶ በመቶ ያጠናቀቁትንና
በማጠናቀቅ ላይ ያሉትን የመንግስት ሠራተኞች፣ ባለሃብቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በታላቅ አገራዊና ልማታዊ መንፈስ
ተነሳስተው ቃላቸውን በተግባር ላይ በማዋላቸው እንዲሁም ሁለተኛ ዙር ክፍያ ለጀመሩት የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ
አስተባባሪ ምክር ቤቱ ምስጋና አቅርቧል።
በስብሰባው ላይ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ
አስተባባሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የም/ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ በረከት ስምኦን እንዲሁም
የም/ቤቱ አባላት የሆኑ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሃብቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የመሳሰሉት ተገኝተዋል።¾
በሙስና የተከሰሱት የኢትዮጵያ
ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ዋስትና ተከለከሉ
በአሸናፊ ደምሴ
በሁለት
መዝገቦች የተመሠረተባቸውን ክስ ያደመጡት አስራ አንዱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች ያቀረቡትን
የዋስትና ጥያቄ፤ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በትናንትናው ዕለት ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም ውድቅ
አደረገው። ተጠርጣሪዎቹ ክስ የተመሰረተባቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮችን በሰፕላየር ክሬዲት ለመግዛት አውጥቶት ከነበረው ዓለም
አቀፍ ጨረታ ጋር በተገናኘ የፌዴራሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ ሙስና ተፈፅሟል በማለቱ ነው።
የኮሚሽኑ
ዐቃቤ ሕግ በእነ ሽፈራው ተሊላ መዝገብ ስር ጉዳያቸውን በአካል ቀርበው የተከታተሉት ሰባት ተከሳሾችን ሶስት የወንጀል ክሶችን
መስርቶባቸዋል። በዚህ መዝገብ ስር በአገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ 1ኛ ተከሳሽ
ሆነው ሲቀርቡ፤ በቅደም ተከተልም በኮርፖሬሽኑ የአገር አቀፍ ፕሮጀክቶች ዋና ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቱሳላ፣ በኮርፖሬሽኑ የአገር
አቀፍ የሰፕላይ ቼን ኃላፊ አቶ ዳንኤል ገ/ስላሴ፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሥልጠናና የሰው ኃይል አስተዳደር
ኃላፊ አቶ ሰመረ አሳቤ፣ በኮርፖሬሽኑ የጨረታ ገምጋሚ ኮሚቴ አባል አቶ አሸናፊ ዮሃንስ፣ የኮርፖሬሽኑ የአገር አቀፍ ፕሮጀክቶች
ቁጥጥርና ልማት ኃላፊ አቶ ፋሪስ አደም፣ በኮርፖሬሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፕሮጀክቶች ፋይናንስ
ኦፊሰር አቶ ብሩክ ተገኝ እና 8ኛው ተከሳሽ በኮርፖሬሽኑ የዲስትሪክት ኔትዎርክ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አዳነ ይገኙበታል። በዚሁ
መዝገብ ስር ሁለት ህንዳውያንም ተካተው መቅረባቸውን መዝገቡ ያስረዳል።
የፌዴራሉ
የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ በዚህ መዝገብ ስር ክስ በመሰረተባቸው የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ላይ ሥልጣናቸውን
ያለአግባብ በመጠቀም ህዝብና መንግስትን ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲያጡና ኪሳራ እንዲደርስም አድርገዋል ሲል ይከሳቸዋል።
የኮርፖሬሽኑ
የስራ ኃላፊዎች እርስ በእርሳቸው በመመሳጠርና የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት በመሻት፤ ህጋዊና የመስሪያ ቤቱን የጨረታ አካሄድ
ባልተከተለ መልኩ ጉድላክ ስቲል ሊሚትድ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር የተጀመረውን የዲስትሪቢዩሽን ትራንስ ፎርመሮችን የመግዛት ውል
የኮርፖሬሽኑ የበላይ ኃላፊዎች ባላወቁት መንገድ፤ በፋይናንስ አቅራቢነት ተመርጦ የነበረው የኮብራ ኢንስታሌሽን ስዋይ ስርቪዬስ
አንዲያ ድርጅት ጨረታውን ጠቅልሎ እንዲወስድና ዕድሜያቸውና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ ናቸው የተባሉ ትራንስፎርመሮችን ግዢ
እንዲፈፀም በዚህም ሀገሪቱ ላጋጠማት ተደጋጋሚ የኃይል መቋረጥና ጥገና የኪሳራ ምክንያት ሆነዋል ሲል በክስ መዝገቡ ይዘረዝራል።
በተመሳሳይም
በሁለተኛው መዝገብ ስር በእነመስፍን ብርሃኔ በኮርፖሬሽኑ የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም የስራ ኃላፊ፣ በኮፖሬሽኑ የሲስተምና
የደንበኞች አገልግሎት ድጋፍ ክፍል ኃላፊ አቶ ሞገስ በላቸው እና በኮርፖሬሽኑ የዲስትርቢዩሽን ሲስተም የቴክኒክ ክፍል ቡድን
መሪ አቶ መኮንን ብርሃኔ በሶስት የተለያዩ ክሶች ይዘረዝራሉ። የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳውም በአጠቃላይ ህጋዊ ጨረታውን
ያሸነፈው የህንዱ ጉድላክ ኩባንያ ሆኖ ሳለ በፋይናንስ አቅርቦት ስም የሶስትዮሽ ስምምነቱን በይፋ ለተቀላቀለው ኮብራ የተሰኘው
የህንድ ኩባንያ ስምምነቱን አሳልፎ በመስጠት፤ የኮርፖሬሽኑ የሕግ ክፍል “ጉድላክ” የተሰኘው ኩባንያ ከስምምነቱ እንዳይወጣ
ቢልም ሳይሆን በመቅረቱ ይህን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጋር የገባውን የውል ስምምነት ማፍረሻ መክፈል
ሲገባው 281ሺህ 792 ዶላር ይዞ እንዲወጣ መደረጉን በመጥቀስ፤ ዐቃቤ ሕግ መንግስትና ህዝብ የሰጣቸውን ሥልጣን ያለአግባብ
ለግል ጥቅማቸው ለማዋል ሲሉ የሀገርን ሀብት ጎድተዋል ሲል ክስ መስርቶባቸዋል።
በትናንትናው
ዕለትም በችሎቱ የቀረቡት የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች የተመሰረተባቸው ክስ ግልባጭ በእጃቸው እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ሙሉ
ክሱ በፍርድ ቤቱ በንባብ ቀርቦላቸዋል። ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝም ክሱ የቅድመ ክስ ዝግጅት እንዲደረግበት የወሰነ ሲሆን፤
ዐቃቤ ሕግ ክሱን ያቋቁሙልኛል ያላቸውን አንቀፆችና ማስረጃዎች ለፍርድ ቤት ሲያቀርብ፤ ተከሳሾች በበኩላቸው ክሱ ላይ ያላቸውን
ተቃውሞዎችና የመከላከያ ኃሳቦች ካቀረቡ በኋላ የዐቃቤ ሕግን የምላሽ አስተያየት በማድመጥ ፍርድ ቤቱ የቅድመ -ክስ ብይኑን
እንደሚሰጥ አስታውቋል።
በችሎቱ
የቀረቡት የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎችም ቤተሰብ አስተዳዳሪዎችና የሚያከናውኗቸው በርካታ ተግባራት እንዳሉ በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ የዋስትና
መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ጠይቀዋል። ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የተቃውሞ አስተያየትም እስካሁን በቁጥጥር ስር ያላዋላቸው ቀሪ
ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን በማስታወስ፣ ተጠርጣሪዎቹ ፈፅመውታል ተብሎ በሚጠረጠረው ወንጀል የተጠቀሰው አንቀፅም ጥፋተኛ ሆነው
ከተገኙ ከ10 ዓመት ያላነሰ እስራትን የሚያስከትል መሆኑን በማስታወስ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲሆን ጠይቋል።
የፌዴራሉ
ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎትም የሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች ሃሳብ ካደመጠ በኋላ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ
ውድቅ በማድረግ ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥቅምት 7 ቀን 2006 ዓ.ም ሰጥቷል።¾
የመላው ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ
ፓርቲ ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ችግር አይፈታም አለ
መስከረም አያሌው
የኦሮሚያ
ክልልን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በኃይል ላይ የተመረኮዘ
መንገድ መጠቀሙ የኦሮሞን ህዝብ ችግር መፍታት እንደማይችል ያሳያል ሲል የመላው ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ገለፀ።
ፓርቲው
ባወጣው መግለጫ ኦህዴድ የኦሮሞን ሕዝበ - ሙስሊም ጥያቄም ሆነ የአጠቃላይ የኦሮሞን ህዝብ መብት ማስከበር እና ፍላጎቱን
የማሟላት የማይችል፤ እንዲሁም የህዝቡን ችግር መፍታት የማይችል ድርጅት ነው ብሏል። ድርጅቱ ጊዜ ካለፈበት በኃይል ችግርን
መፍታት አሰራር ታርሞ ዘመናዊ ወደሆነው ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመጣም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።
ድርጅቱ
በአርሲ ዞን አሳሳ ከተማ የኦሮሞ ሙስሊምን ጥያቄ በጠመንጃ ለመፍታት ባደረገው ሙከራ የሶስት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን፣
በበርካቶች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን እና ንብረትም መውደሙን የገለፀው ፓርቲው፤ ድርጅቱ ካለፈው ስህተቱ ሳይማር በአሁኑ
ወቅትም ተመሳሳይ ድርጊቶችን እየፈፀመ መሆኑን ገልጿል። በዚህም ሳቢያ ችግሩ ተስፋፍቶ በሐምሌ 27 ቀን 2005 ዓ.ም በአሳሳ
ከተማ፣ ከዚያ በፊትም በዶዶላ፣ በኮፈሌ እና በሻሸመኔ የህዝብ ሙስሊሙ ጥያቄ ሊቀሰቀስ ችሏል ብሏል።
“ኦህዴድ
ከዚህ በፊት የፈፀመው ስህተት ሳያንሰው በአሁኑ ሰዓትም ለችግሩ መፍትሔ የጠመንጃ አፈሙዝ በመጠቀም በአስር ሰዎች ላይ ሞት እና
በብዙ ሰዎች ላይም የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል” ያለው ፓርቲው፤ ኦህዴድ እየተጠቀመ ያለው የችግር አፈታት ዘዴ በኃይል ላይ
የተመረኮዘ በመሆኑ ዛሬ ያለውንም ሆነ የወደፊቱን የኦሮሞ ህዝብ ችግር መፍታት የማይችል ድርጅት ነው ብሎታል። እየፈፀመ ያለው
ድርጊት ከፍተኛ ስህተት ከመሆኑም ውጪ መፍትሄ የማያመጣ ስለሆነ ድርጅቱ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ እና ለችግሩ በውይይት መፍትሔ
እንዲፈልግ ፓርቲው ጨምሮ አሳስቧል።¾
(ምንጭ፡-
ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 413 ነሐሴ 01/2005)
No comments:
Post a Comment