Tuesday, August 6, 2013

ሞስኮ ለድግሷ ብዙም ትኩረት የሰጠች አትመስልም

ሞስኮ ለድግሷ ብዙም ትኩረት የሰጠች አትመስልም: Moscow doesn't seem to give much attention to host the IAAF World Championships


በሰላም ገብቻለሁ - ሞስኮ ለድግሷ ብዙም ትኩረት የሰጠች አትመስልም

ትላንት ምሽት ከውድቅት ለሊት በኋላ 7፡15 ላይ የተጀመረው ጉዞ ዛሬ ምሳ ሰዓት ላይ ሞስኮ ቭኖኮቭ አየር ማረፊያ በመድረስ በሰላም ተጠናቋል፡፡
ትላንት አዲስ አበባ ላይ እኝኝ ሲል የዋለው ዝናብ እኩለ ለሊት ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን ስለቅ የሸኘኝም ቀኑን ሙሉ በዋለበት አኳኋን ነበር፡፡ በቦሩሲያ ዶርትሙንድ ዓርማና ስም ባሸበረቀው እና የክለቡ ንብረት በሚመስለው የቱርክ አየር መንገድ ቦይንግ አውሮፕላን ተሳፍሬ 5 ሰዓት ከ25 ደቂቃ በፈጀ ጉዞ ማለዳ ላይ በወደብ ከተማዋ ኢስታንቡል በሚገኘው አታቱርክ አየር ማረፊያ ለሁለት ሰዓት ያህል በቆየሁበት የሽግግር ግዜ የነበረው ሙቀት ምሽት ሸገር ላይ የሸኘኝን ብርድ ለመከላከል የደረብኩትን ሹራብና ጃኬት ለማውለቅ አስገድዶኛል፡፡
ወደመጨረሻው መዳረሻዬ የሚወስደኝ ቀጣይ የቱርክ አየር መንገድ ጉዞም ሁለት ሰዓት ከሀያ ደቂቃ ፈጅቶ በእኛ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 5፡15 (በሞስኮ 6፡15) ለ2013 የዓለም ሻምፒዮና የሚመጡ እንግዶች ከሚገቡበት አየር ማረፊያዎች አንዱ በሆነው የሞስኮው ቭኖኮቭ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ ደረስሁ፡፡ እንደደረስኩ ያየሁት ነገር እነዚህ ሰዎች የዓመቱን ትልቅ አለም አቀፍ ውድድር የሚያስተናግዱ መሆናቸውን ዘንግተውት ነው ወይስ እኔ የገባሁበት አየር ማረፊያ ብዙም እንግዶች የማይስተናገዱበት በመሆኑ? የሚል ጥያቄ ወደአዕምሮዬ እንዲመጣ አደረገ፡፡
በነገራችን ላይ በኢስታንቡል አታቱርክ አየር ማረፊያ በተለያዩ በረራዎች መጥተው መዳረሻቸውን የቭኖኮቭ ኢንተርናሽናል ተርሚናል ያደረጉ ሁለት የስዋዚላንድ አትሌቶች እንዲሁም አንድ የማላዊ 5 ሺህ ሜትር ሯጭ እና አሰልጣኙን ባደረግነው የሀሳብ ልውውጥ ለዓለም ሻምፒዮናው እየተጓዙ እንደሆነ ነግረውኝ ስለነበር እነርሱም ላይ የእኔ አይነት ግራ መጋባት አይቼባቸዋለሁ፡፡
ፓስፖርታችንን ቼክ አስደርገን ለማለፍ በሌሎች ትልልቅ ውድድሮች ላይ ለውድድሩ ለሚመጡ ሰዎች የሚዘጋጅ ልዩ ዴስክ ብንፈልግም ማግኘት ስላልቻልን የሩሲያ እና ቤላሩስ ዜጎችን እንዲሁም ቪአይፒ ዲፕሎማቲኮችን ብቻ ከሚያስተናግዱት መስኮቶች ውጭ የነበርነውን ሰዎች ወደሚያስተናግደው ብቸኛ መስኮት ሄደን ረጅሙን ሰልፍ ለመቀላቀል ተገደናል፡፡
በዚህ ግዜ ይህ የሆነው ምናልባት እኛ ቀድመን ስለመጣን ይሆናል እያልኩ እያሰብ ነበር፡፡ ይህን በማሰብ ላይ እያለሁ ደግሞ ‹‹ሞስኮው 2013›› የሚል አርማ የያዘች እና አርማው የተለጠፈበትን ቲሸርት የለበሰች በጎ ፈቃደኛ ወጣት ወደእኛ መጥታ ለዓለም ሻምፒዮናው የመጣችሁ እንግዶች ናችሁ? ስትለን አዎ ስላልናት ተከተሉኝ ብላ ከረጅሙ ሰልፍ ወደዲፕሎማቲኮቹ መስኮት ሄደን እንድንስተናገድ ልታደርግ ሞከረች፡፡ ዲፕሎማቶቹን ታስተናግድ የነበረችው ሴት ግን ሀገራቸው ላይ ስላለው ትልቅ ውድድር ምንም የማታውቅ በሚመስል መልኩ ለምን ይዘሻቸው መጣሽ? አይነት ጥያቄ በመሰንዘሯ አለቆቿን ደውላ እንድታናግር እና እንድትረዳ በመንገር ቅድሚያ ተሰጥቶን እንድንስተናገድ ተደርገናል፡፡ የፓስፖርት ቁጥጥሩን አልፈን ሻንጣችንን ካገኘን በኋላ ወደሶስት የሚሆኑ ለውድድሩ ለሚመጡ እንግዶች ትራንስፖርት የሚያቀርቡ በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሄድ የምናርፍበትን ሆቴል አሳውቀን እነርሱም የትራንስፖርት አገልግሎቱን የሚሰጡት መኪኖች በየተወሰነ ሰዓት ስለሚመጡ ትንሽ በትዕግስት እንድንጠባበቅ በትህትና ገልፀውልን በአካበቢው በነበሩ ማረፊያ ወንበሮች ላይ ቁጭ አልን፡፡
እንዳጋጣሚ ሆኖ እኔ የተጋበዝኩት በውድድሩ የበላይ አካል ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር ስለነበር በማረፊያ ስፍራው ቁጭ ብለን ትራንስፖርት እስኪመጣ እንድንጠባበቅ ከተነገረን ሰዎች መካከል (እዚህ ጋር የጆርጂያ እና ጥቂት አባላት ያሉት የአንድ አረብ ሀገር አትሌቶችም ተቀላቅለውን ነበር) እኔ ተለይቼ ተጠርቼ የውድድሩ ስፖንሰር ቶዮታ ባቀረበው ምቾት ያለው መኪና ወደማርፍበት ሆቴል እንድሄድ ተደርጌያለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ለእኔ የተደረገልኝን እንክብካቤ ወይም በስፍራው የነበሩት በጎ ፈቃደኞች ሁላችንንም ለመርዳት ሲያደርጉ የነበረውን ጥረትም ሆነ ሌሎች ነገሮችን መግለፄ የጉዞዬ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለወዳጆቼ ለማመላከት ያህል እንጂ ከላይ ለዚህ ፅሁፍ በርዕስነት የተጠቀምኩትን አረፍተ ነገር እንድጠቀም ያነሳሳኝ እኔ ከገባሁበት አየር ማረፊያ እስከማርፍበት ሆቴል 40 ደቂቃ ይፈጃል ተብዬ በነበረው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ሶስት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ በፈጀው ጉዞዬ የተመለከትኩት ነገር ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በ2009 የፊፋ የዓለም የክለቦች ዋንጫን በአቡ ዳቢ እንዲሁም ባለፈው ዓመት የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ለመዘገብ በለንደን በተገኘሁበት ወቅት ከተሞቹ የሆነ ትልቅ የውድድር ድግስ እንዳለባቸው የሚያሳዩ ነገሮችን ከአየር ማረፊያ ጀምሮ እመለከት ነበር፡፡ በሞስኮ የከተማዋን የተወሰነውን ክፍል ባሳየኝ የመኪና ጉዞ ግን ስለዓለም ሻምፒዮናው ውድድር የሚገልፅ ምንም አይነት የማስታወቂያ ፖስተር አልነበረም፡፡
እንዲያውም በየመንገዱ ዳር ጎልቶ ያየሁት ነገር ቢኖር በሁለቱ የከባድ ሚዛን የኦሊምፒክ ሻምፒዮኖች ቭላድሚር ክሊችኮ እና አሌግዛንደር ፖቬትኪን መካከል የፊታችን ኦክቶበር 5 ሞስኮ ውስጥ የሚከናወነውን የቦክስ ግጥሚያ የሚያስተዋውቅ ፖስተር ነው፡፡
በጉዞ እና እንቅልፍ ማነስ በመዳከሜ ምክንያት አክሬዲቴሽኔን ለመቀበልና ውድድሩ በሚካሄድበት ስታድየም አካባቢ ያለውን ሁኔታ ለመመልከት በተጨናነቀ የትራፊክ ፍሰት ውስጥ ለሚደረግ ሌላ አድካሚ የመኪና ጉዞ የሚሆን አቅም ስላልነበረኝ ገብቼ ለመተኛት ተገድጃለሁ፡፡ ይህን መረጃ የፃፍኩትም ተኝቼ ከተነሳሁ በኋላ ድካሙ ቀለል ሲልለኝ በቤስት ዌስተርን ቬጋ ሆቴል 19ኛ ፎቅ ላይ ካለውና የሎኮሞቲቭ ሞስኮን ስታድየም እንዲሁም የከተማውን የተለያዩ ክፍሎች ከሚያሳየኝ የክፍሌ መስኮት አጠገብ ቁጭ ብዬ ነበር፡፡ እንደደረስኩ ሞቃት የነበረው የሞስኮ አየር ሁኔታ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ቅዝቃዜው ያየለ ነበር፡፡
በነገው ዕለት ወደሉዝኒኪ ስታድየም በማቅናት በከተማዋ እምብርት አካባቢ ስላለው ሁኔታ ልገልፅላችሁ እሞክራለሁ፡፡ ዛሬ ካየሁት ነገር አንፃር እያስፈራኝ ያለው አንድ ነገር ግን የትራፊክ መጨናነቁ ከሆቴል ወደስታድየም በሚደረገው ጉዞ ላይም ችግር እንዳይፈጥር ነው፡፡ ጓደኞቼ በድጋሚ ልተኛ ነው... የነገ ሰው ይበለን! 
sodere...

No comments:

Post a Comment