Tuesday, August 6, 2013

ዘረኝነት በምሥራቅ ጀርመን


ዘረኝነት በምሥራቅ ጀርመን

ጀርመን ውስጥ በተለይ በምሥራቅ ጀርመን ዘረኝነት ከቀድሞው እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑን አንድ ጥናት አስታውቋል ። የጀርመን መንግሥት ምስራቅ ጀርመን ውስጥ በሚገኙ ፌደራል ግዛቶች ዘረኝነትን ለመከላከል ተግባራዊ ያደረገው መርህም ለውጥ አለማምጣቱ በጥናቱ ተገልጿል ።
ከ 3 ወራት በፊት በጀርመኑ የላይፕሲሽ ዩኒቨርስቲ በተካሄደ ጥናት መሠረት በቀድሞዎቹ የምዕራብ ጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች ዘረኝነት በአሁኑ ትውልድ ዘንድ እየቀነሰ መጥቷል ። ይህ እየሰየው የሚያሰኝ ቢሆንም በአንፃሩ በምሥራቅ ጀርመን ከ10 ወይም ከ20 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር አሁን ዘረኝነት ተባብሷል ። በመላ ጀርመን 2500 በሚሆኑ ቤቶች በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ከ36 በመቶ በላይ የሚሆኑ ጀርመናውያን የውጭ ዜጎች ወደ ጀርመን የሚመጡት ከሃገሪቱ የማህበራዊ ድጎማ ስርዓት ተጠቃሚ ለመሆን ነው የሚል አስተሳሰብ ነው ያላቸው ። 33 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ስራ ማግኘት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው ጊዜያት የውጭ ዜጎች ወደ ሃገራቸው መባረር አለባቸው ብለው ያስባሉ ።ይኽው ጥናት በሃገሪቱ የውጭ ዜጎች ጥላቻ ከፍተኛ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ከበፊቱ መጨመሩንም ነው ያመለከተው ።
ዶክተር መኮንን ሽፈራው

ምክንያቱ ምንድነው ? መፍትሄስ ? በዛሬው ዝግጅታችን የሚነሱ ነጥቦች ናቸው ። ከዚያ በፊት ግን ዘረኝነት በጀርመን ምን ገፅታ እንዳለው መቀመጫውን በርሊን ያደረገው በጀርመን ዘረኝነትን የሚታገለው ባብል የተባለ ድርጅት ሃላፊ ዶክተር መኮንን ሽፈራው ያብራሩልናል ።
ጀርመን ውስጥ በተለይም በምሥራቅ ጀርመን እያደገ በመሄድ ላይ ያለው ይህን መሰሉ ዘረኝነት የውጭ ዜጎችን ለሞት ለድብደባ ለአካል ጉዳት ከመዳረጉም በላይ ወደ አንዳንድ አካባቢዎች እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል ። ይህ በተለይ ጎልቶ መታየት የጀመረው ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን ከተዋሃዱ በኋላ ነው ። በጀርመን በልዩ ልዩ መልኩ የሚገለፅ ዘረኝነትን በመታገል ና ለመፍትሄውም የበኩሉን ድርሻ በማበርከት ላይ የሚገኘው ባብል የተባለው ድርጅት መሥራች ዶክተር መኮንን ሽፈራው ችግሩ ተዳፍኖ የቆየ መሆኑን ነው የሚያስረዱት ።


እንደ ላይፕዚሹ ዩኒቨርስቲ ጥናት በአሁኑ ጊዜ በምሥራቅ ጀርመን ወጣቶች ላይ የሚታየው ዘረኝነት ፣ ፣ በሂትለር ዘመን ከተማሩትና አሁን በእድሜ በገፉት ጀርመኖች ላይ ከሚንፀባረቀው ዘረኝነት ጋር ይስተካከላል ። የዚያን ጊዜው የዘረኝነት መንስኤ በአጥኚዎቹ እንደተጠቆመው ዘረኛ አስተዳደግ ነው ። በአሁኑ ትውልድ የሚታየውን ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከሥራ አጥነትና ከዝቅተኛ ገቢ ጋር ያያይዙታል ።ሥራ አጥነት በምዕራብ ጀርመን አሁን 6.3 በመቶ ሲሆን በምስራቅ ጀርመን ደግሞ 11.3 በመቶ ነው ። ለበርካታ ዓመታት በኖሩባት በጀርመን ዘረኝነት በመታገልና ከህብረተሰቡም ጋር ተቀራርቦ ለመኖር ባከናወኑት ተግባር እጎአ የ2010 ዓም የጀርመን የውህደት ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑት ዶክተር ሽፈራው አንዱ የችግሩ ምንጭ የመረጃ እጦት ነው ይላሉ ።
ዶክተር መኮንን በአንድ የበርሊን ትምህርት ቤት ገለፃ ሲያደርጉ

መንግሥት፣ ፌደራል ክፍለ ግዛቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋርም ይሁን በተናጠል ዘረኝነትን ለማስቀረት ልዩ ልዩ ጥረቶች ቢያደርጉም የሚፈለገው ውጤት ላይ ለመድረስ ብዙ ይቀራል ።
መንግሥት ዘረኝነትን ለመታገል በየዓመቱ 26 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ያደርጋል ። ከገንዘቡ አብዛኛው ግን ለቢሮ ወጪዎች ለማስታወቂያ ና ለጥናትን ምርምር ሲመደብ የተቀረው ደግሞ ለ 16 የጀርመን ፌደራላል ክፍለ ግዛቶች የፀረ ዘረኝነት መርሃ ግብር የሚውል ነው ዶክተር መኮንን መንግሥት ዘረኝነትን ለመታገል የሚሰጠው ገንዘብ በቂ አይደለም ይላሉ ።ዶክተር መኮንን ከድርጅታቸው የ21 ዓመት ልምድና ከተገኘው ውጤት በመነሳት ችግሩን ለመከላከል መፍትሄ የሚሉትን ሃሳብም ሰንዝረዋል ።
ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ
dw.de

No comments:

Post a Comment