Thursday, August 8, 2013

ግብፅ ስትደነፋ

ግብፅ ስትደነፋ   When I hear Egypt's Rhetoric over Nile,

አማኑኤል ዊንታ
በሌሊት የተነሱ የግብፅ የሳተላይት ፎቶዎችን በአትኩሮት ብታዩ ፍንትው ያለና የማያወላዳ እውነትን ይጋፈጣሉ ከታላቁ የአስዋን ግድብ በካይሮ አድርጐ እስከ ሜዲትራንያን ባህር ድረስ 84 ሚሊዮን የሚጠጋው አጠቃላይ የግብፅ ህዝብ በጣም በሚገርም ሁኔታ የአባይን ዳር ለዳር ተጠግቶ ይኖራል፡፡ ይህም ግብፅን በአለም ላይ ካሉ ሀገራት ሁሉ እራሷን ሙሉ በሙሉ ለጥፋት አደጋ ያመቻቸች ብቸኛ ሐገር ያሰኛታል፡፡
ታላቁ የአስዋን ግድብ ያቋተው ውሃ የናስር ሐይቅ የሚባለውን ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለመፍጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ የናስር ሰው ሰራሽ ሐይቅ 547 ኪ.ሜ ርዝመት 35 ኪ.ሜ ስፋትና 110 ሜ ከፍታ አለው፡፡ ይህ የተፈጥሮ ሐይቅ ቢመታና ውሃው ቢፈስ በሰዓታት ውስጥ ግብፅ ያለምንም ጥርጥር ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጥለቅልቃ ትጠፋለች ይህ ሳይንሳዊ ሐቅ ነው፡፡
በቅርቡ የካይሮና የአዲስ አበባ መሪዎች የተለያዩ የተካረሩ ቃላቶችን ሲወራወሩ አይተናል ሰምተናል፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ውስጤን ቆፍጠን! በሸቅ! ነደድ! የሚያደርግ ነገር ወረረኝ፡፡ አይ ወይኔ ይሄኔ ነበር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በኖሩልን ብዬ  የተመኘሁት በደንብ አርገው ግብፅን ያቀምሱልኝ ነበራ፡፡ አሐ እሳቸው እንዲሁ ነብሳቸውን ይማርና እንኳን የግብፅን የአሜሪካና የአውሮፓ ድንፋታንም ከቁብ አይቆጥሩት እኔ በግሌ የእሳቸው ፓርቲ አባል አይደለሁም ፓለቲካም አልወድም አባቴ ይሙት! ጀግና ናቸው እረ በጣም አዋቂም ናቸው፡፡ ናፈቁኝ ከምር ናፈቁኝ፡፡ ምን ዋጋ አለው “የማንም ልቅምቅም የሰው ልክ አያውቅም!” አለ ያገሬ ሰው፡፡ ግብፆች ደነፋብን የግብፅ ኘሬዝዳንት ሙሐመድ ሙሪሲ ለህዝባቸው የሚከተለውን ድስኩር አሰሙ፡፡
“በእውነቱ እኔ ጦርነት ይጀመር እያልኩ አይደለም ግን በእርግጠኝነት ቃል እገባላችኋለው የግብፅ የውሃ ፍላጐት በማንም በምንም አደጋ ላይ አይወድቅም! አሉ ቀጠሉናም
“የግብፅ የውሃ ፍላጐትና ደህንነት መቸም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ አይገባም በማንም አይሞከርም እንደ ግብፅ ኘሬዝዳንትነቴ እማረጋግጥላችሁ ነገር ቢኖር ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው ይተገበራሉም!” አሉ
ከዛም ቀጠሉና ተረት ተረት የሚመስለውን ግን እርር ድብን ያረገኝን ቀጣዮቹን ሁለት ንግግሮች ቀጠሉ “ግብፅ የአባይ ስጦታ ናት ካልን አባይም የግብፅ ስጦታ ነው!” በማለት ከድሮ ጀምሮ ሲባል የነበረውን አባባል በቴሌቪዥን ሕዝባቸውን ሆ አስባሉበት ቀጠሉናም ደነፉ፡፡
“የግብፃውያን ሕይወት ከአባይ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው…. እንደ አንድ ታላቅ ህዝብ ደግሞ አንዲት ጠብታ ውሃ ከአባይ ላይ ሳትመጣ ብትቀር አማራጫችን አንድና አንድ ነው ደማችን ይፈሳል!” አሉና ፈገግ ጀነን ደንደን አሉ፡፡
እኔም እርር ድብን! ቆጣ! በስጨት! አልኩና ለማን ልተንፍሰው? ኮከቤ ደግሞ ታውረስ በሬው ነውና ለመዋጋትም፣ ይለይልን ኑ ውጡ! ለማለትም አማረኝ ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ መሆኔ ሁሉንም አገደኝ ግን ከምር አንድ ግብፃዊ መንገድ ዳር ላይ ባገኝ ያን ቀን በስሱ በቴስታ ነበር አፍንጫውን ብየ ደም እያሉ ኘሬዝዳንት ሙርሲ የደነፉበትን ደም የማየው በእውነት ምን ችግር አለው በስሱ አንድ ቴስታ ባቀምሰው? ምንም፡፡
ኘሬዝዳንት ሙርሲም ሲያጠቃልሉ “ግብፅ ሁሉንም የአባይ ተፋሰስ ሐገራት ኢትዮጵያንም ጨምሮ በወንዙ ላይ ለሚሰሩት የልማት ኘሮጀክቶች ተቃውሞ የላትም፡፡ ነገር ግን የልማት ኘሮጀክቶች የግብፅን ህጋዊም ሆነ ታሪካዊ መብቶች የሚነኩም የሚያስተጓጉሉም መሆን የለባቸውም፡፡” አሉና ፖለቲካቸውን ቦተለኩ፡፡
የግብፅ የተለያዩ ፖለቲከኞችም የሙርሲን አባባል እያነሱ እያወደሱ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብቅ እያሉ እንዳውም ታላቁን የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ከፍ ሳይል ባጭር እንቅጨው የጦር እርምጃ እንውሰድበት እያሉ ቀባጠሩ፡፡
ታዲያ መለስ ዜናዊ ቢናፍቁኝ ትፈርዱብኛላችሁ? አሃ ሌሎችንማ አየናቸው እኛ ላይ ሲሏችሁ ነው እንጂ የምትደነፉት ጠላት ሲመጣማ ጭጭ ምጭጭ፡፡ ባይሆን በኢቲቪ ወጣ ብላችሁ “ግብፅ ብትደነፋም በኩርኩም ነው የምንላት!” ምናምን እያላችሁ አታፅናኑንም? ድንቄም ፖለቲከኛ! እኔ በእውነት በጣም ተሰምቶኛል ወይ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ፖለቲከኞቻችን መድረሱን ለጀግኖች ለመከላከያ ሰራዊታችን ለቀቅ አድርጉላቸውና በሚዲያችን ዛቻና ድንፋታ እንስማበትና ወንዱ! አንበሳው! እንባባል፡
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ይህንን ሁሉ ችግር የፈጠረው የእኛ የፖለቲከኞች ችግርና ጥበብ ማነስ ነው ግድቡ የኢህአዴግ ብቻ ይመስል ለግንቦት 20 በአል አከባበር ታላቅ ድምቀት ብላችሁ የልደት ኬክ ይመስል አባይን ቦታውን አስቀይሳችሁ በሌላ አቅጣጫ እንዲፈስ አደረጋችሁ ወይም በሳይንሳዊ አገላለፁ (Diversion) ተሰራ፡፡ ግን ይሄ መሆን ያለበት የግብፅም ሆነ ሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሐገራት ቅድሚያ አውቀውትና ተስማምተው መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ግድቡ ሲጀመርም እኮ አብዛኞቹ ሐገራት ተስማምተዋል፡፡ መመካከር ማንን ይጐዳል? ነው ወይስ አባይን ለፖለቲካ ቅስቀሳ ጥቅም ብቻ ነው የገነባችሁት? አባይ የዚህ ወይም የዛ ፓርቲ አባል ነው የሚል ፓርቲ ካለ ከግብፅ ጐን መሰለፍ ይችላል፡፡ አባይ በተለይም ጥቁር አባይ የኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነው፡፡ ለዛም ነው ህዝቡ በጉልበቱም በገንዘቡም ሆ ብሎ እየገነባው ያለው የሚገነባውም! እና እንደ ምክር ወይ እንደተግሳፅ ፖለቲከኞቻችን እዩትና እባካችሁ ለሐገራችን የሚጠቅመውን አድርጉ አዋቂና ጥበበኞችም ሁኑ አንብቡ ተማሩ ተመራመሩ፡፡ መለስ የናፈቁኝ አንባቢ መሪና ተመራማሪ ስለነበሩ ነው፡፡ እንደውም አሁን አሁን በየቀበሌው በየቢሮው የመለስን ራዕይ እናሳካለን እያላችሁ በለጠፋችሁት ወረቀት ስር ይህንንም የምንተገብረው እንደሳቸው በማንበብና በመፃፍ በመማርና በመመራመር ነው በሉበት፡፡ በእውነት እውነቴን ነው፡፡ እኔ ይህንን ጽሑፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ስልጣን ፈላጊ ሆኘ አይደለም ሐገሬን አንድ ግብፃዊ ስነ-ህዝቡ በአደባባይ ሲዘልፋት ሰምቸ ተናድጀና ተቆጥቸ እንጅ አንድ ተራ ሰላማዊ ዜጋ ነኝ ግን እንደኔ ይህንን ስሜት የሚጋሩ ብዙ ኢትዮጵያዊያን አይጠፉምና አስቡበት፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ግብፅ በ2011 ላይ ደርሶባት ስለነበረው የእርስ በእርስ ግጭትና የግብፅን የአሁን ሁኔታ በመላው አለም ላይ ተሰራጭቶ የተለያዩ ኤክስፐርቶች አስተያየት የሰጡበትን መረጃ በመመርኮዝ ለሐገራችን ሕዝቦች ለመንግስታችንና ለሐገር መከላከያ ሰራዊታችን አቀርባለሁ፡፡
ልብ በሉ ግብፅ በታሪኳ ብዙ ጦርነቶችን አድርጋለች ታላላቅ ጦርነቶችን ግን ተሸንፋለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት የጦር ኃይሏ በአፍሪካ አንደኛ በአለም አስረኛ ነው፡፡ በአሜሪካ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከሚያገኙ ሐገራት ከእስራኤል ቀጥሎ ሁለተኛ ናት፡፡ አሜሪካ የእኔ ብቻ ናቸው ሌላ ሐገራት ቴክኖሎጂውን እንዳይሸጡት በሽያጭ አላቀርባቸውም የምትላቸው የብቻዋ ቴክኖሎጂ የሆኑ የተለያዩ ቀላልና ከባድ የጦር መሳሪያዎች ሄልኮኘተርና ጀቶችን ጨምሮ ግብፅን አስታጥቃታለች፡፡ በአጭሩ ግብፅ በአፍሪካ ቁንጮ ላይ ከአቅሟ በላይ የታጠቀች ጉረኛ ሐገር ናት ማለት ይቻላል፡፡
በአንድ ቀላል ምሳሌ እንኳን ለማስረዳት እስራኤልን ከምድረ ገፅ አጠፋለሁ ብላ ከሶስት ሐገራት ጋር ተባብራ በታሪክ የ“6 ቀኑ ጦርነት” የሚባለውን ልትተገብር ስትነሳ፣ ገና ሳይነሱ እስራኤል አጋየቻቸው እንጅ 300 የጦር አውሮኘላኖችን ቦምብና ሚሳኤል አስታጥቃ እስራኤልን ልትወርና ልታጠፋ የሞከረች ሐገር ናት፡፡ ይህም ምን ያህል ድንፋታም ነገር ግን ጥበብ የጐደላት ሀገር መሆኗን በቀላሉ ያስረዳል፡፡
ብዙ አወራሁ ወደ ተሰራጨ ያልኳችሁ ፅሑፍ ልግባና በመፅሐፍ ቅዱስ ትንቢተ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 29 እና 30 ላይ የግብፅን ቅጣት ስለሚያትተው ትንቢት የተሰራጨ አንድ ጽሑፍ ነበር ጽሑፉንም የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች አስተያየታቸውን አስፍረውበት ነበር ከአስተያየቶቹ መካከልም አይ ይህ ትንቢት እኮ ድሮ ገና ድሮ ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በ572 ቅ.ል.ክ አካባቢ በናቡከነፃር ጊዜ ተፈፅሟል ያሉም ነበሩ፡፡ በዚህ አሁንም ድረስ እያነጋገረ ባለ ፅሑፍ ተነስተን እስኪ በደንብ ትንቢቱን በጥሞና እንየው፡፡
በደንብ መታየት ያለበት ነገር የግብፅ የቅርብ ጊዜ እርስ በእርስ መባላት በየአደባባዩ ጐራ ለይቶ መወራወር ከቱኒዚያ በተነሳው የጐዳና ላይ ግጭት ቀጥሎ የአለምን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ የግብፃዊያኑ አመፅ ዋናው አላማም ለ30 አመት ግብፅን አንቀጥቅጦ የገዛውን የሆስኒ ሙባረክን መንግስት መገልበጥ ነበር፡፡ በአሜሪካ መንግስትና በአንዳንድ የምዕራቡ ሐገራት ባለስልጣናት ግፊትም ሆስኒ ሙባረክ ስልጣናቸውን በፌቡራሪ 12 ቀን መልቀቂያ ጠይቀው ለግብፅ ጦር ሰራዊት አስረከቡ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ በግብፅ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ሽኩቻና ብጥብጥ ተፋፍሟል ዋናው ግፊትም ያለው ግብፅ በሐይማኖት መሪዎች የምትመራ ጠንካራና እስላማዊ ሐገር ሆና እንድትቀጥል ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡
ተራማጅ እስላም በሚል መፈክር ስርም ከጀርባ ሁኖ ማርሹን በመቀያየር የሚገኘው “ሙስሊሞቹ ወንድማማቾች” (Muslim brotherhood) የሚባለው ድርጅት እንደሆነ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ቀስ በቀስም በጥበብ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን እየያዘ ገና እየወጣ የሚገኝ ፓርቲ ነው ዋናው አላማውም ግብፅን ጠንካራ የሙስሊሞች ሐገር እንድትሆን ማስቻል ነው፡፡ በቅርቡ የሚታየው ሁኔታ እንደሚያመለክተውም የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ በግብፅ ጦር ውስጥ ያሉ ቁልፍ ሰዎችን እያዳከመና ወደ ፓርቲው እየቀላቀለ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ቀን ከሌት እየሰራ ይገኛል፡፡
ባጭሩ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚገልፁት በጣም የጦፈ የስልጣን መያዝ ፉክክር እንደሚደረግና የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ እንደሚያሸንፍና ተራማጅ እስላም ስልጣን ላይ እንደሚሆን ይገልፃሉ፡፡
ሙባረክ ስልጣኑን ባስረከቡ ማግስት ነው እንግዲህ እስራኤላውያን ነቃ ብለው የግብፅን ሁኔታ በጥሞና ማዳመጥ የጀመሩት የስለላ ኤክስፐርቶቻቸውንም ያሰማሩት፡፡ ምክንያቱም እ.ኤ.አ ማርች 31,1979 ጀምሮ ከ30 አመታት በላይ ያስቆጠረ የሰላም ስምምነት ከሙባረክ ጋር እስራኤል አድርጋ ነበር ሙባረክ ሲወድቅም ስምምነቱ ተቋረጠ፡፡ ባለፉት 30 አመታት ምንም እንኳ ግብፅ በጨቋኙ የሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ ስር ብትሆንም እንኳ ግብፅ ለእስራኤል ደቡባዊ ድንበር መጋጋት የሆስኒ ሙባረክ ወታደሮች ከፍተኛ ጥበቃ ያደረጉ ነበርና ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ያ አስተማማኝ ጥበቃ የለም ስለዚህ እስራኤል ሆየ ነቃ! ብላ ነገሩን መከታተል ጀመረች፡፡
ይህ የእስራኤል ስጋትም ሳይውል ሳያድር እውን መሆኑ ተረጋገጠ ሁለቱ በተባበሩት መንግስታት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁትና እስራኤልን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ሙሉ ጊዜአቸውን ሰውተው የሚንቀሳቀሱት የአሸባሪ ቡድኖቹ የሐማስና የፋታህ መሪዎች ሳይውል ሳያድር ግብፅ ካይሮ ላይ በሚያዚያ 26 ተገናኙና ጦራቸውን አንድ በማድረግ እስራኤልን ለመዋጋት ተፈራረሙ፡፡
የአሸባሪ ቡድኑ ፋታህ ኘሬዝዳንት ሞሐመድ አባስም ንግግራቸውን አሰሙ፡፡
“እኛ ፍልስጤማውያን ከዛሬ ጀምሮ ያንን ጥቁር የልዩነት ዘመናችንን አጠናቀናል! ሐማስ የፍልስጤም ሕዝብ አባልና አካል መሆኑን አውጀናል፡፡ እንግዲህ እስራኤል ከሰፈራ ኘሮግራም ወይም ከሰላም አንዱን መምረጥ አለባት!” ሲሉ ተኮፈሱ፡፡
አሁን በእርግጠኝነት ለመናገር ከዚህ በኋላ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የሚደረግ የሰላም ስምምነት ሊኖር አይችልም፡፡ ቀዩ መስመር ይሉሐል ይሄኔ ነው! ፍልስጤም የምትባል ሐገርን ለማቋቋምና እውቅናን ለመስጠት ፋታህ እና ሐማስ መሞከራቸው አይቀሬ ነው ከዚች ቀን ደቂቃና ሰከንድ ጀምሮም ነበር እስላሞቹ ወንድማማቾችና እስራኤል አይጥና ድመት የሆኑት፡፡
እንግዲህ ቅድም የገለፅኩት የግብፃዊያን ትንቢት በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል ያልኩት ከፅሑፉ ተነስቸ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕዝቅኤል በግልፅ ግብፆች የሚቀጡት ከእስራኤል ጋር አልተባበርም በማለታቸው ነው ይላል፡፡ “ግብፅ ለወደፊቱ አይቀጡ ቅጣት ነው የሚደርስባት ፍርዱም የቆሻሻ መጣያ ቦታ እስክትመስል በግብፅ ይታያል እያለ ቃል በቃል የሚከተሉትን የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያትታል፡፡

ሕዝቅኤል 29 (6:12)
“በግብፅም የሚኖሩ ሁሉ ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ሆነዋልና እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ”

“በእጅ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ ጫንቃቸውንም ሁሉ አቆሰልህ በተደገፈብህ ጊዜ ተሰበርህ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ”

“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እነሆ ሰይፍ አመጣብሃለሁ ሰውንና እንስሳንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ፡፡”

“የግብፅ ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ አንተ ወንዙ የእኔ ነው የሰራሁትም እኔ ነኝ ብለሀልና”

“ስለዚህ እነሆ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ የግብፅንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ፡፡”

“የሰው እግር አያልፍበትም የእንስሳም ኮቴ አያልፍባትም እስከ 40 አመትም ድረስ ማንም አይኖርባትም፡፡”

“ባድማም በሆኑ ምድሮች መካከል የግብፅን ምድር ባድማ አደርጋታለሁ ባፈረሱትም ከተሞች መካከል ከተሞችዋ 40 አመት ፈርሰው ይቀመጣሉ ግብፃውያንንም ወደ አህዛብ እበትናቸዋለሁ በአገሮችም እዘራቸዋለሁ፡፡”

በአሁኑ ሰአት ያለምንም ጥርጥር ግብፅ እስራኤልን ለማጥፋት ለብዙ አመታት ቀን ከሌሊት ሲማስኑ ከኖሩ ሙስሊም አሸባሪዎች ጋር ህብረት ፈጥራለች፡፡

ይህ የአሸባሪነት ትብብርም በቅርቡ እንደ ሰደድ እሳት መቀጣጠሉና ብዙ አሸባሪዎችን በህብረት አሰባስቦ እስላማዊ ወንድማማቾችን አሁን ጊዜው ደርሷል እስራኤል ትወረር ማስባሉ የማይቀር ሐቅ ነው፡፡

ብዙ ሰዎች ከላይ የጠቀስኩትን የሕዝቅኤል 29 ትንቢት ገና ወደፊት አለም ስትጠፋ የሚፈፀም ትንቢት ነው እንጅ አሁን ጊዜው ገና ነው እያሉ ይቃወማሉ፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ ትንቢቱ እኮ ድሮ ገና ድሮ በባሊሎናዊያን ጊዜ ተፈፅሟል ይላሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ልብ ያላሉት ነገር ቢኖር የሕዝቅኤል ትንቢት ስለፍፃሜው ሲተነብይ እሚያወራው ሴዌኔ ስለሚባል ቦታ የሚደርስበትን የወደፊት መከራ ነው የሚዘረዝረው፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ከላይ የዘረዘርኩት የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል እንደሚያትተው ግብፅ በታሪኳ መቸም ቢሆን ለ40 አመታት ያህል ሰው የሌለባት ምድረ በዳ ሆና አታውቅም ይህም ትንቢቱ ገና ወደፊት ለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡

ለብዙ አመታት ስናምንበት የኖርነው የሕዝቅኤል ትንቢት በተፈጥሮው ቅኔያዊ ይዘቱ ያይላል፡፡ ይህንን ለማለት ያስቻለኝ ምክንያትም ሕዝቅኤል ትንቢቱን ሲፅፈው በዛ ጊዜ “የሴዌኔ ማማ” የሚባል ነገር ወይም ቦታ የለም አልነበረም እንደውም እ.ኤ.አ እስከ 1967 ጊዜ ድስ ይህ ቦታ አልተሰራም በ1967 ግን ይህ ቦታ በሚደንቅ ሁኔታ ታላቁ የአስዋን ግድብ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ በግብፅ ደቡባዊ በኩል አባይን ተከትሎ ተገነባ፡፡ “ሴዌኔ” የሚለው ስም የመጣው ሲቭኔ ከሚለው የሒብሩ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም “መግቢያ” ወይም “ቁልፍ” ማለት ሲሆን ይህም ስም የጥንት ግብፃውያንን መግቢያ ያመላክታል፡፡ ከደቡባዊ ግብፅ ወይም ከኢትዮጵያ ተነስቶ አንድ ሰው ወደ ግብፅ ሲገባ የሚያየውን መግቢያ ወይም ቁልፍ በግልፅ ያትታልና፡፡

በጣም ብዙና የተለያዩ ታሪካዊ መረጃዎችን ብናገላብጥ የመፅሐፍ ቅዱስ ሴዌኔ በእርግጥም አስዋን ግድብ ነው ይላሉ፡፡ ከነዚህ መረጃዎች መካከል አንዱ በ1966 እ.ኤ.አ በኬል እና ዳልሽ የተፃፈው የብሉይ ኪዳን ጥናትና አስተያየት የሚለው መፅሐፍ ይገኝበታል፡፡ ግንኙነቱንም ሲያጠናክረው በግሪኮች “ሴዌኔ ብሩዳሽ” እንደፃፈው “ሴርቱዋጅንት” ወይም የመጨረሻዋ የግብፅ ደቡባዊ ከተማ ከኩሽ ማለትም ኢትዮጵያ አቅጣጫና ጐን ናት ይላል፡፡ አሁንም ድረስ ከአባይ ምስራቃዊ ቦታዎች አካባቢ የሚታዩ ኢትዮጵያዊ የሆኑ አንዳንድ የጥንት ስልጣኔ መገለጫዎች በግብፅ ደቡባዊ አዋሳኝ ከተማ ሴርቱዋጅንት አካባቢ ይገኛሉ፡፡

የሚገርመው ነገር ኬል እና ደልሽ በ1866 የብሉይ ኪዳን ጥናትና አስተያየት ሲፅፉ አስዋን ላይ ምንም አይነት ማማ አልነበረም ሕዝቅኤል ትንቢቱን በ570 ቅ.ክ.ል በፊት ሲፅፈውም ምንም አይነት ማማ አልነበረም፡፡ እውነታው ግን ታላቁ የአስዋን ሐይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ በግብፃውያንና በራሻውያን ተሰርቶ በ1967 እ.ኤ.አ እስከሚጠናቀቅበት ቀንና ደቂቃ ጊዜ ምንም አይነት ማማ በአስዋን ላይ አልነበረም፡፡

አሁን ግን ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ በአካባቢው ያለው ብቸኛ ማማና ወደ ላይ የተራራ ያህል ገዝፎ የሚታየው የአስዋን ግድብ እራሱ ነው፡፡ ለዛም ነው ይህ “ሴዌኔ” እየተባለ በትንቢት ሲገለፅ የነበረው ቦታ በአሁኑ ሰአት አስዋን እየተባለ የሚጠራው ቦታ መሆኑን አጋግጠናል የሚሉት፡፡ ግብፃውያኑ የራሽውያንን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ግድባቸውን በተሳካ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሲያጠናቅቁም ተኮፈሱና እስከ ዛሬ ድረስ የሚመፃደቁበትን አባባላቸውን ለልጅ ልጅ እንዲወረስ እያደረጉ እንደ ምሳሌያዊ አነጋገር ይጠቀሙበታል፡፡
“ወንዙ የእራሴ ነው የሰራሁትም እኔ ነኝ” ግብፃውያን

ሕዝቅኤል 29 (2-5)
“የሰው ልጅ ሆይ ፊትህን በግብፅ ንጉስ በፈርኦን ላይ አድርግ በእርሱና በግብፅ ሁሉ ላይም ትንቢት ተናገር፡፡”

“እንዲህም በል - ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላላ በወንዞች መካከል የምትተኛና ወንዙ የእኔ ነው ለራሴም ሰርቸዋለሁ የምትል ታላቅ አዞ የግብፅ ፈርኦን ሆይ እነሆ በአንተ ላይ ነኝ፡፡”

“በመንጋጋህ መቃጥን አገባብሃለሁ የወንዞችህንም አሶች ወደ ቅርፊትህ አጣብቃለሁ ከወንዞችህም መካከል አወጣሀለሁ የወንዞችህም አሶች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ ይጣበቃሉ፡፡

“አንተና የወንዞችህን አሶች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ በምድርም ፊት ላይ ትወድቃለህ እንጅ አትከማችም አትሰበሰብም መብልም አድርጌ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች ሰጥቼሃለሁ፡፡”

ትንቢቱ ዝም ብሎ በመጀመያ ሲታይ የሚመስለው ለግብፅ ንጉስ ፈርኦን ፓሮህ የተፃፈ ይመስላል ቀስ እያላችሁ በደንብ መፈተሽ ስትጀምሩ ግን ትንቢቱ የተፃፈው “በባህር ላይ ስለሚኖረው” ታላቅ አዞ መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡

ቀጥሎም አንተና የወንዞችህ ወይም የአባይ አሳዎች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎችም መብል አደርግሃለሁ እያለ ያትታል፡፡

አባይ በየአመቱ እየተንደረደረ በከፍተኛ ሙላት ነበር ወደ ግብፅ የሚገባው ነገር ግን ግድቡ ከተሰራ በኋላ ሰጥ ለጥ ብሎ ነው ግብፅ ውስጥ የሚጓዘው በትንቢቱ እንደተገለፀው አባይን እንደገና በከፍተኛ ሙላት እያስጋለቡ በግብፅ ውስጥ ለማስጓዝ ብቸኛው መንገድ አንድ እና አንድ ብቻ ነው ግድቡን ማፍረስ፡፡

ሌላው አስደናቂ ነገር ይህ ታላቅ ግድብ የተገነባው በጣም በትልልቅ ብረቶችና ኮንክሪቶች ተጠፍጥፎ ከመሆኑ የነሳ የዘርፉ ባለሙያዎች የአስዋን ግድብ በምንም አይነት ቦምብ ቢመታ ሊፈርስ አይችልም፡፡ ከኒውክሌር ቦምብ በቀር ማለታቸው ትንቢቱን ገና ያልተፈፀመ ስለመሆኑ ያረጋግጣል፡፡ ኒውክሌር ቦምብ የአሁን ቴክኖሎጂ ነውና፡፡




እስራኤላዊያን ጠበብቶች ምን አሉ?
በ2002 የእስራኤል የፓርላማ አባል የነበረ አቪጐር ሊበርማን የተባለ ሰው ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ይህች በየጊዜው ለእስራኤል ችግር መነሻ እየሆነች ላስቸገረችው ግብፅ የምትባል ሐር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚሆን መፍትሄ አግኝቻለሁ ብሎ ንግግሩን ያሰማው፡፡

“እስራኤል በቀላሉ ግብፅን በአንድ ኒውክሌር ቦምብ ድምጥማጧን ማጥፋት ትችላለች አለ” ልብርማን ስለ ግድቡ በደንብ ነበር ያጠናው ያሰማራቸው ረዳቶችም አስዋን ግድብ በጣም ትልቅና ግዙፍ ከመሆኑ የነሳ በተራ ቦምብ እንደማይፈርስ ተረድቶ ነበርና ኒኩሌየር ቦምብ ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ተንትኖ አስረዳ፡፡

ሌላኛው የፓርላማ አባል ይጋል አሎን ቀጠለና ይህንን ጥሩ ዜና የምስራች ለእስራኤላዊያን በአደባባይ አበሰረ፡፡ እነዚህ ሁለት ጀግኖች አብዛኞቹ እስራኤላዊያን የሚያውቁትን ነገር ግን በውስጣቸው አምቀው የያዙትን እውነት በአደባባይ ያበሰሩ ጀግኖች አደረጋቸው፡፡ ሊበርማን ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ድረስ፣ ይጋል ደግሞ ለሰባት አመታት በሚኒስቴርነት ሐገራቸውን አገልግለዋል፡፡

ሊበርማንና ይጋል እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ግብፃውያን አንገታቸውን ደፍተው እድሜልካቸውን መፍትሄ የማያገኙለትን የቤት ስራ ሰጥተዋቸዋል፡፡

እነኚህ ሁለት እስራኤላዊያን ሲናገሩም የእስራኤል የማንነት ጥያቄ በግብፃውያን ወረራ የሚስተጓጐል ከሆነ ጨዋታው የሚሆነው እንደዛ በምትመፃደቁበት ግድባችሁ ላይ ይሆናል በማለት አስረገጡ፡፡

“በኑክሊር ቦምብ አስዋንን እናፈርሰዋለን፡፡ በውሃውም በሰዓታት ሰምጣችሁ ታልቃላችሁ አርፋችሁ ቁጭ በሉ፡፡ “ይኸው እነሱም አርፈው እስከ ዛሬ ቁጭ ብለዋል፡፡

የሚከተሉት የማጠቃለያ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በመጨረሻው ቀን ላይ ያተኩራሉ ልብ ብላችሁም አስተውሉ የሴዌኔ ማማም ተጠቅሷል፡፡

(ሕዝቅኤል 30 1፡6)
“የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ የሰው ልጅ ሆይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል”

“ጌታ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል” ዋይ በሉ ለቀኑ ወዮ ቀኑ ቅርብ ነው የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው የደመና ቀን የአህዛብ ጊዜ ይሆናል፡፡

“ሰይፍ በግብፅ ላይ ይመጣል ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል የተገደሉትም በግብፅ ውስጥ ይወድቃሉ ብዛትዋንም ይወስዳሉ መሰረቷም ይፈርሳል፡፡”

“ኢትዮጵያና ፋጥ ሎድም የደባለቀም ሕዝብ ሁሉ ኩብም ቃል ኪዳንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ፡፡”

“እግዚአብሄር እንዲህ ይላል ግብፅን የሚደግፉ ይወድቃሉ የሐይሏም ትእቢት ይወርዳል ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔ ድረስ በእርስዋ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ ይላል ጌታ እግዚአብሄር፡፡”

ለዚህም ነው ግብፅ ለመኖሪያ የማትመች የተንኮለኞችና የእግዚአብሔር ቃል ተቃዋሚዎች ሐገር በመሆኗ ለ40 አመት ያህል ማንም የማይኖርባት ምድረ በዳ አደርጋታለሁ ያለው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በሕዝቅኤል 38 ላይ እስራኤልን ተባብረው ከሚያጠቋት የጐግ ሐይሎች ጋር ግብፅ ያልተጠቀሰችውም እኮ ስለማትኖር ነው እንጂ ብትኖርማ የመጀመያ ቋሚ ተሰላፊ ነበር እኮ የምትሆነው፡፡

በራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር በተበከለ ውሃ የተጥለቀለችን አንድ ሐገር ለማፅዳት የሚፈጀውን ሐይልና ገንዘብ አስቡትና ምን ያህል አስቸጋሪ ነው ብላችሁ እራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ወይም ከመጨረሻው ቀን በኋላ በእግዚአብሄርና በተከታዮቹ የሚፀዳው ቦታ ግብፅ ይሆነ ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል? እባካችሁ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖችም በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር በሉ “ግብፅ ሆይ አርፈሽ ቁጭ በይ! በእሳት አትጫወች! ግድባችንን እንዳንሰራ ወንድ የሆነ ያስቆመናል! አለዛ በደህና ጊዜ የሰራሽውን የአስዋን ግድብ መጥፊያሽ ይሆናል! አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ከምታስቢው በላይ ነቃ ያለ ነው እንኳን ለወደፊቱ ድሮ ለሄደብን አፈርም ካሳ መጠየቁ አይቀርም” እኔስ እችን ፅፌ ትንሽ ንዴቴ ተንፈስ አለልኝ! እናንተስ?

የምወዳትን ኢትዮጵያ እግዚአብሄር ይባርካት፡፡
አመሰግናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment