Wednesday, November 6, 2013

የስደተኛው ማስታወሻ እና ግድፈቶቹ (ክፍል አንድ) -ዳንኤል አበራ

ሰሞኑን የአንድ መጽሃፍ “የስደተኛው ማስታወሻ” ቅጅ በድረ መረብ ከመሰራጨቱ በፊት እና በኋላ አነጋጋሪ ሆኗል። ከጸሀፊው ተስፋዬ ገብረአብ ስብእና ጋር ተዳምሮ በመጽሀፉ ውስጥ የታጀሉት ጽሁፋዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እናም ሌሎች ግድፈቶች አንድም ይሁነኝ ተብሎ ለአንድ ግብ በመሰራቱ፤ አንድም ባለማወቅ በመደረጉ ለአማርኛ ጽሁፍ አንባቢያን እነዚሀን ነቅሶ ማሳየቱ አግባብ ሆኖ ታይቶኛል። በዚህ እና በቀጣይ ጽሁፎቼ እነዚህን ቋንቋ እና ጽሁፍ ተኮር ግድፈቶች አሳያለሁ።
ለመሟሟቅ ለምን በገጽ 418 አንጀምርም። ተስፋዬ በጽሁፉ መጨረሻ ገጽ 418 እንዲህ ይላል “አንባብያን ሆይ! ስለዚህ መፅሃፍ ያላችሁን አስተያየት ብትልኩ ደራሲው በደስታ ይቀበላል። ኢሜይል፡…” የፕሮግሬስ የመጻሕፍት ማዘጋጃና ማሳተሚያ ቤት ያሳተማቸው ሶስት መጻህፍትም መጨረሻ ገጻቸው እንዲህ ይነበባል።
1) “ማክሲምካ ደራሲው ኮንስታንቲን ስታኒዩኮቪች አንባብያን ሆይ! የፕሮግሬስ የመጻሕፍት ማዘጋጃና ማሳተሚያ ቤት ስለዚች መጽሐፍ ትርጉም ዝግጅትና እትም ያላችሁን አስተያየትና አሳባቸሁን ብትገልጹለት በደስታ ይቀበላል። አድራሻው … “ገጽ 111።
2) ጃሚላ ደራሲው ችንጊስ አይትማቶቭ “አንባብያን ሆይ! የፕሮግሬስ የመጻሕፍት ማዘጋጃና ማሳተሚያ ቤት ስለዚች መጽሐፍ ትርጉም ዝግጅትና እትም ያላችሁን አስተያየትና አሳባቸሁን ብትገልጹለት በደስታ ይቀበላል። አድራሻው …” ገጽ 143።
3) ታራስ ቡልባ ደራሲው ኒኮላይ ጎጎል “አንባብያን ሆይ! የፕሮግሬስ የመጻሕፍት ማዘጋጃና ማሳተሚያ ቤት ስለዚች መጽሐፍ ትርጉም ዝግጅትና እትም ያላችሁን አስተያየትና አሳባቸሁን ብትገልጹለት በደስታ ይቀበላል። አድራሻው …” ገጽ 180። አወይ መመሳሰል! በነዚህ መጻህፍት አያያዥ (ስለዚህ) ቃል ስራተ ነጥብ (!) እንኳን አይለያይም? ተስፋዬ መቸም በጽሁፍ ከታፊነት አይታማም ባይሆን ግምኛ መመሳሰል ብለን እንለፈው።
ተስፋዬ ጽሁፉን ሲጀምር ““ግዕዝ” (ግ.አ.) ተብሎ ካልተጠቀሰ በቀር የአውሮፓውያንን የዘመን አቆጣጠር ተጠቅሜያለሁ።” በማለት አውጇል። ይህ ደሞ ይሁነኝ ተብሎ የተደረገ ነው። ተስፋዬ ምክንያቱንም አልነገረንም። ግን መገመት እንችላለን። ምን አግዶን? (እንደ) ግዕዝ (ዘመን አቆጣጠር) የሚለው ቃል የተካው (እንደ) ኢትዮጵያ (ዘመን አቆጣጠር) የሚለውን ቃል ነው። አስቀድሜ እንዳልኩት ምክንያቱንም አልነገረንም። የኔ ግምት ተስፋዬ ኢትዮጵያ ከሚለው ቃል ቃሉም ከሚወክለው ጉዳይ ጋር ችግር አለው ማለት ነው። መቸም ተስፋዬ የአፍሪካ ቀንድ ብሎ ለሚፈጥራት ሀገር ምንም ነገር ከኢትዮጵያ ላለመጠቀም አስቦ ከሆነ ስንጥር ሳይሆን ግንድ የሚያክል ስህተት እየሰራ ነው ባይ ነኝ።
ለጸሃፊ ተስፋዬ ትምህርት የሚሆን ከሆነ ይቺን የ “ቃላት ጨዋታ” ልመርቅ። (እንደ) ኢትዮጵያ (ዘመን አቆጣጠር) የሚለው ሀረግ እንደ አቻው (እንደ) ጎርጎሮሳውያን (ዘመን አቆጣጠር) ወይም (እንደ) ምእራባውያን (ዘመን አቆጣጠር) አንድም መልከአ ምድርን ያሳያል አንድም ጂኦ-ፖለቲካዊ ምድርን አመላካች ነው። ዘመን አቆጣጠርን ገላጩ ቃል ኢትዮጵያ፤ ጎርጎሮሳውያን፤ ምእራባውያን ቋንቋን አመላካች ስም ስያሜም አይደለም፣ አያሳይም ወይም አይጠቀምም። ተስፋዬ ግዕዝን ለዘመን ሲጠቀም ይህንን ግድፈት ስርቷል። የሱ ቃል ቋንቋን እንጂ መልካምድራዊ ጂኦ-ፖለቲካዊ ምድርን አመላካች ስላልሆነ።
ይህ ይሁነኝ ተብሎ የተደረገ ለውጥ “አበሻ” በሚለው ቃል አጠቃቀምም በጉልህ ይታያል።
አንድ በኢ-መደበኛ አጠቃቀም ከጥንት ጀምሮ አበሻ የሚል ቃል በተውላጣዊ/በገላጭ አጠቃቀም ህዝብ ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያዊ ለሚለው ቃል በምትክነት ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀምበት ኖሯል።
እስኪ የተስፋዬን ሀበሻ የሚለውን ቃል አጠቃቀም እንይ። ይሁነኝ ብሎ አበሻ የሚለውን ቃል በጽሁፉ ሲጠቀምበት በአመዛኙ በአሉታዊ ጎኑ ነው። አስር ማስረጃዎች እጠቅሳለሁ።
1) “መቼም በዚህ አይነት ሳይቤሪያ ወይም ግሪንላንድ ብንሄድ አበሻ ይኖራል። የኛ ሰው ምን ያልገባበት አለ? ቁራ የሆነ ህዝብ!”
2) “ዛሬ ህዝበ አበሻ አለማየሁ ተገዶ በቀደደው የስደት መንገድ በፈቃዱ እየነጎደ ነው።”
3) “አበሻ መሰደዱ ብቻ ሳይሆን ስንቁን እንኳ መች ይተዋል? ”
4) “ሞቅዲሾ ከዘመቱት ሃበሾች ጋር የተያያዘ ክፉ ትዝታ ይኖራቸው ይሆን? ወይ ደ’ሞ “አበሻ እባብ” እንደሚለው ነባር የሶማሌያ ብሂል እባብ መስዬ ታይቻቸው ይሆን?”
5) “አበሻ ሲባል ግን ወሬ ብቻ!”
6) “አባቷ አበሻ ነው።” [መጽሃፉ ውስጥ ይህንን ሀረግ ተስፋዬ የተጠቀመበት አበሻው ትዳር ፈቶ ልጅ አስወልዶ ጥሎ ሂዷል በሚል እሳቤ ነው]
7) “በመካከሉ ዮናታን አበሻ እንደመሆኑ ይሉኝታ ያዘው መሰለኝ፣ ጠጋ ብሎ እንዲህ አለኝ።”
8) “በቅዱስ ሚካኤል እግር ስር የወደቀው “ሰይጣን” መልኩ አበሻ ይመስላል።”
9) “የአበሻ ምቀኛነት መቸም የማይገባበት ቦታ የለም።”
10) “አበሻ ሲባል ሳቁን እንኳ የሚደብቅ እርጉም! አበሻ ባልሆን ይሻለኝ ነበር!”
በተስፋዬ ጽሁፍ ከአስር አበሻ የሚል ቃል እና እሳቤ አጠቃቀም አንድም አዎንታዊ አላገኘሁም። ተስፋዬ በጽሁፉ “አበሻ” የሚለውን ቃል በአዎንታዊ መልኩ የተጠቀመው ወይ ስለ ኦሮሞ ወይ ስለ ኤርትራ ሲያወራ ነው ። ማስረጃዎች፤ 1) “የኦሮሞ ኤሊት እንደማንኛውም አበሻ በነጮች ፊት የበታችነት የማይሰማው፣ አያትና ቅድመ አያቶቹ ነጭን አርበድበው…”፤ 2) “ግብዣ ተደረገልን… በኤርትራ ገጠሮች ለእንግዶቻቸው የሚያቀርቡት ትልቁ ግብዣ ዶሮ ወጥ በእንጀራ ነው። በመላ ሃበሻ ልማድና ባህል መሰረት መጀመሪያ ወጡና እንቁላሉ ተበላ።”
ተስፋዬ ሳያውቀው ራሱን በጽሁፉ የተቃረነ ይመስለኛል። ተስፋዬ እንዲህ ይላል “ብዙውን ጊዜ እኛ አበሾች “ችግር” የምንለው የዳቦውን እጥረት ነው። የፍቅር እጥረት እንደ ችግር አልተመዘገበም።” የፍቅር እጥረትማ “አበሽ” የለበትም። ከራሱ ከተስፋዬ ጽሁፍ እነዚህን ጥቅሶች ማየት ይቻላል። 1) የእንስሳት ፈጣሪ… በረቂቅ ህሊና – ሁሉን አሳዳሪ ”እንዲሉ አንድ አበሻ በፈገግታ ተውጦ ወደኔ ሲመጣ አየሁ። ሰላምታም አልሰጠኝ። ከመድረሱ፣ “አበሻ ነህ? ”ሲል ጠየቀኝ። “እንዴታ!” ስል በደስታ መልስ ሰጠሁ።
2)ወደ ፎቁ እየወጣን ሳለ ስሜታዊ ሆኜ ተናገርኩ፣ “አበሻ እንደማገኝ እንኳ ጠርጥሬ ነበር። ከሃበሾች ጋር በአንድ ክፍል እመደባለሁ ብዬ ግን አልጠበቅሁም ነበር። በእውነቱ እድለኛ ነኝ።
ይቺን መጣጥፍ ላሳረግ። ተስፋዬ ሊሳሳት ሆነ። ስለ ሀበሻ አዎንታዊ በሆነ መልኩ ሊጽፍ፣ ሊጠቅስ ተስፋዬ እንዲህ አለ “‘አቢቹ’ የሚለው ቃል ልቤ ውስጥ በፍቅር ጠልቆ የገባው በርግጥ ከጥቂት ወራት ወዲህ ነበር። ይህም በቼኮዝላቫኪያዊው አዶልፍ ፓርለሳክ ተፅፎ፣ በተጫነ ጆብሬ የተተረጎመውን መፅሃፍ ካነበብኩ በሁዋላ ነው።” ተስፋዬ ያልጠቀሰው የመጽሀፉ ርዕስ ምን ነበር መሰላችሁ? የሀበሻ ጀብዱ!
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com
 http://www.revolutionfordemocracy.com/2013/11/06/83-27/

No comments:

Post a Comment