በዚህ ሳምንት የመገናኛ ብዙኃኑ ያወጡት መረጃዎችና ዜናዎች እጅጉን አሳዛኝ ናቸው፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ በስደት ያሉ ኢትዮጵያውያን በስቃይና በእንግልት ውስጥ መሆናቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች፣ ፎቶዎችና ዘገባዎች በመመለከት ልባችን የከበደበት ሳምንት ነው፡፡
ከዚህ በፊት ኢትዮጵያውያን በነጠላ መደብደባቸውን፣ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን፣ ከፎቅ መወርወራቸውን፣ የአካል ጉዳት
የደረሰባቸው መሆኑን፣ መደፈራቸውን፣ ያለ ደመወዝና ንብረት ከአገር መባረራቸውን ወዘተ. መስማት የተለመደ ነበር፡፡
ለዘመናት የእህቶቻችንን አስከሬን ተቀብለናል፣ ህሊናቸውና አካላቸው የተጎዱትንም ወደ አገራቸው ተባርረው
ተመልክተናል፡፡ መንግሥትም ቢዘገይም የተወሰነ ዕርምጃ በመውሰድ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት የከፋ እየሆነብን ነው፡፡
የሳዑዲ መንግሥት ሕገወጥ ናቸው ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ከመደብደብና ከማሰቃየት ባለፈ የገደላቸውም እንዳሉ
እየተሰማ ነው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየመንገዱ በደም ተጨማልቀውና ሰውነታቸው ተላልጦ መመልከት ሰብዓዊነትን
ይፈትናል፡፡ ሪፖርተርም ‹‹በሳዑዲ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ቁጣ ቀሰቀሰ›› በሚል በዘገበው ዜና
‹‹ሴቶች ይደፈራሉ፣ ይታረዳሉ፣ ነፍሰ ጡሮችና ሕፃናት ጭምር ያሉ ሲሆን፣ የተሰበሰቡበት ቦታ ንፅህና የሌለውና በጣም
የተፋፈገ በመሆኑ ስቃያቸው እየጨመረ ነው፤›› በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ ኤምባሲ ስለግድያውና
እንግልቱ ማብራሪያ ከመጠየቅ ባለፈ የተወሰኑትን ስደተኞች ወደ አገራቸው በመመለስ ላይ ነው፡፡ የሳዑዲዎችን
የሰብዓዊነት ግንዛቤ ለማወቅ እስካሁን በተለያዩ ዘመናት የደረሰብንን ኩነት በምልሰት መመልከት በቂ ቢሆንም
‹‹ኢሰብዓዊነታቸው›› በግልጽ የሚታወቅና ገሃድ የወጣ መሆኑን ማሳያ የተወሰኑ ነጥቦች እናነሳለን፡፡ የዓለም አቀፉ
ማኅበረሰብ ስለ ሰብዓዊነትና ሰብዓዊ መብት በሚለፈፍበት በዚህ ዘመን ሳዑዲን የመሰሉ አገሮች ያለውግዘት በኩራት
የመታየታቸውንም ነገር ለመመልከት እንሞክራለን፡፡
ሰብዓዊ መብትና የዓረብ አገሮች
የዓረብ አገሮች በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው በአሉታዊ መልኩ ከሚጠቀሱት ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ አገሮቹ
እንደማንኛውም አገር የሕግ ሥርዓት ለሰብዓዊ መብት ዕውቅና የሚሰጡ ቢመስሉም፣ በተግባር ‹‹ሰብዓዊነትን›› የሚፈትኑ
ድርጊቶችን በመፈጸም ይታወቃሉ፡፡ ብራያን ዊታከር ‹‹What is really wrong with the middle
east?›› በሚለው መጽሐፉ የዓረብ አገሮቹ ሰብዓዊ መብትን እንደ ፋሽን የሚያዩትና ለመተግበርም ሆነ ላለመቀበል
አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ስለመሆናቸው ይገልጻል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያን የመሰሉ የዓረብ አገሮች ከሰብዓዊ መብት ትርጉምና
አፈጻጸም አንፃር መሀል ገብ ተደናጋሪዎች (In dilemma) የሚባሉ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል የዓለም አቀፉ
ማኅበረሰብ ከተስማማበት መሠረታዊ ሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ላይ ልዩ ሁኔታን ያበጃሉ፤ አንዳንዶቹንም
መብቶች ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ዓረባዊ ባህላቸውና ሃይማኖታቸው እንደሆነ መጽሐፍት ያስረዳሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለሰብዓዊ መብት ቦታ ለመስጠት የሚያስቡ መሆኑን ለመግለጽ አንዳንድ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነትን
ይፈርማሉ፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን መፈረም በራሱ የሰብዓዊ መብቶችን ለመፈጸም ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ በአንድ
በኩል ስምምነቶች የሚፈጸሙበትን ጠንካራ ግዴታዎች አያካትቱም፡፡ ለምሳሌ የዓረቦቹ አገሮች የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት
በግለሰብ አመልካችነት የተዘረጋውን የመፈጸሚያ ዘዴ አይቀበሉትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስምምነቶቹ አገሮች ከባህልና
ከሚከተሉት ፖሊሲ አንፃር የማይመቻቸውን ድንጋጌ በተአቅቦ (Reservation) ማስቀመጥ መፍቀዱ ነው፡፡ በአንዳንድ
አጋጣሚዎች በስምምነቶቹ የሚቀመጡ ተአቅቦዎች ስምምነቶቹን ዋጋ የማሳጣት ውጤት አላቸው። ሌስቤዝ ሊዥናሂድ የተባለች
ምሁር ‹‹Reservations to UN Human Rights Treaties: Ratify and Ruin?›› በሚል
መጽሐፍ ይህንን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጻዋለች፡፡
‹‹By making reservations to human rights treaties states frequently
undermine essential rules, and indeed essential human rights guarantees.
The Impression is that many states, when ratifying, at the same time
ruin the treaty.››
በመርህ ደረጃ አገሮች ከስምምነቱ ዓላማ ጋር ተቃራኒ የሆነ ተአቅቦ ማድረግ እንደማይችሉ ቢታወቅም በተግባር
ይህንን መከላከል አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ የመን ዓለም አቀፍ የዘር መድልኦን ለማስቀረት የወጣውን ስምምነት
ስታፀድቅ ፖለቲካ መብቶችን፣ የጋብቻ መብቶችን፣ የውርስና የሃይማኖት መብትን በተመለከተ በአንቀጽ 5(c) እና (d)
ተአቅቦ በማስቀመጧ በእነዚህ ነጥቦች መድልኦ ማድረጓን ቀጥላለች፡፡ ይህንን ተአቅቦ የተወሰኑ አገሮች በመቃወም
አቤቱታ ያስመዘገቡ ቢሆንም፣ ቁጥራቸው ሁለት ሦስተኛ ባለመሆኑ ተአቅቦው ሊነሳ አልቻለም፡፡
የሳዑዲ ዓረቢያን ጉዳይ ከተመለከትን ነገሩ ከዚህም የባሰ ነው፡፡ ብራያን ዊታከር እ.ኤ.አ. በ2009 በጻፈው
መጽሑፍ እንደገለጸው፣ ‹‹በዓለም ላይ በወጥነት በሴቶች ላይ መድልኦ የምትፈጽመዋ ቀዳሚ አገር ሳዑዲና ሌሎች አሥራ
ሰባት የዓረብ አገሮች የተባበሩት መንግሥታት በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ዓይነት መድልኦ ለማስቀረት የተፈረመውን
ስምምነት (CEDAW) ፈርመዋል፡፡›› ጸሐፊው ይህንን የማይታረቅ የሳዑዲ አቋም አገሪቱ የያዘችበትን ዓላማ
ኃላፊዎቿን ጠቅሶ ሲናገር፣ ‹‹Saudi does not consider itself bound by any part of
the convention that conflicts with the norms of Islamic law›› ብሏል፡፡ የሳዑዲ
አቋም በውል የማይታወቅና ባልተወሰነ ሕግ የተቀነበበ ተአቅቦ እንደሆነ ዴንማርክ መተቸቷን ጸሐፊው አስተውሏል፡፡
የእስልምና መሠረተ እምነት ከሰብዓዊነት ጋር የተሳሰረ መሆኑን ለሚገነዘብ የሳዑዲ ባለሥልጣናት የሰብዓዊ መብት
ጥሰትን የሚፈጽሙት የራሳቸውን አካባቢ ባህልና ልምድ መሠረት አድርጎ መሆኑን በቀላሉ ይረዳል፡፡
የሳዑዲ ኢሰብዓዊነት መገለጫዎች
የሳዑዲን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተለየ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ብዙ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ምሁራን
ይስማማሉ፡፡ የሂዩማን ራይትስ ዎች የመካከለኛው ምሥራቅ ምክትል ዳይሬክተር ዶ ስቶርክ የሳዑዲን የሰብዓዊ መብት
ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡፡
‹‹Many countries have problematic records, but Saudi Arabia stands
out for its extra ordinary high level of repression and its failure to
carry out its promises to the Human Rights council››
ብዙ አገሮች በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው መጥፎ የሚባሉ ቢኖሩም፣ የሳዑዲ የባሰ ስለመሆኑ የስቶር መደምደሚያ በቂ
ገላጭ ነው፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ፍቅረኛ በመሆኗ የሰብዓዊ መብት ጥሰቷ ተጋንኖ በዓለም
አቀፍ ደረጃ አይነገርም እንጂ በኢሰብዓዊነት ቀዳሚ አይገኝላትም፡፡ ሂውማን ራይትስ ዎች በተለያዩ ጊዜያት
የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ሳዑዲ ሁሉም ዓይነት ሰብዓዊ መብቶች የሚረገጡባቸው መሆኗን ይገልጻሉ፡፡ የሰብዓዊ መብት
ተሟጋቾች ጋዜጠኞችና ሲቪል ማኅበራት መታሰር፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ መድልኦዎች፣ የፖለቲካና የነፃነት
አፈና፣ የፍትሕ ሥርዓት ደካማነትና የሞት ቅጣት በተቋሙ የተገለጹ ክፍተቶች ናቸው፡፡
በሳዑዲና በሌሎች አገሮች ዜጎች ላይ የሚፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአብዛኛው ከስደተኛ ሠራተኞች ጋር
በተያያዘ የሚፈጸመው ነው፡፡ ‹‹As if I am not Human: Abuses against Asian Domestic
Workers in Saudi Arabia›› በሚል በሂዩማን ራይትስ ዎች የተሠራው ጥናት ሳዑዲ የሠራተኞች ደመወዝ
የማይከፈልባት፣ ዕረፍትና ነፃነት የሌለባት፣ የተለያዩ የአካል፣ የሥነ ልቦናና የወሲብ ጥቃት መናኸሪያ ሆናለች፡፡
በጥናቱ እንደተገለጸው በሳዑዲ የቤት ሠራተኞች ከሠራተኛ ሕግ የተገለሉ፣ (ቪዛን መያዝና ማስተላለፍን ጨምሮ)
ለቀጣሪው ሰፊ መብት በሚሰጥ የካፋላ ሥርዓት (The kafala system) የታሰረ፣ አስገዳጅ ሥራና ባርነትን
የመሰለ የሥራ ሁኔታ የተንሰራፋበት ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ2011 ‹‹Domestic Workers Convention›› በማፅደቅ
ለሠራተኞች መሠረታዊ መብቶችን ያጎናፀፈ ቢሆንም፣ ሳዑዲን ጨምሮ የዓረብ አገሮች ኮንቬንሽኑን ለመፈረምም ሆነ ብሔራዊ
ሕግጋታቸውን ለመለወጥ እየሠሩ አይደለም፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያን በተመለከተ በእስያዎችና በአፍሪካውያን የቤት ሠራተኞች
ላይ ብዙ ግፍ እየተፈጸመ በኢሰብዓዊነቷ ፀንታለች፡፡ በቅርቡ የሳዑዲ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት የቤት ውስጥ
ሠራተኛን የሚገዛ ደንብ አፅድቋል፡፡ ይህ አዲስ ደንብ የቤት ውስጥ ሠራተኛ በቀን ዘጠኝ ሰዓታት እንዲያርፉ፣
በሳምንት አንድ የዕረፍት ቀን እንዲኖራቸው፣ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ደመወዝ የሚከፈልበት የአንድ ወር ዕረፍት
እንዲኖራቸው ደንግጓል፡፡ ሆኖም ይሄው ደንብ የቤት ሠራተኞቹ የእስልምናን ሕግ ወይም የአገሪቱን ሕግና ደንብ
ካላከበሩ የቤት ውስጥ ሠራተኞቹ እንዲባረሩ ወይም እንዲቀጡ፣ የቤት ውስጥ ሠራተኞች ማንኛውንም ሥራ ያለ በቂ
ምክንያት ከመሥራት እንዳይቆጠቡ ጠንካራ ግዴታ ይጥላል፡፡ ይህ ሕግ በግራ የተሰጠውን በቀኝ የሚነጥቅ ከመሆኑ
በተጨማሪ የቤት ውስጥ ሠራተኞቹን በጽሑፍ ለማይታወቅና ወሰኑ ላልተገደበ ግዴታ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ በሌላ በኩል
እንደማንኛውም የዓረብ አገሮች የቤት ውስጥ ሠራተኞች መብታቸው ሲረገጥ ጥያቄያቸውን በኅብረት ለማቅረብ የሚችሉበት
የሕግና የአተገባበር ወሰን አለባቸው፡፡ በብዙኃኑ አገሮች ከሌላ አገር ተወስደው የሚሠሩ የቤት ውስጥ ሠራተኞች
ማኅበር የማቋቋም መብታቸው በሕግ የተከለከለ ሲሆን፣ በአካል ተገናኝቶ ስለችግራቸው ለመነጋገር እንኳን የጊዜና
የመንቀሳቀስ መብት ገደብ አለባቸው፡፡
በኢሰብዓዊነት የመሸለም ተቃርኖ
ከላይ የገለጽናቸው በሳዑዲ የተንሰራፋው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አገሪቷን ከሰብዓዊ መብት ጽንሰ ሐሳብና
አተገባበር ያፋታት ቢሆንም፣ የተባበሩት መንግሥታት አገሪቱን ከመቅጣት ይልቅ መሸለምን መርጧል፡፡ ባለፈው ሳምንት
በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉባዔ (Human Rights Council) የአባላት ምርጫ ላይ
ቻይናና ኩባን ተከትላ ሳዑዲ ዓረቢያ የጉባዔው አባል ሆናለች፡፡ ይህ ጉባዔ የቀድሞውን የተባበሩት መንግሥታትን
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የተካ፣ ለሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብት መከበር እንዲኖር የሚሠራና በአባል አገሮች ላይ ሁሉ
አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ (Universal Periodic Review) የሚያከናውን ነው፡፡ የጉባዔው አባላት ሆነው
የሚመረጡ አገሮች በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው ጥሩ መዝገብ ያላቸው፣ በአገራቸው የሰብዓዊ መብት ለውጦችን ለማምጣት
ቁርጠኛ የሆኑና በርስ በርስ መገማገሚያው ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑ ናቸው፡፡
ሳዑዲ ለዚህ ጉባዔ አባልነት ስታመለክት በየአውዱ ተቃውሞ ገጥሟታል። ስድስት የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ባወጡት
መግለጫ ሳዑዲ ዓረቢያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዋን ካላሻሻለችና የዜጎቿንና የውጭ ዜጎችን የሰብዓዊ መብት ጥሰት
ካላሳመረች የጉባዔው አባል ልትሆን እንደማይገባ ወትውተዋል፡፡ እነዚህ ቡድኖች ለሳዑዲ ንጉሥ በጻፉት ደብዳቤ
እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ሐሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ ታስረው የሚገኙት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የሲቪል
ማኅበራት አባላት እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ ሳዑዲ እ.ኤ.አ. በ2009 በሰብዓዊ መብት ጉባዔ ባቀረበችው ሪፖርት መሠረት
የሰብዓዊ መብት ሁኔታዋን አለማሻሻሏ ለአባልነት ብቁ እንደሚያደርጋት ተጨማሪ መከራከሪያ ሆኗል፡፡ ስድስቱ ቡድኖች
ሳዑዲ በጉባዔው የተሰጣትን አስተያየት በማስታወስ አስተያየቶቹን እንድትተገብር ጠይቀዋል፡፡ የወንድ የበላይነትን
በማስፈን በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ መድልኦዎች እንዲቆሙ፣ ሕፃናትን ጨምሮ በማንም ላይ የሞት ቅጣት እንዳይፈጸም
መከልከልና ለውጭ አገሮች ሠራተኞች ተገቢውን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እንድትሰጥ ሳዑዲ ተጠይቃለች፡፡
ቡድኖቹ ከጠየቁት በተጨማሪ የሳዑዲ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ለጉባዔው አባልነት ብቁ እንደማያደርጓት መተንተን
ይቻላል፡፡ ቀዳሚው ሳዑዲ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምታሳየው አለመተባበርና እንቢታ ነው፡፡ የተባበሩት
መንግሥታት የመቆጣጠሪያ ተቋማት እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ የሳዑዲን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ለመመርመር ጉብኝት
እንዲያደርጉ ቢጠይቁም፣ እስካሁን ሳዑዲ ባለመፍቀዷ የተሳካለት የለም፡፡ ምርመራው ቢከናወን ኖሮ ኢትዮጵያውያንን
ጨምሮ በሳዑዲ የግዞት ቤቶች የሚሰቃዩት የሌሎች አገሮች ዜጎች ዓለም አቀፋዊ ውግዘትን ባስከተለ ነበር፡፡ የተባበሩት
መንግሥታትን የማይተባበር አገር እንዴት ለሰብዓዊ መብት ጉባዔ አባልነት እንደምትበቃ የመረጧት አካላት ብቻ ናቸው
የሚያውቁት፡፡ ሁለተኛው ሳዑዲ የተባበሩት መንግሥታት ያወጣችውን ዋና ዋና የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን ያልፈረመች
አገር መሆኗ ነው፡፡ የሲቪልና የፖለቲካ ቃል ኪዳን ስምምነት፣ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ቃል ኪዳን
ስምምነት፣ የፀረ መድልኦን ለማስቀረት የተፈረመው ስምምነትና የኢኮኖሚ ስደተኛ ሠራተኞችና የቤተሰቦቻቸውን መብቶች
የሚደነግገው ዓለም አቀፍ ስምምነት የሳዑዲ መንግሥት ካልተፈረመው ውስጥ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ስቶርክ ሁለቱ ምክንያቶች
በሁሉ አቀፍ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት ግምገማ ላይ ሊታዩ ይገባቸው እንደነበር ሲገልጹ፣ ‹‹Saudi Arabia’s
exceptionally poor record of cooperation with the UN and its refusal to
ratify major human rights legislation should be key features of
universal periodic review›› ብሏል፡፡ ሌላው የውጭ ዜጋ የሆኑ ሠራተኞችን በተመለከተ በዓለም አቀፍ
ደረጃ የሚስተዋለው የሳዑዲ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ ለአሠሪ ፈቃድ ሥልጣን የተተወ የሠራተኞች መብትና ተከትለው
የመጡት ደመወዝ ያለመከፈል፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጥቃቶች፣ የግድ ሥራና ባርነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ የሳዑዲ
መገለጫዎች የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ አባል ከሆነችም በኋላ በኢትዮጵያውያን ላይ መቀጠሉ አገሪቷ ለሰብዓዊ መብት
መጠበቅ ያላትን ዝቅተኛ ቦታ አመላካች ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት አሠራር ግን ለምዕራባውያን ኃይሎች የሚደግፉ አገሮችን በዝምታ የሚመለከት፣ የደሃ
አገሮችን ካልሆነ በኢኮኖሚ ደህና የሆኑ አገሮችን የማይመለከት፣ ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በአደባባይ
ለማውገዝ የሚዘገይ በመሆኑ ሳዑዲን ሸልሟታል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉባዔ አባልነት ሰብዓዊ መብትን በማስፋፋትና
በማስጠበቅ በተደረገ አስተዋጽኦ አለመሆኑ ከሕጋዊ ሰነዱ አፈጻጸሙ እጅጉን የራቀ መሆኑን ያመላክታል፡፡ በአንድ ጽሑፍ
አሜሪካዊ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በዚህ የተባበሩት መንግሥታት አካሄድ ላይ ሲሳለቅ፣ ‹‹No State no
matter how poor its human rights record, is barred from membership. Even
states under Security Council sanction for human rights abuse, may
become member›› ይላል፡፡
ምን ይደረግ? ምን አይደረግ?
ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ የደረሰባቸውን ሞትና እንግልት መነሻ አድርጎ ብዙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ወዳጆች
ቁጣቸውን በአደባባይ ገልጸዋል፡፡ የአገራችን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በጉዳዩ እጅጉን ተናድደው ለአፍሪካውያን
አቻዎቻቸው መግለጻቸውን ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ ሳዑዲ በአገሯ የሚገኙትን የውጭ ዜጎችን ሕገወጥ ሆነው ባገኘቻቸው መጠን
ሕጋዊ ዕርምጃ የመውሰድ መብቷ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሕገወጥ ናቸው በሚል ግን በአደባባይ መጎተት፣ ማቁሰል፣
ማሰቃየትና መግደል በዓለማዊውም በመንፈሳዊውም ሕግ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው፡፡ በአደባባይ ግድያ የሚያምን
አገር ሕግ፣ የሕግ ሥርዓት፣ ፍርድ ቤትንና ፍትሕን የማያውቅ መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አገራችን ይህንን
የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአገሮቹ መካከል ያለውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጥኛ መነሻ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ዜጋውን
ከሌላ አገር ጥቃት የማይጠብቅ መንግሥት ሕዝባዊ መሠረቱን ማጣቱ አጠያያቂ ስለማይሆን ከኤምባሲው ማብራሪያውን
ተቀብሎ፣ የግንኙነቱን መስመር- ቀይም ይሁን አረንጓዴ- ማስመር ይጠበቅባታል፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት የአፈጻጸም ሥርዓት ለሀብታሞቹ አገሮች ያደላ ቢሆንም፣ መንግሥት ማስረጃዎቹን
መሠረት አድርጎ ለተባበሩት መንግሥታት አቤቱታ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ሳዑዲ በፈረመቻቸው የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች
መሠረት የሰዎችን በሕይወት የመኖር፣ የመሥራትና የነፃነት መብት ልታከብር ይገባል፡፡ ካላከበረች ዓለም አቀፍ ሕግ
በሚፈቅደው መጠን ከድርጊቷ እንድትቆጠብ፣ ተጎጅዎችን እንድትክስና ይቅርታ እንድትጠይቅ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡
ከዚህ በፊት ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ሳዑዲ በመከላከያ ሚኒስቴሯ አማካይነት የተናገረችው፣ አሁንም
በዜጎቻችን ላይ የፈጸመችውን ግድያና እንግልት መመርመር፣ ማጥናትና ተገቢውን የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ግድ
ይላል፡፡ እነርሱ ሰፋፊ የእርሻ መሬት አገራችን ላይ ተቀብለው ሕዝባቸውን እየመገቡ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ደሃ
እህቶቻችን በጉልበታቸው ያገኙትን የደመወዝ መከልከልና ማሰቃየት ሚዛናዊ ካልሆነ ለአገራችን ጎጅ መሆኑ ነጋሪ
አይፈልግም፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም አሁን ድምፃቸውን ካላሰሙ እስካሁን
ስለአገራችንም ስለሌሎችም የተናገሩትን ለማመንና ለመቀበል እንቸገራለን፡፡ ማንም በፍትሕ የሚያምን አካል
‹‹በኢሰብዓዊነት የሚከብርን›› አገር ድርጊት ካልተቃወመ ዓለሚቱን ተጋርተን መኖራችን ትርጉም ያጣል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው getukow@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/11/18/56544-2/
No comments:
Post a Comment