ኢትዮጵያውያን
እንደ አሁኑ ተገፍተን ገደል ጠርዝ የቆምንበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም። እስከ አሁን ትንንሽ መሸሻ ስለነበረን
ፍርሃታችንን እንኳን ከሰው ከራሳችንም ደብቀን ስናፈገፍግ ኖረናል። ፈሪነታችንን ባባቶቻችን ጀግንነት፣ ውርደታችንን
ባባቶቻችን ኩራት እያለበስነው መጓዝ የማያዛልቅ ለመሆኑ ከሰሞኑ የበለጠ ምስክር ምን አለና።
ያጋጠመን
ብሄራዊ ውርደት ከፊሎቻችንን ከእንቅልፋችን ገና ሲያባንነን ብዙዎቻችንን አጥንታችን ድረስ ገብቶ ተሰምቶናል።
አባቶቻችን “ሞት ሲዘገይ የቀረ ይመስላል” እንዳሉት ባንዳንዶች ላይ የደረሰው ውድቀት እኛን ስላልነካን የሚቀር
መስሎን ነበር። በገዥዎቻችን በየለቱ በምትወረወረዋ ከፋፋይ የቤት ስራ ተጠምደን ግዙፉ ህልውናችን አዳጋ ላይ መሆኑን
እንኳ ማየት ተስኖን ነበር።
የአገርን አንድነት የሚያስጠብቅ እድሜ ልኩን ቀበሮ ጉድጓድ የኖረ ሰራዊት ሲበተን፣ የጥርሱ ወርቅ በመዶሻ ሲወልቅ፣ መሳርያውን አስረክቦ ቤተሰቡ ዘንድ መድረሻ ትራንስፖርት ሲለምን ምን አድረረግን?
በአገሪቷ አንጡራ ሃብት የተማሩ ምሁራን ከብቸኛው ዩኒበርስቲ አርባዎቹ ሲመነጠሩ፤
አማራው እንደዋና ጠላት ተቆጥሮ ገደል ሲጣል፣ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የጮሁት ፕሮፌሰር አስራት እስር ቤት ሲበሰብሱ፣ ብሎም በግፍ እንዲሞቱ ሲደረግ፤
ኦሮሞው የተለያየ ስም እየተሰጠው ሲገደል፣ እስር ቤቱን ሲያጣብብ፤
አኝዋኩ ከገዛ መሬቱ ተነቅሎ ለሳውዲና ለህንድ ሃብታሞች እንዲለቅ ለማድረግ እንዳውሬ ሲታደን፤
መምህሩ ስርዓተ ትምህርቱ እንዲሻሻልና መብቱን በመጠየቁ ማህበሩ ሲበተን መሪዎቹ ሲታሰሩና አሰፋ ማሩ በጠራራ ፀሃይ ሲገደል፤
ነጋዴው ከሙያው ተፈናቅሎ በወያኔ ኩባንያዎች በሞኖፖል ሲታፈን፤
ህዝቡ በነጻ የመረጣቸው ወኪሎቹ ሲታሰሩና የምርጫ ኮሮጆ ሲገለበጥ፤
በሰላም ተቃውመው የወጡት የአጋዚ ኢላማ ሲሆኑ፤
ጋዜጠኞች እውነትን በመዘገባቸው ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ፣ ሲታገዱና ሲሰደዱ፤
የኦርቶዶክስ አማኞች ሆኑ ገዳማት ሲደፈሩ ፤
ሁለት ዓመት ሊሞላው ያለ የእስልምና ተከታዮች እንቅስቃሴ ሲቀጠቀጥ፤
ተቃዋሚዎች መሪዎችቸው ባሸባሪነት ክስ ወህኒ ወርደው ሲማቅቁና ያሉትም ከእስር ባልተናነሰ እንዲኖሩ ሲገደዱ፤
የት
ነበርን?? ይህ ሁሉ ሲፈጸም የት ነበርን?? እያልን መጠየቁ ጅል የሚያስመስል ቢሆንም፤ ምን ያህል እንደተኛንና
ለዚህ ሁሉ ውድቀት ከአገሪቱ ጠላቶች ያላነሰ ስህተት መፈጽማችንን ያስገነዝበናልና። ዛሬ በእህቶቻችን ጩኸት ምክንያት
እንባ ባረጠበው ዐይናችን ትናንትን አሻግረን ማየት ግድ ይለናል። የጠላቱን ምንነት ብቻ የሚያውቅና የራሱን
ድክመትና ጥንካሬ ያልተገነዘበ ለድል አይበቃምና።
ይህ ሁሉ ተራ በተራ በስልት ሲፈጸም አንድ ሆነን መነሳት አቅቶን ዛሬ ጽዋው ሞልቶ መፍሰስ ሲጀምር የነቃን ይመስላል።
ዛሬም
መንቃታችን አልዘገየም። ንቃታችን በቅጡ ሊያዝ ግን ይገባዋል። የብሄራዊ ውድቀታችን ጥልቀቱ ጎልቶ የወጣው በሳውዲ
ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግፍና ይባስ ብሎ የወያኔ ኢህአዴግ መንግስት ያሳየው እብሪተኝነት ነው። ወያኔ
ባስቀመጠልን ትንንሽነት ተወስነን ስንባላና ስንነታረክ ብዙ ወርቅማ ጊዜ አሳልፈናል። የሚቆጨው ግን ካሁን በኋላ
የምናሳልፈው ከንቱ ጊዜ ካለ ነው።
በሳውዲ አሸዋ ላይ የፈሰሰው የወገኖቻችን ደም የአማራ፣ የኦሮሞ፣
የትግሬ፣ የሶማሌ፣ የክርስቲያን፣ የእስላም፣ የኦነግ፣ የግንቦት ሰባት፣ የኢህአፓ ወዘተ..ብለን የምንለየው
አይደለም። ሬሳቸው የተጎተተው፣ የተደፈሩት፣ የታጎሩት ከውሻ ያነሱ ሆነው የታዩት በኢትዮጵያዊነታቸው ነው። ዛሬ
በሲቃ “አድኑን” እያሉ የሚጮሁት ወገኖቻችን “ኢትዮጵያውያን ድረሱልን” እያሉ ነው። “የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ
መንግስት የለንም” ብለዋል በድምጻቸው።
ለሳውዲዎች ስጋና ፍራፍሬ፣ አበባና ማዕድናት፣ ገረድና እቁባት
የሚሆኑ ህጻናት እየመለመሉ በማቅረብ በሃብት የደለቡ የወያኔ ባለስልጣናት ይደርሱልናል የሚል ብዥታ የላቸውም።
ህገወጦች ላይ እርምጃ የመውሰድ መብት አላቸው የሚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ወንድም እህቶቻችን ላይ የሚፈጸመው ግፍ
ይቁም ያሉ የሰማያዊ ፓርቲ ሰዎችን ለምን ሳውዲዎችን አወገዛችሁ ብሎ የሚቀጠቅጥ መንግስት የኛ ነው ብለው
አይቀበሉትም።
አድኑን ብለው የጠየቁት እኛን ነው።
ማዳን ያለብን ዛሬ ባደባባይ የሚጮሁትን ወገኖቻችንን ብቻ አይደለም። ማዳን ያለብን አገራችንንና እራሳችንን ካለንበት ውርደት ነው።
መታገል
ያለብን ለዚህ ያበቃንን ስርዓት ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን ጨቋኝ ስርዓት በጸጋ ለመሸከም ያበቃንን ድክመታችንንም ነው።
ያ ደግሞ ያንድ ሰሞን ሰላማዊ ሰልፍና ግርግር የሚመልሰው አይደለም። ደጋግሞ ከሚያጠቃን ስሜታዊነት መላቀቁ የትግሉ
ቅድመ ሁኔታ መሆን አለበት።
ወያኔዎች የለመዱንና አሁንም ተስፋ የሚያደርጉት ያንድ ሰሞን ጫጫታችን
እንደጉም ተኖ ወደነበርንብት የየግል ቁዘውማ እንድንገባና እነሱ ባቀዱልን ክፍፍል ስንፋጅ የዘረፋና ዘረኛ
አገዛዛቸውን በሰፊው ለበቀጠል ነው። አቦ ፀሃይ የሞቀውን እውነት በመደጋገም ላሰለቻችሁ አልፈልግም። “ወሬ ቢበዛ
በአህያ አይጫንም” ተብሏልና ምን እናድርግ ወደሚለው እንሻገር።
በዚች አገር ለውጥ ለማምጣትና ካለንበት
ብሄራዊ ውድቀት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመውጣት የተወሰነ ቡድን፣ ድርጅት ሆነ ግለሰብ ሃላፊነት አይደለም። ሁላችንም
የራሳችንን ሃቅምና ችሎታ እየመረመርን በየት ብሰለፍ የበለጠ አስተዋጾ አደርጋለሁ የሚለውን ካወቅን በኋላ የማንንም
ጎትጓችነት ሳንጠብቅ መንቀሳቀስ ነው። ሁሉም ለዚች አገር ማድረግ የሚችለው ትንሽ ነገር አለው። ያም ትንሽ ነገር
ሲጠራቀም ነው ትልቅ ብሄራዊ ሃቅም የሚሆነው። እስቲ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንጀምር።
ምሁራን፡
አገሪቷ በሌላት አቅም አስተምራን በአገር ውስጥና በዓለም ተበትነን እንገኛለን። ለዚይች ድሃና ኋላ ቀር ለምንላት
አገር ምን ያህል እንደሰራንላት ራሳችንን እንጠይቅ። እስካሁን ለውጥ ለማምጣት እየተማገዱ ያሉትንና ከባዱን መስዋዕት
የከፈሉትን ዋጋቸውን ሳንረሳ ሌሎቻችን አንድም ምን ማድረግ እንደምንችል ባለመገንዘብ ሌላም በመማራችን ያገኘነው
መልካም እድል እንዳይደናቀፍና እንዳይጓደል እያየን እንዳላየን ተኝተን ቆይተናል። ምኝታው ይብቃን። የያዝነው
ሳይጓደል ጭምር ብዙ አስተዋጾ ማድረግ ስለሚቻለን ከልብ የበኩላችንን እናድርግ። በዩኒቨርስቲ ምኩራቦች፣ በትላልቅ
ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ድርጅቶች፣ በልዩ ልዩ ዘርፍ ተደላድለን ሌሎችን በሽሙጥ ብንወርፍ ወይም እንደሰጎኗ
ራሳችንን ብንቀብር ምን ጥቅም አለው። ቢያንስ ቢያንስ ምናችሁም ሳይነካ ህዝቡን በማሳወቅ ለመስራት እንዳሁን የተመቸ
የቴክኖሎጂ ጊዜ የለም። ያወቀ ህዝብ ሃያል ይሆናል። በዚህ ዙርያ ተሳትፎውን ቀድማችሁ የጀመራችሁም ለማን
እንደምትጽፉ አስተውሉ። ለአሜሪካኖች፣ ለፈረንሳዮች አይደለም ለኢትዮጵያውያን መሆን አለበት። በቀላል ኢትዮጵያዊ
ቋንቋ ጻፉ ካልሆነም ስራችሁ ተተርጉሞ እንዲደርሰው አድርጉ። ለተማረውና የነገር መላላጫ ሲያወጣ ለሚውለው ክፍል
ከሆነ ስራችሁ ኢላማውን ስቷል።
ፖለቲከኞች፡ ጊዜአችሁንና
ሃቅማችሁን የራሳችሁን ዓላማ በማስረዳትና ደጋፊ በማጠናከር እንጂ ሌላውን ጥላሸት በመቀባት አትዋትቱ። እስካሁን
ጠንክሮ ያለመውጣታችሁ ትልቁ ችግር የወያኔ ዱላ ወይንም የህዝቡ ቸልተኝነት ብቻ አይደለም። የዓላማ ጥራትና ጽናት
ጉድለት ነው። ዓላማችሁ ጠርቶ ከታወቀ፣ በዚያም ጸንታችሁ የምትታገሉ ከሆነ ከምትፈልጉት በላይ ኃይል ይከተላችኋል።
እንደሰርገኛ ላንድ ሰሞን ግርግርና ሞቅ ሞቅ አድርጓችሁ የሚሸሸው ከናንተ የሚያገኘውን ስላጣ ነው። አርቲፊሻል አበባ
ላይ ማር አገኛለሁ ብሎ የሚሰፍር ንብ የለም።
በቀለምና በጊዜያዊ መአዛ ሳይሆን በይዘታችሁ ማር የሚቆረጥባችሁ ሆናችሁ እስካልተገኛችሁ ድረስ መጠውለግ የራሳችሁ ውጤት ነው።
ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፡
እስካሁን በየቦታው የሚደረገውን ሰባዊ መብት ጥሰት በማጋለጥ የተጫወታችሁት ሚና ቀላል ባይሆንም ከመሰል ግርጅቶችና
ግለሰቦች ስራችሁን በማቀናጀት ሚዛናዊ የሆነውን ሪፖርት ለህዝቡና ለሚመለከተው ክፍል ሁሉ በማቅረን ትጉ።
መረጃዎችም የሚሰባሰቡበት የዳታ ማዕከል ፍጠሩ። ተመራማሪዎች፣ የታሪክ ሰዎች፣ ፍርድ ሰጪ አካላት፣ አጠቃላይ ህዝቡ
በቀላሉ የሚያገኛቸው ይሁኑ።
የሃይማኖት አባቶች፡ የሃይማኖት
መሰረታዊ ተልዕኮ ለፍትህ መቆም ነው። ፍትህን የማይሰብክና ለፍትህ የማይቆም እምነት ፈጣሪ ከሰጠው ተልዕኮ ውጭ
ነው። ፖለቲካን አይደለም ፍትህን ስበኩ። በደልን ማንም ይፈጽመውማን ማውገዝ አለባችሁ። ከዚያ የዘለለ ከናንተ
አይጠበቅም። የታላላቅ ሃይማኖቶች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ፍትህ ሳይኖራት ሃይማኖቷ ምን ፋይዳ ይኖረዋል።
ጋዜጠኞች፡
ሃሳብን በነፃነት መግለጽ ባልተለመደባት አገራችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የህዝብ ድምጽ ለመሆን የታገሉት በርካታ
ቢሆኑም፣ ብዙዎቹ በእስር ቢማቅቁም፣ ከፊሎቹ ቢሰደዱም ትግሉ አልሞተም። መስዋዕቱ የከፋ ቢሆንም አሁን ካለንበት
በበለጠ እንድንታገል እንጂ እንድንዘናጋ የሚያደርግ ሁኔታ ስለሌለ ትግላችን በእጥፍ እንዲጎለብት እንነሳ። በተለያየ
መንገድ ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ እንዲደርስ መሻትና መታገል የጊዜው አብይ ጥያቄ ነው። የዘመኑ ቴክኖሎጂ በፈቀደልን
ሁሉ መንገድ መጠቀምና ሃቅምን አስተባብሮ መስራት ውጤቱ ትልቅ መሆኑን አይተናልና እንቀጥልበት።
ዲያስፖራ፡
ይህንን ክፍል ለይቼ ያነሳሁን ያለምክንያት አይደለም። ለትግሉ ወሳኝነት ባይኖረውም ተጽዕኖው ከባድ ስለሆነ ነው።
በግድም በውድም አገሩል ለቆ የሄደው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ቀላል አይደለም። የማይገኝበት የዓለም ክፍልም የለም።
የኤኮኖሚ ሃቅሙና ዕውቀቱ ደግሞ በሚገባ ከተያዘ አገሪቱን ካለችበት የድህነት አዘቅት ከሚያወጧት ሰፊ ሃብቶች ትልቁ
በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ነው። እስከ አሁን የገንዘብ አቅሙን ወያኔ ለድሜው ማራዘምያ በስልት ተጠቅሞበታል። ይህ
ሊያበቃ ይገባል። ዲያስፖራ በነጻነት ከወያኔ ተፅዕኖ ውጭ ስለሚኖር ምንም ጉዳት ሳያገኘው ህዝቡን ለነፃነት የሚያበቃ
ትግል ውስጥ መሳተፍ ይችላል። በድህነት የሚማቅቁ ቤተሰቦችን መቶና ሁለት መቶ ዶላር በየጊዜ በመወርወር ከችግር
ማላቀቅ አይቻልም። ስርዓቱን በመለወጥ በነፃነት ሰርተው የሚኖሩባት አገር መፍጠሩ ዘላቂነት አለው። ሳይዘገይ ፈጥኖ
መድረሻው አሁን ነው።
ሌላው ኢትዮጵያዊ፡
ቀሪው ኢትዮጵያዊ ዳር ቆሞ ከሌሎች ተአምር ከመጠበቅ ራሱን ባመነበት አቅጣጫ አሰልፎ መንቀሳቀስ ያስፈልገዋል።
ከላይ የተጠቀሱትን የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሰባዊመብት ተሟጋች ተቋማት፣ የሃይማኖት ድርጅቶች፣ ማስሚድያዎች፣ የሲቢክ
ተቋማት እንዲጠናከሩ አባል ሆኖ እውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብን ማበርከት የመከራውን ጊዜ ያሳጥራል። በሳውዲና በሌሎችም
የአረብ አገሮች የሞቱና የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ድምፅ ገንፍለን እንድንወጣ ያደረገን ሁሉ ተመልሰን ወደወትሮው
ምሽጋችን አንግባ። ተጋድሎአችን በተግባር ነፃነት እስኪገኝ መቀጠል አለበት። ጽዋው ሞልቶ ፈስሷል። ብሄራዊ
ወርደታችን ገደል ጫፍ አድርሶናል። ከዚህ በላይ መገፋት የሚያመጣው ውጤት ማንነታችንን ማጣት ነው የሚሆነው።
ሰልፉ፣ ጩኸቱ፣ ለቅሶው ይቁም ባይባልም ተጨባጭ ወደሆነ ተግባር ይቀየር።
ኢትዮጵያ ወደ እውነተኛ ክብሯ ትመለስ!
ዜጎቿ ከብሄራዊ ውርደት ይዳኑ!
በደልን የመታገል እንጂ የመሸከም ጽናት አይኑረን!
ፍቅርና መተባበር በሁሉም ኢትዮጵያዊ ይስፈን!!
ጸሃፊውን በ amerid2000@gmail.com ማግኘት ይችላሉ
https://ecadforum.com/Amharic/archives/10198/
No comments:
Post a Comment