(መሪ ቃሉን ፋሲል ተካልኝ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየን ከያኔ አብርሃም አስመላሽ ካቀረበው የግጥም መድብል
አንዷን ስንኝ ወስጄ ነው የዛሬውን ጹሑፌ ያቀረብኩት ። ግጥሙን በሙሉ ለማንበብ የዘ-ሐበሻን ድሕረ-ገጽ ከፍተው
ያንብቡ።)
እኔ የዚህ ጹሁፍ አቅራቢ በደርግ ዘመነ መንግሥት በአንድ ጊዜ በአራት የወንጀል ዓይነቶች ተጠርጥሬ ታስሬ በልዩ
የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ 214 ሀ እና ለ ወይም ንኡስ አንቀጽ 23 ተብለው በተጠቀሱ ድንጋጌዎች ይመስለኛል የሞት
ፍርድና የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት በሚያስቀጣ ወንጀል ተከስሼ ነበር።ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንዲሉ
በነዚህ ባለጊዜዎችም እንዲሁ ታስሬ በዋስ ተፈትቼ ጉዳዩ በተንጠልጠል ላይ እያለ ወደዚህ አገር ለመምጣት ችያለሁ።
አፍላው የወጣትነት ዘመንና የጉርምስናውን ወቅት እናት አባት ባሉበት ከቤተሰብ ሳይለዩ ከአብሮ አደግና ከሰፈር ጓደኛ
ጋር ጊዜን በደስታ ማሳለፈና ለአካለ መጠን ሲደርሱም ዲል ባለ አዳራሽ ወዳጅ ዘመዱ ተጠርቶ ጋብቻ መፈጸም አቅም
በሚመጥነው ደረጃ ተመድቦ በመሥራት ወላጅን መጦር ቤተሰብን ማስተዳደር ሀገርን ማገልገል የሚባል ወዘባው ጠፍቶ
ይህችን ጥቂት ጊዜ የምንቆይባትን አጭር እድሜም በትግል ማሳለፍ አንድ አዲስ ትውልድ ተወልዶ ባደገበት አገር
በትውልድ ቀየው ለሙያ ሳይበቃ በትምህርት ቤት ሕይወቱን በውል ሳያገናዝብ ጧት ወጥቶ ማታ ለመመለስ ዋስትና በሌለበት
የባንዳ ልጆችና ብረት አምላኪዎች ተደራጅተው ሀገር በሚያውኩበት መፈጠርና የተንጠለጠለች ሕይወት ይዞ መኖር መኖር
ሊባል ይችላልን? እኔ በሕይወት አለሁ ቢያንስ ያሳለፍኩትን የጨለማ ሕይወት አሁንም ያለሁበትን የባርነት ዘመን ኑሮ
መናገር እችላለሁ ሳይኖሩ የሞቱ ሴት እህቶቼንና ወንድሞቼን ሳስብ እጅጉን ልቤ በሀዘን ቀስት
ይወጋል።ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ- ሀገሬ ኢትዮጵያ-የኢትዮጵያን ሕዝብ የምወድ -ለሀገሬ እድገትና ብልጽግናን የምመኝና
የምሠራ -እንዴት በትውልድ ሀገሬ መማር፤መሥራት ፤ንብረት ማፍራት ፤ ቤተሰብ መመሥረትና ቤተሰቤን ማስተዳደር፤ መጦር
ያለባቸውን ወላጆቼ መጦርና በነጻነት መኖር ይነፈገኛል?እንደኔ የዜግነት መብታቸው ተገፎ የትውልድ ሀገራቸውን ጥለው
እንዲሰደዱ የተገደዱ ፤በሀገራቸውም ሌሊት ከመኖሪያ ቤታቸው እየታፈኑ ቀን ከሚሠሩበት የሥራ ገብታ እየተዘረፉና
በየጎዳናው እየታፈሱ እስር ቤት አጨናንቀው የሚገኙ እህትና ወንድሞቼ እውን በቁማቸው አልሞቱም? ሳይኖሩ መሞት ቢባል ስህተት ሊሆን ይችላልን?
ወይንስ ይኸም ኑሮ ነው ሊባል ነው። ? ሕይወትን ለማትረፍ በሚደረግ ጥድፊያ የሰሃራን በርሃ ለማቋረጥ ሲሉ
ስንቶቹ ሕይወታቸውን አጡ ።ስንቶች ኢትዮጵያውያንን የዱር አውሬ በላቸው፤ስንቶችስ ውሃ እንደጠማቸውና መብላት
እንደፈለጉ ሞቱ፤ስንቶቹስ በሞት አፋፍ ላይ ይገኛሉ?የወገንን ሕይወት ለማትረፍ እነማን ናቸው ግንባር ቀደም
የቆሙት?እውነት ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ጠልተው ወይም ጠግበው የሚሰድዱ ይመስላችኋል?በፈላ ዘይትና ውሃ
የሚቀቀሉት? በየዐረቡ መዲና ጎዳና ላይ በጥይት የሚገደሉትና ፎቅ ላይ ተጥለው ተከስክሰው የሚሞቱት ጠግበው ነው? ህጻናቶቹ
የ15ና የ16 ዓመት ወጣቶች ሀገር ጥለው ሲወጡ በሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ሴተኛ አዳሪነት እንኳን አልሆን
ብሏቸው ሲሰደዱ ማንም የዐረብ ውርጋጥ ተቀብሎ ሲማግጥባቸው የሚሰማ ጀሮ የሚያስብ ሕሊና ላለው ይዘገንናል።«ኧረ ጎበዝ እኛን ኢትዮጵያውያንን ምን ነካን? ምን አይነቶቹ ትውልዶች ነው የተፈጠርን»? ጠግበው እንደወጡ የሚፈርጅባቸው ማን ነው ምን አግኝተው ማን አብልቷቸው ጠገቡና ነው እንዴትስ ጠግበው የተሰደዱ የሚባሉት ኢትዮጵያን የመሰለች ሀገር ያለው ሰው ሀገሩን ይጠላል እንዴ? በጭራሽ ይህ የማይታሰብ ነገር ነው። ይልቅስ ጥሬ ሀቁን እንነጋገርበት ካልን እናንተም እኔም ምሥጢሩን በሚገባ እናውቀዋለን።ምናልባት ይህንም እንደሚሥጥር ቆጥረነው ከእኛ ለተወለዱት በግልጽ ባለማሳወቃችን ጉዳዩ እንቆቅልሽ ሊሆንባቸው ይችል ይሆናል ። አሁንም ሌላ ስህተት ፈጸምን ማለት ነው።መረገም ይሉታል ይህ ነው።
ዋናው የችግሩ መንስኤና ተጠያቂው ህወሃትና የህወሃትን ደም የተጣቡ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ኃይሎች ሲሆኑ
ሌሎች ለዚህ ችግር መምጣት የመጀመሪያውን በር የከፈቱ ያደቆኑ ፤ያካኑ ዛሬም ያን ጮማ ምላሳቸውን እንዲያርፍ
ያለደረጉ የትውልድ ማለቅ ያጀገናቸው ኤርትራን ያስገነጠሉ፤ህወሃትን እዚህ ያደረሱና በርጅና በህወሃት በር ደጅ
እየጠኑ ህወሃትን የሚያበረታቱ የቀደምት የድርጅት አመራሮችና አባላትም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየቀለዱ ያሉ መሆናቸው
ግልጽ ሊደረግና ሕዝቡ ሊያውቃቸው ይገባል።« በተለይም አማራውንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን»
የኢትዮጵያ ኋላቀርነት፤ ድህነት፤ማይምነት፤የዴሞክርሲ መታፈን፤የዜጎች እኩልነት አለመከበር ምክንያት አድርገው
የተነሱና ለኢትዮጵያ አንድነትና በነጻነት ተከብራ እንድትኖር ሳይታክቱ የታገሉትን እየታገሉም እያሉ በሽምግልናቸው
እንኳ ርህራሄ ማድረግ ያልቻሉና የገደሉ (ክቡር ቢትዎደድ አዳነ መኮነንን ይመለከታል)፤የካቲት 1966ቱን የሕዝብ
እንቅስቃሴ ያስማረኩና ህወሃትን ያነገሱ በስም ሕብረ-ብሔር በተግባር ግን የአማራን ዘር ለማምከን ከጧቱ የተነሱና
የዘመሩ የመጡበትን መንገድ መመርመር አሁን ደግሞ መንገዳቸውን አስተካክለው ካልተጓዙ ያችን የጥፋት ካርዳቸውን
ማሳየት ብቻ ሳይሆን እንዳለ የድርጅቶችን ተግባር እየመዘዝን መረጃውን እያወጣን ታቀቡ ልንላቸው ዝግጁ
ነን።ምክንያቱም አሁን ላለው ትግል ተመክሮውም ሆነ አጠቃላይ መርሁ እጅግ የሚጎዳ በመሆኑ እንጅ ወደ ኋላ ተመልሶ
የነገር ቋንጣ ለማመንዥክ ወይም ታግየበት ሳይጠቅመኝ ጉድ አድርጎኝ ቀረ በሚል ስሜት በመገፋትና ፀፀት አይደለም።
ችግርን አለማወቅ አንድ ችግር ሲሆን ችግሩን እያወቅን ችግሩን ማስወገድ አለመቻል ግን የጎርፍ ውሃ እያሳሳቀ እንደሚወስደው ሰው እየሳቁ እንደመሄድ ነው የሚቆጠረው።
መተማመን ከሌለ እውነት አይኖርም” እውነት ከሌለ ፍቅር አይኖርም” ፍቅር ከሌለ ደግሞ ሰላምና አንድነት
አይኖርም” ሰላምና አንድነት ሳይኖር ደግሞ የሚፈለገውን ዓላማ ከግቡ አደርሳለሁ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።
መተማመን ፦ በአባትና ልጅ ፤ በባልና ሚስት ፤ በወንድማማች ፤ በእህትማማች ፤ በወንድምና እህት ፤
በአክስት አጎት ፤ በቤተዘመድ ፤ በአብሮ አደግ ጓደኛሞች ፤ በቤተክህነት በሚያገለግሉ የሃይማኖት አባቶች ፤
በመስጊድ በሚያገለግሉ ሸኮች ፤ በአንድ ዓላማ በተሰለፉ የድርጅት ሰዎች ፤ በመንግሥት ሥራ ተሠማርተው በሚሰሩ
ሰራተኞች ፤ በስቪክ ማህበራት ፤ በንግድ ድርጅቶች ፤ በወታደሩ ፤ በደህንነቱ ፤ በፖሊሱ ፤በግብረ-ሰናይ
ድርጅቶች(ኤንጅኦ) ፤ በሙያ ማህበራት ፤ በገበሬው…ወዘተ ከጠፋና የውሃ ሽታ ከሆነ ረጅም ዓመታት አለፉ።
እውነት፦ በአባትና ልጅ ፤ በባልና ሚስት ፤ በወንድማማች ፤ በእህትማማች ፤ በወንድምና እህት ፤
በአክስት አጎት ፤ በቤተዘመድ ፤ በአብሮ አደግ ጓደኛሞች ፤ በቤተክህነት በሚያገለግሉ የሃይማኖት አባቶች ፤
በመስጊድ በሚያገለግሉ ሸኮች ፤ በአንድ ዓላማ በተሰለፉ የድርጅት ሰዎች ፤ በመንግሥት ሥራ ተሠማርተው በሚሰሩ
ሰራተኞች ፤ በስቪክ ማህበራት ፤ በንግድ ድርጅቶች ፤ በወታደሩ ፤ በደህንነቱ ፤ በፖሊሱ ፤በግብረ-ሰናይ
ድርጅቶች(ኤንጅኦ) ፤በሙያ ማህበራት ፤ በገበሬው…ወዘተ በዓለማችን ከጠፋ ረጅም ዓመታት አለፉ።
ፍቅር፦ በአባትና ልጅ ፤ ባልና ሚስት ፤ ወንድማማች ፤ እህትማማች ፤ ወንድምና እህት ፤ በአክስት
አጎት ፤ በቤተዘመድ ፤ በአብሮ አደግ ጓደኛሞች ፤ በቤተክህነት በሚያገለግሉ የሃይማኖት አባቶች ፤ በመስጊድ
በሚያገለግሉ ሸኮች ፤ በአንድ ዓላማ በተሰለፉ የድርጅት ሰዎች ፤ በመንግሥት ሥራ ተሠማርተው በሚሰሩ ሰራተኞች ፤
በስቪክ ማህበራት ፤ በንግድ ድርጅቶች ፤ በወታደሩ ፤ በደህንነቱ ፤ በፖሊሱ ፤በግብረ-ሰናይ ድርጅቶች(ኤንጅኦ)
፤በሙያ ማህበራት ፤ በገበሬው …ወዘተ ከተወገደ ረጅም ዓመታት አለፉ።
ሰላምና አንድነት፦ በአባትና ልጅ ፤ በባልና ሚስት ፤ በወንድማማች ፤ በእህትማማች ፤ በወንድምና
እህት ፤ በአክስት አጎት ፤ በቤተዘመድ ፤ በአብሮ አደግ ጓደኛሞች ፤ በቤተክህነት በሚያገለግሉ የሃይማኖት አባቶች ፤
በመስጊድ በሚያገለግሉ ሸኮች ፤ በአንድ ዓላማ በተሰለፉ የድርጅት ሰዎች ፤ በመንግሥት ሥራ ተሠማርተው በሚሰሩ
ሰራተኞች ፤ በስቪክ ማህበራት ፤ በንግድ ድርጅቶች ፤ በወታደሩ ፤ በደህንነቱ ፤ በፖሊሱ ፤በግብረ-ሰናይ
ድርጅቶች(ኤንጅኦ) ፤በሙያ ማህበራት ፤ በገበሬው…ወዘተ ከደፈረሰ ረጅም ዓመታት አለፉ።
በነዚህ ምክንያቶች የአገራችን ሉዓላዊነት ማስከበር ሳንችል ቀረን ፤ በእኩልነትና በመፈቃቀር ፤ በመተማመን ላይ
የተገነባ አንድነት ለመፍጠር አልችል አልን ፤ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ አምባገነን ወራሪዎችን ታግሎ መጣል
ሲገባ እጅ መንሳትና አጎንብሶ መሄድን መረጥን ፤ በብዕራቸው ህወሃትን በሚያስጨንቁት ላይ ተሳለቅን ፤ ከህወሃት
አፍንጫ ሥር ተደራጅተው እየታገሉ ያሉትን ህወሃት መጠነ ሰፊ ግፍ ሲፈጽምባቸውና ግፉ በዝቶ ሲፈስ ከሚገባው በላይ
ሲሄድ እዚህ በላይ ማለፍ አትችልም ቁም ማለት ተሳነን። ይህ ሁሉ የህወሃት ጌቶች በደደቢት ህወሃትን ያደቆኑበት
እኩይ መርህ መሆኑን እናውቃለን(ምዕራባውያንና ዐረቦች)። ዳሩ ግን ባርነትን መርጠናልና በባርነት መኖርን የመረጠው
በፈለገው መንገድ መሄድ መብቱ ነው። ጣልቃ መግባትና ማደናቀፍ ግን አይችልም መብቱ የለውም ጉዳዩ የሀገር
የኢትዮጵያ ጉዳይ ነውና።ባርነትን አልቀበልም እታገለዋለሁ ያለ ደግሞ ባርነትን ሊያስወግድ የሚችለውን የትግል ስልት
አንድነትን ሰንቆ መነሳት የግድ ይለዋል።በውጭ የሚገኘው ስደተኛ ኢትዮጵያዊ በአብዛኛው የመጣበትን ወይም ለስደት
ያበቃውን ምክንያት ጠንቅቆ የሚያውቅ ይመስለኛል።በመሆኑም ነው ህወሃት በውጭ ድጋፍ እንዲያጣ ያደረገውና በዓለም
ዙሪያ በየመድረኩ እየተሸነፈ የሚወጣው።ይህን ከዕለት ዕለት እንደ ሰደድ እሳት የሚቀጣጠል የሕዝብ እንቅስቃሴ
የህወሃት ግብረ በላዎች ወይም በትናንሽ ንግድ ወይም በኮንዶኒየም ጎጆ ተደልለው ለስለላ የተሰለፉ ሊገቱት
አለመቻላቸውና የህወሃት ሥርዓት ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሚያመለክት ነው።ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ግን
እላይ የጠቆምኳቸውን ችግሮች ተሸክሞ እየተጓዘ ነው። እንግዲህ እነዚያን የሰላም የአንድነትና የአብሮነትን መሠረታዊ
እንቅፋቶች አስወግደን ብንቀሳቀስ ኖሮ ኢትዮጵያ የትና የት ትደርስ እንደ ነበር መገመት ያዳግትም።እዚህ ላይ
የህወሃት ደጋፊዎችን ካነሳሁ ዘንዳ በውጭ ምን እንደሚሠሩ አንዳንድ ግልጽ መሆን ያለባቸውን ነገሮች ማስመር ካለብን
ቀደም ብለው በደርግ ዘመነ መንግሥት በሱዳንና ኬኒያ እንዲሁም በሌሎች አገሮች የወጡ፤ በዲቪ የወጡ፤በኢትዮጵያ
ኤምባሲ በፓስፖርት የወጡ፤በሀገር ሀብት ለትምህርት የተላኩ ሲሆን በኤምባሲው አማካኝነት በተለያዩ የስቪክ ማህበራት
የተደራጁና በየትኛውም የሥራ መስክ በመግባት ለህወሃት መዋጮ በማዋጣት የሚረዱ፤የህወሃትን የውሸት እድገትና
ጸረ-ሕዝብ ፖለቲካ የሚያናፍሱ፤በስለላ ተግባር የተሰማሩ፤ጠንክሮ የታገላቸውን በገንዘብ የተለያየ አይነት ጥቃት
እንዲደርስበት ማድረግ፤ከሥራ ቦታም ችግሮችን በመፍጠር ሠርቶ እንዳይበላ በማድረግ የተሰማሩ…ወዘተ ሲሆን ሀገር ቤት
የሚገኘውን ጥቅምና ጠቀሜታም የሚጋሩ ናቸው።ከባለ ሥልጣናት ጋር የቅርብ ዝምድና ያላቸው የግል ድርጅቶችን በአጭር
ጊዜ ከፍተው የከበሩና አሰሪ ከመሆናቸውም በላይ ሀገር ቤት ባለሥልጣናቱ የሚዘርፉትን የሀገር ሀብት የሚያሸሹና
በባንክ የሚያስቀምጡ እነዚሁ እኛ መሀል የተሰገሰጉ ትግርኛ ተናጋሪዎችና የሌላው ነገድ አባል የሆኑ ሆዳሞችንም
ያካትታል።ስለዚህ እነዚህን ለይቶ ማውጣትና ህዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግ ያስፈልጋል።
መቀበል አለመቀበል የእያንዳንዱ የግለሰብ ባሕርይ የሚወስነው ቢሆንም ከ40 ዓመት እና ከዚያ በላይ
እድሜ ክልል ውስጥ ያለን(የምንገኝ) ኢትዮጵያውያን የታሪክ ግርዶች፤ሀገራዊ ኃላፊነት የጎደለን፤ግዴታችን
የማንወጣ፤ፈሪና ስግብግቦች፤የሌላው ኢትዮጵያዊ ችግርና እንግልት የማይሰማን፤እኛ ላይ ትንሽ ነገር ጎድላ ስናይ ግን
ከጋለ ምጣድ ላይ እንደፈሰሰ ዘይት የምንጨረጨር፤ሆዳሞችና የማንጠግብ፤ብልጣ ብልጦች ፤ አስምሳዮችና ውሸታሞች
መሆናችን ሳናቅማማ መራሩን በሀገር የማዳንና የመጥፋት ጉዳይ የሚቀርብ ነቀፌታ ወይም ሂስ በፀጋ ልንቀበል ግድ
ይለናል።የትግሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ሊቀመጥ የሚገባው »መፈክርም« ይህ ሊሆን ይገባዋል ብየ አምናለሁ። የቆሸሸ
ልብስን ለማጠብ ዝም ብሎ ውሃ ውስጥ መጨመር የቆሸሸውን ልብስ ሊያጸዳው አይችልም ሳሙና መጨመርና በእጅ ማሸት
ወይም ማሽን ውስጥ አስገብቶ እድፉን ማስለቀቅ ያስፈልጋል። እኛም በውስጣችን ያለውን ቆሻሻ ሳናጸዳ ለማስመሰል
የምናደርገው የማታለል ስልት መታረም አለበት።የትግሉ እንቅፋት ከመሆን ዝምታም እኮ አንዱ እርዳታ ሊሆን ይችላል።
ከዋናው ጠላት ለመድረስ በመንገድ የሚገጥሙንን እንቅፋቶች ለመጠቆም ብዙ ሀተታ ስለአበዛሁ ይቅርታ እየጠየቅሁ
የሀገርና የሕዝብ ጠላት የሆነው ህወሃት የቆመለት ዓላማ መጀመሪያ የተከተለውን መንገድ ኪሱ ውስጥ አስገብቶ ሳያስብ
የገጠመውን እድል ማለትም ተገንጥሎ ታላቋን ትግራይ ሪፐብሊክ መቀየስ ሳይሆን እነአዲሱን ኩማና በረከት ተፈራ ዋልዋን
እያስመሩ ሀገርን ከጫፍ እስከ ጫፍ መመረሽና መክበር ነበር።ከመክበርም አልፎ አገር መግዛት ተቻለ አገር መግዛት
ደግሞ ብዙ ጊዜ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት ነበር 22 ዓመት አሁንም «አብዮታዊ ዴሞክራሲ»የምድር አምላክ ስለሆነ
በያንዳንዳችሁ አእምሮ እስኪሰርጥ ሌላ 40እና 50 ዓመት ስጡን ይህን ካልፈለጋችሁ ሰላም አታገኙም እንደ እባብ
እራስ እራሳችሁን እያልኩ እፈጃለሁ አለ።እያደረገም ነው።ሌላ-ሌላም ይደረጋል።ምን ይደረግ ዓላማቸው ነውና እነሱ
ለቆሙለት ዓላማ ቆመዋል።አልሳካ ሲል ደግሞ የሚበትኑትን በትነው ትግራይ ላይ ለመተከልና የተረፍነውን ለማድማት ያቀዱ
ስለመሆናቸው ስጋት ሊኖረን አይገባም።ከዚያ ሁሉ በፊት ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምንና የሚይኮራ የስልጣን
ጥማት በሽታ ያልወረረው ኢትዮጵያዊ ወገን ህወሃት ለጥፋት ይህን ያህል ተግቶ ሲሰራ ራሱን በምን ደረጃ ሊመድብ
ሊገምት እንደሚችል ሊጠይቅ ይገባዋል።እኛ ታሪክ ልንሰራ አልቻልንም ፤አልሠራንም ቀደምት ወላጆቻችን የሠሩትን ታሪክም
መጠበቅና ማስከበር አልቻልንም ለምን?እስኪ ሁላችንም ሊያግባባ የሚችል አንድ ዋናው የችግራችን መንስኤ ይህ ነው
የሚል የፖለቲካ ይሁን የታሪክ ተመራማሪ የችግሩ መንስኤ ይህ ነው ይበለን።የፖለቲካ ሥልጣን ፍላጎት፤ዘረኝነት፤ጥቅም
ፈላጊነት፤ክብር ፈላጊነት፤ውሸታምነት፤ማናክሎኝነት፤ፍርሃት…ወዘተ ከመሆን አያልፍም ብየ በግሌ አስባለሁ።ህወሃት ግን
አንድ ነገር ብቻ ዓይወድም ይፈራል። እሱም አንድነትን ነው።ህወሃትን አንድነት የሚያስበረግገው ጉዳይ
ከሆነ ለምን አንድነት አንፈጥርምና ህወሃት ገደል እንዲገባ አናደርግም? ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያነሳው አንገብጋቢ
ጥያቄም ይኸው የአንድነት ጥያቄ ነው።ዳሩ ግን የተቃዋሚ ኃይሎች፤የእምነት ተከታዮችና የሃይማኖት መሪዎች፤የስቪክ
ማህበራት የባሰውን ሕዝቡን በመከፋፈል የጎላ ሚና ተጫወቱ እንጅ አንድነትን ሊያመጣ የሚችል ለም የሆነ ንጣፍ
ሲመሰርቱ አልታዩም። ችግርን በውይይት የመፍታት ባህላችን ኋላ ቀር በመሆኑ ምክንያት ህወሃት 22ኛውን አንገት
አስደፊ አገዛዝ አገባዶ ወደ ሌላኛው ዓመት እያኮበኮበ ይገኛል።የሚገርመው ግን በህዝብ አንቅሮ የተተፋና ውስጡ
በችግር የተወጠረን ድርጅት መታገልና ማስወገድ አለመቻላችን ነው።ሕዝብ በያለበት ሆኖ ይጮኻል ግድያው አፈናው፤እሥራቱ
ቀጥሏል ከአንድ አካባቢ በመጡ ጥቂት ጠባቦችና ጎጠኞች።ተቃውሞውም በተናጠል ቀጥሏል።ወደ ተግባር ሊለወጥ ግን
አልቻለም።ህወሃት የተቃዋሚውን ሆነ የሕዝቡን የልብ ትርታ በማዳመጥ ዝምታ እንዲሰፍን ተራ በተራ በነገር እየተነኮሰ
ማስተንፈሱን አላቆመም።የሚፈራው አንድነት እንዳይመጣ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ሲገኝ እኛ ግን ህወሃትን ማስፈራራት
እንኳን አልቻልንም።ዋናው ችግርም ፍላጎታችን የሥልጣን እንጅ የሕዝብን ጩኸት መሠረት ያላደረገ ከመሆን
አይዘልም።ለወር ያህል የቀጠለውና አሁንም መፍትሄ ያላገኘው በሳውዲ አረቢያና አካባቢ የዐረብ አገሮች በኢትዮጵያውያን
ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘግናኝ አስገድዶ መድፈር፤ጎዳና ላይ ገድሎ መጎተት፤በሰይፍ መታረድ፤በርሃብና
ውሃ ጥማት በበሽታ ማሰቃየት በጅምላ እስር ቤት መታጎር ምክንያት በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጣቸውን በተለያየ
መንገድ ማሰማት ሲችሉ በሀገር ቤት በሰማያዊ ፓርቲና አንድነት የሞከሩትን ተቃውሞ ማሰማት ህወሃት አያገባችሁም
ብሏል።ሌሎች ድርጅቶች ደግሞ ትርፍ ፍለጋ ሲራወጡ ይስተዋላል።ወከባውን ለማርገብ ህወሃት ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው
እየተመለሱ ነው ይበል እንጅ እውነታው ሌላ ነው።ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ አገራቸው ብትሆንም አዲስ አበባም ሆነ
ሳውዲ ዐረቢያ በተመሳሳይ መንገድ እንደተያዙ መዘንጋት አይኖርብንም።ሀገርን ጥሎ ለመሰደድ ተቋም አደራጅቶ የሸጠ
ህወሃት ነው።ከሳውዲ መንግሥት ጋር ተባብሮ እልቂት ያወጀውም ህወሃት ነው።ስለዚህ ንግዱን ትተን መጀመሪያ አስከፊውን
ስአርት ማስወገድና ከዚያ በኋላ ደግሞ ንግድ ያሰበውም ሆነ ወንበር የፈለገው እንደፍላጎቱ ለመሆን ሊንቀሳቀስ
ይችላል።አሁን የነብስ አድን ጉዳይ ስለሆነ ሁላችንም አቅሙ በፈቀደልን መጠን ለወገን እንድረስለት።በመጨረሻም ይህችን
መጣጥፌን ስሞነጫጭር አንድ ዜና ሰማሁና ብዙ ነገሮች ወደ ኋላ ውስደውኝ ትዝ አሉኝ።በሽግግር ወቅት እንበለው
ጠቅላይ ሚንስትር የነበረው ታምራት ላይኔ በሲቢየስ ራዲዮ ኢንተርቪው ሲደረግ አዳምጨ የተዳፈነው ሁሉ ሊጎለጎል ነው
ብየ አስብኩና ይህን ሰው ቀረብ ብሎ ማነጋገር ከተቻለ ኢትዮጵያን ከዚህ ያደረሰው ጉዞ ምን እንደሆነ ፍንትው አድርጎ
ሊያሳየን ስለሚችል ከተቻለም ሌላውን ያሬድ ጥበቡንም ጨምሮ አፍነው የያዙትን ምሥጢር እንዲተነፍሱ ማድረግ በጣም
አስፈላጊ ሆኖ ይታየኛል በተለይ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ኢህዴንን አንቀበልም ብለው ህወሃትን የመረጡበትና ህወሃት
የኢህዴንን ዶክመንት የጠለፈበት ታሪክ አሁን ለደረስንበት የሀገር ጥፋት ምንጩ እዛ ላይ ስለሚነሳ።
በቸር ይግጠመን
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!
ጌታቸው ከሰ/አሜሪካ
1/ወንጀለኛው ዳኛ ፦
ዳኛ የለም እንጅ ቢኖርማ ዳኛ
እጁን አስሮ እግሩን በመጫኛ?
ዳሩ ዳኛ የለም
ቢተውት ግድ የለም።
—ወንጀለኛው ዳኛን የጻፉት ክቡር ሐዲስ ዓለመየሁ ሲሆኑ እነዚህን ስንኞች ሁልጊዜ የተዛባ ነገር ስመለከትና
ውስጤ ሲከፋ የማጉረመርምበት በመሆኑ አገራችን ዳኛ እስከምታገኝና የሕግ የበላይነት እስከሚከበር ድረስ ይህን የወሮ
በላና የወራሪ ሥርዓት እስከምናስወግድ ድረስ እንዲህ እያጉረመረምኩ ትግሌን እቀጥላለሁ እንጅ ዳኛ የለምና ህወሃትን
ታግሎ መጣል መተው አለበት አላልኩም። ወንጀለኛው ዳኛ ብለው የጻፉት ክቡር አቶ ሐዲስ ዓለመየሁም ዳኛ የለም ብለው
ተስፋ አልቆረጡም ነበር። መሪና አታጋይ የሆኑ መጽሐፍትን በመጻፍ በወቅቱ የነበረውን ሥርዓት አስከፊነት ፍንትው
አድርጎ በማሳየት አስነበቡ አሳወቁን እንጅ።
እህህ! ሀገሬ እህህ! ሀገሬ ሀገሬ ኢትዮጵያ
ሳልኖርብሽ ብሞት ጥፋቱ የማን ነው መቼ ኖርኩብሽና መቼ አይቸሻለሁ
አንች እየናፈቅሽኝ ሀገር እንደሌለው በየባዕዳው አገር እንከራተታለሁ
አራቱን ማእዘን ጓዳ-ጉድጉዳሽን ዘልቄ ሳላየው
የኔውስ እድሌ ተሰዶ መኖር ነው
አወይ ስደት ክፉው ሁሉ ይመኘዋል
እንደኔ ቢቀምሰው መቼ ያስበዋል
አንች ሀገር ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
የደማልሽ ሲጋዝ ያደማሽ ሲበላ
አወይ ጊዜ ሞኙ ስንቱን አጃጃልከው
አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ ማለቱ ሳያንሰው
እንዴት ባገሩ ላይ መኖሪያ ያጣል ሰው
ተው እናንተ ሰዎች እሱ ነው ድንበሩ
ሁሉ ዘራፍ ካለ ይጠፋል ሀገሩ
ስማኝ አንተም እንደሌላው አፈር ትለብሳለህ አፈር ትሆናለህ
ድንጋይ ተንተርሰህ ትቢያም ትሆናለህ
እመነኝ ካንተጋር ተጣልተህ
በፍርሃት ተውጠህ
ቅዥቱ በዝቶብህ
በሀሰት መስክረህ ይገደሉ ያልከው
» » ይታሰሩ ያልከው
በሐሰት መስክረህ ይሰደዱ ያልከው
» » ይራባቸው ያልከው
ሀገሬን ለመሸጥ ፊርማ ያሰፈርከው
ሕዝቤን ለመጨረስ ምክር የመከርከው
ጥቁር ካባ ለብሰህ ሐሰት የፈረድከው
ፍትሕን አዛብተህ ሕጉን ያፈረስከው
ወንጀለኛው ዳኛ ለሆድህ ያደርከው
የኮተቤው ዳኛ ለሆድህ ያደርከው (ኮቴቤ የህወሃት ዳኞች መፈልፈያ ፋብሪካን ይመለከታል)
ፍርድ እየገመደልክ ስንቴ ልትኖር ነው?
እምነቴን እንዳጣ ነገድ እንዳይኖረኝ
ትውልድ እንዳልተካ ዘርም እንዳይኖረኝ
ሀብት እንዳላፈራ ድኻ ልታደርገኝ
ዜግነቴ ጠፍቶ ሰንደቄን እንዳላይ
የሀገሬ የጥንት አባቶቼ ታሪክ እንዳይታይ
ባህል ወግ ልማዴ ቅርሴ እንዳይታወቅ በዚህች ምድር ላይ
አብረን እንዳንወግን እኛን ልትለያይ
ነገር ስታሻኩት ጥላቻን ስታምጥ
አገር ልታጠፋ ሕዝቤን ልትበጠብጥ
ቆላ ደጋ ስትል በየአገሩ ስትሮጥ
ክፉ ቀን ተጣራ ወዴት ልትገባ ነው
ምላስህ ሊታሰር ልሳንህ ሊዘጋ እየተጠራህ ነው
ጦሩ ሲመክትህ ገንዘቡ ሲያወጣህ ደህንነት ሲያድንህ
እኮ እናይሃለን እብሪቱ ትቢቱ ከመሞት ሲያድንህ
zehabesha
No comments:
Post a Comment