Friday, November 22, 2013

ቅኝ ገዥወቻችን አረቦች ሆኑ እንዴ ሳᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ


እኛን በታሪክ አስቦት የምንኖረውን የኢትዮጵያ ትውልዶች ሲያኮራን የኖረው በአያት ቅድማያቶቻችን ተጋድሎ በነጻነት መኖራችን ነው። እንዲህ ሆነ። እዚህ ዳላስ ለብዙ ጊዜ የማውቀው የውጭ ዜጋ በተገናኘንበት ጊዜ ሁሉ የጣሊያንን የሁለተኛው አለም ጦርነት ሳያስታውሰኝ አያልፍም። እናም ሊያስታውሰኝ የሚከጅለው ለትንሽ ከቅኝ ግዛት አመለጣችሁ ይለኛል። እኔም እንደልማዴ በጀሮ ከአባቴ የሰማሁትን ገድል ሳልነግረው አልፌ አላውቅም። እርሱም የበለጠ እንደምበሳጭ ስለሚያውቅ አይ እንግሊዝ ባይደርስ እንደሌሎች አፍሪካውያን ተገገዝታችሁ ነበር በማለት ክርክራችን ሳያልቅ። መልከም ነገር ሳንነጋገር እንለያያለን።
እርግጠኛ ነኝ ብዙ ኢትዮጵያውያን በእንዲህ ያለ የታሪክ ትዝታ። ሌሎች በሰሩት እንደምንብራራበት ነው። ኩራታችንም ለአንዳንዶቻችን የአባቶቻችንን፣ ሌሎቻችን የአያቶቻችንን ተጋድሎ የእኛ ይመስል ስንተረትረው እንገኛለን። ከዚህ የትዝታ ኑሮ የምንወጣበት ጊዜ ግን በጣም ይናፍቀኛል።
ወያኔ አዲስ አበባ ሲገባ በታዛቢነት የሽግግር መንግስት ያሉትን ቧልት ስብሰባ ሲያካሂዱ ኢሳያስ አፈወርቂን ጋብዘውት እንደነበር ትዝ ይለኛል። እናም ያኔ ኢሳያስ ቅኝ ገዣችን ነበር ማለት ነው። በዚያ ስብሰባ ኢሳያስ አማረኛን ተጸይፎ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስብሰባውን መካፈሉንም ሰማሁ። ታዲያ እርሱም በደንብ በማያውቀው ቋንቋ፣ ብዙወች ተሰብሳቢወችም የሱን ቀርቶ የቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ሰው ቢናግርም እንኳን መስማት የማይችሉትን ጨምሮ ስብሰባው መደረጉን ባስታወስኩ ቁጥር ትርጉሙ ምን እንደነበር ለማወቅ እቸገራለሁ። አስቡት ያኔ ኢሳያስ አማረኛ የማይናገር ሆኖ ሳይሆን ቋንቋውን ተጸይፎት እንደሆን ለሁላችን ግልጽ ነው። መለስ ዜናዊ እንኳን በጭንቅ በተያዘበት ወቅት በመቶ አመት የእድሜ ግድብ ይሳለቅባት የነበርን አገር ወደሦስት ሽህ እንዳደረሳት ሰምተናል። ያች በክፉ ቀን (ከወዳጁ ከኢሳያስ ጦር የተማዘዘባት) ከአለፈች በኋላ ግን ያው ጨርቅ ያላትን ሰንደቅ አላማ ቃሉን ከፍጻሜ አድርሶ የተባበሩት መንግስታትን የባንዲራ ቀለም በማህል ለጥፎባት አለፈ። እናም ዛሬ ሰንደቅ አላማችን ልክ የዛሬ 78 አመት ቦዶሊዮ እንዳወረዳትና ለአምስት አመታት እንደረገጣት ሁሉ ዛሬም መዳረሻዋ እንደጠፋ ለመሆኑ ማንም የሚስተው አይደለም። ያኔ ግዜው በአርበኞች ተጋድሎ አጥሮ ልክ በወደቀች በአምስት አመት እድሜ ሚያዚያ 27፣ 1933 እ ኢ አ ወደቦታዋ ተመልሳለች። ዛሬ ግን ጊዜውም እየረዘመ ሄⶌል መቸ እንደምትመለስም የሚያውቅ የለም።
ለዚህ ጽሁፍ ወደአነሳሳኝ ጉዳይ ልመለስ። አንዳንድ ወገኖች ስለዚህ ዘረኛ ስርአት ሲጽፉ ወይንም ሲናገሩ ወራሪ መንግስት ነው ይላሉ እና እንዲህ አይነት ወገኖችን ሰው ይህን አስተሳሰባቸውን በጀ አይልላቸውም። መችም ትቂት ሰወች በታሪክም ቀድመው አንድን ነገር ይታያቸውና ሌላው እንደ ጅል እንዲቆጥሩ ያደርጋቸዋል። ምናልባት እኔም ከብዙሀኑ እረድፍ የነበርሁ ይመስለኛል። ያልተዘጋው የሰሞኑ የወገኖቻችን ከባእድ አገር የሚሰማው የሲቃና የመከራ ጥሪ ለየት አድርጎ የ22 አመታቱን የአገዛዝ ዘመን ያሳየን ይመስለኛል። ሚኒሊክ ቤተመንግስት የገቡት ሰወች ቁመናቸው ኢትዮጵያዊ ይመስል እንደሁ እንጅ እየተረጋገጠ የመጣው አስተሳሰባቸው፣ ስራና ተግባራቸው ዛሬ ቁልጭ ብሎ እንደታየው ለባእድ የሚሰሩ ቅጥረኞች ለመሆናቸው የሰሞኑ ስራቸው ቀልጭ አድርጎ እያሳየን ነው። ለዚህ ዘር ወይንም ለዚያ ዘር ቁመናል የሚሉትም ከአለቆቻቸው ከመጣ የአፍ እንጅ የተግባር እውነታ እንደሌለው እያሳየ ነው። ግን ለአገዛዛቸው ፍቱን መድሀኒት ስለሆነ የከፋፍለህ ግዛውን ስራተ አስተዳደር ይቀጥሉበታል። ግን እስከመቸ ነው ከወርቅ ናችሁ ሲሉት የሚታለለው?
ሌላው አስገራሚው በዚህ የክፉ ክፉ በሆነው ሰሞን የተረዳነው ለአለቆቻቸው ምን ያህል ትሁትና ሽር ጉድ ባይ መሆናቸውን ነው። እዚያ ሳውዲ ያለው አንባሳደርን ከአንድ የአረብ ጋዜጠኛ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ፤ ጋዜጠኛው እንደጋዜጠኛ ሳይሆን እንደ አንድ ስራ አስኪያጅ ነበር የሚቃጣው። በግልባጩ አንባሳደር ተብየው ለአለቃው ተግሳጽ መልስ የሚሰጥ ሰራተኛ ይመስል ነበር። ከፍርሀቱ በላይ አንገቱን ማቅለስለስና ጣቶቹን ማሻሸቱን ላየ የሚገርም ትይንት ነበር። እናም ይቅርታ ጠየቀ። ለምን ስለምን ይቅርታ ጠየቀ ተብሎ ቢጠየቅ የንጹሀን ደም በአረብ አደባባይ እንደጎርፍ በመፍሰሱ ይሆን? አረቦች በሳውዲ ያሳዩንን ጨካኝነት ቅጥረኛቸው መንግስት ተብየው በአዲስ አበባ አደባባይ ወገኖቻችንን አሰረ ገረፈ አሰቃየ በመዲናችን ልክ እንደባእዳኑ ደግሞ አሳየን። ምክንያቱ አንድ ነው ለምን የወገኖቻችሁን ሰብአዊ መብት ትጠይቃላችሁ ነው መልሱ።
ምናልባት አስተውላችሁ ይሆናል። የወያኔ ደጋፊወችና አባላት በተለየም በውጭ የፕሮፓጋንዳውን ስራ እያጧጧፉት ነው። አግጦና አፍጦ የወጣውን እውነት በፅልመተ ሀሰት ለመተካት ሁለት አፎት ያለው ስለት ይዘው መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ሁሉም እንዲያስተውል የሚገባው ጉዳይ ግን በሳውዲ ጎዳናወች የተቀጠቀጡ ወገኖቻችን። በአደባባይ በውሻ መሳይ ሳውዲ ተጎትተው የተደፈሩ እህቶች ከአንድ ዘር ወይንም ከአንድ ሀይማኖት የተፈጠሩ አይደሉም። የሰሞኑን ጣእር ለየት የሚያደርገው ሁሉም ዜጋ ተነክቷል። ትግሬ፣ አማራ፣ ወይንም ኦሮሞ፤ ጉራጌና ሌላ ዘር አልተለየም ግፉ ለሁሉም እኩል ደርሷል። በሳውዲ ወገኖቻችን ሲገደሉ ሲደፈሩ ወይንም መከራን ሲቀበሉ ሙስሊሙና ክርስቲያንም ተለይቶ አይደለም። አረቦቹ ንቀታቸውና ጭካኔአቸው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ መሆኑን አሳዩን። አዲስ አበባ ያሉት ዘረኞችና በውጭ የሚኖሩ ካድሬወቻቸው ምናልባት የሳᎀኤል ሀቲንግተን (the clash of civilization) የተሰኘውን አስተሳሰብ ሊጎትቱ ሳይፈልጉ አይቀርም። የዘር ነገር አልሰራም የሀይማኖቱንም ሞከሩት ያም ከሸፈ። አሁን ገሀድ እየታየ ያለው እነሱ የአረብ ተቀጣሪወች መሆናቸው ነው። ይህን ሀሳብ የሚያጠናክር ሹክሹክታም አለ። የዜና አውታሮች የአባይን ጉዳይ አስመልክተው ብዙ ቢሉም የጉዳዩ ባለቤት የሆነችው ግብጽ ግን ትንፍሽም አላለች። እና አሁን እየሰማነው እንዳለው ሹክሹክታ ከሆነ ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ በነፍስ ወከፍ ለግድብ አንዲያዋጣ አፍንጫውን ይዞ አያስከፈለ፣ ግብጻውያን ግን የውጤቱ ተካፋይ እንደሚሆኑ የውል ሰነድ እንዳለ እየሰማን ነው (ይህ ደግሞ በእውነት ከተጠናቀቀ ማለት ነው)። ይህ ከሰሞኑ በወገኖቻችን ላይ ከሚፈጸመው ግፍ እና ግፉ እንዲቆም ለዜጎች ተከላካይ መንግስት አለመኖሩ ጋር ተዳብሎ ሲታይ፤ የቅኝ ገዥወቻችን አረቦች ለመሆናችው ብዙ ማስረጃ አያስፈልገውም ማለት ነው። ኤርትራን ለማስገንጠልም ሆነ ወያኔን በትጥቅና ስንቅ አቅፎ ደግፎ ከዚህ ለማድረስ የአረብ ፔትሮ ዶላር መፍሰሱ ታሪክ ይመሰክረዋል።
በዲፕሎማሲው አለምና በአለማቀፍ ሕግ ብዙ እውቀት ያላቸው ምሁራን እንዳሉን እገምታለሁ። መልካም ፈቃዳቸው ከሆነ ስ[i]ለዚህ አዲስ ክስተት የሚአይውቁትን በተለየም በአገሮች መካከል ሊኖር ስለሚገባው የዜጎችን አየያዝ ቢያሳዩን እንዴት መልካም በሆነ። እንደኔ ተራ ኢትዮጵያዊ ምንም ፖለቲካ ሳይጨመርበት ወይንም ምሁራዊ የዲፕሎማሲ ቋንቋ ሳይጋርደው በጥሬው የሚታየው እውነታ ኢትዮጵያና እትዮጵያውያን መንግስት እንደሌለን ነው። በአረቦች ተወልዶና ተመንድጎ ለእጅ አዙር ገዥነት የተዘየደ ነገር ነው። በቅኝ ባንያዝና የውጭ ተጸኖ ባይኖርብን በንጹሀን ዜጎቻችን ላይ እየተካሄደ ያለው ኩነት ወደሙሉ ጦርነት የሚወስድ ነበር። ከዚህ የላቀ ብሔራዊ ውርደት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቆምና ነው። ብዙ ሀገራት የአንድ ዜጋ መብት ሲገፈፍ በባእድ እጅ እስከ ከባድ ግጭት መድረሱን አሳይተውናል። እስኪ እንደምሳሌ ከዚህ በታች ከ፫፯ አመት በፊት የሆነን ኩነት ተመልከቱት።
ብዙ የምታስታውሱ ወገኖች ትኖራላችሁ በጁን 27፣ 1976 እ ኤ አ ሁለት የፖለቲካ ቡድኖች ማለትም የ German revolutionary cell የተባለው ድርጅትና Popular Front for The Liberation of Palestine በትብብር 248 ተሳፋሪ የያዘ A300 Airbus የፈረንሳይ አውሮፕላን ከቴላቪቭ ወደ ፓሪስ ይበር የነበር ጠልፈው መጀመሪያ ቤንጋዚ ሊቢያ አዲያርፍና ሦስት ተጨማሪ የጠለፋው ቡድን አባላትን ጨምረው ወደ ዩጋንዳ እንዲበር አደረጉት። በዩጋንዳ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማርፊያም በኢዲአሚን ዳዳ መንግስት ተፈቅዶላቸው አሳረፉት። በዚህ አውሮፕላን 100 ይሁዳውያን ስለነበሩ ነው ዋና የጠለፋው ምክንያት። ጠላፊወቹም ከዩጋንዳው ኤዲ አሚን ጋር ቀድመው ተስማምተው ስለነበር በዚያኑ ቀን 47 ይሁዳዊ ያልሆኑ ተሳፋሪወች ተለቀቁ። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ 101 ይሁዲ አለመሆናቸው ከተጣራ በኋላ ተለቀዋል። ቀሪወቹ 100 ይሁዳውያንና ይሁዲ ያለሆነው ፈረንሳዊ ፓይለት ካፒቴን ባኮን ከበረራው ቡድን አባላቱ ጋር ሆኖ ከተያዙት ተነጥሎ የማይሄድ መሆኑን ስለገለጸ ከቀሪ እስራኤላውያኑና ይሁዳዊ እምነት ከነበራቸው ጋር ቀሩ። ጠላፊወቹ ከጁላይ አንድ ቀን ጀምረው በእስራኤል የታሰሩ አርባ ፍልስጤማውያን ካልተፈቱ አንድ በአንድ ይሁዳውያኑን የሚገድሉ መሆናቸውን አሳወቁ። ሆኖም ጥያቄአቸው ሳይመለስ አንድ ሳምንት እንደሆነው ጁላይ 4, 1976 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር የእስራኤል አየር ሐይል  Operation Entebbe በሚል ስያሜ በእስራኤል የመከላከያ ሐይል የታቀደው ዜጎችን የማስለቀቅ በረራ 100 የእስራኤል ኮማንዶወችን ጭኖ ወደ ኢንቴቤ በረረ። 2500 ማይል ተጉዞ ማታ ኢንቴቤ አረፈ። እስራኤልዋውያኑ በ90 ደቂቃ 45 የዩጋንዳ ወታደሮችን እና ሁሉንም ጠላፊወች ገድለው 30 mig-17 mig-21 የሶቪየት ሰራሽ ተዋጊ አውሮፕላኖችን አቃጥለው ሦስት መንገደኞች እና ኦፕሬሹኑን ይመራ የነበረው ኮማንደር መስዋእት ሆነው፤ እስራኤል ዘጎቿን በጀግንነት ነጻ አወጥታለች። ይህ ገድልና ተመሳሳይ ተግባሮች አገሮች ነጹሐን ዜጎቻቸውን ከጠላቶቻቸው እጅ ለማስለቀቅ ያደረጉትና በተግባር የታዩ ስራወች ናቸው።
ወደዛሬይቱ ኢትዮጵያ ስንመለስ ዜጎች በመላው አለም ተበትነው የእለት ኑሮ ለማሸነፍ ከመታገል ባሻአገር በባእድ እንደዚህ እንደሰሞኑ በግፍ ሲጨፈጨፉ አንድ አገሪቱን እወክላለሁ የሚል መንግስት ሊደርስላቸው ቀርቶ ከገዳዮቻቸው አባሪና ተባባሪ ሲሆን ምን ሊባል ይችላል፧ እስከዛሬ አገሪቱ በጠላት እጅ የወደቀች ያክል መሆኑን ያልተረዱ ሁሉ እንዲገነዘቡት የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግስት ስራና ተግባራቱ አጋልጠውታል። [1]
ጎበዝ እንነሳ፤
እንተባበር፤ድር ቢያድር አንበሳ ያስር ይባል አይደል።
Samuelshiferaw32@gmail.com

 https://ecadforum.com/Amharic/archives/10198/

No comments:

Post a Comment