- ከአስተዳዳሪው ጋራ የጥቅም ግንኙነት ያላቸው የቅ/ላሊበላ ደብር ሰበካ ጉባኤ አባላትና የአስተዳደር ሠራተኞች፣ ለመኪና ‹ሽልማቱ› ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ (በአንዳንድ ምንጮች መረጃ እስከ ብር 800,000 - 1.5 ሚልዮን) ከደብሩ ካዝና ወጪ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡ ለ‹ሽልማቱ› የሚገዛው ሞዴል ዶልፊን መኪና እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡ ይህም በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አንዳንድ አድባራት በሽኝት ስም በተፈጸሙ የመኪና ‹ሽልማቶች› ጋራ ተዳምሮ ሙሰኛ የአድባራት አስተዳዳሪዎች የመክበርያ መንገድ እየኾነ እንደመጣ አመላካች ኾኗል፡፡
- ‹‹መነኩሴ ቢሸለም መስቀል እንጂ መኪና ምን ያደርግለታል?›› የሚሉ የቅ/ላሊበላ ደብር ካህናትና ምእመናን፣ ‹‹አባ ገብረ ኢየሱስ በሕግ መጠየቅ እንጂ ሽልማት አይገባቸውም›› በሚል ኅዳር ፲፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ለከተማው ከንቲባ ምሬቱን ገልጦአል፤ ፖሊስ ጣቢያውንም በአቤቱታ አጨናንቆ ውሏል፡፡ አባ ገብረ ኢየሱስ የመኪና ‹ሽልማቱን› ለመቀበል አሁን ካሉበት አዲስ አበባ ወደ ላሊበላ ተመልሰው በሚገኙበት የሽኝት መርሐ ግብር ላይም ከፍተኛ ተቃውሞውን ለማሰማት ተዘጋጅቷል፡፡ የሽኝት እና የ‹ሽልማት› መርሐ ግብሩን ከብዙኃኑ ካህንና ምእመን እይታ ውጭ በአዳራሽ/በደብሩ የአብርሃም ሆቴል/ ለማድረግ ታስቧል፡፡
- የመኪና ግዥው ሂደት ወደ አዲስ አበባ በተላኩ የአስተዳዳሪው ጥቅመኞች እንዲከናወን የተደረገው፣ አባ ገብረ ኢየሱስ የደብሩን ሰበካ ጉባኤና የአስተዳደር ሠራተኞች ሰብስበው ‹‹መሸኛ ይሰጠኝ›› በማለት የ‹መሸኛውን› ገንዘብ መጠን ጠቅሰው መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ይህንኑ ለማስፈጸም ‹‹የልደት በዓል አከባበርን በሚመለከት ለመወያየት›› በሚል ሰበብ በደብሩ ምክትል ሰብሳቢና ጸሐፊ አስተባባሪነት በተጠራ የካህናት ጉባኤ ላይ፣ ‹‹ከደብሩ ካዝና ገንዘብ ወጪ ተደርጎ እንድንሸኛቸው ብፁዕ አባታችን ፈቅደዋል›› እየተባለ የተሰበሰበ የተጭበረበረ የካህናት ፊርማ ለሀ/ስብከቱ መቅረቡ ተነግሯል፡፡
- ሀ/ስብከቱ ቀደም ሲል በተፈጸሙ ምዝበራዎች ምክንያት አባ ገብረ ኢየሱስ የደብሩን ሒሳብ እንዳያንቀሳቅሱ አግዷቸው ሳለ፣ ለተባለው የ‹ሽልማት› መኪና ግዥ ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ እንዲኾን መፍቀዱ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱን በከፍተኛ ደረጃ እያስወቀሰ ነው፡፡ የሀ/ስብከቱ ጸሐፊ የተሰጠውን የግዥ ፈቃድ መቃወማቸው ተዘግቧል፡፡
- የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት በደብሩ አብያተ መቅደስ ባካሄደው ድንገተኛ የቅርስ ቆጠራ÷ በቤተ መርቆሬዎስ በቅርስነት የተመዘገበው ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ ከተመዘገበበት የተለየ ኾኖ ተገኝቷል፤ በቤተ ገብርኤል በቅርስነት የተመዘገበ ኵስኵስት በቦታው አልተገኘም፤ በዚኹ ቤተ መቅደስ የሚገኝ የወርቅ መስቀልም ስለ መቀየሩ እየተነገረ ነው፡፡ ጽ/ቤቱ ኹኔታውን ለሚመለከተው አካል በሪፖርቱ እንደሚያሳውቅ ተገልጦአል፡፡
- ባለፈው ሳምንት እሑድ የላሊበላ ከተማ ፍትሕ ጽ/ቤት በቅርስ አጠባበቅ ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ለመስጠት የደብሩን አስተዳደርና ካህናት በጠራበት ስብሰባ ላይ፣ ስለቅርስ ቆጠራና ርክክብ አስፈላጊነት ሐሳቦች በሚነሡበት ወቅት፣ አባ ገብረ ኢየሱስ አሠልጣኞቹን በተደጋጋሚ ተግሣጽ ለማሸማቀቅ ሲሞክሩ መስተዋላቸው ከጠፉትና ከተቀየሩት ቅርሶች ጋራ በተያያዘ ከፍተኛ የሕዝቡ ጥርጣሬ እንዲጠናከርባቸው አድርጓል፡፡ ወቅቱ አባ ገብረ ኢየሱስ ከሓላፊነታቸው ከመነሣታቸው ጋራ የተገናኘ ከመኾኑ አንጻር ተተኪው አለቃ ጽ/ቤቱን ተረክበው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ጠቅላላ የቅርስ ቆጠራና የደብሩ ገቢዎችና ወጪዎች ኦዲት የማድረግ አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠየቀ ነው፡፡
- ከቤተ ደናግል በፈለሰ የደንጊያ መንበር እና ከአብያተ መቅደሱ ጋራ በቅርስነት በተመዘገቡ ጎጆ ቤቶች ቃጠሎ ጋራ በተያያዘ የቅርስ ማውደም ከፍተኛ ወንጀል ተጠርጣሪ የኾኑት አባ ገብረ ኢየሱስ÷ በርካታ የልማት ሥራ እንዳከናወኑበት የሚናገሩለትን ደብር የቱሪዝምና ልማት ተቋማት ገቢዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው አሠራር በመመዝበር ከባድ የእምነት ማጉደልና በሐሰተኛ ሰነድ ፈጠራ ከፍተኛ ወንጀሎችም ተጠርጣሪ ናቸው፡፡
- ከሐሰተኛ ሰነድ ፈጠራ ጋራ በተያያዘ በተጠረጠሩበት ወንጀል የፖሊስ መጥሪያ የወጣባቸው አባ ገብረ ኢየሱስ፣ የተጠርጣሪነት ቃላቸውን የሰጡ ሲኾን ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆና መዝገቡን አደራጅቶ ለከተማው ፍትሕ ጽ/ቤት ዐቃቤ ሕግ ማስተላለፉ ተዘግቧል፡፡ የተጣለባቸውን ሓላፊነት ወደ ጎን በመተው የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት በመመዝበርና ለግል መበልጸጊያ በማዋል በተጠረጠሩባቸው ከፍተኛ ወንጀሎች ጥፋተኛ ኾነው ከተገኙ ከ10 – 20 ዓመት የሚደርስ እስራትና ጽኑ እስራት ይጠብቃቸዋል፡፡
- በቃለ ዐዋዲው የተወሰነውን የሥራ ዘመን በመፃረር ለስድስት ተከታታይ ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ (በተለይ ተተኪውን አስተዳዳሪ ተቀባይነት ለማሳጣት ከወዲኹ እያሳደሙና የሥነ ልቡና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ክፉ ወሬዎችን እያስወሩ ናቸው የተባሉት የምክትል ሰብሳቢው እና ጸሐፊው) ኹኔታና ከአስተዳዳሪው ጋራ ከፍተኛ የጥቅም ግንኙነት ያላቸው የደብሩ ሠራተኞች አፈጻጸም በጥልቀት እንዲፈተሽ እየተጠየቀ ነው – ‹‹አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ›› እንዳይኾን!
- ተተኪው የደብሩ አለቃ (መምህር) እና በአዲስ መልክ መዋቀር የሚያስፈልገው የደብሩ አስተዳደር ሊፈጽሟቸው ስለሚገቡ አምስት ቀዳሚ የጥንቃቄና የእርምት ርምጃዎች መካከል የሚከተሉት ነጥቦች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡- 1) የቅርስ ቆጠራ፣ የገንዘብ እና ንብረት ወጪና ገቢ ኦዲት ተደርጎ ግኝቱ ይፋ እንዲደረግ፣ ጉድለቱ እንዲታወቅ በአያሌው ይጠበቃል፡፡ 2) በቤተ መዘክሩ ቅርሶች ከመጸዳጃ ቤት በታች በአልባሌ ኹኔታ እንደተቀመጡ ተገልጦአል፤ ይኸው ጉዳይ ትኩረት አግኝቶ የቅርሶቹ አቀማመጥ ብቻ ሳይኾን የቤተ መዘክሩ አስተዳደርም በተገቢው አሠራርና ባለሞያ ሊደገፍ ይገባል፡፡ 3) የሥራ ዘመኑን ጨርሶ ለተጨማሪ ሦስት ተከታታይ ዓመት በሥልጣን ላይ የሚገኘው ሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው የተፈቀደለት የሥራ ዘመን የተላለፈው በመኾኑ ከሓላፊነቱ ሊሰናበት ይገባል፤ የአስተዳደር ሠራተኞችም ከአባ ገብረ ኢየሱስ አስተዳደር ጋራ የነበራቸው የጥቅም ግንኙነት በጥልቀት እየተፈተሸ ተገቢው ርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ 4) አብያተ መቅደሱን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች በሚስተናገዱበት የትኬት ቢሮ በተሻለ የቋንቋ ክህሎት የሚግባባና በቱሪዝም ማኔጅመንት የሠለጠነ፣ ገቢውን ከመቆጣጠር አንጻርም ታማኝ በኾኑ ሠራተኞች የተደራጀ መኾን ይኖርበታል፤ በአዲስ አበባ ቱሪስቶችን አደራጅቶ ለመላክ በሚል የተከፈተው የጉዞና ጉብኝት ቢሮ በአባ ገብረ ኢየሱስ የጥቅመኝነት መረብ ውስጥ እንዳለ የሚጠረጠር በመኾኑ ለደብሩ ታማኝ በኾነ የሠለጠነ ባለሞያ እንዲንቀሳቀስ መደረግ ይኖርበታል፡፡ 5) የአስተዳደርና የቅጥር ሥርዐቱ ከመበላሸቱ የተነሣ በሠራተኞች ላይ ከፍተኛ አድልዎና በደል የተፈጸሙባቸው የደብሩ ሆቴሎች (ቤተ አብርሃም፣ ቤተ ይምርሓ፣ ሰባት ወይራ እና የእንግዳ ማረፊያው) አስተዳደርና የሠራተኞች ብቃት ከመልካም ገጽታ አንጻር ጥንቃቄ ሊደረግበት ያስፈልጋል፡፡
- የላሊበላ ካህናትና ምእመናን በምሬት እንደገለጹት፣ መሸለም ሳይኾን በሕግ መጠየቅ ይገባቸዋል የሚባሉት አባ ገብረ ኢየሱስ ወደ አዲስ አበባ – እንጦጦ ርእሰ አድባራት መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ያደረጉት የእልቅና ዝውውር እርሳቸው እንደሚሉት ጠይቀው ሳይኾን ታዝዘው ያደረጉት ነው፡፡ ይኸውም ቢኾን ዝውውሩ በጸደቀበት የኅዳር ፲፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ‹‹ሕዝብ የተነሣበትንና ያባረረውን እንዴት እንመድባለን፤ ምደባው ቆይቶ መታየት ይኖርበታል›› በሚል በከፍተኛ ደረጃ አነጋግሮ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ የመሰል የሕግ ተጠያቂዎች ጉዳይ ግን ማነጋገር ብቻ ሳይኾን አስተማሪና ምሳሌያዊ የኾነ ርምጃ ይወሰድባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አመራር ይጠበቃል፡፡
- በመጨረሻም፡- በአባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን አስተዳደር የተመረረውና በቃሉም በሕይወቱም ምሳሌ ኾኖ የሚመራው አባት የናፈቀው የላሊበላ ካህንና ምእመናን አዲሱን የደብሩን ተተኪ መምህር (አስተዳዳሪ) በደማቅ አኳኋን ለመቀበል ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ላይ መኾኑ ታውቋል፡፡ ወደ ቅ/ላሊበላ ደብር ተዛውረው የተመደቡት አዲሱ መምህር፣ የእንጦጦ ርእሰ አድባራት መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ከሁለት ዓመታት በላይ ያስተዳደሩት መልአከ ፀሐይ አባ ወልደ ትንሣኤ አባተ ናቸው፡፡ http://haratewahido.wordpress.com
No comments:
Post a Comment