Thursday, November 21, 2013

የኃይሌ ገ/ሥላሴ ‘‘ታላቁ ሩጫ’’ ለሳዑዲ አረቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች መታሰቢያ ሯጮች ሪቫን እንዳያደርጉ ከለከለ


በዘሪሁን ሙሉጌታ
Haile
በመጪው እሁድ በታላቅ ድምቀት በሚካሄደውና በአፍሪካ በግዙፍነቱ ቀዳሚ በሆነው ‘‘ታላቁ ሩጫ’’ ላይ የሚሮጡ ተሳታፊዎች በሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ጉዳት በሐዘን ለመግለፅ ጥቁር ሪቫን አድርገው እንዲሮጡ ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረበውን ጥሪ የ‘‘ታላቁ ሩጫ’’ አስተባባሪዎች ተቃወሙ።
የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባላት በሳዑዲ አረቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች ላይ የደረሰውን ግፍና በደል ለዓለም አቀፍ ህብረተሰብና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስገንዘብ በሩጫው የሚካፈሉ ተሳታፊዎች ጥቁር ሪቫን በማድረግ ሐዘናቸውን እንዲገልፁ ሲል ወስኗል። የታላቁ ሩጫ አስተባባሪዎች በጉዳዩ ላይ እንዲተባበሩና አጋርነታቸውን እንዲገልፁ ለማድረግ በደብዳቤ ጥያቄውም እንደሚያቀርብ የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት አስታውቋል።
የታላቁ ሩጫ አስተባባሪዎች ግን የሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ አንደግፈውም ሲሉ ጥሪውን ተቃውመዋል። ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት ዳግማዊት አማረ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ‘‘ፕሮግራሙ የስፖርት ዝግጅት ነው፤ ዓላማውም የተለየ ነው፤ ሕብረተሰቡን ማቀራረብና ሀገሪቱን በበጎ አይን ማስተዋወቅ ነው። ስፖርት ዋናው ተልዕኮው ሰላም ነው። በዝግጅቱም ላይ የራሳችን ዓላማ አለን። ሁሉም ሰው ለዚህ አላማ እንዲሮጥ ነው የምንፈልገው። ከዚህ ቀደም በተባበሩት መንግስታት የተቀየሱ ስምንቱ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ባለፉት አራት አመታት ያንን ስናስተጋባ ቆይተናል። በዘንድሮ አመትም ‘‘ለተሻለች ኢትዮጵያ እንሩጥ’’ የሚል መልዕክት ነው ያለው’’ ብለዋል። በተጨማሪም ሁሉም የሩጫው ተሳታፊ በግዴታ የተሰጠውን ቲሸርት መልበስ አለበት። ሌላ ነገር የለበሰን ተሳታፊ እንደተሳታፊ አንቆጥረውም ሲሉ የገለፁት አስተባባሪዋ በቲሸርቱ ላይ የተፃፈው ‘‘ለተሻለች ኢትዮጵያ እንሩጥ’’ የሚለው መልዕክት እንዲስተጋባ እንፈልጋለን ሲሉ አስተባባሪዋ ጨምረው ገልፀዋል።
“ታላቁ ሩጫ” የራሱ አላማዎችን አንግቦ የሚካሄድ መሆኑን የጠቀሱት አስተባባሪዋ ዋነኛውና ቀዳሚው የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ማስተላለፍ፣ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት፣ እርዳታ ማሰባሰብና በጎ ገፅታን ማጎልበት ነው ብለዋል። ፕሮግራሙ በስፖርት ዝግጅትነቱ ይወሰድልን ሲሉም አሳስበዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድ ጉዳዩን በማስመልከት እንደገለፀው ፓርቲው ታላቁ ሩጫን ሐዘን ለመግለፅ ለመጠቀም የተገደደው ዜጎች እየሞቱ በመሆኑ ብሔራዊ የሐዘን ቀን መታወጅ ስላለበት ጭምር መሆኑን፤ መንግስት በዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በአግባቡ ገልፆ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማወጅ ሲገባው የቁጥር ጨዋታ ውስጥ በመግባቱ ነው ብሏል። ባለፈውም ቅዳሜ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኑም በተመሳሳይ ጥቁር ሪቫን አድርጎ እንዲጫወት ፓርቲው ማሳሰቡንም አያይዞ ገልጿል።
ታላቁ ሩጫ ስፖርታዊ መድረክ ሆኖ ሳለ ፖለቲካዊ ጉዳዩ ወደ ስፖርት ማምጣቱ ተገቢ አይደለም ለሚለው አስተያየት ወጣት ብርሃኑ ተጠይቆ ‘‘በሳዑዲ አረቢያ እየደረሰ ያለው የዜጐች ሰቆቃ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። በሩጫው የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር ሪቫን ያድርጉ ስንል ሰማያዊ ፓርቲን ይደግፉ ማለታችን አይደለም። ለወገኖቻቸው ሰቆቃ ሐዘናቸውን ይግለፁ፤ ለአለም አቀፍ ህብረተሰብም ያስታውቁ ነው ያልነው’’ ሲል ከፖለቲካ ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም ብሏል። ከዚህ በፊት ግራዚያኒን በመቃወማችን ፖለቲካ ተብሎ ነበር፤ አሁን ደግሞ የሳዑዲ መንግስት መቃወም የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰዱ ተገቢ አለመሆኑንም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጨምሮ አስታውቋል።
‘‘ታላቁ ሩጫ’’ በመጪው እሁድ ህዳር 15 ቀን 2006 ዓ.ም መነሻና መድረሻውን ጃንሜዳ በማድረግ ይካሄዳል። 500 ያህል የውጪ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ 37ሺህ ተሳታፊዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዜና ከሰንደቅ ጋዜጣ/ ርዕስ ከዘ-ሐበሻ

No comments:

Post a Comment