Friday, November 29, 2013

ሲያጌጡ ይመላለጡ እንዳይሆን! Must read for women


Written by መታሰቢያ ካሣዬ, AddisAdmassNews.com
በፀጉር ቀለሞች ውስጥ ካንሰር የሚያመጡ ኬሚካሎች አሉ የመዋቢያ ምርት አትዋዋሱ! የመዋቢያ ምርቶችን በውሃ ማቅጠን አደጋ አለው
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የሆነችው ህሊና ለፊቷ ቀለል ያሉ ሜካፖችን መጠቀም የጀመረችው ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ ፊቷ እጅግ ወዛማ በመሆኑ ወዙን እየመጠጠ የተሻለ ገጽታ ሊያጐናጽፋት እንደሚችል የተነገራትን የፊት ማጽጃ ሜካፕ ለአመታት ስትጠቀም ቆይታለች፡፡ በሥራዋ አጋጣሚ በየደረሰችባቸው አገራት ሁሉ የኮስሞቲክስ (የመዋቢያ ዕቃዎች) መሸጫ መደብሮችን ሳትሳለምና የተለያዩ አይነት ኮስሞቲክሶችን ሳትሸምት ወደ አገሯ አትመለስም፡፡ ከፊቷና ከምትለብሳቸው ልብሶቿ ጋር የሚሄዱ (ማች የሚያደርጉ) የፊት ማስዋቢያ ኮስሞቲክሶችን በየቀኑ ትጠቀማለች፡፡ እንደ አይኗ ብሌን በምትሣሣለትና ከወር ገቢዋ አብዛኛውን ወጪ እያደረገች ዕለት በዕለት በምትንከባከበው ፊቷ ላይ ችግር ሊደርስ ይችል ይሆናል ብላ ለአፍታም አስባ አታውቅም፡፡ ከወራት በፊት ለሥራ ወደ ካናዳ ተጉዛ በነበረችበት አጋጣሚ የገዛችውንና ጓደኞቿ ሁሉ ብራንድ ምርት ነው እያሉ ያደነቁላት ሜካፕ መኪናዋ ውስጥ ለሣምንታት መቀመጡ ትዝ አላትና አውጥታ መጠቀም ጀመረች፡፡ ከቀናት በኋላ ፊቷን የማሳከክና የመለብለብ ስሜት ይሰማት ጀመር። ግራ ገባት፡፡ ምንድነው? ስትል ራሷን ጠየቀች፡፡ የማሳከክ ስሜቱ ቡግርና ሽፍታን አስከትሎ ቀጠለ፡፡ ግራ ቢገባት የተለያዩ ተፈጥሮአዊ የፊት መንከባከቢያ መንገዶችን ተጠቅማ ችግሯን ለማስወገድና የህመም ስሜቱን ለመቀነስ ጥረት አደረገች፤ ግን አልተሳካላትም፡፡ ከዕለት ዕለት የፊቷ ገጽታ እየተበላሸ የቡግርና የሽፍታው መጠን እየጨመረ መሄዱ እጅግ አሳሰባትና የቆዳ ሃኪም ለማግኘት ወደ አለርት ሆስፒታል አመራች፡፡ የመረመሯት ሐኪም የተበላሹ የኮስሞቲክስ ምርቶችን በመጠቀሟ ሳቢያ የፊቷ ቆዳ በእጅጉ መጐዳቱንና ረዘም ያለ የህክምና ክትትል ማድረግ እንደሚኖርባት ነገሯት፡፡ እንዴት ተደርጐ? አለች፡፡ የምጠቀመው ብራንድ በሆኑ ምርቶች ነው፡፡ የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን በሚገባ አንብቤና አረጋግጬ ካልሆነ ገዝቼ አላውቅም፡፡ ታዲያ እንዲህ አይነት ችግር እንዴት ሊገጥመኝ ቻለ? ስትል ዶክተሯን ጠየቀች፡፡ ሃኪሟ የኮስሞቲክስ ምርቶች በጤና ላይ ችግር ሊያደርሱ የሚችሉበትን ሁኔታ በዝርዝር አስረዷት። በምርቶቹ ውስጥ ባክቴሪያና ፈንገስ እንዳይራባ ለማድረግና የኮስሞቲክሶቹን ጠረን ለመቀየር ታስበው የሚጨመሩት ኬሚካሎች በቆዳ ላይ ከባድ ችግር እንደሚያስከትሉና ችግሩ የቆዳ ካንሰርን ሊያስከትል እንደሚችል አረዷት፡፡ ለሣምንታት በመኪናዋ ውስጥ ያቆየችው ሜካፕ በፀሐይና ሙቀት ሣቢያ የኬሚካሉ ይዘት ተቀይሮ ለባክቴሪያና ፈንገስ መራቢያ ምቹ በመሆን የደረሰባትን ችግር እንደፈጠሩባት ነገሯትና ህክምናውን እንድትጀምር አደረጓት፡፡ ላለፉት ሁለት ወራት ህክምናዋን እየተከታተለች የተበላሸ የፊት ገጽታዋን ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ ነች፡፡ እንደህሊና ሁሉ በርካቶች በሜካፕ መዘዝ ሣቢያ የሃኪም ቤት ተመላላሽ ደንበኛ ለመሆን ተገደዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመዋቢያ ምርቶችን አጠቃቀም አለማወቅ፣ በኮስሞቲክሶቹ ላይ የተፃፉ መረጃዎችን በአግባቡ አንብቦ መረዳት አለመቻል፣ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች መጠቀም እንዲሁም የመዋቢያ ምርቶችን እየተዋዋሱ መጠቀም ዋንኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የመዋቢያ ምርቶችን (ኮስሞቲክሶችን) ቀደም ብለው መጠቀም የጀመሩት ጥንታውያኑ ግብፃውያን እና ሮማውያን ሲሆኑ ጊዜው ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡ ሊድ፣ መዳብና የተቃጠለ የአልሞንድ ፍሬ ተቀላቅሎ የሚሰራው የአይን ማስዋቢያ (ኩል) ግብፃውያኑ በስፋት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ቀስ በቀስም የመዋቢያ ምርቶቹ በአሠራር እየተሻሻሉ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ጀመሩና በርካቶች ተጠቃሚ ሆኑ፡፡ ለሜካፕ መስፋፋት ትልቁን ሚና የተጫወተው የሆሊውድ መቋቋምና የፊልም አክተሮቹ ራሳቸውን ለማሳመርና ለመቀየር በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ዋንኛ ተፈላጊ ነገር እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ የባሌትና የኦፔራ ዳንሰኞች በመድረክ ሥራቸው ወቅት ሜካፖችን መጠቀም እያዘወተሩ መሄዳቸው ለሜካፕ መስፋፋት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ውጫዊ ገጽታችንን ለማስዋብና ለመቀየር ከምንጠቀምባቸው የመዋቢያ ምርቶች (ኮስሞቲክሶች) መካከል የፊት ሜካፖች፣ የእጅ፣ የፊትና የእግር ክሬሞቹ፣ ከፀሐይ ብርሃን ለመከላከል የምንጠቀምባቸው ቅባቶች (ዱቄት መሰል ምርቶች) ሽቶዎች፣ የፀጉር ቀለሞች፣ ዲኦደራንቶች፣ የከንፈር ቀለሞችና የጥፍር ቀለሞች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የመዋቢያ ምርቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ (ሁሉም ማለት ይቻላል) የጠረን መቀየሪያና ምርቶቹ እንዳይበላሹ አድርገው ለማቆየት የሚረዱ ኬሚካሎች ይጨመርባቸዋል። እነዚህ ኬሚካሎች ደግሞ በአብዛኛው ለከፍተኛ የጤና ችግር ሊዳርጉ የሚችሉ ናቸው፡፡ የቆዳና የአባላዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት ዶክተር ታደገ ኃይሉ እንደሚናገሩት፤ በኮስሞቲክስ ሣቢያ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ዋንኞቹ ምክንያቶች የኮስሞቲክሶቹን ጠረን ለመቀየርና ኮስሞቲክሶቹ እንዳይበላሹ አድርጐ ለማቆየት እንዲረዱ ታስበው የሚገቡ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች ካንሰርን ለሚያስከትሉና የሰውነታችንን የሆርሞን ምርቶች ሊያዛቡ ለሚችሉ የጤና ችግሮች ይዳርጋሉ። ካንሰር አምጪ የሆኑ ኬሚካሎችን በስፋት እንደሚይዙ ከሚነገርላቸው የመዋቢያ ምርቶች መካከል ዋንኛው የፀጉር ቀለም እንደሆነ የገለፁት ዶ/ር ታደገ፤ ዛሬ ዛሬ የፀጉር ቀለም አምራች ድርጅቶች ካንሰር አምጪ የሆኑ ኬሚካሎችን በተመሳሳይ ምርቶች በመተካት ከገበያ እያወጧቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ በፀጉር ቀለም ሳቢያ የሚከሰተውን ችግር ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት አስችሏል ማለት አይደለም፡፡ ዛሬም በዚሁ ኬሚካል ሳቢያ ለካንሰር የሚዳረጉ በርካታ የፀጉር ቀለም ተጠቃሚዎች አሉ ብለዋል፡፡ ባይቲዮኖል፣ ክሎይፎርም፣ ሜቲሊን ክሎራይድና ሜሪኩሪ ኮምፓውንድ የተባሉት ኬሚካሎች ካንሰር አምጪነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ፣ ከፀጉር ቀለም ምርት ግብአትነት እንዲታገዱ ተደርገዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የኮስሞቲክስ ምርቶች ለፀሐይ ብርሃንና ለሙቀት ተጋልጠው መቀመጥ እንደሌለባቸው የሚናገሩት ዶ/ር ታደገ የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት በኮስሞቲክሶቹ ውስጥ ያሉትን ኬሚካሎች ይዘታቸውን በመቀየር ባክቴሪያ እንዲራባባቸው እንደሚያደርግና ይህም ለከፍተኛ የጤና ችግር እንደሚዳርግ ገልፀዋል። የመዋቢያ ምርቶች የራሳቸው የሆነ የመጠቀሚያ ጊዜና የአጠቃቀም ሥርዓት አላቸው ያሉት ባለሙያው፤ መመሪያዎችን በአግባቡ ማንበብና መረዳት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ የመዋቢያ ምርቶች በመግለጫቸው ላይ ተጽፎ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ከሌለ በስተቀር በውሃ ማቅጠን እጅግ አደገኛ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተሩ፤ ውሃ የኬሚካሎችን ይዘት በቀላሉ በመቀየር ለጤና አደገኛ ይሆናል ብለዋል፡፡ የአይን ማስካራ ከሌሎች የኮስሞቲክስ ምርቶች በበለጠ በቀላሉ ጉዳት ያደርሣል፡፡ ማሳካራን በምንጠቀምበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄን ማድረግ እንደሚገባን ያስገነዘቡት ዶክተር ታደገ፤ ያለጥንቃቄ በሚደረግበት ወቅት የአይን ሽፋሽፍቶች እንዲረግፉ፣ እንዲጐብጡና ተሰብረው በአይን ብሌናችን ላይ ጭረት በመፍጠር አይነ ሥውርነትን ሊያስከትሉ ለሚችሉ የጤና ችግሮች ሊዳርጉን እንደሚችሉ አስገንዝበዋል፡፡ ኮስሞቲክሶችን መዋዋስና ችግሩ በመዋቢያ ምርቶች ሣቢያ የሚከሰት የጤና ችግሮች መካከል መዋቢያዎችን በመዋዋስና በጋራ በመጠቀም ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮች ናቸው። በመዋቢያ ምርቶች መቀቢያዎች (ስፖንጆች፣ የማስካራ ብሩሾች) የመሳሰሉት ባክቴሪያዎችን አጣብቀው በላያቸው መያዝና ማስቀረት ስለሚችሉ፣ በጋራ በምንጠቀምበት ወቅት በቀላሉ ኢንፌክሽኖችንና ቫይረሶችን ከአንዱ ወደ አንዱ ለማስተላለፍ ይችላሉ፡፡ አንድን የመዋቢያ ምርት ተቀብተው ሳያስለቅቁና በአግባቡ ከሰውነትዎ ቆዳ ላይ ሳያራግፉ ሌላ አይነት የመዋቢያ ምርት መጠቀምም እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ሌላኛውን አይነት መዋቢያ በቆዳዎ ላይ ከማሳረፍዎ በፊት ቀድሞ የነበረው መዋቢያ መልቀቁን ማረጋገጥ ይጠበቅብዎታል፡፡ መዋቢያዎችን ከፊትዎ ላይ ሳያስለቅቁ ወደመኝታዎ አይሂዱ፡፡ ኮስሞቲክሶችና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሁሉም ኮስሞቲክሶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በግልጽና ሊታይ በሚችልበት ሁኔታ መገለጽ ይኖርባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ከመድረሱ በፊት በተለያዩ የአቀማመጥ ችግሮች ሳቢያ ለብልሽት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ የውበትና ጤና ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት፤ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው የተቃረበ የመዋቢያ ምርቶችን ስንጠቀም ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች እንደሚገልፁት፤ የከንፈር ቀለሞች (ሊፒስቲክና ቻፒስቲኮች) ተመርተው ለገበያ ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ ለአንድ አመት ያለስጋት መጠቀም ይቻላል፡፡ ምርቶቹ ተከፍተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ግን ከአራት ወራት በላይ ማቆየቱ አደጋን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ኮስሞቲክሶችን በዘፈቀደ መጠቀምና ችግሩ የመዋቢያ ምርት ተጠቃሚዎች በአብዛኛው ስለሚጠቀሙት የመዋቢያ ምርት ምንነት፣ በውስጡ ስለሚይዛቸው የኬሚካል አይነቶችና ስለሚያስከትሏቸው ችግሮች፣ መዋቢያውን በምን መልኩ መጠቀም እንደሚገባቸው እንኳን ሣያውቁ በዘፈቀደ ሲጠቀሙባቸው ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ በጤና ላይ ሊያደርስ የሚችለው ችግር በቀላሉ የሚገለጽ አይሆንም። ሌላው የመዋቢያዎችን ምንነት ሳያውቁ ከየሱቁና ከየመደብሩ በመግዛት በጥቅም ላይ የማዋል ችግር ነው፡፡ በአገራችን በገበያ ላይ ከሚገኙት የመዋቢያ ምርቶች መካከል በሰለጠኑት አገራት ሙሉ በሙሉ በበቅም ላይ እንዳይውሉ የታገዱና ከገበያ የወጡ ምርቶች ይገኙበታል። እነዚህ ምርቶች በአገራችን በየሱቁና በየመንደሩ ይቸበቸባሉ፡፡ ከየት እንደመጡ፣ ከምን እንደተቀመሙ፣ ለምን ጥቅም እንደሚውሉ አንዳች መረጃ በሌለበት ሁኔታ በየሱቁ ይሸጣሉ፡፡ ቤትኖቬትና ዳርኖቬት የተባሉት ቅባቶች በርካታ ሴቶች ለፊት ውበት ማሳመሪያ እያሉ ከየሱቁ እየገዙ ከሚጠቀሟቸው ምርቶች መካከል ዋንኞቹ ናቸው። እነዚህ ምርቶች በውስጣቸው በያዙት ለጤና እጅግ አደገኛ ኬሚካሎች ሣቢያ ከሰለጠኑት አገራት የኮስሞቲክስ ገበያ ውስጥ እንዲወገዱ ተደርገዋል፡፡ ተፈጥሮአዊ የመዋቢያ ምርቶች ጠቀሜታቸውና የሚያስከትሉት የጤና ችግር ከተለያዩ የእጽዋት አይነቶች እየተቀመሙ የሚዘጋጁ የመዋቢያ ምርቶች በውስጣቸው ምንም አይነት ኬሚካል ባለመኖሩ ለጤና የሚሰጡት ጠቀሜታ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ምንም አይነት የጐንዮሽ ጉዳት የላቸውም። ይሁን እንጂ እነዚህን ምርቶች በምንጠቀምበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ እነዚህን መዋቢያዎች ወዲያውኑ በጥቅም ላይ የማናውላቸው ከሆነ የሚያስከትሉት ጉዳት የከፋ ይሆናል። ምክንያቱም መዋቢያዎቹ በውስጣቸው ባክቴሪያና ፈንገስ እንዳይራባባቸው ለማድረግ የሚያስችል ኬሚካል ባለመኖሩ ለኢንፌክሽንና መሰል ችግሮች ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡ በአጠቃቀም ወቅት ሊደረግ የሚገባ ጥንቃቄ ሜካፕዎን ለሙቀትና የፀሐይ ብርሃን አያጋልጡት በመዋቢያ ምርቶች ላይ ውሃን ፈጽመው አይጨምሩ ሜካፕዎ ቀለሙና ጠረኑ ከተቀየረ ፈጽመው አይጠቀሙት ሜካፕ ተዋውሶ መጠቀም እጅግ አደገኛ ለሆነ የጤና ችግር ያጋልጣል ሜካፕዎን በአግባቡ ተጠቅመው፣ በአግባቡ ከድነው በትክክለኛው ቦታ ያስቀምጡ በመኪና እየተጓዙ ኮስሞቲክሶችን አይጠቀሙ የፊት ማስዋቢያ ፓውደሮችና የፀጉር ስፕሬይዎች ሽታቸው በሳንባ ላይ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ወደ አፍንጫዎ አስጠግተው በጥልቀት አያሽትቱአቸው፡፡ የአይን ኢንፌክሽን(ህመም) ካለብዎ ማስካራ፣ ሻዶ፣ ላይነር የመሳሰሉትን የአይን ማስዋቢያዎች አይጠቀሙ፡፡ ሲያጌጡ ይመላለጡ እንዳይሆን ሜካፕ ስንጠቀም በጥንቃቄ ይሁን!!

sodere

No comments:

Post a Comment