Tuesday, November 19, 2013

ሰቆቃወ ወገን (አበራ ለማ)

ግጥም - Poem

ሰቆቃወ ወገን (አበራ ለማ)



STOP violence against Ethiopians in Saudi Arabiaአበራ ለማ
ረሀብ፣ ስቃይ እንግልቱ - መች አንሶህ አንት ወገኔ
ስደትን ምርኩዝ አድርገህ - መግባትህ ከምድር ኩነኔ?
ምን ሊበጅህ? ምን ሊቤዥህ? ከቤት እሳት ከደጅ እሳት
ማምለጫ የለህ መሸሸጊያ - መድረሻ የለህ አንዳች ጥጋት፤
ክብር ኩራትህ - እንደራፊ ተላይህ ላይ ተቀዶ
ኢትዮጵያዊ ስምና ሰንደቅ - ማላገጫ ሲሆን እባር ማዶ፤
ማን ያስጥልህ? ማን ይድረስልህ ወገኔ?
ማን ይዋስህ? ማን ይሁንህ ምስለኔ?
ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ
መች ባለ'ዳ ሊል ቢሮሌ? ...

የትናንት ትናንት ሕመምህ - ያገርህ ጣውንታት ውጋት
የደርቡሹ፣ የፓሻው፣ ያታቱርኩ ሎሌ የግብጹ ባንዳ ጥቃት
አያት ቅማያትክን እንዳልበላ - ደሞ ባንተ ላይ ዙሮ መጣ
ያረብ ዘይቱ ቡላ ብስናት - ስካር አምቡላው ታናቱ ወጣ?
ለካስ የጀማላ ዛር አንጎልም የለው - ቲፈጥረው ኖሮን አንኮላ
እጎዳና ላይ ሰው አርዶ - ደሙን ጠጥቶ ሥጋውን ቆርጦ ሲበላ፤
ማን ያስጥልህ? ማን ይድረስልህ ወገኔ?
ማና ይዋስህ? ማን ይሁንህ ምስለኔ?
ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ
መች ባለ'ዳ ሊል ቢሮሌ? ...
እውን አላህ እግር ጥሎት - ታረብ አገር ሂዶን ኑሯል
እሳኡዲ ጎራ ብሎ - ሳጥናኤልን ጠይቆታል?
"ሰውን ከሰው ለይተህ - ከትፈህ ብላ ብዬሃለሁ?"
እያለ እየጠየቀ - የራስ ፍጥርቱን እምባ
እሱ ራሱ እያዘራ - እሱ ራሱ እያነባ ...
"'አላህ አክበር! ...' አትበለኝ - ባፍ ጉቦ አትደልለኝ!
መካ መዲናን ጉቦ ሰጥተህ - የድሃ እምባ፣ የድሃ ደም፣ የድሃ ነፍስ አትገብረኝ!
ካንተ ጋር ውልም የለኝ - ንግግር እርቅም የለኝ! ..."
እያለ አላህ የማታ ማታ ፍርዱን ሰጥቶ
ግፉዓን ይቤጁ ይሆን - ስቅየታቸው ግዘፍ ነስቶ?
ያ የጥንት የጠዋቱ ጌታ - ልዑል እግዚአብሔር በርትቶ?
ያለያማ ማን አለው? ማን አለው ደራሽ?
ማን ያስጥለው? ማን ይድረስለት ወገኔ?
ማን ይዋሰው? ማን ይሁነው ምስለኔ?
ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ
መች ባለ'ዳ ሊል ቢሮሌ? ...
 http://www.ethiopiazare.com/art-56/poem/3148-sekokawe-wegen-by-abera-lemma

No comments:

Post a Comment