Wednesday, November 6, 2013

ጅብን ለመውጋት አህያን ተጠግቶ ነው ወይስ ተኩላን? (ገረመው አራጋው ክፍሌ/ኖርዌይ)

ገረመው አራጋው ክፍሌ/ኖርዌይ
”ማን ነው ግንቦት ሰባትን ማጥላላት የሚቻለው? ግንቦት ሰባት ከሻቢያ ጋር በመሥራቱ አይደለም እንዲህ የተጠመደው? እሰይ! እንኳን ከሻቢያ ጋር የሠራ! እልልልልልልል…..! አሁንም ከሻቢያ ጋር አይደለም ከሰይጣን ከራሱ ጋርም ቢሆን ተደራድሮ ይሥራ! እኔም ባገኘሁት አጋጣሚ ከሰይጣን ጋርም ቢሆን ለመሥራት አሁን ቃል ገባሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ግንቦት ሰባትን የሚቃወም የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት እንደሆነ አድርጌ እወስዳለሁ፡፡ ”
ግንቦት 7 ውጊያ ቢገጥም ልንደግፈው ፈቃደኛ ነን:: እየተቃወምነው ያለነው ግንቦት 7ን ወይም የመረጠውን የትግል ስልት አይደለም:: መንገዱ ሁሉ የተዘጋበት ሰው ቢሸፍት ትክክል አይደለም ሊያሰኝ አይችልም:: የምንደግፈው ግን ኤርትራን መሰረት አድርጌ እዋጋለሁ የሚለውን ቅዠት እርግፍ አድርጎ የሚተው ከሆነ ነው::
መቸም ቢሆን ሻእቢያ የሚታመን ድርጅት አይሆንም: ተፈጥሮው በራሱ ታማኝ እንዲሆን አይፈቅድለትም:: በተንኮል ተጸንሶ: በተንኮል ጎልብቶ በተንኮል እዚህ የደረሰ ነው:: ኤርትራ ተገንጣዮችን የምትረዳበትን ምክንያት ማሰብ ያስፈልጋል:: ኤርትራ እንደ ኦነግና ኦብነግ ያሉት በታኝ ድርጅቶች እንዳሰበው ስላልሆኑለት ብቻ ነው ወያኔን የሚያዳክም ህብረ ብሔራዊ ድርጅት የፈለገው:: ወያኔ ክፉኛ የተጎዳ ከመሰለው ግን ከኋላ ተኩሶ እንደሚመታ መታወቅ አለበት:: አሊያም ግንቦት 7ን በስለላ መረብ ገንዞ የሻእቢያ ጉዳይ ፈጻሚ ሮቦት ማድረግ ብቻ ነው::
ወያኔ እየደከመ መስሎ ከታየ ሻእቢያ ከኋላ ሲተኩስባችሁ ያኔ ይገባችሁዋል:: በ1997 ዓ.ም ወያኔ መሰረቱ የተናጋ ሲመስል ሻእቢያ ከወያኔ በላይ በቅንጅት ላይ ዘምቶ እንደነበረ የተገነዘባችሁ አይመስለንም:: ከሻእቢያ ስር ሆናችሁ ለምታደርጉት ትግል በነጻነት በራሳችሁ ጊዜ አቅዳችሁ የምትፈጽመት ይኖራል ብላችሁ አትገምቱ:: የት እንዳላችሁ የሚያሳውቅ አንገታችሁ ላይ የተንጠለጠለ ቃጭል አስሮ በቅርብ እርቀት ይከታተልሀል:: የተጠናከርክ ከመሰለው መሪወችህን አስሮ ወይም ገሎ ይበትንህና ጥፋቱን ሁሉ በሌላ አሳቦ እንደገና በመረበሽ ተግባር ብቻ እንድትወሰን አሰባስቦ ሌላ አመራር ሊያስመርጥህ ይችላል:: ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ እንደማታነሳ መተማመኛ ብታቀርብም ተሰሚነት አይኖርህም:: ከኢትዮጵያ ተነጥለው ኤርትራን ማሳደግ አለመቻላቸው በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ አንሰው መገኘታቸው ከምንም በላይ ይረብሻቸዋል:: እና የሚፈልጉት ከኤርትራ ያነሰች ኢትዮጵያን ነው:: ሻእቢያ መቸም ቢሆን በአንድነቷ የጸናች ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር የሚፈልግ ቡድን አይደለም::
ኤርትራ ውስጥ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን በእስር እንደሚማቅቁ ይታወቃል:: ሻእቢያ ኢትዮጵያ ላይ ቂም አለኝ የሚለውን አንስቶ ከሆነ መጀመሪያ እኒህን ሰዎች በመፍታት ሰላማዊነቱን ያረጋግጥ:: ይህንን ለማስፈጸም የግንቦት 7 አመራሮች ምን አድርገዋል ? ተጨማሪ ሰለባወችን ማሰባሰብ ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው:: ለወገን ክብር እንስጥ:: አውሮፓና አሜሪካ ቁጭ ብሎ የዋሁን ኢትዮጵያዊ ወደ አላስፈላጊ ማእዘን መግፋት ትክክል አይደለም ብቻ ሳይሆን ሀላፊነት የጎደለውም ተግባር ነው::
የዛሬዎቹ የግንቦት 7 መስራችና መሪዎች የትናንት የወያኔ ተባባሪና አገልሎት ሰጭ፣ የዛሬ የወያኔ ተቃዋሚዎች ፣ የኢትዮጵያና የሕዝቧ መሰሪ ጠላቶች ናቸው።  ለወያኔ መንገድ እየጠረጉ ከፍተኛ አገልግሎት ያደረጉ፣ የአገርቱን ምስጢር፣ልዪ ልዪ መረጃዎችንና ሰነዶችን ፣ መግቢያ መውጫውን የሰለሉና ያሳዪ፣ የመሩና ቤተመንግሥት ያስገቡ ዛሬ በውጭ ያሉ ተቃዋሚ የሚባሉ ባንዳ ወያኔዎች ናቸው።ከወያኔ ቀፎ የወጣ ወይም ያመለጠ ሁሉ ወደ ብሔራዊ አንድነት ቀፎ ሊገባም ሆነ ማር ሊሰጥ አይችልም።የተመረዘ ነውና።
በሀገራችን ውስጥ ለመሠረታዊ መብቶች መጣስ፤ ለአንድነታች መናጋትና የማያባራ የአመጽ አዙሪት ውስጥ ለመውደቃችን በዋናነት ተጠያቂው ወያኔ /የወያኔ ፖሊሲና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የተዘረጋው አፋኝ ሥርዓት ነው። የሀገራችንን አንድነትም ከእለት ወደ እለት አሳሳቢ ወደሆነ አደጋ እየገፋው የሚገኘው በዋናነት ይኅው ገዥው ወያኔ ነው። ይህ አደጋ እንዲቆም፤የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ስንል ትግላችን የወያኔ የግፍ አገዛዝ ማሰወገድ ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን አንድነት በምንም መልኩ ለድርድር በማያቀርብ ሁኔታ የህዝባችን መብት ሙሉ ለሙሉ ማስከበር፣ ፍትህ የሰፈነበት ሥርዓትን መመሥረትና መገንባትን ይመለከታል። ይህ ብቻ ሳይሆን በወያኔ ፀረ-አንድነት ፖሊሲ አንድነቷን ያጣችውን፣ ዳር ድንበሯ የተሸራረፈውን  ኢትዮጵያን በአካባቢውም ሆነ በአፍሪካ ተገቢና ታሪካዊ ቦታዋን እንድትይዝ የሚያስችል መሠረትን መጣል ነው።
ታሪክ እንደሚያሳየን ኢሳያስም ሆነ እሱ የሚመራው ድርጅቱ ሻኣቢያ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ንደ ጠላት በመመልከት የተዳከመችና የፈራረሰች ትዮጵያ ንድትሆን ምኞታቸው ብቻ ሳይሆን ሳያሰልሱ ሠርተዋል። ከዚህም በመነሳት የትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚጻረር ተግባሮች ያራምዳሉ፤ ያስፋፋሉ፤ ይደግፋሉ። ከተቻላቸው በትዮጵያ ውስጥ የነሱን ሻንጉሊት መንግሥት ለማንገስ ይጥራሉ። የማይሳካ ሲመሰላቸው ደግሞ ጠንካራ ትዮጵያዊ መንግሥት ንዳይኖር በሁሉም መልክ ይጥራሉ። ይህን ከርባ ላላነስ ተከታታይ ዓመታት የተካሄደን እውነታ መዘርዘር ባያስፈልግም ላለፉት  22 ዓመታት ከወያኔ ያካሄዷቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባሮች ማንነታላቸውን አመላካች ነው።   
እያስጮኸን ያለው ለመስዋእትነት እንዲሰለፍ የሚደረገው ወጣት ወገናችን በመሆኑና መስዋእትነታቸውም ውጤት አልባ ለሆነ ነገር እንደሆነ ስለምናውቅ ነው:: ግንቦቶች ወይ ሻእቢያን አላወቃችሁትም ወይም የተደበቀ አጀንዳ አላችሁ:: ሻእቢያ እየተጠቀመ ያለው “ጅብን ለመውጋት አህያን ተጠግቶ ነው” የሚለውን ብሂል ነው:: እናንተ እየተጠቀማችሁ ያላችሁት ግን “ጅብን ለመውጋት ተኩላን ተጠግቶ ነው” የሚለውን ብሂል ነው:: ይገባል: ሌላ አማራጭ መንደርደሪያ መጥፋቱ:: ይህ ግን ሻእቢያን የመጨረሻው ተመራጭ አያደርገውም:: ምክንያቱም ሻእቢያ ከማንም በላይ ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ ኢትዮጵያዊያን ስለሆነ::
ወያኔ በህዘባችን ላይ የሚያካሂደው ግፍ ሞልቶ በመፍሰሱ የተነሳ ወያኔ ይወገድልን እንጂ የፈለገው ይምጣ የሚል አመለካከት አልፎ አልፎ ሲንጸባረቅ ይታያል። የዚህ ዓይነቱ  አመለካክት በሥርዓቱ  የመማረር ውጤት እደሆነ ግልጽ ቢሆንም፣ ወደምንፈልገው ዘላቂ ሰላም፣ ብሄራዊ ጥቅምና የህዝብ መብት መከበር ሊያደርስ መቻሉ ግን እጅግ አጠራጣሪ ነው።
ኤርትራንና ሻኣቢያን በተመለከተ የኢትዮጵያ ህዝብ ገና ብዙ ያልተዘጉ አጀንዳዎች፤ ያልተቋጩ ጉዳዮች አሉት። ይህ ጉዳይ በመሠረቱ ነፃ መንግሥት መሥርተን የኢትዮጵያን ድንበርና ጥቅም አስጠብቀን ከመጓዝ ጋር እጅግ የተሳሰረ ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት ይህንን ታላቅ ሀገራዊ አጀንዳ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንዲዳፈንና እንዲደበዝዝ ከሚያደርጉ እርምጃዎች ራሱን መቆጠብ አለበት። አደጋው ሲታይ ደግሞ የማስጠንቀቂያ ደወል ማሰማት ሀላፊነት ከሚሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚጠበቅ ነው።
ኢትዮጲያና ኢትዬጲያዊነት ለዘላለም ይኖራል። ወያኔ ግን በተባበረ የኢትዮጲያዊያን ጠንካራ ክንድ ይወገዳል!!

 http://www.revolutionfordemocracy.com/2013/11/06/69-29/

No comments:

Post a Comment