የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ሕግና ሰብዓዊ መብት ቋሚ ኮሚቴ ያዘጋጀውን በአገሪቷ ውስጥ ተከሰቱ የሚላቸውን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን
የሚያሳይ ሪፖርት፣ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ይፋ አደረገ፡፡
ይህ ባለ 30 ገጽ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት አሁን ኢትዮጵያን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው የኢሕአዴግ
መንግሥት በዓለም አቀፍ ሰነዶችና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በመጣስ፣ በዜጐች ላይ
ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸመ ይገኛል በማለት ይከሳል፡፡
ሪፖርቱ በሦስት ክፍሎች የተደራጀ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ክፍል በአንድነት ፓርቲ አባላት ላይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ
ጥሰቶች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ በሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች አባላት ላይ ያተኩራል፡፡
ሦስተኛውና የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ከየትኛውም ፓርቲ የፖለቲካ ወገንተኝነት በሌላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ
የተፈጸሙ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን አካቷል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሄደ ነው ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመዋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል
ያለውን ሪፖርት ይፋ ከማድረጉም በላይ፣ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች
በንፁኀን ዜጐች ላይ የሚፈጸሙትን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አንዳንድ የአርትኦት ሥራዎች ከተከናወኑ በኋላ
አባሪዎችንም በመጨመር በአጭር ጊዜ ውስጥ የፓርቲው ድረ ገጽ ላይ ሊገኝ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጉዳዩ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ሪፖርቱ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለእንባ ጠባቂ ተቋም፣
ለፌዴራል መንግሥትና በሪፖርቱ ለተጠቀሱ የክልል መንግሥታትም ይሰራጫል በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎችን ለመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም ሪፖርቱ እንደሚላክ ዶ/ር ነጋሶ አክለው አብራርተዋል፡፡
ሪፖርቱ አገዛዙ በንፁኃን ዜጐች ላይ ይፈጸማሉ ካላቸው ዋና ዋና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች መካከል የሚከተሉትን
ይጠቅሳል፡፡ በድብደባ አካል ማጉደል፣ በሕገወጥ መንገድ በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ አስሮ ማሰቃየት፣ ማዋከብ፣
ማስፈራራት፣ በማስገደድ መረጃ ከፓርቲያቸው እንዲያመጡ ማድረግ፣ የፖለቲካ አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ፣ ከፖለቲካ
ተሳትፎ እንዲርቁ በቤተሰብ በኩል ጫና ማድረግ፣ መኖሪያ ቤትን በሕገወጥ መንገድ መበርበር፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ
ግለሰቦችን በእስረኞች ማስደብደብና በቤተሰብ፣ በጓደኛ፣ በሃይማኖት አባት እንዳይጐበኙ መከልከል የሚሉና ሌሎችም
ተካተውበታል፡፡
‹‹በጥቅሉ ሥርዓቱ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ዕውቅና የሰጣቸውንና ከአንቀጽ 14 እስከ 28 የተዘረዘሩትን
የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ ዕቀባ በማድረግ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት ሆኗል፤›› በማለት
ይከሳል፡፡
https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/11/05/45565/
No comments:
Post a Comment