Monday, October 14, 2013

በ1ኪሎ ቁርጥ ሥጋ እና በ12 ድራፍት ብርጭቆ – እውነትና ከሕደት………(ከ ይድነቃቸው ከበደ)


ooohhhh
(የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ሀላፊ)
ኪነ-ጥበብ ምኞታችን፣ደስታችን፣አዘናችንን እና ክፋታችን የምናይበት እና የምናዳምጥበት የህይወታችን ነፀብራቅ ነው፡፡ ኪነ-ጥበብ ህይወትን ቀለል አድርጎ ከማዝናናት ባለፈ በገለሰብ አስተሳሰብ ላይ የራሱ የሆነ በጎ ወይም በጎ ያልወነ አስታውጾ የሚያበረከት ጥበባዊ ሃይል ነው፡፡ይህ ሃይል በመልካም አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ ወደ ህብረተሰቡ ውስጥ ሲገባ የሚኖረው አገራዊ ፋይዳ እጅግ በጣም የበዛ ነው፤፤ በመሆኑም ኪነ-ጥበብ እንዲህ አይነቱ ጠቀሜታ እንዲኖረው የሚያደርጉት በጥበብ ሙያ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ናቸው ፤እነኚህ ባለሙያዎች ሙያቸው ከመሬት የፈለቀ ሣይሆኖ በልምድና በት/ት የዳበረ ጥበባዊ ተስጥኦ ነው፡፡
ከኪነ-ጥበብ ዘርፎች ውስጥ ከሚመደቡት አንዱ ቴአትር ነው፤ ቴአትር በአገራችን ያለው ተቀባይነት ቀላል የሚባል አይደለም ፤ቴአትር አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ የቴአትር ባለሙያዎች የከፈሉት ዋጋ ከዕድሜቻው፣ ከገንዘባቸው እና ከዕለት ተዕለት ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ጎምዶ ያስቀረባቸውን የሚያውቁት ዋጋውን የከፈሉት እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ ቢሆንም በቴአያትር ጥበብ የዝወትር እንቅስቃሴችን መጥፎዉንና የተሸለውን በመለየት ጥበባዊ በሆነ መንገድ እየተዝናናን እንድንማርበት ለሚያደርጉ የቴአትር ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ስንመለከትና ስናደምጥ እውነትም ለሙያው እድገት የተከፈለ ነገር እንዳለ ያስገነዝበናል፡፡
ስለሆነም ለቴአትር ባለሙያዎቻችን ከትላንት ዛሬ የምንሰጣቸው ከበሬታና አድናቆት የሚበረታታና የሚያስደነቅ ነው፤ይህ ደግሞ ለቴአትሩም እድገት የሚጠቅም ነው፡፡ይሁን እንጂ በቀርብ በብሔራዊ ቴአትር ቀደምት ባለሙያዎች ላበረከቱት አስታዋጽኦ በማስታወስ የሽልማት ፕሮግራም የተዘጋጀ ቢሆንም ዝግጅቱ እውነትና ከሕደት የተቀላቀለበት ነበር፡፡
‹‹……. ቀደምት ባለሙያዎች እንዲገናኙና ባለፈው ላደረጉትም አስታውጽኦ ሽልማት መሰጠቱ ተገቢነት ያለው ድርጊት ነው፡፡ባለሙያዎቹ ሲገናኙና በመነፋፈቅ ፈቅራዊ ሰላምታቸውን ሲለዋወጡ ስመለከት እጅጉን ደስ ብሎኝ ነበር የምከታተለው፡፡ እየቆየሁ ሲሄድ በውስጤ ቅሬታ ተሰማኝ በብሔራዊ ቴአትር በተከናወነው ስርአት ላይ በሞት የተለዩትን ተነሱ፤ በነፍስ ያሉት ግን ተገኝተው የሚመሰገነው ተመሰገነ፤ የሚሸለመው ተሸለመ እዚህ ላይ ነው ቅድም የጀመረኝ ቅርታዬ የበረታብኝ፡፡………. ››
በማለት በብሔራዊ ቴአትር ቤት የተካሄደውን ሽልማት ስነስርአት በኢቲቪ ፕሮግራሙን ሲከታተል የነበረ ሰው ትዝብቱን እና ቁጭቱን በሎሜ መፅሔት በባለፈው ሳምንት ዕትም ላይ ያስነበበን፡፡
እኔም የሰውዬውን ትዝበት እና ቁጭት አብዝቼ የምጋራው ነው፤ አርቲስት ደበበ እሸቱ በሙያው ከበሬታን ያተረፈ ለብሔራዊ ቴአትር ቤት እድገት የተቻለውን አስታውጾኦ ያበረከተ እና በህይወተ ከቀሩልን አንጋፋ አርቲስቶች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ማንኛውም ሰው የሚሰጠው ምስክር ነው፡፡እውቁ አርቲስት ደበበ እሸቱ ተዋናይ፣ኮሜዲያን፣ አዘጋጅ ሆነ ለረዥም ዓመታት አገልግሏል፡፡ በመድረክ ፣ በሬዲዩ፣ በቴሌቪዥን፣ በፊልም ስራ እና በጋዜጠኝነት ሙያ ሠርቷል፡፡ ቤተ መንግስት ተገኝቶ አፄ ኃይለሥላሴን ከሥልጣን ሲወርዱ ያነጋገራቸው ጋዜጠኛ ደበበ እሸቱ ነው፡፡ የተለያዩ ሃላፊነቶችን ይዞ ሠርቷል ፤ በአፍሪካ የመድረክ ሙያተኞች ማህበር በሊቀመንበርነት መርቷል እንዲሁም በአትላንታ አንድ ቀን በስሙ ተሰይሞለታል፡፡ የአርቲስት ደበበ እሸቱ የጥበብ እረዥሙ የህይወት ጉዞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኪነጥበባት ወ ቴአትር ተጀምሩ በብሔራዊ ቴአትር የቀጠለ ሲሆን በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ያበቃ ነው፡፡
ስለ አርቲስቱ ካነበብኩት እና ከማቀው ይህን ብልም ከእኔ እውቀት ማነስ ያስቀረውበት መልካም የሆኑ ስራዎቹ እንደሚኖሩት ተስፋ አደርጋለው፡፡ በመሆኑም በብሔራዊ ቴአትር ቤት በተካሄደው የማስታወስ እና የሽልማት ስነስርአት ላይ አርቲስት ደበበ እሸቱን ለማስታወስም ሆነ ለመሸለም አለመቻሉ ከምን እንደመነጨ አንድ ለበዓሉ ዝግጅት ቅርብ የሆነ ለሆዱ ያደራ አርቲስት በ1ኪሎ ቁርጥ ሥጋ እና በ12 ድራፍት ብርጭቆ በፈጀ ወጪ እውነትና ክሕደትን ዘርዝሩ የተናገረው፡፡ ይህን ሰው ሆድ አደር ያልኩበት ምክንያት የሚያውቀውን እውነት በፍራቻ ምክንያት በአደባባይ አለመግለፁ እንዲሁም የዝግጅቱ አስተባባሪ ከሆኑት ውስጥ አንዱ እንደመሆኑ መጠን የራሱን እምነት ወይም አቋም በዝግጅቱ ሂደት ላይ ምንም ሳይገልፅ ሌሎችን ለመኮነን የሄደበት መንገድ ነው፡፡
ይህ ለበዓሉ ዝግጅት ቅርብ የሆነው አርቲስት የቀረበለትን ምግብ እና መጠጥ እየጠጣ አርቲስት ደበበ እሸቱ በሙያው አንቱታን ያተረፈ ለቴአትር ሙያ እድገት አስታውጾኦ ያበረከተ መሆኑ እና በቀድሞ የሙያ አጋሮቹ ፍቅርና ከበሬታ ያለው መሆኑን ምግብና መጠጥ ለጋበዘው ሰው ገልጾአል፡፡ ንግግሩን ሲቀጥል ‹‹ ደቢሾ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ስለሆነ በፕሮግራሙ ላይ እንዲሳተፍ አልተፈለገም ፤ በሱ ጉዳይ ላይ ስንቱ አፈ ልጉም ሁሉ ልወደድ በሚል አፉን ፈታ መሰለህ፡፡ የሚገርመው ግን ደቢሾ ወደ ቴአትር ቤት አንድ ሁለት ጊዜ መጥቶ በነበረ ጊዜ ሁሉም እንዴት እየተንደረደሩና እላዩ ላይ እየተጠመጠሙ እንደሚስሙት አይ ነበር እነዚያው ሰዎች አሁንም እንዳይጠራ ብለው ሲሞግቱ በጣም ነው የተገረምኩት ፡፡ ዋናው ደግሞ ስራ አስኪያጁ እንዴት እንደተቃወመና በጭራሽ ሊጠራ አይገባም ፤ እሱ የሚጠራ ከሆነ እኔ በበዓሉ አልገኝም ስራዬንም እለቃለው አለ ! በቃ ያንን ስንሰማ ሁላችንም ፈራን……….. ስማ እንግዲህ ይህ በእኔና ባንተ የሚቀር የግል ጨዋታ ነው፤ የኔን ስም በጽሁፍም ሆነ በግልም ለደቢሾም ቢሆን እንዳታነሳ፤ አደራህን ነገ የሚሆነውን ማን ያውቃል ? ›› በማለት የነገሩን ሂደት ሰፋ አድርጎ የገለፀው፡፡
ውድ አንባቢያን 1ኪሎ ቁርጥ ሥጋ እና 12 ድራፍት ብርጭቆ የፈጀ ወጪ በመሸፈን በብሔራዊ ቴአትር ቤት የተካሄደውን የሙያ ክሕደት እውነቱ እንዲወጣ ያደረገው አርቲስት እና ምግብና መጠጥ አሸንፎት እውነቱን የተናገረው ሌላኛው አርቲስቲ ሙሉውን ታሪክ መስከረም 18 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው ሎሚ መፅሔት ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡
ወደ መነሻዬ ልመለስ እና አርቲስት ደበበ እሸቱ እድሜ ልኩን በሙያው ያገለገለ እውቅ አርቲስት ነው ፡፡ በዚያው መጠን አሁን ባለው በገዢው ስርዓት ለታየው ብልሹ አስተዳደር ግንባር ቀደም በመሆን ሲተች እና ሲታገል ነበር በዚህም ምክንያት ለተደጋጋሚ እስር እና ለተደጋጋሚ ይቅርታ ጥያቄ ተዳርጓል፡፡ ይህ ግለሰባዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ላበረከተው በጎ አስታውጾ በየትኛውም በኩል መመዘኛ ሊሆን አይገባም !!! እርግጥ ነው ገዢው መንግስታችን ለልማታዊ አርቲስቶች ያለው ድጋፍ ቀላል የሚባል አይደለም ፤ ልማታዊ አርቲስቶችም ለኢህአዴግ መንግስት ያላቸው ድጋፍ ወደር አይገኝለትም፡፡
አርቲስቶቻችን ሰው እንደመሆናቸው መጠን የራሳቸው የሆነ የሃሳብ ነፃነት ያላቸው ሲሆን በዚህ መብታቸው በመጠቀም የሚፈልጉትን የፖለቲካ አስተሳሰብ የመደገፍ ሳይመስላቸው ሲቀር የመተቸትና የመቃወም መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ተፈጥራዊ የሃሳብ ነፃነት መብት በሃይል ወይም በጥቀማጥቅም በመደለል እና በማስገደድ የአንድ የፖለቲካ ስርአት ብቻ ደጋፊና አቀንቃኝ ማድረግ የሞራል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
በመሆኑም እንዲህ አይነቱ አካሄድ ለአርቲስቱም ሆነ ለሙያው እድገት ጉዳት እንጂ ጠቀሜታ የለውም፡፡ በአገራችን የፖለቲካው ስርአት ሲለወጥ የአገር መከላኪያ ሠራዊት ( ጦሩ) እየተለወጠ በአዲስ መልክ እየተቋቋመ ተቸግረናል ፡፡ አሁን ደግም የመከላኪያ ሠራዊት ( ጦሩ) ብቻ ሳይሆን አርቲስቶቻችንም ከፖለቲካ ስርአታችን ጋር እየተቀየሩ በአዲስ መልክ ልናያቸው ይሆን ? ፡፡ እንዲህ አይነቱ አደገኛ ከስረት ውስጥ ከመግባታችን በፊት የነገሩን አካሄድ ሊመረመር ይገባል ፡፡
በመሆኑም በአርቲስት ደበበ እሸቱ ላይ የተፈጸመው የሙያ ከሕደት እጅግ በጣም የሚያሳዝን እንዲሁም የሚያሳፍር ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ አገርን አስተዳድራለው ከሚል መንግስት እንደሰፈር ጉልበተኛ ጎረምሳ እልህ በመጋባት በአርቲስቱ ላይ የሙያ ከሕደት እንዲፈፀም ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ አስታውጾኦ በመንግስት ካድሬዎች በመፈጸሙ ሌላኛው አሳፋሪ እንዲሁም አስቂኝ ነገር ነው፡፡
ስለዚህም ለእውነት ያደሩ ሙያተኞች እንዲህ አይነቱን አሳፋሪ ተግብር ለህዝብ ከማጋለጥ ባለፍ ለሙያቸው እና ለእራሰቸው እድገት የሚበጀውን ቀና መንገድ ለማምጣት ውጫዊ እና ውስጣዊ ሙያዊ ትግል ሊያካሂዱ ይገባል፡፡ በተጨማሪ በቀብር ስነስርአት ላይ ጥቁር ለብሶ እና በእመም ጊዜ ለመታከሚያ ገንዘብ ለመሰብሰብ ከመታየት በለፈ በሙያቸው እውቅ የወኑትን አርቲስቶች በህይወት እያሉ በማሰብ እና በማበረታታት ሙያዊ አጋርነታቸውን ለእውነት የቆሙ አርቲስቶች ሊያሳዩን ይገባል፡፡

zehabesha

No comments:

Post a Comment