Thursday, November 14, 2013

ሙሴ ወዴት ነህ? – ከመኳንንት ታዬ (ደራሲና ገጣሚ)


ከላኛው ዘመን የሰው ልጅ በእግዚያብሔር እጅ ተበጃጀና ሲያበቃ ድንግል ሃሳብ የነበረው አንዱ ቅዱሥ አዳም የምር እና የምሬት ምክንያት የሆነችውን ሔዋንን ካገኘ በሗላ፤ እያለ ታሪኩ ይጓዝና ፤በስተመጨረሻው ወደ አንድ ጥግ ተጉዞ ህዝቤ ብሎ የሚጠራው ህዝብ ከምድር ምሃል ከምትገኝ አንዲት ስፍራ ላይ በዝተው ተባዝተው ሲኖሩ አባት ልጆቹን እንዲቀባ ቀብቶአቸው ነበርና ጥለው ማረዱን አግኝተው ማርፈዱን አላወቁበትም። በዚህም ሀጢያታቸው በዝቶ ልባቸው ከፍቶ ታናሽ ወደ ሆኖአቸው ሌሎች ወገኖች አሳልፎ ሰጥቶአቸው ለዘመናት እንዲኖሩ ግፍን እንዲጨልጡአት ወስኖ በምርኮ በግብፅ ምድር ሲኖሩ የበደል ጠል በላያቸው ረሰረሰና ክፉኛ ተጎዱ። Ethiopians in Saudi
የቀኑ መምሸት የለሊቱ ንጊት ለእነሱ ምንም ማለት ሳይሆን እንደው ግፍ ብቻ እንደው መኖር ብቻ ሆኖ ምሬት አንጀታቸውን ቢበጥሰው ፤ግፉ ቢገፈግፋቸው ዛሬን አሜን የማይሉት የዛን ለታ የነበረ፤ እኛ አሁን ድረስ የምናወሳው የአህዛብ አገር የክፋት ዜማ ጆሮአቸውን ቢሰቀው ፤የፈርኦን ልብ ደንድኖ ስጋቸውን እንደ ላስቲክ ቢልጠው ፤ጀርባቸውን ጅራፉ ቢመልጠው ለቀንበሩ አቅም ቢያጡ አሜንታ ብቻ ኑሮ መረራቸው። በልመና የአምላክን ደጃፍ በእንባቸው እንዳያርሱ ግዜው ገና ነበርና ፀሎታቸው እንዳያርግ ሰማይ በደመና አጎበር ተዘግቶ የገዛ እንባቸው እና በግፍ የሚፈነጥቀው ላባቸው ፤የገዛ ሰውነታቸውን ከማራስ ያለፈ አልነበረም።ከዚህ ሁሉ በሓላ ግን መዶሻ የሆነው የራሔል እንባ ከሰማየ ሰማያት ተወርውሮ የንጉሰ ንግስቱን የእግዚሐብሔርን እግር አረጠበና እግዚያአብሔር ወደምድር አየ።በዚህ ሁሉ ምሃል እግዚያብሔር ቀኑ ገና መሆኑን አለ እንጂ ስራውን አለቆመም ነበርና ሙሴን ለጦር እቃነት አዘጋጅቶ ሲያበቃ ነገሩ እንዲህ ሆነ።በፈርኦን ፊት ግርማ መጎስ እየሆነው ፤አሮንን አንደበት አድርጎ ጉዞ ወደ ፈርኦንና ወደግዛቱ ተጀመረ።
በርግጥም እግዚያአብሔር አየ።ፈርኦን እስራኤልን እየቀዳ ሲያጠጣቸው ከነበረው መከራ ላይ ለራሱ ከተጨለፈለት በሓላ ሁሉ አብቅቶ ጉዞ ወዳ እስራኤል ሆነ። በዚህን ግዜ ሙሴ አብሮ ነበር ።የታሪካቸው መጀመሪያ ከግብፀና ከግብፃዊያን ውጪ ሆኖ በዚዩህ ኤርትራን ሲያቋርጡ ያልቆረጠለት ፈርኦን ቢከተላቸው ሙሴ አድነን አሉ ።ጩኸታቸው የጋሸበባቸውና ለግፍ እድል ዳግም የተሰጡ እስኪመስላቸው ተላቀሱ። ሙሴ አድነን አድነን ።አዎ ያንግዜም ሙሴ ከነሱ ጋር ነበርና ህዝቡም ሁሉ ተሻገሩ። ፈርኦንም ከነሰራዊቱ ሰጠመ፤ አዎ ጉዞ በአንድነት ከሙሴ ጋር ወደተስፋይቱ ምድር። 600 መቶ ሺ ሠው በአንድ ሰው ምሪት።ግና የሰው ልጅ ከአፈር በመሰራቱ ቆሻሻ አያጣውምና ዳግም በደሉ እግዚያአብሔርን አስቀይመው በዚህም አምላካቸው ሲቆጣ ሙሴ ነበር። በነገድ በተከፋፈሉና እኛ እናንተ በተባበሉ ግዜ ሙሴ ነበር ።የጣኦት አምልኮ በነበረና እግዚያብአሔርን የመገዳደር ክፋት በተጠናወታቸው ግዜ ፤ በአምልኮ ባእድ አስቸገረው ሀጢያታቸው ሲያስመርር ሙሴ ነበር ።
በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ እግዚያአብሔር አዝኖ ነበርና የ40 ቀኑ መንገድ ወደ 40 አመት ተለውጦ፤ ከሰማይ ለሚወርድላቸው መና ጥያቄ ሲኖራቸው ጥጋብ እያናፈላቸው ፤የግብፅን ሽንኩርት ፤ከሰማይ ከሚወርድ መና በረከት የተሻለ እንደሆነ ፤ሲናገሩ ሙሴ እየሰማቸው እርሱ አብሮ ነበር።በሙሴ ፀሎት የእግዚያብሔር ሃይል ከጠላት እጅ አድኖአቸው ባሉበትና የጉዞ ምርጫቸው ተሳክቶ እነሱ ግን መሰናክል ሆነው ራሳቸውን ለከፋ ክፋት በጣሉበት ግዜ ሁሉ እግዚያአብሔር አስኪመረርና “ይህን ህዝብ ላጥፋውና በሌላ ህዝብ ላይ እሾምሃለሁ ቢለው እነሱን ከምታጠፋ እኔን ከህይወት መዝገብ ፋቀኝ” ብሎ ሙሴ ከአምላኩ ጋር አታካራ በገጠመ ግዜ እነሱም ነበሩ፤ ሙሴም ነበር ።በርሃብና በእርዛት ፤በስደትና በመከፋፈል ብሎም አምልኮ በተበላሸና የእግዚአብሔር ካህናት በበደሉና እግዚአብሔር ባዘነ ግዜ ሁሉ ሙሴ ነበር ።እርግጥ ነው ወደተስፋይቱ ምድር እያሱና ካሌብ ቢደርሱም ለህዝቡ አንድ ሆኖ የኤርትራን ባህር ለመሻገር ሙሴ ስላኖራቸው ኖረው ነበር ።ዛሬስ ሙሴ ለእኛ ወዴት ነህ ? ይህ የእኛ ጥያቄ ነው።
በጎጥና በጎሳ በተከፋፈልንበት ፤በሓይማኖት በተጋጨንበት ፤የገዢዎች ቀንበር ትከሻችንን በላጠን ግዜ ካህናተ እግዚያአብሔር መንገድ ስተው ፤በደል በተዛመዳቸው ግዜ ሙሴ ቢኖረን ኖሮ ትውልድ ገበናው ተገልጦ የሃጢያት ስብራት አሰነክሶት ሃሞቱን አፍሶ ጠጥቶ ለምን እንዴት መቼ ማለት ረስቶ ሃገር ብቻዋን ስትቀር ፤የእድሜ ጣራ ሳይገድበን ትልቅ ትንሽ አስተሳሰባችን መሬትን በእኩል ረግጦ፤የህሊና ጎጆአችን ሲያዘምብን ፤እኛ አፍርሰን ባእድን እንዲሰሩልን ስንማፀን ለምን? ከዚህ ተመለስ፤ የሚለን ሙሴ ቢኖረን እንዴታ።ይኼም ብቻ ባይሆን ፤ ከሆነው ሁሉ ጠቂቱን ገልፀን ለመጨረስ ያህል እንጂ ውሃ የበላውን አንድነታችንን በወረቀት ደረት ላይ ብቻ ሰፈሮ ግርጊዳ የሚቧጥጠው ማንነታችንን ባጣናው ግዜ ሙሴ ቢኖረን ኖሮ።ህፃናት ባዝራ ከድንጉላ ለመኖር ኑሮአቸው ሰልችቶአቸው ፤ግና ሞት እንደ ወላፈን ወደሚለበልባቸው እሳት ወደሆነው ስደት ሲወጡ ፤የእናት እንጎቻ እንኳን በቅጡ ተቆርሳ ሳትጎረሳቸው ፤ጨክነው ሔድው ከባህር ሲገበና ሲሞቱ በባኢዳን ሐገር እንደ ውሻ ሲረገጡ ሙሴ ኖሮን ቢሆን አቤቱ እንዴታ ።በሆነው ሁሉ ሙሴ ቢኖረን ዘንዳ አቤቱ ሙሴ ወዴት አለህ? እንላለን።እኛም እነሱን ነንና እነሱም እኛን ነበሩና ።
ቸር ያገናኘን!!! 

zehabesha 

No comments:

Post a Comment