በሰከነ አእምሮ ማሰብ ካልቻልን ሁሌም አደጋ ላይ ነን፡፡ ለሰከነ አእምሮ ደግሞ ሁል ጊዜ ስለሕሊና
መኖርን ይጠይቃል፡፡ ሕሊናውን የሚክድ ግን ለእውነት ሳይሆን በውሸት፣ በአድርባይነት ወይም በሴረኝነት አልፎም በአረመኔነት ይኖራል፡፡
ሰው ባለወቀው ነገር ቢሳሳት ሕሊናው ነጻ እስከሆነ ድረስ ላጠፋው
ጥፋት ካሳም ይሁን ይቅርታ ለማድረግ አልጎደፈም፡፡ ሳያውቅ በማትፋቱ ቢያዝንም አንዴ ካወቀ በኋላ ጥፋቱን ባለመድገም ጥፋቱን ይበቀለዋል፡፡
ለሕሊናውም እርካታና ካሳ ይሆንለታል፡፡ እውነትን አውቀው ግን የካዷት ሕሊናቸው አንዴ ስለጎደፈ በጎ ነገርን ለማሰብ አእምሮአቸው
አይቻለውም፡፡ ሁሌም ክፉ የሆኑ መንገዶችን ሲገነባ ይኖራል፡፡ ውለታ፣ ሕዝብ፣ አገር፣ የመሳሰሉት ሁሉ ሕሊናቸው በበጎ ላልታነጸ
ሰዎች ምናቸውም አይደለም፡፡ ለግል ለሚሉት ጥቅማቸው መሳካት ሲሉ በሚሊዮን ሕዝብ ቢያልቅ አገር ቢፈርስ ታሪክና ማህበረሰብ ደብዛው
ቢጠፋ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ሰዎች በበጎ ሕሊና የሠሩት ታሪክ ለእነዚህ ሕሊናቸው ለመረቀዙት አደገኛ ወጥመድ ስለሚሆንባቸው የበጎ
አሳቢዎቹን ታሪክ ማርከስና ማውደም ተቀዳሚ ተግባራቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ጥሩ ጉልበት የሚሆናቸው የሰዎች እውነትን መዘንጋትና
በሌሎች ስብከት ስሜታዊ መሆን ነው፡፡ መሠሪዎች የሰዎችን ልጆች ለመሠሪ ዓላማቸው መሣካት የሞት ዕራት የሚጠቀሙበት
ዋነኛው አጋጣሚ የራሳቸው የሰዎች ልጆች ስሜተኝነትና እውነታን ለማየት አለመቻል ነው፡፡
ሰሞኑን አኖሌ በተባለ ቦታ ከመቶ ዓመት በፊት በታላቁ ምኒሊክ አገርን አንድ የማድረግ ሂደት በነበረ
ጦርነት የጡትና እጅ መቁረጥ ግፍ በምኒሊክ ዘመቻ ተፈጽሟል በሚል አንደ መታሰቢያ የተባለ ሐውልት በመቆሙ ምክነያት ብዙዎች እየተነጋገሩበት
ይገኛል፡፡ የተባለው ግፍ በዚያ ዘመን ሊሆኑ ከሚችሉ ክስተቶች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ከመገመት ያለፈ ግን የተጨበጠ መረጃ ሊገኝለት
የቻለ አይመስልም፡፡ ሐውልቱም ሲቆም አፈታሪክን መሠረት አድርጎ እንጂ ተጨባጭ መረጃን መሠረት አድርጎ አይደለም፡፡ ሐውልቱን ያቆሙት
መታሰቢያና አስተማሪ ቢሉትም ብዙዎች በተቃራኒው በሕዝብ መካከል ጥላቻን ለመፈጠር የቆመ ሐውልት ነው ሲሉ ይተቹታል፡፡ ይበልጠውን
ደግሞ ድርጊቱ ተፈጸመ ከተባለ ከመቶ ዓመት በኋላና የተረጋገጠም
መረጃ ባልተገኘበት ሁኔታ መሆኑ በእርግጥም ዓላማው ከበጎ ሕሊና የመጣ እንዳልሆነና ይህን ትውልድ ለመመረዝ የታሰበ እንደሆነ ተፈርጇል፡፡
እኔም ይህን ሐውልት የማየው የጥላቻ ምልክት እንጂ አስተማሪና መታሰቢያ እንደሆነ አይደለም፡፡
በአንድ
የራሴን አስተያየት ባስተላለፍኩበት ጽሑፌ ኦሮሞ ነኝ የሚለው ብዙው ሕዝብ በታላቁ ኢትዮጵያዊ ሚንሊክ
ላይ ያለው ጥላቻ ከምን የመጣ ነው? ሐውልቱን ጨምሮ ብዙ ነጥቦችን አንስቼ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ ኦሮሞ ነኝ የሚለው ሕዝብ (ይቅርታ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ
በብዙዎቻችን የአስተሳሰብ እንጂ የዘር ጉዳይ እንዳለሆን ላሳስብ እፈልጋለሁ) በምኒሊክ ታሪክ የነበረውን ድርሻ ጠቆም ማድረጌን እያስታወስኩ
ለዛሬ በተሸለ ላቀርበው ወደድኩ፡፡
ታላቁ ምኒሊክ ጥፋትም ይሁን ልማት ሠሩ ያለ ኦሮሞ ከተባለው ሕዝብ አልሠሩትም፡፡ በአገር መገንባቱም
ይሁን አገርን ከጠላት ወረራ ለመከላከል በተደረጉ ጦርነቶችም ሆኑ ሌሎች የታላቁ ምኒሊክ ታሪኮች ኦሮሞ ከተባለው ሕዝብ በላይ ድርሻ
አለኝ የሚል ሕዝብ እንዳለ አላውቀም፡፡ የታላቁ ሰው የታሪክ ዘመን
ደግሞ ዛሬ ከየትኛው አገሪቱ ካለፈችበት ዘመናት ሁሉ ትውልድና ሕዝብን የሚያኮራ ተግባራት የተሠሩበት ዘመን ለመሆኑ ልንክደው የምንችለው
አይደለም፡፡ ይህ ታሪክ ግን እውነትን ለማይወዱ ሕሊናቸውን ለካዱ
የግል ጥማቸውን ለማርካት ብቻ ለሚኖሩ ታላቅ ጋሬጣ ስለሆነባቸው ይህን
ለዜጎች ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ አልፎም የሌሎች የግፍ አገዛዝ በተጫናቸው የአለም ሕዝብ ሁሉ እንደ ተምሳሌት የሚታየውን
ታሪክ ማራከስ ከተቻለ ማጥፋት ተቀዳሚ ተግባራቸው ነው፡፡
ምኒሊክ
አማራ ከተባለው ሕዝብ እንደሆኑ ቢታመንም አማራ የተባለው ሕዝብ በምኒሊክ ታሪክ የነበረው ድርሻ ከኦሮሞ ከተባለው ሕዝብ ጋር ሊወዳደር
የሚችል አይመስለኝም፡፡ አኖሌም በሉት፣ ችለንቆ ወይም ወላየታ፣ ወይም ለአላም ሳይቀር አድስ ምዕራፍን በማሳየት የሚታወቀው አድዋ
በምኒሊክ በኩለ ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ በበላይነት የተሳተፈባቸው ጦርነቶች እንደሆኑ እረዳለሁ፡፡ በእርግጥም የምኒሊክ የጦር መሪዎች
በብዛት ኦሮሞ ከተባለው ሕዝብ እንደሆኑ ታሪክም መዝግቦት የሚገን እውነት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በጦርነቶቹ የነበሩ ድሎችም ሆኑ
ጥፋቶች ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ በበላይነት የተሳተፈባቸው ናቸው፡፡ ኦሮሞ በተባለው አርሲ ሕዝብ አኖሌ ላይ ዛሬ ሐውልት የቆመለት
ግፍ ደረሰ ከተባለ ደግሞ ተጠያቂው በበላይነት ኦሮሞ ከተባለው ሕዝብ የነበረው የምኒሊክ ሠራዊት ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ ኦሮሞ የተባለው
ሕዝብ ሌላ ቦታ ያለ ኦሮሞ በተባለ ወንደሙ ላይ የፈጸመው ግፍ ነው፡፡ ሆኖም ከሆነ የገደለው ባሌ የሞተው ወንድሜ ብለን ከማዘን
በቀር የበቀል ሐውልት ልናቆምለት ባልተገባን ነበር፡፡
ምኒሊክ
ጦርነቶችን ሁሉ ተገደው እንጂ ወደው በማን አለብኝነት የደሩባቸው ጊዜ አልነበረም፡፡ አገርን አንድ በማድረግ ሒደት ብዙዎችን ያለጦርነት
ወደ አንድነት ያመጡ ሲሆን አልፎ አልፎ በነበሩ የአካባቢ መሪዎች ለሠላም እምቢ ማለት ወደ ጦርነት አምርቷቸዋል፡፡ አኖሌ፣ ጨለንቆና
ወላይታ ጉልተው በታሪክ የተጠቀሱት ናቸው፡፡ ምኒሊክ በጦርነቶቹ ሁሉ ድል አድራጊ ቢሆኑም በጦርነቶቹ በነበሩ ጥፋቶች ይልቁንም የሰዎች
ሕወት መጥፋት እጅግ ያዝኑ እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ በጦርነት ምክነያት ሕዝቡ በመጎዳቱ ካዘኑባቸው ጦርነቶች አንዱ ደግሞ የአርሲው
አኖሌ ጦርነት እንደነበር በታሪክ ተጠቅሷል፡፡ በወቅቱ በነበሩ ልማዶች አሸንፎ የገባ ጦር (ወታደር) የተሸነፋን ሕዝቡና ንብረቱን
መማረክ እና ለራሱ እንደሎሌ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ይህን ግን በአርሲ ሕዝብ ላይ ወታደራቸው እንዳያደርገው እንዲህ ሲሉ ነበር
ያስጠነቀቁት "ወንድምህ የአርሲ ሕዝብ በአላወቀው ነገር በዚህ ጦርነት እጅጉን ተጎዳ አሁን ግን ወንድምህን የአርሲን ሕዝብ
እንደሎሌህ ልታደርገው አልተፈቀደልህም" ነበር ያሉት፡፡
ዛሬ
እየተነሳ ያለው ሐርካ ሙራ እና ሐርማ ሙራ እንደ አንድ የጦርነት ክፉ ውጤት ተከስቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሆነም ደግሞ ከምኒሊክ እውቅና
ውጭ በአንዳንድ ወታደሮች የተደረገ ግፍ እንጂ በምኒሊክ ትዕዛዝ እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ ምኒሊክ በባሕሪያቸው እንኳንስ የሴትን ልጅ
ጡት መቁረጥ ቀርቶ በየትኛው መልኩ ሰው እንዲጎዳ የሚፈልጉ ሰው አይደሉም፡፡ ጦርነቶቻቸውም የዓላማ እንጂ የትኛውንም ሕዝብ ይሁን
ግለሰብ ለመጉዳት ታስቦ አልነበረም፡፡ ከውጊያ ድል በኋላም በተዋጓቸው ላይ የበቀል ሳይሆን የፍቀር አቀባበል ነበር ያደርጉላቸው
የነበረው፡፡ ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ምኒሊክ የጀግና ትክክለኛ
ባሕሪ ያላቸው ናቸው፡፡ ጀግና የዓላማ እንጂ የግል ጠላት የለውም፡፡ በአኖሌም ለሕዝቡ ያደረጉት ይህንኑ ነው፡፡ ጀግና በጀግንነት
እንደ ጠላት የተዋጋውን ያደንቃል፣ ያከብራልም፡፡ ድል ቢያደርገው እንኳን ክብሩን አይነፍገውም፡፡ ድል ሲያደርግ ስለ አላማው መሳካት
ይደሰታል እንጂ ስለጠላት ሞት ደስ አይለውም፡፡ እንዲህ ያለ ጀግና ደግሞ በጦርነት ድልን እንጂ ሽንፈትን የማየት ዕድሉ በጣም አነስተኛ
ነው፡፡ ይህ የምኒሊክ ልዩ መገለጫ ነበር፡፡
እንግዲህ
ምኒሊክ እንዲህ ባለ የጀግንነት ባሕሪያቸው ለባሕሪያቸውና ለዓላማቸው ከተስማሟቸው ጀግኖች ሠራዊታቸው ጋር በዘመናቸው ያተቀዳጇቸውን
ሁሉ ድሎች ለታሪክ አስመዝግበዋል፡፡ ምኒሊክ በስኬታማነታቸው አንድ ሰው በእድሜው ሊሰራው ከሚችለው በላይ እንደሆነ አረዳለሁ፡፡
ማንም አይደለም በኢትዮጵያ በዓለም ላይ እንኳን በአለፉት 500ና ከዚይም በሚበልጥ ዘመናት እንደምኒሊክ ውጤታማ የሆነ መሪ አለ
ብዬ አላምንም፡፡ ካለ የታሪክ ምሁራን አከሌ የሚባል የዚህ አገር መሪ ቢሉ በአስመዘገቧቸው ውጤቶች ልናወዳደራቸው እንችላለን፡፡
ምኒሊክ የደሀ አገር መሪ ባይሆኑ ኖሮ በተባበሩት መንግስታት ሳይቀር መታሰቢያ የሚቆምላቸው ሰው ናቸው፡፡ ተምሳሌትነታቸው ለሕዝብ
ሁሉ ነበርና፡፡ በተለይም የቀኝ የቀኝ ገዥዎችን አይነኬነትና አይበገሬተን ባመከነው ድላቸው ብቻ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአለም ምሳሌ
የሚሆኑ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ታሪክና ክብር ደግሞ ኦሮሞ በተባለው ሕዝብ የበላይነት የተከናወነ ነው፡፡ እኔ ጎደሬና ጎጃሜ
ምኒሊክ ዘመን ጉልህ ድርሻ ነበራቸው የሚል ታሪክ አላውቅም፡፡ አማራ የተባለው ሕዝብ ድርሻ በምኒሊክ ታሪክ ትልቅ ነበር ከተባለ
ደግሞ በየትኛውም መሥፈርት ኦሮሞ የተባለውን ያህል ድርሻ የለውም፡፡
ችግሩ
የሚጀምረውና ዛሬም ያለው ብዙው ትውልድ የታላቁን ሰው ታሪክ ሊያንኳስ የሚሞክረው የምኒሊክ ታሪክ በአብዛኛው የሸዋ ሕዝብ የበላይነት
መሆኑ ነው፡፡ የምኒሊክ አጋር የነበረ ኦሮሞም በሉት አማራ በብዛት ከሸዋ መሆኑ ዛሬ ስልጣን ላይ ላሉት ወለጋም በሉት አርሲ፣ ጎጃሜም
በሉት ጎንደሬ እንዲሁም ትግሬ እንደራስ ታሪክ ሊታይ አልቻለም፡፡ ትግሬው አጼ ዮሐንስን እንጂ ምኒሊክን ታላቅ ማድረግ አይፈልግም፡፡
ሁለቱም ለእኔ የኢትዮጵያ መሪዎች ናቸው አከብራቸዋለሁ፡፡ ምኒሊክን ግን እኔ በታሪክ ከማውቃቸው ሁሉ የላቀ አደርጋለሁ፡፡ ጎጃሜና
ጎንደሬውም ለሸዋ ነጋሲያን የእኔ ለማለት ቅር ይለዋል፣ ወለጋና አርሲው የአማራ ነጉስ በማለት እራሱን ከታሪክ ባለቤትነት ለማራቅ
ጎራ ይፈጥራል፡፡ ሸዋ ዛሬ አንገት ደፊ ሆኗል፡፡ ኦሮሞ ሸዌው የጀግናው የጎበና ዳጬ ሥም በክብር ፋንታ ስድብ ሆኖበት አፍሯል፡፡
ተሳዳቢዎቹ ታሪክን ጥላሸት በመቀባት በትውልድ የራስ መተማመን እንዳይኖር እንቅልፍ አጥተው ነው የሚሰሩት፡፡ አማራው ሸዌ እንደዛው
ለአገር ያበረከተው አሰተዋጽዖ ከስድብ ተቆጥሮበት ነፍጠኛ ጨቋኝ እየተባለ ተገፍቷል፡፡ እውነታው ግን የሸዋ ሕዝብ (ኦሮሞም በሉት
አማራ) ዛሬ ላለችው ኢትዮጵያ አጥንትና ደሙን ገበረላት እንጂ ትምህርት እንኳን አዲስ አበባ ዙሪያ ሰፍሮ እንደሌሎች አልደረሰውም፡፡
ይህ ሕዝብ ግን የሚኖረበት ቦታ በፈጠረለት አጋጣሚም ሊሆን ይችላል ከሌሎቹ በተሻለ ከዘረኝነት ልክፍት ነጻ ነው፡፡
በአጠቃላይ
ሲታይ ለታሪክ ብክለትም ሆነ መስተካካል ዋነውን ሚና የሚጫወቱት ምሁራንና ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ
ሕዝብ የራሱን ታሪክ የሎሎች ነው ተብሎ በምሁራንና በፖለተከኞች ስለሚሰበከው ለራሱ ታሪክ ባለቤት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ
የታወቀ ታሪክ አለው ተብሎ ቢነገር እንደ አገው ሕዝብ ታሪክ ያለው ሕዝብ ለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ ዛሬ አክሱም፣ ላልበላና ብዙ የሰሜን
ኢትዮጵያ የሰውልጅ ጥንታዊ ጥበቦችን የሚያሳዩ ስነ ሕንጻዎች አማራ ወይም ትግሬ የተባለው ሕዝብ የገነባቸው ሳይሆኑ ጥንታዊያኖቹ
አገዎች ያበረከቷቸው ናቸው፡፡ ዛሬ ግን ይህ ህዝብ የእነዚህ ድንቅ ሥራዎች ባለቤት እንደሆነ ምን ያህል እንደሚያውቅ አላውቅም፡፡ ይልቁንም እነዚህ
ሥራዎች ለልሎች ወንድሞቹ ይበልጠውን ንብረት ሆነዋል፡፡ አገሪቱንም
ወክለው የአገር ኩራትና ድምቀቶች ሆነው እናያቸዋለን፡፡ በተመሳሳይ የአገር ክብርና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታና የብልጽግናም ፈር
ቀዳጅ የነበረው የምኒሊክ ዘመን ታሪክ ኦሮሞ ከተባለው ሕዝብ በላይ የተሳተፈበት ባይኖርም ታሪኩ ግን መሪው አማራ ነው ተብሎ ስለታመነ
የአማራ ተብዬው እንጂ የኦሮሞ ታሪክ እንደሆነ ለማሰብ ብዙዎቻችን እድሉን አጥተናል፡፡ ይልቁንም ይህን ታሪክ ኦሮሞ በተባለው ሕዝብ
እንደ አንድ የታሪክ ኪሳራ ተደርጎ እንዲታይ ተደርጓል፡፡ በአገርን አንድ ማድረግ የነበረው ተሳትፎ ቢዘነጋ እንኳን በቀጭ ግዛት
ለነበሩ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ነጋሪትን ያስተጋባው አደዋ እውነታ ከየትኛውም ሕዝብ በላይ ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ የፈመው
ታሪካዊ ገድል እንጂ አደዋ ትግራይ ስለሆነ የትግራይ ሕዝብ የበላይነቱን
ሚና የተጫወተበት አይደለም፡፡ ለዚህ የራሱ ለሆነው ታሪክ ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ ባይተዋርነት ሲሰማውና ብዙዎችም በጥላቻ ሳይቀር
ሲመለከቱት ሌሎች የእኔ ብለው በየአመቱ ያከብሩታል፡፡
ለዚህ
ሁሉ ደግሞ ኦሮሞ የተባለውን ሕዝብ ከኢትዮጵያነቱና ከታሪክ ባለድርሻነቱ ነጥለው ለራሳቸው መጠቀሚያ ሊያደርጉት በሚፈልጉ በእርግጥም
እያደረጉትም ባሉ የዚሁ ሕዝብ ነን ብለው የኦሮሞ ታሪክ አዋቂ ምሁራንና ፖለቲከኞች ነን ባዮች የጥቅም ጥመኞች የረጩት መርዝ ዋነኛ
ምክነያት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ኦሮሞ የተባለውን ሕዝብ በቀድሞ መንግስታት ተበዳይ ነህና ነጻ እናወጣሀለን
በሚል ሁሉም መሞከሪያ ሲያደርገው እናያለን፡፡ አሳዛኙ ግን ሆሉም ሕዝቡን በተበከለ ታሪክ እየመረዙ ከሌሎች ጋር በሠላም እንዳይኖር
ከማድረጋቸውም በላይ ሁል ጊዜ አመጽ አነሳሽ እያደረጉ ለጥይትና ለብዙ እንግልት ዳርገውታል፡፡ ሁላችንም ገሀድ የምናውቀው ሀቅ በመጀመሪያዎቹ
የኢሕዴግ አመታት ኦሮሞ የተባለውን እወክላለሁ የሚለው ኦነግ የተባለው ድርጅት መሪዎች በቦሌ በኩል በሠላም የተሻለ ኑሮ የኖሩበታል
ተብሎ ወደታመነ አገር ሲሸኙ ደሀው ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ ልጅ ኦነግ ነህ እየተባለ ሲገደልና ሲማቅቅ ኖረ፡፡ ዛሬም ድረስ ይህ ችግር
አለ፡፡ መሪዎቹ የነበሩት ግን አሁንም የውጪው አገር ሲበቃቸው በሠላም
ወደ አገራቸው ተመልሰው በመረጡት ቦታ እየኖሩ ነው፡፡ እስኪ ይህ እውነት አይደለም? በሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ ልጆች
ግን ኦነግ ተብለው የት እንደገቡ እንኳን አይታወቅም፡፡ ኦነግ ተብዬውም ዓላማው ሕዝብን ነጻ ማውጣት ሳይሆን እንዲህ የሕዝብን ልጆች
በሌላው ላይ ጥላቻ እንዲያሳድሩ ነበር፡፡ በዚህ ሂደት የመመጣው ጥፋት ለመሪ ተብዬዎቹ ምናቸውም አልነበረም፡፡ እነሱ ከጅምሩ የግል
ጥቅም እንጂ የሕዝብ ነገር መቼ ገዷቸው፡፡
ኦነግ
ከተባለውም ውጭ ያሉት ዛሬ ኦሮሚያ የተባለውን ክልል የሚያስተዳደረወን መሪዎች ጨምሮ ኦሮሞ ለተባለው ሕዝብ ምንም ራዕይ ያላቸው
አደሉም፡፡ ሕዝቡን ከሌላው ሕዝብ ጋር በሠላም እንዳየኖር በተፈጠረውም ባልተፈጠረውም ታሪክ ይበክሉታል፡፡ ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ
የቱንም ያህል በአገሪቱ ትልቁን ቁጥር የያዘ ቢሆንም በአገር ውስጥ በሚኖረው ተጽዕኖ ውሱን እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በልማቱም ቢሆን
ከሌሎች ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ ሕዝቡ ስለ ልማትና ዕድገት እንዲያስብ ሳይሆን አሁን ያለው ትውልድ በልተወለደበት ዘመን ስለተፈጠሩም
ስላልተፈጠሩም ታሪክና ተረቶች እየተሰበከ ከሌሎች ጋር በሠላም እንደይኖር ሆኗል፡፡ ሀያ ምናምን አመት ስለ አማራ የተባለው ሕዝብ
ጨቋኝነት ተነገረው፡፡ ግን ዛሬ እንመረዋለን የሚሉት የሰጡትን ነጻነት አላየንም፡፡ ይልቁንም ከሌሎች በሠላም እንዳይኖር ሌላ የተመረዘ
በጥላቻ ያደገ አዲስ ትውልድ በመፈጠሩ ዛሬ በየ ዩኒቨርሲቲውና በየትምህርት ተቋሙ የብሔረሰብ ጠብ አንሽ ሆኖ እናየዋለን፡፡
በአዲስ
አድማስ ስለአኖሌ አስተያየታቸውን ከሰጡት የኦሮሞ ሕዝብ ተወላጅ ነን የሚሉት ምሁራን በአብዛኞቹቹ የአኖሌን ሐውልት መቆም እንደ
መታሰቢያና አስተማሪ የሚያዩት ናቸው፡፡ ታሪኩ ነበር ወይ ተብለው ሲጠየቁ ግን የሰጡት ምላሽ አሳዛኝ ነበር፡፡ አገሪቱን በርዕሰ
ብሔርነት የመሩት ዶ/ር ነጋሶ በሐውልቱ መቆም ተስማምተው ስለታሪኩ እውነታነት ግን ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው ይመክራሉ፡፡
እንደሳቸው አባባል አፈታሪክም ከታሪክ መረጃዎች አንዱ ስለሆነ የቱንም ያህል ተጨማሪ የማረጋገጫ ጥናት ቢያስፈልገውም 20 ሚሊየን
ብር ያወጣ ሐውልት ማቆም ተገቢ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሐውልቱን በአስተማሪነቱም በሉት በመታሰቢያነቱ እንውሰደው የደረግ በሚሉት ተጨማሪ
ጥናት ይህ ታሪክ ውሸት ሆኖስ ቢገኝ ምን ለማስተማር ወይም ማንን ለማሰብ ቆመ፡፡ ሌላኛው የኦፌዴን መሪ እንደነበሩ የምናውቃቸው
በአለፉት መንግስታት ጉልህ ሚና የነበራቸው አቶ ቡልቻ ደግሞ ሌላ ከምሁር የማይጠበቅ አስተያየት ሲሰጡ ተነበዋል፡፡ ለእሳቸው ታሪኩ
እውነት መሆኑ ማረጋገጫቸው አንድ የዩኒቨርሲቲ የነበረ ሰው ስለነገራቸው ነው፡፡ ምን ማለት ነው? የታሪክ ማረጋገጫ ማለት ዛሬስ
ብሎ ብሎ እከሌ አለኝ እከሌ አላለም ሆነ እንዴ? ይልቁንም እሳቸው በእድሜያቸው ለዚህ ታሪክ ቅርብ ስለሚሆኑ ከወላጆቻቸው በቀጥታ
ሊሰሙት በቻሉ የተሻለ መረጃ በሆነ፡፡ አቶ ቡልቻ በአለፉት ሁለት መንግስታት ሊያውም ትልልቅ በተባለ ቦታ ማገልገላቸውና በእድሜያቸውም
የገኙት ልምድ ለሕዝብ የሚበጅ ጥሩ ዕድል ነው ብዬ ባምንም ብዙ ጊዜ እሳቸው ለራሳቸው ተደማጭ እሆናለሁ ብለው የሚያስቡትን እንጂ
የሕሊናቸውን የሚናገሩ አይመስሉኝም፡፡ በአለፉት መንግስታት ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ ተበድሏል ሲሉም ምን ማለታቸው እንደሆነ አይገባኝም፡፡
ልብ በሉ እኔ አልተበደለም የሚል መከራከሪያ ለማቅረብ ሳይሆን የሰውዬውን አካሄድ እክል ለመጠቆም ነው፡፡ አቶ ቡልቻ የሚያምርባቸው
ዛሬ እንደ ድልድይ ሆነው የኦሮሞ የተባለውን ሕዝብ ከሌላው ጋር አንድ የሚሆንበት እድል ማመቻቸትና በሠላም እንዲኖር ማድረግ፣ ታሪክ
የሚበክሉትንም በገሰጽ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ኦሮሞ የተባለውን ሕዝብ መጠቀሚያ ለማድረግ እንጂ ለሕዝቡ ተቆርቋሪ
የሆኑ ምሁራንና ፖለቲከኞች ልናይ አልቻልንም፡፡ ይልቁንም ሕዝቡን ከራሱ ታሪክና ከሌሎች እየለያዩት ማንነቱን እንዲምታታበት፣ ሌሎችንም
እንዲጠላና ጽንፈኛ እንዲሆን ብዙ መከሩት፡፡
በመጨረሻ
ሕዝቡን የራሱን ታሪክ የሌሎች እንደሆነ አድርጋችሁ ባዶ አታስቀሩት፡፡ የምኒሊክ ታሪክ ከሌሎች በጎላ ኦሮሞ የተባለውን ሕዝብ ያሳተፈ
ቢሆንም አነሰም በዛም በሌሎች የታሪክ ሂደቶች ሁሉ ይህ ሕዝብ በክፉውም በበጎውም ተሳታፊ ነበር፡፡ ሁሉም ያስብበት እውን የምኒሊክ
ታሪክ የማን ነው?!
አመሰግናለሁ
የታላቋ
ቀን ልጅ ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment