Friday, May 9, 2014

ገና ብዙ ያልከፈልንው እዳ አለብን! ማስተዋላችንን ያመከነው ዘረኝነት



ድሮ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ አመፅ ተነሳ ከተባለ ምክነያቱ ሁሉም አንድ የሆነበት ተማሪው ሁሉ ስለ ሕዝብ ሆኖ የሕዝብ በደልን ለመቃወም ወይም ደግሞ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የገጠማቸውን የጋራ በደል ለመቃወም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች ረበሹ ከተባለ ያው ከዘረኝነት ችግር ያለፈ አይሆንም፡፡ በተለይም ደግሞ አማራ፣ኦሮሞና ትግሬ ነን ብለው የሚያምኑ ተማሪዎች ሁሌም ለትምህርት ተቋማቱ ሠላም መደፍረስ ምክነያት ናቸው፡፡ብዙሱ ጊዜ ደግሞ ችግሩ ኦሮሞ ነን ብለው የሚያምኑት አማራ ወይም ትግሬ ብለው ራሳቸውን ከመደቡት ጋር በሚኖር ግጭት ነው፡፡ ይሄው ዛሬ ከታች ጀምረን አንተ ኦሮሞ፣ አማራ….ወዘተ እያልን ያሳደግናቸው ናቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆኑት፡፡ ይቀጥላል እነዚሁ እየተመረቁ ወደ ሥራ ዓለሙም እየገቡ ነው፡፡ እንግዲህ ሕዝብንም ለማስተዳደር እነዚሁ እየተቀላቀሉ ነው፡፡ በሌላው ጥላቻንና በቀል የዳበረ አእምሮ እንዴት ሕዝብ የተባለውን ሊያገለግል ይችላል፡፡ ብዙዎች ዘረኝነትን ለአፋቸው ሲያወግዙ እንሰማለን ግን ዋና የዘረኝነቱ አስተሳሰብ ሥር እንዲሰድ በተግባር የሚያግዙት እነዚሁ አውጋዦች ነን የሚሉት ናቸው፡፡
የሌሎቹ የአገሪቱን ማህበረሰብ እንዳለ ሆኖ ከላይ የጠቀስቸው ብሔር ተብዬዎች በአገሪቱ ውስጥ ካላቸው ተጽኖ ፈፃሪነት አንጻር ትልቁን ድርሻ የያዙ ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ ኦሮሞ የተባለው በሕዝብ ብዛትም በቆዳ ስፋትም አንጻር ሲታይ ግዙፍ ድርሻ አለው፡፡ ከላይ እንደ ጠቆምኩት ትግሬና አማራ ተብዬዎቹ ብዙም አይጋጩም፡፡ ኦሮሞ ተብዬው ግን ከሁለቱም ይጋጫል፡፡ ምክነያቱም በብዙዎች ዘንድ ባለው አስተሳሰብ ኦሮሞ ተብዬው ኩሽቲክ ነው ተብሏል አማራና ትግሬ ተብዬዎቹ ደግሞ ሴሜቲክ ናቸው ተብሏል፡፡ በቃ መሠረታዊ የዘር ማንነት ጥላቻው የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው፡፡ ግን አንዷም ብትሆን ስለማንነቷ መናገር የሚያስችላት መረጃ የላትም ቋንቋ ከለያየው በስተቀር፡፡ አውቃለሁ ከደም ማንነት ቀጥሎ ቋንቋና ባሕል አንድን ሕዝብ እንደ ጎራ ለመመደብ መስፈርቶች ናቸው፡፡ የጎሳ ግጭትም በሌሎችም አለ፡፡ የእኛ ግን ራሳችንን እንኳን ለይተን ባለወቅንበት ሁኔታ አንዱ ለሌላው ጠላቱ ሲሆን ነው፡፡ ማንነው ኩሽ ማነው ሴም?? ሁሉም አበሻ (ቅልቅል) ከመሆኑ በቀር ማንን ከማን በገጽ እንለየዋለን! አንዳንዶቻችን እውንም በምናውቀው መረጃ ብዙ ሕዝብን የሚወክል ደም አለን፡፡ ማን ነህ ብንባል ግን የአንዱን የዘመኑን ክፍፍሎች እንጠራለን፡፡ አንድ ከዚህ በፊት አንስቼው የነበረውን ቁም ነገር አዘል የአንዲት ሴት ንግግር ላንሳና ወደ ዋናው ጉዳዬ ልግባ፡፡ አንዷ ኢትዮጵያዊ (ከእነ አያቷ መጥራት ማንነቷን ስለሚያሳወቅ የመጀመሪያ ስሟን  ቀይሬዎለሁ የአባትና የአያቷ እንዳለ ነው) ሥሟ ሠላማዊት (ተቀይሯል) ደበላ ኪሮስ ነው፡፡ አንድ መስሪያቤት ልትቀጠር ትሄድና ብሔረሰብ ተብላ ትጠየቃለች፡፡ እኔ ብሔረሰብ የለኝም ብላ ትናገራለች፡፡ ጠያቂው የግድ ያስፈልጋል ይላታል፡፡ የእንጀራ ነገር ሆኖባት አማራ ትለዋለች፡፡ ጠያቂው ደግሞ መስማት ያልፈለገው ነበርና በንዴት ደበላ ብሎ አማራ አለ? ይላታል፡፡ አሷም ነገሩ አናዷት ነበርና  ሰውዬው እንድትልለት የፈለገውን ስላወቀች ኪሮስ ብሎ ኦሮሞ አለ? ብላው በንዴት ቢሮውን ለቃለት ወጥታለች፡፡ ይህ ብዙዎቻችንን ማንንም የማንወክለውን የሚገጥመን ነው፡፡
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ለምን ለዜጎች መጥፋት ምክነያት ይሆናል? አዲስ አበባ ለመልካም ብትሰፋ የሁላችንም መስፋቷ ደግሞ ሌሎች ወገኖቻችንን የሚጎዳ ከሆነም ችግሩ የሁላችንም ሊሆን በቻለ ነበር፡፡ አለመታደል ሆነና ኦሮሞ ነኝ የሚለው ሕዝብ አዲስ አበባን የኔነች ባይ ነው፡፡ በሕዝብ ብዛትም ሆነ አዲስ አበባ ባላት ንብረት ተቋዳሽነቱ ግን ኦሮሞ ነኝ የሚለው ሕዝብ ድርሻው ከሌሎች ቢያንስ እንጂ አይበልጥም፡፡ አዲስ አበባ ዋና ከተማም እንደመሆኗ የሁሉም እንጂ ኦሮሞ ነኝ ለሚለው የተለየች ልትሆን ባልተገባት፡፡ አሁን ሁሉንም እንደወረደ መናገር አፈልጋለሁ፡፡ እያድበሰበስን ያለፍንው ሁሉ እየቆየ ጠንቅ ሆኖብናል እና፡፡ ሲጀምር ለእንደኔ ያለው አሮሞነትም ይሁን ሌላ መሆን የአመለካከት ካለሆነ የደም ማንነት አይደለም፡፡ ሲቀጥል የደም ልዩነት ቢኖር እንኳን አንዱ ከአንዱ መኖር የግድ ይላልና እኔ እንጂ አንተ ድርሻ የለህም ማለት አለመብሰል ነው፡፡ ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ አስተዳደር ኦሮሞ ነኝ ብሎ ያመነውን ሕዝብ ሆን ብሎ እየተጠቀመበት እንደሆነ እንኳን ኦሮሞ ተብዬ ምሁራን ያስተዋሉት አይመስልም፡፡ ብዙ ጥፋቶች ምሁር ተብዬዎቹ ናቸውና ጠንሳሾቹ፡፡ ሕዝቡማ ባሕሉ አብሮ መኖር ነው፡፡ ዶሮን ሲያታልሏት አይነት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ድርሻ አለው እየተባለ ሲደለል ኖሯል፡፡ ኦሮሚያ ተብዬ ግን እንኳንስ በአዲስ አበባ ተጨማሪ ሚና ሊኖረው በራሱ ብቻ በሚተዳደረው ቀሪ ሰፊ ግዛቱ እንኳን ሚናው ያው ወደ ታች ከተመነዘረ የዘረኝነት ጠንቅ ያልተላቀቀ ነው፡፡  የኦሮሚያ መሪ ተብዬዎቹ ራሳቸው አዲስ አበባ ለመኖር ስላሰቡ ብቻ ምንም ከአዲስ አበባ ጋር ከሌላው በተለየ ግንኙነት የሌለውን ሕዝብ ፊንፊኔን ተነጠቅን ተነስ እያሉ ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ለአደጋ ሲዳርጉት እናያለን፡፡  ኦሮምያ ተብዬው የሕዝብና የአገር ልማት የሚሰማቸው ቢሆኑ ግን መቀመጫቸውንም ማንነታቸው እንኳን ተገልጦ በማይታይበት አዲስ አበባን ሙጭጭ ባላሉም ነበር፡፡ ዛሬ በብዙ ክልሎች ያሉ ከተሞች እያሸበረቁ ሲሄዱ የኦሮምያ ከተሞችም የተሻለ እድገት ባሳዩ ነበር፡፡ ለአጭር ጊዜ እንኳን አዳማ የኦሮምያ አስተዳደር በተዛወረ ጊዜ የከተማዋ እድገት ምን ያህል ተፋጥኖ እንደነበር እናውቃለን፡፡

አዲስ አበባ ስትሰፋ በዙሪያው ያሉ ነዋሪዎች በተለይም ደግሞ በመሬት የሚተዳደሩ ገበሬዎች ተጎጂ ናቸው ብሎ ማሰብ ትክክል ነው እውንም ሕዝብን ዋስትና በማይሰጥ መልኩ መስፋፋቱ ከተካሄደ፡፡ ከተማዋ ግን መስፋቷ የግድ የሚልበት ጊዜ አለ፡፡ ሥለ ሕዝብ የሚያስብ አስተዋይ ካለ ግን ከመስፋፋቱ ጋር በተያያዘ ሊጎዱ የሚችሉ ዜጎች ካሉ መንግስት እየኖሩት ካለው ኑሮ በላይ ዋስትና የሚሆናቸውን ነገር ማዘጋጀቱ ፍትሐዊ ነው፡፡ ጉዳዩ ግን ለተጎጂ ዜጎች ከማዘን ሳይሆን የራስን ጥቅም ያስቀራል ብሎ በማሰብ ስለሆነ የአዲስ አበባ ወደ ጎን መስፋት መሬት በመሸጥ ለሚኖሩ መሪ ተብዬዎች ችግር ነው እንጂ እንኳንስ በሩቅ ያለው ኦሮምም ይሁን ሌላው ሕዝብ የከተማዋ ስፋት የሚነካቸውንም የመጎዳ ላይሆን ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ወደ ሜዳማዎቹ የገበሬው እርሻ ስትስፋፋ ማንም የተናገረ የለም፡፡ ዛሬ ከተማ የሆኑትን በዙሪያዋ ያሉትን ታጠቃልል ሲባል ግን ዜጎችን ለግድያ የደረሰ ሆነ፡፡ ደግሞ ችግሩ በከተማዋ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ሳይሆን ከሌላው ርቆ ካለው ሕዝብ የተለየ የአዲስ አበባ መስፋትና መጥበብ የማይመለከታቸው ዜጎች ለመሞታቸው ምክነያት ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ ግን የራሳቸውን ጥቅም በዜጎች ደም ሊያቆዩ ባሰቡ ጠንቀኞች ለዜጎቹ ርሕራሄ በሌላቸው መሪዎችና በተማሪና ሠላማዊ ነዋሪዎች ላይ ኢላማ በሚለማመዱ የሕዝብ ጠላት በሆኑ ተኳሾች ሆነ፡፡  እነሱ ይኖራሉ የሞተው ግን ለቤተሰቡና ለማህበረሰቡ አጎደለ፡፡
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ችግር ከሆነ መሪ ተብዬዎቹ እዛው ለምን አልጨረሱትም? አምቦ ስለ አዲስ አበባ ከሌላው የተለይ ምን አለው? ይልቁንስ በማስተር ፕላኑ ተጠቃለዋል የተባሉት ከተሞች ለምን ጠያቂ አልሆኑም? የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ችግር የሆነው ለማንነው? በእኔ ግምት በዙሪያው ያሉ ከተሞች ነዋሪዎች ወደ አዲስ አበባ መጠቃለላቸውን የሚጠሉት አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም የኦሮምያ መሪ ተብዬዎች ትልቁ የገቢ ምንጭ የሆነው የመሬት ሽያጭ ለዚህ ሁሉ ችግር ምክነያት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መቼም በተሻለ እኛ እናለማዋለን ብለው እንደማያስቡ እርግጠኞች ነን፡፡  አዲስ አበባ መሽገው ስለራሳቸው ድሎት ሌላውን  ለጥፋት እየዳረጉ የደም እንጀራ ከመብላት ወጣ ብለው ለአንድ ከተማ መልማት ምክነያት ቢሆኑ አዲስ አበባም ሌላ ተጨማሪ መሬት ስትል አግባብ የሆነውን ጥቅም/ካሳ ለዜጎች የማስከፈል አቅም በኖራቸው፡፡ እነሱ ከተማቸው ፊንፊኔ ስለሆነች ሌሎችን ለማየት አይን የላቸውም፡፡ ከተማ የነበሩት ወደ እርሻነት ተቀይረው ዜጎች የመንግስት ያለህ ሲሉ አልሰሙም፡፡ ጂማ ስትታረስ ብዙ ዓመት ሆናት! በከተሞቻቸው የሚያልፉ መንገዶች ደረጃቸውን ባልጠበቅ ተገንብተው ዝም አሉ፡፡ ትልቅ ተብዬዋን አዳማን ጨምሮ ዋና መንገዶቻቸውን አስተውሉ፡፡ ሕዝቡ ለትራፊክ ፍሰት በአረዓያነት የሚጠቀስ ባሕል ያለው ዛሬ ደም በተጠሙ ጠመንጃ እንጋቾች ነዋሪዎቿና የአስተናገደቻቸው ተማሪዎቿ የሞቱባት አምቦንም ተመልከቷት፡፡ እስኪ ለማወዳደርም ወደ ሌሎች ክልሎች በተለይም ደቡብን ጨምሮ ከላያ የጠቀስኳቸውን ክልሎች ተመልከቱ፡፡

አምቦ ብዙ ጊዜ የዚህ መንግስት ኢላማ እንደሆነች እናውቃለን፡፡ ግማሹም ድሮ ዛሬ መንግስት የሆኑት ከጫካ በመጡ ጊዜ የአምቦ ሕዝብ ተዋግቷቸው ስለነበር ለበቀል ይመስላል፡፡ የኦሮሞ ወካይ ነን የሚሉ ቡድኖች ደግሞ የአምቦን ሕዝብ ምርጥ ኦሮም በሚል ራሱን ከሌላው እንዲለይ አድርገዋል፡፡ መሠረታዊ ጥቅሞች ላይ ግን አምቦና ሕዝቧ ሞትና ሥቃይ እንጂ የደረሳቸው የለም፡፡ እባብ ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው አሉ፡፡ አንዱ ሳያየው ነው ሁለተኛ ግን በሌላ ቀን ከአንዱ ጓደኛው ጋር ሲሄዱ መንገድ ላይ እባብ ተጠቅሉ ያይና ጓደኛውን አንተ ያ ባለፈው የነደፈኝ ነገር ይሄውልህ ብሎ በእጅ ነክቶ ሲያሳይ ነው ይባላል፡፡ እስከመቼ እኛን ለሚገድሉን መጠቀሚያ እንደምንሆን አላውቅም፡፡ ሕዝቡን አንተ ኦሮሞ፣ አማራ ምናምን እያሉ ለራሳቸው መሳሪያ እንዲሆንላቸው አዘጋጁት፡፡ በሌላ አገር የተፈጠረን አንድ ችግር ሲያመቻቸው የአንተን ወገን እንዲህ ያሉ እንዲህ አደረጉት እያሉ በውል በአላወቀው ጉዳይ ለሞት ሳይቀር ዳረጉት፡፡ ኦሮሞም ከሆነ አምቦ ከሌላው የተለየ ኦሮሞ አይደለም! የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በቀጥታ ከነካቸው ቦታ ነዋሪዎች በተለየ የአምቦንም ሆነ ርቆ ያለውን ሌላው የኦሮሞም ይሁን ልላ ሕዝብ የሚመለከተው አይደለም፡፡ ለኦሮሞ ተማሪዎች በተለየ ሁኔታ የአዲስ አበባ ጉዳይ የሚመለከታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ ችግር ሆኖ ሲገኝ የሁሉም መሆን አለበት፡፡ ኦሮሞ ነኝ የሚለው ብዙ ሕዝብ ከሌሎች ጋር አንድ ሆኖና ተፋቅሮ እንዳይኖር ለዓመታት ሕዝቡን እናስተዳደራለን የሚሉ መሪ ተብዬዎች የአስተሳሰብ ብክለትን ፈጥረውበታል፡፡ ማንነቱን አስጥለውታል! ብዙ ኦሮሞ ነኝ የሚል ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱንም ለመቀበል በጣር ነው፡፡ የሚገርመው ግን ኦሮሞ ነኝ ያለው ትግሬ ወይም አማራ ነኝ ካለው የሚለዩበት ነገር የለም፡፡ ቋንቋ ከሆነ ብዙ ኦሮሞ እንደሆኑ የማያምኑ ኦሮምኛን ኦሮሞ ነኝ ከሚለው በላይ ይናገሩታል፡፡ ባሕልም ብትሉ ኦሮሞ ነኝ ከሚለው ሌላ ነኝ የሚለው ቦረና በሉት ሌላውን ይኖረዋል፡፡

አሁንም ደግሜ እላለሁ በየዩኒቨርሲቲ ያሉ ኦሮሞ ነን የሚሉ ተማሪዎች ራሳቸውን ያገላሉ፡፡ ዛሬ የአምቦ ጉዳይ አምቦ ለሚኖረው ኦሮሞ በሉት አማራ፣ ትግሬ፣ ወይመ ሌላ ከሚመለከተው በላይ ቦረና ወይም ሐረር ያለ ኦሮሞ ነኝ ባይ የሚመለከተው አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ በተለይም ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኦሮሞ ነን የሚሉት ራሳቸውን ለየት ሲያደርጉ አይተናል፡፡ ሌሎቹ ጋርም ችግር አለ ግን ኦሮሞ ነን እንደሚሉት አይከፋም፡፡ ስለ አዲስ አበባ ጉዳይ የኦሮሞ ተማሪዎችን የተለየ ሊያደርጋቸው ባልተገባም፡፡ ችግሩ ሆኖ ቢገኝ ሌሎችም ፍትሕ ጎሏል በማለት በአንድነት በተቃወሙ ሞትም ካለ በሞቱ፡፡ ከዚያ ጉዳዩ የጎሳ ሳይሆን የሕዝብ ይሆናል፡፡ የሁሉም ወገን ደምቷልና፡፡

አሁንም እላለሁ ሌሎች በፈጠሩብን ስሜት አንሂድ፡፡ እኛ አንድም ብዙም ነን እንጂ የተለያየን አይደለንም፡፡ የአምቦ ችግር በመጀመሪያ ለአምቦ ነዋሪዎች፣ ከዚያም አምቦና አዋሳኟ እያለ እንጂ ሌሎች በሰበኩን ስብከት ሌላ አገር ያለ ወገኔ ብሎ ሊያስብልን አይገባም፡፡ ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ባዕድ ጎረቤት የሚለው ብሒል ያለ ምክነያት አይደለም፡፡ ደግሞስ እነሱ አሉን እንጂ ዝምድናውስ ቢሆን መቼ ቀርቶብን፡፡ ማን ነው ራሱን አሮሞ ነኝ፣ አማራ ነኝ ወይም ሌላ ብሎ የዘር ማንነቱን የሚያረጋግጥ፡፡ ያም ሆኖ እኛ ሰዎች ነን! በዘር ከሆነ ሁሌም አለዋለሁ አማራ ከሆነው ጎጃሜ ኦሮሞ ከሆነው ቦረና በላይ ኦሮሞ ለሆነው ወለጋ በደም ቅርበት እንዳለው እናውቃለን፡፡

እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን! አሜን!  
   
የታላቋ ቀን ልጅ ግንቦት 1 2006 ዓ.ም.


No comments:

Post a Comment