Sunday, May 4, 2014

የአንድነት ፓርቲ ያካሄደው ሠላማዊ ሠልፍ


አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትኅ ፓርቲ እሁድ፤ ሚያዝያ 26 ቀን 2006 ዓም «የእሪታ ቀን» በሚል አዲስ አበባ ውስጥ የተቃውሞ ሠላማዊ ሰልፍ አካሄደ። በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተለያዩ ብሶቶችን የሚያንፀባርቁ መፈክሮች፥ የተሰሙበትና አልባሳትም የታዩበት እንደነበር የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል።
ሰልፈኞቹ፤ መንግሥት የመብራት፣ የስልክ፣ የውሃና ሌሎች የመሰረተ-ልማት አቅርቦቶችን እንዲያሻሽልና መልካም አስተዳደርን እንዲያሰፍን ጠይቀዋል። የታሰሩ ጦማሪያን፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም አሳስበዋል። የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በሰልፉ ላይ ባሰሙት ንግግር፤ ባለፉት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች፣ ዩኒቨርስቲዎች እና ትምህርት ቤቶች፤ የተካሄደዉ የግድያ የድብደባ እና የእስራት እርምጃዎችን «ግዙፍ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች» ሲሉ በጥብቅ አዉግዘዋል።
በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ አዲስ አበባን የጎበኙት የአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ኢትዮጵያ ለሲቪክ ማኅበራትና ለጋዜጠኞች የተሻለ ነፃነት እንድትሰጥ መጠየቃቸዉ እና ባለፈዉ ሳምንት ማለቂያ የታሠሩት የድረ-ገፅ ጸሀፍትና ጋዜጠኞች ጉዳይም እንዳሳሰባቸዉ መግለፃቸዉ ይታወቃል። ጋዜጠኞች በህትመት፤ በኢንተርኔትም ሆነ በትኛዉም ዓይነት መገናኛ ብዙሃን የሚያከናዉኑት ኅብረተሰቡን እንደሚያጠናክር፤ እንደሚያነቃቃና ፤ለዴሞክራሲም መጠናከርና ድምፅ ሊሆን እንደሚችልም ኬሪ መግለፃቸዉ ይታወሳል።
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትኅ ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተለያዩ ብሶቶችን የሚያንፀባርቁ መፈክሮች እና አልባሳትም የተሰሙበትና የታዩበት እንደነበር የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል። ሠልፉን በቦታው ተገኝቶ የተከታተለው ወኪላችን ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሮ ልኮልናል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማጫወቻውን ይጫኑ
ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ

No comments:

Post a Comment