በውቤ አለማየሁ
ከጀርመን
በሳውዲ
አረቢያ በወንድምና እህቶቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን አሰቃቂ ግፍና መከራ ለመቃወም በትላንትናው እለት ህዳር 5
ቀን 2006 ዓ.ም በጀርመን ፈራንክበርት ሳውዲ አረቢያ ቆንስላ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተገኝቼ ነበረ።በሰልፉ
ለይ ለመሳተፍ በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ነበር ወደ ባቡር ጣቢያው ያመራነው።በለሊት
የተነሳንበት ዋነኛ ምክንያት ሰልፉን በጠዋት ለመጀመር ዕቅድ በመያዙ ነው። እኔ ካለሁበት አካባቢ በርካታ ቁጥር
ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶቼም ተሳታፊዎች ነበሩ።እለቱ በሳውዲ አረቢያ በምስኪኑ ህዝባችን ላይ መፈፀም
የጀመረው ግፍና መከራ “አስረኛውን ቀን” ያስቆጠረበት ነበር።በእነኚህ አስር ቀናት የሰው ልጅ ደም በየሜዳው እንደ
ጎርፍ ሲወርድ ፤አካሉ ደግሞ እንደ እንጨት ሲፈለጥና ሲቆረጥ አይተናል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች በኩል ከስፍራው የሚወጡ የቪዲዮና የፎቶ ምስሎች እንደሚያመለክቱት የሳውዲ አረቢያ
ደህንነቶችና ወጣቶች እንዲሁም አሰሪዎች እህትና ወንድሞቻችን ላይ እጅግ ዘግናኝና አሳዛኝ ድርጊት
ፈፅመዋል።አንዳንዶቹ “የድርሱልን ጥሪ” ሲያሰሙ ከልብ የሚያስለቅሱ ናቸው።እንኳን አይደለም አስር ቀናት በመከራና
በጭንቀት የሆነች አንዲት ደቂቃ ከዓመት ትስተካከላለች።
ሰላማዊ ሰልፋችን በፍራንክፈርት ሳውዲ አራቢያ ቆንስላ ልክ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጠዋጡ አራት ሰዓት ነበር
የተጀመረው።በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ህፃናትን በመሸከሚያ ጋሪ የያዙ እናቶች፣ ወጣቶች ፣አዛውንቶችና የሀይማኖት አባቶች
ሳይቀሩ በተለያዩ የጀርመን ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተገኝተው ነበር።በጀርመን ሀገር የሚገኙ ኤርትራውያን
ወንድሞቻችን በሰልፉ ላይ የኢትዮጵያና የኤርትራን ባንድራ በመያዝ “እኛ ኤርትራውያን በኢትዮጵያውያን ላይ
የሚደርገውን በደል እንቃወማለን ” የሚል መፈክር አሰምተዋል።
ዘር፣ሀይማኖት፣ ብሔርና የፖለቲካ አስተሳሰብን ሳንለይ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ወንድሞቻችን
ኤርትራውያን በሳዉዲ አራቢያ ቆንስላ የተገኘንበት ዋነኛ ዓላማ የሳውዲ አራቢያ መንግስትና ህዝብ በንፁሀን
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ እየፈፀሙት የሚገኘውን አሰቃቂና ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በፍጥነት እንዲያቆሙ
ለመጠየቅ ነው። ከዚህ ባለፈ መስማት የተሳነውንና ዝምታን የመረጠውን አንባገነኑን መንግስት “በዲፕሎማሲያዊ መንገድ
ህዝባችንን ከመጨፍጨፍ እንዲያድንልን” ለመጠየቅ ነው። የሰላማዊ ሰልፍ ሁነቱን ለመዘገብ በስፍራዉ ለሚገኙ የሀገር
ውስጥና ዓለም አቀፍና መገናኛ ብዙሃን ኢ-ሰብአዊ ድርጊቱ ሲፈፀም በዝምታ መመልከት ለመረጡት ዓለም አቀፍ
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ባጠቃላይ ለዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እንዲያሳዉቁልን ለማድረግ በማሰብ ነው ።
ለሰላማዊ ሰልፉ ከተሰባሰብንበት መንገድ ፊት ለፊት አንድ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ ይታያል። የህንፃው እያንዳንዱ ፎቅ
ለተለያዩ አማካሪና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተከራየ መሆኑን ህንፃው መግቢያ ላይ የተዘረዘሩት ፅሁፎች ያስረዳሉ።
የሳውዲ አረቢያ ቆንስላ በዚህ ሰማይ ጠቀስ በሆነው ህንፃ ሀያ አራተኛ ፎቅ ላይ ነው የሚገኘው።
ሰላማዊ ሰልፋችን ከዚህ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ ትይዩ ቢበዛ በአስር ሜትር ርቀት ላይ ተጀመረ። ሰላማዊ ሰልፉችን
“ሰብአዊነትንና የሀገር ክብርን” መሰረት ያደረገ በመሆኑ የሰላማዊ ሰልፉ ስሜት እየጋለ መጣ። ሁላችንም የሰልፉ
ተሳታፊዎች ያች የሶስት ሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤት የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ በሳዉዲ አረቢያ “ንጉሶች”
ስትደፈር ታየችን።የህዝባችን ሰቆቃና ጩሀት፣ መከራና እንግልት እያንዳንዳችን ላይ የተፈፀመ አድርገን አሰብነው።
በእውነት ኢሰብአዊ ድርጊቱን ለመሸከም ይከብዳል።በአስር ሜትሮች ርቀነው የነበርነውን የሳውዲ አረቢያ ቆንስላ
የሚገኝበትን ህንፃ መግቢያ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠርነው። የህንፃው መግቢያና መውጫ በሰልፉ ሙሉ ለሙሉ ተዘጋ።
የህንፃው መግቢያ ላይ ደህንነት የሚያስጠብቁ ፖሊሶች ቢኖሩም ፖሊሶቹ ወደ ህንፃው ውስጥ እንዳንገባ ከመከልከል
ውጭ ሰላማዊ ሰልፋችንን በሰላማዊ መንገድ እንድናደርግ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን ከመወጣት ውጭ ሰላማዊ ሰልፉን በትዝብት
ይመለከቱ ነበር።ሰላማዊ ሰልፉ ቢያንስ ለሶስት ሰዓታት ተደርጓል። በዚህ እለት በተመሳሳይ ሰላማዊ ሰልፎች በመላው
አውሮፓ በእንግሊዝ ሎንዶን፣በሲውዲን ስቶኮልምና በሌሎች የአውሮፓ ዋና ዋና ከተሞች እንዲሁም በአሜሪካን ዋሽንግተን
ዲሲ ይደረግ ነበር።በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በዓለማችን ዋና ዋና ከተሞች ሰላማዊ ሰልፉ ሲደርግ በኢትዮጵያ
የሚገኙ ወገኖናችን ግን በመንግስት ክልከላ ምክንያት በሀገር ቤት የሳውዲ አረቢያ መንግስትን ድርጊት ማውገዝ
አልቻሉም።
አስራ አንደኛዉ ቀን
ይህ እለት በሳውዲ አረቢያ ያለው ሰቆቃና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አስራ አንደኛ ቀኑን የያዘበት ነው።ይህ እለት
ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ ሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ሰላማዊ ሰልፍ የጠራበት እለት ነው ።ሰላማዊ ሰልፉ ከሚደረግበት
ሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን በአምባገነኑ መንግስት የሚታዘዘው የደህንነት
ክፍሉና ፖሊሶች በሰልፊ ተሳታፊዎች ላይ ከባድ ድብደባና እስራት በመፈፀም ሰልፉ እንዲበተን አድርገዋል።አሶሺየትድ
ፕሬስ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴታን ሽመልስ ከማልን ጠቅሶ እንደዘገበው ሰልፉ የተበተነው “ሰልፈኞቹ ሰላማዊ
ሰልፍ እንዲያደርጉ ስላልተፈቀደላቸው ነው” ።ሽመልስ እንዳለው “ሰልፈኞቹ ሳውዲ አረቢያ ላይ ጥላቻ የሚፈጥሩ
መልዕክቶችን በመያዛቸውና እነኚህ መልዕክቶችም ኢትዮጵያ ከሳውዲ አረቢያ ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት የሚያሻክር
በመሆኑ ነው” ብሏል። ሰማያዊ ፓርቲ “የኢትዮጵያ መንግስት ከሳውዲ አረቢያ መንግስት ጎን በመቆም ዋና ተባባሪ
መሆኑን አስመስክሯል” ሲል ባውጣው መግለጨ የአምናገነኑን ኢህአዴግ መንግስት ድርፊት አውግዟል።
በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን የሰቆቃና የመከራ ድምፃቸውን ማሰማት ከጀመሩ ቀናቶች ቢቆጠሩም የሀገሪቱ
ጠላት የሆነው አምባገነኑ መንግስታችን ግን ህዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን አሰቃቂ ግፍና መከራ ቢያንስ
በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንኳን ለመፍታት አልቻለም።
በሀገር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሳውዲ አረቢያ ኢ-ሰብአዊ ድርጊትን በሰላማዊ ሰልፎች መቃወምና ሰላማዊ
ሰልፎችንም በሀገራችን ማድረግ አልቻሉም። ወገናችን ለተፈፀመበት ግፍና ሰቆቃ ህዝባችን በሀገሩ መጮህ ተልክሏል።
አምባገነኑ መንግስታችን ሰላማዊ ሰልፍ “በባዕድ ሀገራት ከተሞች እንጂ በኢትዮጵያ አታደርጉም፤አትችሉምም ”
ብሎናል።መንግስት ተብዬው ኢህአዴግ በሀገራችን ባዳ አድርጎናል።መንግስታችን በሀገራችን ባዳ ሲያደርገን በሌሎች
የዓለማችን ዋና ዋና ከተሞች የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ግን በትውልድ ሀገራችን ማድረግ ያልቻለውን ሰላማዊ ሰልፍ
በባዕድ ሀገራት ማድረግ ችለናል። በዚህም ምክንያት እኛ ኢትዮጵያውያን “ሰላማዊ ሰልፎችን በባዕድ ሀገራት ብቻ
እንድናደርግ ነው እንዴ የተፈርደብን? ” ብዬ እንድንጠይቅ ተገደድኩ። ቢፈረድብንስ …..ግን ፍርዱ እስከመቼ?
zehabesha
No comments:
Post a Comment