Thursday, November 14, 2013

በሳዑዲ 35 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራችን መልሱን ብለው እጅ ሰጥተዋል፤ ዛሬ አንድ ሰው ተገድሏል


(ዘ-ሐበሻ) ሙሉ ቀን ሳዑዲ ሪያድ ውስጥ የተኩስ እሩምታ ሲንጣጣ ነበር የዋለው። ወደ ሃገሬ መልሱኝ ብዬ እጄን ሰጥቻለሁ ሲል ለዘ-ሐበሻ በስልክ አስተያየቱን የሰጠው ወጣት ጀማል መቼ ወደ ሃገሩ እንደሚመልሱት ግራ እንደተጋባ ይገልጻል። “በአሁኑ ወቅት ታግተን የተቀመጥነበት ቦታ መጸዳጃ ቤት የለውም፤ ትልቅ ሰርግ የሚደገስበት ጊቢ ውስጥ ስላስቀመጡን ዝናብ ጥሎ መጠለያ ስለሌን ሲቀጠቅጠን ውሏል” ሲል የዛሬውን ውሉውን ያስረዳል። “የዛሬው ለየት የሚለው እኛ ከታሰርንበር አካባቢ ሴቶቹን ለይተው ወደ አልታወቀ ቦታ ስለሚወስዷቸው፤ ብዙቹም ሰርተው ያፈሩትን ያንገታቸውን ሃብል ወርቅ ሳይቀር በሳዑዲ ወጣቶች እና ፖሊሶች እየተዘረፉ በመሆኑ ከኛ ተነጥለው የትም አይሄዱም በሚል በተነሳ ችግር የተኩስ ልውውጥ ተነስቶ ነበር” የሚለው ጀማል “የጓደኛዬ ሚስት ከሶስት ቀን በፊት ከመንገድ ላይ ታፍሳ ከተወሰደች በኋላ ከ3500 በላይ የሳዑዲ ገንዘብና ወርቆቿን ወስደው መንገድ ላይ ጥለዋት ሄደው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ከሚፈልጉ ወገኖች ጋር ተቀላቅላ አግኝተናታል” ሲል የኢትዮጵያውያኑን ውሎ ያስረዳል። saudi ethiopian boy
“በቀን ወደ 400 የሚጠጋ ስደተኛ ወደ ሃገሩ ይላካል ተብሎ ተነግሮናል። ሆኖም ግን እጃችንን የሰጠነው ሰዎች 35 ሺህ እንሆናለን። እነዚህን ሁሉ ሰዎች ለማመላለስ ስንት ቀን እንደሚፈጅ ወገን ይፍረደን። በዛ ላይ የታሰርንበር ቦታ ምግብ የለም፤ ዝናብ ይደበድበናል፤ ብርድ አለ፤ መጸዳጃ ቤት የለውም። ለማን አቤት ይባላል?” ሲል የሚጠይቀው ጀማል በዛሬው የተኩስ እሩምታ አንድ ኢትዮጵያዊ ተገድሏል፤ ሌላ አንዲት ሴት ደግሞ እዚያው የታሰሩበት ቦታ ወልዳለች ሲል ያለውን ነገር አጫውቶናል።
በአሁኑ የት ቦታ ነው የታሰራችሁት በሚል ዘ-ሐበሻ ላቀረበችለት ጥያቄ ጀማል “ሪያድ ሽፋ የሚባል አካባቢ ነው ያለነው፤ ወገን ይድረስልን” ካለ በኋላ በሳዑዲ በተለይ ሴቶች እያበዱ ጨርቃቸውን ጥለው እየሄዱ ነው ሲል የወገኖቹን ሰቆቃ በስልክ አውርቶናል።
ዘ-ሐበሻ አሁንም ጉዳዩን ተከታትላ ትዘግባለች።
በዚህ አጋጣሚ፦
ዘ-ሐበሻ ርዕሰ-አንቀጽ፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ነገ ሐሙስ፣ አርብ፣ እሁድ እና ሰኞ የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች በሳዑዲ ያሉ ወገኖቻችንን በማስመልከት ይደረጋሉ። ለሰልፍ የምንወጣ ሰዎች ሳዑዲ ውስጥ በ እስር ላይ ያሉ፣ ወደ ሃገር ቤት ለመግባት እየጠበቁ ያሉ፣ በሥራ ላይ ያሉም ወገኖች ስላሉና በነርሱም ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሳዑዲ አረቢያን ባንዲራ ከማቃጠልና ስሜታዊ ርምጃዎችን ከመውሰድ መቆጠብ እዛ በስቃይ ላይ ላሉት ወገኖች ማሰብ ነው። እኛ እዚህ መጥፎ ነገር ባደረግን ቁጥር እዛም በወገኖቻችን ላይ ስቃዩ እየበረታ ይሄዳል። በመሆኑም በሰላማዊና በበሰለ መንገድ የሳዑዲ ኢምባሲዎች ቆመን ለወገኖቻችን የሚጠቅመውን ነገር ብቻ እንድንጠይቅ ዘ-ሐበሻ ጥሪዋን ታቀርባለች።

zehabesha

No comments:

Post a Comment