ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ
በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ ከእኛ ወገን ለአንተ እናት ሆናህ በእሷ በኩል በሥጋ ትዛመደን በመረጥካትና ስለብዙዎች ልቧ (አእምሮዋ) ሐዘንን (ነብዩ እንደተናገራት ፍላጻዎችን)
ሁሉ ያስተግድ ዘንድ ባጸናሀት፣ ቅድስት፣ ንፅህትና ዘላለማዊት ድንግል በሆነች እናትህ ማሪያም ሥም ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ!
አሜን!
ባለፈው ጽሑፌ ማይክሮ ችፕስ 2 ጽሑፍ ስለሐይማኖት መበረዝ ለመዳሰስ ሞክሬ ነበር፡፡ የሀይማኖትን ነገር ካነሳን ብዙ
ውስብስብ ነገሮች ስላሉ በባለፈው ይብቃንና ዘሬ ወደ ባህልና መበረዝ ልወስዳችሁ ወደድሁ፡፡
ጎጂ ሊሆኑ የሚችሉ ባህሎች እንዳሉ ሆነው፤ ባህል በአብዛኛው ለአንድ ማህበረሰብ ለመንፈሳዊም ለቁሳዊውም ብልጽግና
ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ሰው እንደማህበረሰብ ነዋሪነቱም ባህል ሊኖረው የግድ ይለዋል፡፡ በሕብረት አብሮ ለመኖር ሕዝብን አንድ አድርጎ
ለማሰተሳሰር ጉልህ ጉልበት አለውና፡፡ በጎ ባህሎች ሊዳብሩና የተፈለገውን ብልጽግና ለማምጣት የሚችሉት ግን በጎ አሳቢ፣ ለሕዝብ
የሚጨነቁ ቃላቸው የሚደመጥ ሽማግሌዎችና የሕዝብ መሪዎች ባሉባት ማህበረሰብ ነው፡፡ ሽማግሌዎች ባለፉባቸው ዘመናት ስለ ሕዝባቸው
ችግር መፍትሔ በመስጠት የኖሩት የኑሮ ብቃታቸውና በእድሜ ያካበቱትን ልምድ ለተተኪ ትውልድ ለማስተላልፍ ያላቸው ኃላፊነት ባህል
ለእድገት አስተዋጽዖ ይኖረው ዘንድ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በተቃራኒው እንደሀይማኖቱ ሁሉ ባሕልንም ለራሳቸው ጥቅምና ተደማጭነትን ለማትረፍ
እንደ መሳሪያ የሚጠቀሙ ሽማግሌዎችና መሪዎች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ባሕል እድገትን በማምጣት ፋንታ ውድቀትን ሊያስከትል ይችላል፡፡
እንደነዚህ ያሉ ሽማግሌዎች ባሉበት ማህበረሰብ፣ ወገኝነት፣ ዘረኝነት፣ ወራዳ የሆኑ አስተሳሰቦች ከዚያም በላይ የክፉ መናፍስት አምላኪነት
እንደ ባህል የሚታዩበት ነው፡፡ በእንደዚህ ያሉ ማህበረሰብ ጥበብ ቦታ የላትም፡፡ ምክነያቱም መሪ ተብለው ያሉት ራስ ወዳድ ሸማግሌዎች
ጥበብ ልታጋልጣቸው ስለምትችል አጥብቀው ይዋጓታል፡፡
በአገራችን የእደጥበብ ችሎታ ያላቸው የተለያየ መጥፎ ሥም ሲሰጣቸው ሥራ የማይሰሩ አውደልዳዩች እንደ ጨዋና/መኳንንት
የታዩበት የዘመናት ታሪካችን የዚህ አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ደግሞ ሆን ተብሎ በቀድሞ ዘመን በአገሪቱ በሀይማኖት መሪነት
የሚመጡ ግብጻውያን የሚስጢር ሴራ የተደረገ እንደሆነ ይታማል፡፡ ዋነኛው ምክነያት ደግሞ አባይን ሊያቆም የሚችል በጥበብ የበለፀገ
ትውልድ እንዳይኖር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በሥራቸው ዛሬም ድረስ አለምን የሚያስደምም ጥበብ ከነበራቸው የዛግዌያውያን (ላሊበላውያን)
ወደ ወገኞቹ ሰሎሞናውያን ስልጣን እንዲዛወር የተደረገውም በተመሳሳይ ሴራ እንሆነ ይታማል፡፡ ብዙዎቻችን ባናውቅም ዛግዌያውያን ስልጣንን
እንዳይጋፉ በልዩ ውል ታስረው ነበር፡፡ ይህም እስከ አጼ ኃ/ሥላሴ የደረሰው የዋቅ ሹሞች ንግስና ነው፡፡ ዛግዌያውያን (አገው)
በዚህ ተደልለው ለዘመናት በቆየ ሴራ ዛሬ ፍጹም ጥበብ አልባ የሆነ ወገኛ ትውልድ እንዲኖራቸው ተደርገዋል፡፡ የታሪክ ተመራማሪ ነን
የሚሉ የአገራችን ምሁር ተብዬዎች ይህን ሴራ ግልጽ አድርገው ሊያወሩት አቅም ባይኖራቸውም ጉዳዩ እዚህ ቀለበት ውስጥ እንዳለ ማስተዋል
መልካም ነው፡፡
በአገራችን አብዛኛው የታሪክ ሂደት የእድል ጉዳይ ሆኖ
ያፈራናቸው ሽማግሌዎች ስለሕዝብ የሚጨነቁና ጥበብ በዚች አበር እንድትበለፅግ የሚያበረታቱና ትውልድን በጥበብ መታነጽን የሚመክሩ
ሳይሆን ባሕልን ለራሳቸው ጥቅም የሚበርዙ ጥበብ ራሷ የምትጠላቸውና
የተፋቻቸው ወገኛ ሽማግሌ ተብዬዎች ናቸው፡፡ ጥበብን ወደአገር ለመጋበዝ የሞከሩ መሪዎችንም እንቅፋት በመሆን ይታወቃሉ፡፡ በዚህ
ሁሉ ሂደት አገሪቷ ጥበብ የነጠፈችባት ባሕል ሁሉ ወግ ብቻ የሆነባት፣ ድህነትና የኑሮ ጉስቁልና ሕዝቦቿን በባርነት አንቆ የዛሬውን
ትውልድ ለሌሎች ባህሎች ባርነት ተላልፎ የተሰጠባት ሆናለች፡፡ ይህ የታሪክ ሂደት ለሌሎች እንደ ጥሩ አጋጣሚ ስለሆነላቸው ዛሬ ያለነውን
ትውልድ በእነሱ ወግና ስርዓት እንድንማልል አስገድዶናል፡፡አዋራጅ የሆኑ የሌሎች ክፉ ባሕሎች ሳይቀር የምንናፍቅ የራሳችን ጥሩ የተባሉትን
የባህል እሴቶችን የምንንቅ ወይም በራሳችን የምናፍር የዛሬ ኢትዮጵያውያን ተፈጠርን፡፡ ዛሬ በተለይ በትላልቅ ከተሞቻችን የሚስተዋሉ
ከውጭ ወደ አገራችን የገቡ የባህል ጉድፎች ብዙዎች ተበላሽተናል፡፡ ሌሎች የረከሱበትን ባህላቸውን ሳይቀር ማስተናገድ እምቢ አላልንም፡፡
በተለይ ለውጭ ባህል ወረራ አዛማችነት ዋና መሳሪያ የሆነው ሥራ መስራት የማይወደው በማምታታት ለመኖር የሚፈልግና ማጭበርበርን እንደ
ችሎታ የሚቆጥር የጨነገፈ አእምሮ ያለው የሕዝብ አካል ነው፡፡ የባህል መበረዝ ወረራው ሀማኖታዊ በሐይማኖት፣በበጎ አድራጊነት ሽፋን
ከሚገባው እስከ ፍጹም ርኩሰትን በገሀድ የሚያዛምት ነው፡፡ ሁሉም ዓላማቸው አንድ ነው ያለንን ማሳጣት፣ ማንነታችንን ማሳጣት፡፡
ዛሬ በከተሞቻችን በተለይ የቱሪስት መዳረሻ በሆኑት ለመስማት እንኳን የሚከብዱ የባሕል ብረዛዎች እናያለን፡፡ የአዲስ
አበባ የባሕል መበከል ፍጥነት ደግሞ ከሁሉም አስደንጋጭና አሳሳቢ ነው፡፡ ቀድሞውንም ማንነቱን በማያውቅ ትውልድ (ኃላፊነት ባለው
ማህበረሰብ ያላደገ) በሌሎች ባዕዳን ባሕሎች ላለመበከል የሚቋቋመበት አቅም የለውም፡፡ በዓላት ሳይቀሩ ከነባሮቹ ወደ ሌሎች ተቀይረዋል፡፡
ቫላንታይን (መጥፎ ተብሎ ባይባልም ግን የራስ ያልሆነ ሌሎችን በመሆን ራስን ማጣት ስለሚያስከትል)፣ ሐሎይን (በቀጥታ የሰይጣን)፣
ክሪስማስ ተሪ (የማይመስለን)፣ ሌሎችም፡፡ ዘንድሮ ሐሎይን በአዲስ አበባ በይፋ የመገናኛ ሽፋን ሳይቀር ነበር ያለው፡፡ በራስ የሚተማመኑ
እንደ ሩሲያ ያሉ አገራት ግን ይህን በዓል በግልጽ ነበር በማውገዝ የአገራቸው ሕዝቦች እንዳያከብሩት ያስጠነቀቁት፡፡ እኛ ጋር ማን
ከልካይ አለ? ለብዙዎች ዜጎቻችን እንደነዚህ ያሉ ባዕድ ባሕሎች የዘመናዊነት
መገለጫዎች ናቸው፡፡ ሆን ተብለው ራስን ለማሳጣት የሚደረጉ የባሕል በካይ ሴራዎች እንደሆኑ ብዙዎቻችን አንረዳም፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ
ውሻ ይደፋብሻል!
በየከተሞቻችን እየተስፋፉ ያሉ አንዳንድ አዳዲስ የንግድ
ዘርፎችም ከሌሎች በተወረሱ ባህል ጉድፎች የተበከሉ ናቸው፡፡ ብዙዎች እንደነዚህ ያሉ ንግዶች ደግሞ የመጡት ብዙም የበሰለ ትምህርት
በሌላቸው በሌሎች አገራት በስደተኝነት ቆይተው በመጡ ዜጎች ነው፡፡ ብዙዎቻችን ሌሎች አገራትን ለማየት ዕድሉ የገጠመን (በስደትም
ይሁን ወይም በሥራ ወይም በትምህርት) ኢትዮጵያውያን ምን አዚም እንዳለብን ባይገባኝም የሌሎች አገራት የእድገት ሚስጢር ምን ሊሆን
እንደሚችል ለማወቅ ከመሞከር ይልቅ የእነሱን የረከሰ ባህል ወርስን ነው የምንመለሰው፡፡ በአጼ ኃ/ሥላሴ ዘመን ለኪነ-ጥበብ ትመህርት
ወደ ፈረንሳይ ተልከው የነበረ ተማሪዎች (ማቹን አዛውንት ሥብሀትን ጨምሮ) ይዘው የተመለሱት እንደነ ውቤ በረሀን የመሳሰሉ መንደሮችን
ለመፍጠር ያስቻላቸውን ልክፍት ነው እንጂ ኪነጥበብን ለማሳደግ ያስቻላቸውን ዕውቀት አልነበረም፡፡ ብዙዎቹም እነሱ ፍልስፍና በሚሉት
ግን ባዶ በሆነ የአስተሳሰብ ልክፍት ኖረው ሌሎችን በክለው ሞተዋል፡፡ በተመሳሳይ ወቅትና ከጃፓን አገር ወደ ሌሎች አገራት ለጥበብ
ተልከው የነበሩ ተማሪዎች ሲመለሱ የተላኩበትን ጥበብ ሳይሆን ባዕድ ባሕል ወደ አገራቸው ይዘው በመመለሳቸው የአገራቸው መንግስት
ሌላውን እንዳይበክሉ በሞት እንደቀጣቸው ይነገራል፡፡ በዘመናችን ወደ አረብ አገር የሚሄዱ ብዙ ሴቶቻችን ሲመለሱ የሚጀምሩት አብዛናው
የንግድ አይነት የሼሻና ጫት ቤት ነው፡፡ ጫት የእኛው አገር ቢሆንም አሁን ያሉት አይነት የጫት መቃሚያ ቤቶች በአብዛኛው ከአረብ
አገር በመጡ ሴቶቻችን የተበረከቱልን እርግማኖች ናቸው፡፡ ብዙዎች እዛም እያሉ ሥራቸው ይሄው ነበርና፡፡ ትንሽ አደጉ በተባሉት የሌሎች
አገራት ተሰዳጅ ዜጎች ደግሞ በማሳጅ አገልግሎት ንግድ በኩል መዳራትን እያስፋፉ ያሉ ናቸው፡፡ በመሠረቱ የማሳጅ አገልግሎት በሌሎች
አገራት ከሕክምና ጋር የተያያዘ ፋይዳ ያለውና ሁሉም በሥርዓትና በሕግ የሚካሄድ ቢሆንም እንኛ ያለው ሥርዓትና ሕግ በማይጠበቅበት
አገር የባሕል ብክለትን የሚያስከትል አደጋ ሆኗል፡፡ ሲጀምር እንዲህ ያሉ አገልግሎቶች መሰጠት ያለባቸው በሙያ በሠለጠኑ ከዚያም
በላይ ልዩ ተፈጥሯዊ ክህሎት ባለቸው የሙያ ስነምግባሩንም በውል በሚያከብሩ ባለሙያዎች መሆን ሲገባው በአገሪቱ የሥራ መሥፈርት አለመኖር
ምክነያት ማንም እየተነሳ የሚያቦካው ሕዝብንም የሚበክል ከመሆኑ በተጨማሪ በሙያው የሰለጠኑትን ባለሙያዎችንም ስነምግባሩን ተከትሎ
መሠርት ስላላስቻላቸው ወይ እነሱም ከስነምግባር ወጥተው ይሰራሉ ወይም አቁመዋል፡፡ በእንዲህ መልኩ እነኳንስ ከጅምሩም ጥሩ ያልሆኑት
የባዕዳን ባሕሎች ቀርቶ ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ዕውቀቶቻቸውም ሌሎች ተቀጽላ ነውረኛ ተግባሮቻቸው ጋር ስለሚመጡብን ማንነታችንን ለማሳጣት
ዳርገውናል፡፡
ሌላው ከባህል ጋር የተያያዘው ብክለት ቋንቋ ነው፡፡ ዘሬ ንግድ ቤቶቻችን በኢንግሊዘኛ ካልተሰየሙ ውጤታማ የሚሆኑ
አይመስለንም፡፡ ምን ልክፍት እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም እኔ ራሴ በአንድ ወቅት የአንድ ድርጅት ሥም ለመሰየም እድሉን አግኝቼ የጠቆምኩት
የኢንግሊዘኛ ሥያሜ ተቀባይነት አግኝቶ እስካሁንም በዛው ሥም ይጠራል፡፡ ካላጣሁት ሌላ አገርኛ መጠሪያ ኢንግሊዘኛ መምረጤ አሁን
ላይ ትልቅ ሥህተት እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ተራ ካፌና ምናምን ሳይቀር አገርኛ መጠሪያ ይሸክካቸዋል፡፡ አሳፋሪነቱ ብዙዎቹ ሥያሜዎች
ራሳቸው ባለቤቶቹ ትርጉሙን የማያውቁት፣ ሌሎች ደግሞ ውርደት እንደሆነ እንኳን ሳናስብ የሌሎች አገራት ከተሞችን ቦታዎችን አስተዋዋቂ
አገልጋይ ባሪያዎች ሆነናል፡፡ አንድም ኢንግሊዘኛ ተናጋሪ ዝር የማይልባቸው ካፌዎቻችንና ምግብ ቤቶቻችን የምግብና መጠት ዝርዝር
የሚቀርብልን በኢንግሊዘኛ ነው፡፡ ለባሮች የጌቶቻቸውን ቋንቋ መናገር ዘመናዊነት ነው፡፡ ባለፈው ቋንቋ በትምህርቶቻችን ላይ እያስከተለ
ያለውን አደጋ ለመጠቆም ሞክሬ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የት/ቤቶቹ ስያሜም እንደዛው፡፡
በአገራችን ዛሬ ጥሩ ሥያሜ ካላቸው የንግድ ዘርፎች ባንኮችና የሕክምና ማዕከላት (ከነሱም የተወሰኑት ችግር አባቸው)
የተሸለ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረታዊ ምክነያቱ እነዚህን ተቋማት ለመመሥረት ቀድሞውንም በዕውቀት የበለጸጉ ዜጎች
ስለሚሳተፉባቸው ነው፡፡ በሌሎቹ ግን ትላልቆቹን ንግድ ዘርፎች ሳይቀር ገንዘብ ብቻ መስፈርት የሆነባቸው ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ በተማሩ
ዜጎች የሚቋቋሙ የንግድ ተቋማት አገርኛውን ሥያሜ አላብሰዋቸው ለጆሮም ለአይንም ለማንነትም ጌጥ ሆነው እናያቸዋለን፡፡ በጥሩ ጎኑ
ስለሆነ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ዝና ያለውን የ "ዳንዲ ቦሩ" ት/ቤትን ስያሜ ውበት እንምሳሌ ባቀርበው ት/ቤቱን
ማስተዋወቅ አይሆንብኝም፡፡ እኔም ከሥሙ በቀር አላውቀውም፡፡ ሥያሜው ኦሮምኛ ሲሆን "የነገው መንገድ" ማለት ነው፡፡
ብዙዎች አዲስ አበቤዎች ግን ይህ ት/ቤት በባዕድ ቋንቋ ወይም የሌላ አገር ሰው ሥም ስለሚመስላቸው ይወዱታል፡፡ ኦሮምኛ ነው ብትሏቸው
ብዙዎች ቅር ሊሰኙ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ በእነዚህ ሰዎች አስተሳሰብ በኦሮምኛ የተሰየመ ት/ቤት እንዴት ተደርጎ ጥራት ያለው
ትምህርት ይሰጣል? በባርነት የወደቀ አእምሮ ይሄንኑ ያስባል፡፡ እንዲህ ያሉ ሥያሜውቻችን ግን ሌሎችን በእኛ ሥር እንዲወድቁ ጉልበት
እንዳላቸው አናስተውልም፡፡ ባዕዳን እነግዶቻችን ሲመጡ ምን ማለት ነው ብለው እንዲገደዱ እግረ-መንገዳቸውንም የእኛን አንድ
ነገር አውቀው እንዲሄዱ እናደርጋቸዋለንና፡፡ በራሳቸው ቋንቋ በእኛው አገር ንግዶቻችን ተሰይመው ሲያዩ ግን ይስቁብናል፡፡ አእምሮአችንም
የነሱ ባሪያ እንደሆነ ማወቅ ስለሚያስችላቸው ሌሎች ተጨማሪ ለእነሱ የምንገዛባቸውን ባሕሎቻቸውን እንደልብ ይሞሉናል፡፡
በሌላ በኩል በባዕድ አገር ያሉ ዜጎቻችን ንግዶቸውን በአገራቸው ቋንቋዎች ሥያሜ በቀር በሚኑሩበት አገር ቋንቋ ቢሰይሙ
ስለሚያሳፍራቸው አገርኛውን ሥያሜ ቅልጥ ባለው የባዕዳን ከተማ ይጠቀማሉ፡፡ በዚህ መልኩ ባዕዳኑም የተለየ ሥያሜ በማየታቸው ይጎበኟቸዋል
እንጂ አይርቋቸውም፡፡ ይህ እውነት ነው ማንነታችንን የሚያሳይ ምልክት ሲያዩ ሰዎች ይደነግጣሉ! ይፈሩንማል! ያከብሩንማል! ዛሬ
በአሜሪካ ከተሞች የሚታዩ አበሻ አገሩ ላይ ያልደፈራቸው የንግድ ሥያሜዎች ማንነትን በመግለጽ በባዕድ አገር ክብርን ለማግኘት እንደሆነ
ብዙዎች አናስተውልም፡፡ አገር ቤት ያሉት ግን ውጭ ናፋቂ ስለሆኑ ሁሉም ከውጭ ካልመጣ ደረጃውን የጠበቀ አይመስላቸውም፡፡ ሌላው
ክፋት እንዲያ በባዕድ አገር ሲከበርበት የኖረው ሰውም አገር ቤት ሲመጣ ረስቶት ይሁን ወይም ሌላ አዚም እንጃ ተቀይሮ በባዕድ ሥያሜ
ሊከበር የሞክራል፡፡ ምነአልባትም በአገርኛው ብሰይም ሕዝብ አይቀበለኝም ከሚል፡፡
በእነዚህ ሁሉ ራሳችንን እያጣን እንደሆነ እንረዳ፡፡ ራስን ደግሞ ሳይሆኑ ጥበብን ማሰብ አይቻልም፡፡ ጥበብ በራስ
የመተማመን ውጤት ናትና፡፡ የእኛው ባሕል በአብዛኛው በሀይማኖትና በቀደምት ጥልቅ የሕይወት መሠረት ላይ የቆመ በመሆኑ እስካሁንም
ለአለም ሳይቀር የምናበረክተው አለን፡፡ ዛሬ ሴቶችን ማክበር የሚያስተምሩን ባዕዳኖቹ እነሱ ሴቶቻቸውን እንደ ዕቃ የሚቆጥሩ እንደነበሩ
ማን ይነገራቸው፡፡ ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ አህያ አብራኝ ትተኛ (ቆዳ እንጥፉልኝ) አለ እንደተባለው ነው፡፡ የሴቶቻቸው ሥያሜ
ሳይቀር ከተወለዱባቸው ቤተሰቦች ተለወጡ ወደአበባቸው ባል ቤተሰብ ሥም የሚቀየርበት ምክነያቱ ይሄው ነበር፡፡ በእኛው አገር ግን
ሴትን ንጉስም ጅግናም ትወልዳለች እየተባለ የሚሰጣት ክብር ሊጎለብት ባለመቻሉ የራሳችንን ከሌሎች ተማሩ እየተባልን እንጋታለን፡፡
አሁን ያለንው ዜጎች የምናውቀው የአገራችንን በሴቶች ላይ ያለውን ክፉ አመለካከት ነው፡፡ ከመጀመሪያው እንደዚ ግን አልነበረም፡፡
ብዙ ዛሬ የምናያቸውም አስተሳሰቦች ቀደም ብለው ወደ አገራችን ከመጡ ባዕዳን የተወረሱ ናቸው፡፡ በተለይም ከአረቡ ምድር፡፡ ይህች
አገር ስብዕናን ከምንም በላይ ለማክበር በታሪክ የመጀመሪያ ናት፡፡ የትኛውንም አይነት እምነት ወይም አስተሳሰብ ቢኖረው ስብዕናው
የከበርለታል፡፡ የነብዩ መሐመድ ተከታዩች ወደ አገራችን ሲገቡ በክርስትና እምነት ተከታዩ ንጉስ ተቀባይነት ያገኙት በዚህ ስብዕናን
ከምንም በላይ የማክበር ፍልስፍና እንደሆነ እናስተውል፡፡ በእርግጥም ከልዑል አምላክ የሆነች ፍልስፍና ይሄንንው ታሳሰባለች፡፡ በቀደሙት
ፈላስፋ መሪዎቻችን በብዙ አገራት እንደተደረገው በሀይማኖቱ ምክነያት የተሰየፈ፣ ወደ እሳት የተጣለ ሰው ታሪካችን አስነብበንም፡፡
በኋለኘው ዘመን ያስተናገድናቸው የሀይማኖት ጦርነቶች (የዩዲት፣ ግራኝ) እነዚያ ልዩ ፍልስፍና የነበራቸው ጠብባን መሪዎች በመከኑበት
ዘመን እንደሆን እናስተውል፡፡ በሌሎች አገራት ግን ታሪካቸው ሁሉ አረመኔያዊ የሆን ጨካኝነት እንደሆነ አናስተውልም፡፡ ለብዙዎች
ዘር መጥፋት ምክነያቶችም ናቸው፡፡ የጊዜ ነገር ሆነና ዛሬ እነሱ እኛን ሊያስተምሩን የሞክራሉ፡፡ ለእነሱ የተገዛ ባሪያ አእምሮ
ስላለንም እነሱ ሲነግሩን ነው የምንሰማው፡፡ የራሳችንን የኖረ ታሪክና ባሕላችንን ፍልስፍናዎች በዘመናዊነት ዛሬ በማምጣት ልንጠቀምባቸው
አንሞክርም፡፡ የነጠፈ አእምሮ! የእኛን ጥሩውን ሳይቀር መጀመሪያ ያጣጥሉብንና እኛ በቃ እነሱ ካሉ መጥፎ ነው ብለን ስንጥለው አንስተውት
የራሳቸው አድርገውት እኛን ሊያስተምሩን ይሞክራሉ፡፡
አንዲት ብዙ ጊዜ የምትነገር እንደተረት ቁምነገር አዘል
ምሳሌ አቅርቤ ለዛሬ እዚህ ላይ ላብቃ፡፡ ሰውዬው በግ ሊሸጥ በጉን ተሸክሞ ወደ ገበያ ሲሄድ ያዩ ሶስት ሌቦች በጉን
እንዴት ከሰውዬው እንሚነጥቁት ዘዴ ሲያፈላልጉ አንደ ሀሳብ መጣላቸው፡፡ ሀሳቡም በተለያየ ርቀት ሆነን በመንገዱ ላይ እንቀመጥና
በተመሳሳይ ቃል ውሻ ተሸክመህ የምተሄደው ወዴት ነው እንለዋለን፡፡ ሶስታችንም በተለያየ ቦታ ይህንን ካልነው እውንም ውሻ ነው እንዴ የያዝኩት ብሎ በጉን ይጥለዋል ያኔ እኛ እንወስደዋለን ተባብለው፡፡
በተለያየ ርቀት መንገዱ ላይ ይጠብቁት ጀመር፡፡ የመጀመሪያው ሌባ ጌታዬ ምነው በጠራራ ጸሀይ ውሻ ተሸክመህ ትሄዳለህ ይለዋል፡፡
ሰውዬው ሌባ እንደሆነ አላወቀም ግን በንግግሩ ተናዱ ሌባውን ሰድቦት የያዘው በእርግጠኝነት በግ እንሆነ አስቦ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡
ሁለተኛው ሌባ ጋር ሲደርስ ሌባው ከበፊቱ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ምንው ጌታዬ ውሻ ተሸክመው በገበያ ቀን በሕዝብ መሃል ይሄዳሉ ይለዋል፤
ሰወዬው እንደመጠራጠር ብሎ ቀዝቀዝ ባለ ተግሳጽ ሌባውን አልፎ ወደ ገበያው ጉዞውን ቀጠለ ከተማ ሊደርስ አካባቢ ሦስተኛው ሌባ በተመሳሳይ
ግን ከሁለቱም በሚያስደነግጥ ሁኔታ ጌታዬ ምን ነክቶዎት ነው በገበያ ቀን ይህ ሁሉ ባለበት ውሻ ተሸክመው ወደከተማ የሚገቡት ይለዋል፡፡
ያን ጊዜ ባለበጉ እውነትም የተሸከምኩት ውሻ ነው እንዴ ይልና በጉን ከሸክሞ አውርዶ ይለቀዋል፡፡ እነዚያ ሌቦች በጉን ወደሚሮጥበት
ተከትለው ወሰዱት፡፡ የእኛም ነገር እንዲሁ ነው! በሚቀጥለው በአገር አስተዳደሮቻችን ያሉ ማክሮቺፕሶችን አደርሳችኋለሁ፡፡
እስከዚያው ልዕል አማልክ በቸር ያቆየን! አቤቱ የምናስተውልበትን አቅም ፍጠርልን!! አሜን!
የታላቋ ቀን ልጅ ሕዳር 4ኛው ቀን 2006 ዓ.ም (Son of the great day 13th
of November 2013)
No comments:
Post a Comment