ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ
በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ ከእኛ ወገን ለአንተ እናት ሆናህ በእሷ በኩል በሥጋ ትዛመደን ዘንድ በመረጥካትና ስለብዙዎች ልቧ
(አእምሮዋ) ሐዘንን (ነብዩ እንደተናገራት ፍላጻዎችን) ሁሉ ያስተናግድ ዘንድ ባጸናሀት፣ ቅድስት፣ ንፅህትና ዘላለማዊት ድንግል
በሆነች እናትህ ማሪያም ሥም ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
ብፁዕ አባታችን፡ ከዚህ
በፊት የጻፍኩልዎት ደብዳቤ ይደረስዎት አይድረስዎት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን እንደደረሰዎት እገምታለሁ እኔ ለአንባብያን በማህበራዊ
ድህረገፆች እንዲነበብ ባደርገውም በደብዳቤው መልዕክት የተሳቡ አንዳንድ ሰዎች የእኔን ፍቃድ ጠይቀው በቀጥታ በፋክስ እንላኩልዎት
ነግረውኛል፡፡ ጉዳዩ ዛሬ ደግሜ ከማነሳው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የበፊቱንም ደብዳቤ በድጋሜ አንባብያንም ይሁኑ እርሶም ማመሳከር
ትችሉ ዘንድ ከዚሁ መልዕክት ጋር አያየዛለሁ፡፡ ከጉዳዩ መመሳሰል ባሻገር የወራቶቹም መመሳሰል ነገሩን በውል ላስተዋለው አስገራሚ
ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ወራት በመላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የጾምና ጸሎት እንዲሁም የንስሃ መቀበያ ወቅት እንደሆነ ልብ እንበል፡፡
ልክ የዛሬ ዓመት በዚሁ የጾም ወቅት ተከስቶ የነበረ (እንደውም የዛሬ ዓመት በጌታ ሕማም መታሰቢያ ሳምንት በነበረው የጾሙ ጊዜ
ነበር) ጉዳይ ዛሬም ተከስቶ ሳየው ተገረምኩ እናም ተመሳሳይነት ያለው መልዕክት በድጋሜ ለእርሶና ለቤተክርስቲያኒቱ የውጭ ግንኙነጽ
ኃላፊ እንዲሁም ለትዝብት ለሕዝብ ማስተላለፍ ፈለግሁ፡፡ ይህ ጉዳይ የመልአከ መንክራት (መምህር)ግርማ ወንድሙን አገልግሎት ይመለከታል፡፡
ሰሞኑን በአቡነ ገሪማ መምህሩን አስመልክቶ እንደተጻፉ የሚያሳዩ ሁለት
ተቃራኒ መልዕክት ያለቸው ደብዳቤዎች ለሕዝብ በማሕበራዊ ገጾች በመድረሳቸው የዛሬ ዓመት ተከስቶ የነበረው አይነት ወዥምበር በሕዝብ
ዘንድ ፈጥረው ታላቅ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆነው ሰንብተዋል፡፡ የመጀመሪያው
ደብዳቤ ከሰባት ወር በፊት እንደተጻፈ የሚያመለክት ሲሆን ደብዳቤው ለመምህሩ ዕውቅና የሰጠና አገልግሎታቸውንም ዓለም ዓቀፍ እንዲሆን
የፈቀደ ሲሆን በቅርቡ በተመሳሳይ ፊርማና ማህተብ የወጣው ሌላ ደብዳቤ ደግሞ የበፊቱን በማጭበርበር የወጣ ብሎ የሚከስና የሚያወግዝ
ነው፡፡
አሁን ጥያቄው የመምህሩ ችግር ወይንስ የእርሶና የፀሀፊው ሊቀ ጳጳስ
ጽ/ቤት ችግር ነው የሚል ነው፡፡ መምህሩ በተጭበረበረ ማህተብና ፊርማ
ሌላ ቦታ ያሰሩት ደብዳቤ ከሆነ በእርግጥም መምህሩ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ግን ከእርሶ ጽ/ቤት የወጡ ደብዳቤዎች ከሁኑ መምህሩን
የሚያስጠይቃቸው አንዳች ጉዳይ አይታየኝም፡፡ ደብዳቤዎቹ ግን በተጭበረበረ
ማህተብ የተጻፉ አይመስሉም፡፡ ፊርማውምና ቲተሩም ቢሆን የሊቀ ጳጳሱ
የራሳቸው እንደሆነ አናያለን፡፡ እነዚህ ተቃራኒ መልዕክት ያላቸው ደብዳቤዎች እንዴት በአንድ ሰው ፊርማ ወጡ ለሚለው የብዞዎች ግምት
የጸ/ቤቱ እንደሆነ እንጂ የመምህሩ እንደሆነ አያሳይም፡፡ በተመሳሳይ የዛሬ ዓመት ከዚሁ ከእርሶ ጽ/ቤት የመምህሩን አገልግሎት ያወገዘውና
ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ያገደው ደብዳቤ ከፍተኛ የሆነ ግድፈትና
የጽ/ቤቱን ደረጃ የማይመጥን በልዩ ሴራ የደብዳቤን ይዘት፣ ሥርዓትና ቅደም ተከተል እንኳን በማያውቁ ግለሰቦች እንደተጻፈ
አንበበናል፡፡ የአሁኖቹም ቢሆኑ ከቤተክርስቲያን መሠረታዊ መርሆ ወጣ ባሉ የጎደፉ ሕሊናዎች ሊሆኑ እንሚችሉ አንዳንድ ቃላቶችንና
የሁኔታዎችን ሂደት እናያለን፡፡
የመጀመሪያው ደብዳቤ ስሕተት ነው ከተባለና ሁለተኛው እውነተኛ ሆኖ
የመምህሩ አገልግሎት እውንም የሚወገዝ አይነት ከሆነ መምህሩ በይፋ የሚሰጡትን አገልግሎት በፖስታ በሚታሸግ ደብዳቤ ብቻ ሊያውም ለማይመለከተው ሁሉ (አገልግሎትዎ ስህተት ነው ከተባለ የሚመለከተው
በመጀመሪያ መምህሩን ነው) የጅምላ ደብዳቤ መጻፍ ስህተት ይመስለኛል፡፡ ይህ ደብዳቤ የተጻፈው በፊት ለተፈው ስህተት ለተባለው ምላሽ
ብቻ ከሆነም የበፊቱ ለሚመለከተው ሁሉ ይላልና ይሄም ለሚመለከተው ሁሉ ቢባል ችግር የለውም ካልንና የመምህሩ አገልግሎት ግን ስህተት
የለውም ተብሎ ከታመነ ሁለተኛው ደብዳቤ ከመጻፉ በፊት ቢያንስ የበፊቱ በምን አግባብ እንደሆነ ተጠንቶ መምህሩም ተጠይቀው ስህተቱ
ይት ጋር እንዳለ ከተረጋገጠ በኋላ ሊሆን ይገባው ነበር፡፡ የመጀመሪያው ደብዳቤ ማንም ይጻፈው ማንም የመምህሩ አገልግሎት ግን እስከታመነበት
ድረስ እንደተባለው የበፊቱ ከጽ/ቤቱ ያልወጣ ወይም አግባብ ባልሆነ ሁኔታ የወጣ ከሆነ ደብዳቤውን ማውገዝ ተገቢ ነው በምትኩ ግን
የመምህሩን አገልግሎት የሚደግፍ ሌላ ትክክለኛ ደብዳቤ መስጠት የበጎ ሕሊና አሰራር ከመሆኑም ባሻገር አጋጣሚዎችን ለራሳቸው ፍላጎት
ሊጠቀሙ የሚያስቡትን በር መዝጋት ነበር፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን የሁለተኛው ደብዳቤ ይዘት የመምህሩን አገልግሎት አንቀበልምና ፍቃድ
አለኝ ቢሏችኁ አተቀበሏቸው ጭምር ይመስላል፡፡ በዚህ የይዘት ትርጉም ደግሞ መምህሩ አሁን በይፋ ተጻፈላቸውም አልተጻፈላቸውም በአለም አቀፍ ደረጃ እየሰጡት ያለው አስተምህሮትና የፈውስ አገልግሎት በቤተክርስቲያኒቱ ሥምና በእርግጥም በቤተክርስቲያኒቱ አብያት
ቅጥር ውስጥ እንደሆነ ስናስብ አገልግሎታቸውን በይፋ መንቀፍ ድፍረት በልታጣ ነበር፡፡ በይዘትና ደረጀ ሚዛን ሲመዘኑ ግን ሁለቱም
ደብዳቤዎች የተንገዳገዱና ነገር እንዳለባቸው እንረዳለን፡፡ መምህሩ ግን የሚያውቁት ነገር ያለ አይመስልም፡፡
እኔ የመምህሩን አስተምህሮትም ሆነ የፈውስ አገልግሎት በአትኩሮትና
በመገረም በአካልም በጉባዔያቸው በመገኘት ጭምር የምከታተል ሰው ነኝ፡፡
የመምህሩ አስተምህሮት ዛሬ እንደ አሸን የፈሉት ተራ ሰባክያን አስተምህሮት ከጩኸት የዘለለ ሕይወትን ለመለወጥ አቅም የሌለው ሳይሆን
በትኩረት ለአዳመጠው ጥልቅ የሆነ ከልዑል አምላክ ዘንድ በምትፈስ ጥበብ/ፍልስፍና የተዋበ አእምሮና ሕሊና እውነትን እንዲጋፈጧት
የሚያስገድድ ነው፡፡ በተግባር የሚያደርጉት የልዑል እግዚአብሔርን ኃይል በገሀድ ማሳየትና የጠላታችንን ሴራ ማጋለጥ የአገልግሎታቸው
ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህ ነበርና ጥንታዊው የሐዋርያት ክርስትና፡፡
ዛሬ ግን ጰውሎስ እንህ አለ፣ እንዲህ አደረገ፤ ዮሐንስ እንዲህ አለ እንዲህ አደረገ ከሚለን በቀር እነዚያ ታላላቅ ተአምራትን በጌታ
ሥም የሚያደርጉትን የሚያደርግ ለመኖሩ ማረጋገጫ እንኳን አጥተናል፡፡ በአንጻሩ ቀሚሳቸውን አስረዝመው እጅጌያቸውን አስፍተው በከተማ
በመንገማለል በአለባበሳቸውና በአነጋገራቸው ሊከብዱብን የሚሞክሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በእንዲህም አይነት ሳይገደቡ በቤተክርስቲያንና
በሕዝብ ገንዘብ የራሳቸውን ዓለም የሚቀጩት ይሄ ለቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደርና ሥርዓት አደገኛ ኪሳራ ሆነዋል፡፡ ይህን እውነት
ሕሊናችን ሊክደው አይችልም፡፡ በጎ ነገርንና ለልዑለአማላክ መገዛትን በቀጥታ የሚናገሩት ግን መምህሩን ጨምሮ በበጎ አይን አይታዩም፡፡
መምህሩ በልዑል አማላክና በቅዱሳኑ ሥም ከክፉ መናፍስት በመናፍስቱ ከሚመጡ ደዌያትንና የኑሮ ምስቅልቅሎች የተጨነቁትን መታደጋቸው
አደገኛ ጠንቋይ አስማተኛ አሰኝቷቸዋል፡፡ እርግጥ አስማተኛ መባላቸውን እኔም ብሆን ቅር የምሰኝበት አይደለም፡፡ የመምህሩ አስማት ግን ሌሎች ክፉዎቹ የሚጠሩት ሳይሆን፣ ኃያሉና ጉልበትን
ሁሉ የሚያንበረክከው የክርስቶስና ስሙ በስማቸው የታተመው የቅዱሳኑ ግን ሥም እንደሆነ በአየናችን አይተናል እኛም እንድንሞክረው
አድርገው ብዙዎች በሥሙ ክፉውን መንፈስና ጠንቆቹን እተዋጉት ይገኛሉ፡፡ ይህ አስማተ መለኮት መተተኞቹ የሚቋቋሙት አይደለም፡፡ መምህሩ
ጠንቋይና መተተኛ ላለመሆናቸው እኛ ምስክሮች ነን፡፡ ችግሩ ቤተክርስቲያንን
የወረሯት መተተኛ ደብተራዎችና ጠንቋዮች ሥራቸው እየከሸፈባቸው ስለሆነ የመምህሩን ከምድረገጽ መጥፋት አጥብቀው ይፈልጉታል፡፡ መጻሕፍ
ይጠቅሳሉ፣ ሴራ ይሸርባሉ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ይሞክራሉ፡፡ ግን የልዑል አማላክን ክንድ ሊያጥፍ የሚችል ማን ነው! ሌሎች የተደነባበሩትን
ለማደናገር ይሞክራሉ፡፡ አልቀረባቸውም ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል በማለት የመምህሩን የማዳን ፀጋ ሊያጣጥሉ ይሞክራሉ፡፡
ጌታም ሆነ ሐዋሪያቱ ምልክትን እንድንመረምር አስጠነቀቁን እንጂ አይተን እንዳናምን አልተናገሩም፡፡ ጌታንም ሆነ ሐዋሪያትን የተቀበሏቸው
ብዙዎች በአዩት ተዓምር እንጂ በትምህርታቸው እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ደግሞ በተግባር የማይገለጥ እምነት የለመድንው ተረት አይነት
እንጂ እንዴት እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ በሥሙ ለሚያምኑት ሁሉን ያደርጉ ዘንድ ሥልጣንን እንደሰጣቸው ሲታወስ ምንም ማድረግ የማንችል
የመተተኞችታ የክፉ መናፍስት መጫወቻ የሆንን ግን ክርስቲያነ ነን ብለን የሚናምን እስኪ ለክርስትናችን ምልክቱ ምንድነው?
እውነት እንደ መምህር ግረማ ብዙዎችን ከዘመናት ጭንቅ የገላገለ ማን
ነው? ብዙዎችንስ እምነታቸውን እንዲያውቁ ያደረገ ማን ነው? ብዙዎቻችን እኮ ክርስትናው ከተረት ያለፈ ትርጉም አልሰጠን ብሎ ነበር!
የየትኛው ሰባኪ አስተምሮት ነው ብዙዎችን ከሌላ እምነት ወደክርስትናው የመለሰ? ሰብከት ተብዬዎች ብዙዎች ጦርነትን መለያየትን የሚያውጁ
አይደሉም እንዴ! ማነው እንደ እኚህ መምህር ዘር ሳይል ሀይማኖት የተሰጠውን ፀጋ ለሁሉም በእኩል ሊያበረክት የወደደ፡፡ ዘረኝነትና
ጎጠኝነትን የሚያስፋፉ አይደሉም እንዴ ዛሬ ቤተክርስቲያኒቱን የወረሯት፡፡ ማን ነው እን እኚህ መምህር ለቤተክርስቲያን ልማት ተሳታፊ
የሆነ፡፡ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለቤተክርስቲያን ዛሬ እያስገባ ያለው በእሳቸው ትምህርት አይደለም እንዴ? ማንው ይህንን ሁሉ
ገቢ ለቤተክርስቲያን እያስገባ በነጻ አንዳች ደሞዝ እንኳን ሳይቀበል የሚያገለግል፡፡ በየክብረ በዓል በአሰልቺ ሁኔታ የሚሰበሰብን
ገነዘብ ካላካፈላችሁን፣ አበል ካልከፈላችሁን የሚሉ ሰባክያንና መዘምራን
አይደሉም እንዴ ዛሬ የሞሉን፡፡ የጌታን ትዕዛዝ በለመጠበቃቸው ግን መካኖች እንደሆኑ አይረዱም፡፡ በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ
ይላልና፡፡ እንደመምህሩ ያለ ጸጋ ሊኖረው የሚፈልግ ገዘብን ወዶ ሊሆንለት አይችልም፡፡
አባ በእናንተስ መካከል (በጳጳሳቱ ማለቴ ነው) ስለመምህሩ ለምን ይሄን
ያህል መለያየት ተፈጠረ? ጥሩና አስተዋይ መሆናቸውና በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑት ብዙዎቹ ጳጳሳት መምህሩን በትክክልም ሲደግፉ
በጉባዔያቸውም እየተገኙ ሕዝቡን ሲባርኩ አይተናል፡፡ ደብዳቤዎቹ ማን እንደጻፋቸውም ስለማናውቅ ተጭበረበሩ እንበል፡፡ ግን እኮ አይናችን
እያየ ጆሮአችንም እየሰማ ከእናነተ እኮ የመምህሩን አገልግሎት አለም አቀፋዊነት በአንደበታቸው ነው የተናገሩት፡፡ ይሄም ፊልም ነው
ሊሉ ይችላሉ፡፡ እኛ ግን በአካል ተገኝተን የያየንና የሰማን ምስክሮች ነን፡፡ ደግሞ እግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት የማንንም ፍቃድና
እውቅና ማግኘት ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ጥንታዊው የሐዋሪያትም ጉዞ በካህናትና በነገስታት ፍቃድ ሳይሆን ከአምላካቸው የተሰጠውን
ትዕዛዝ ብቻ ከመፈጸም ነበርና፡፡
አባ አሁንም አላለሁ ሕሊና የልዑል አምላክ እንደራሴ ነው፡፡ እውነት
ግን ከሕሊናም በላይ ስለሆነች በልዑል አምላክ የምትመሰል ናት፡፡ እግዚአብሔር እውነት ነውና፡፡ በሕሊናችን ካልበደልን እውነትን
ብንስታት እንኳን የእውነት ባለቤት እግዚአብሔር እውነትን እንድናውቃት ያደርጋል፡፡ ሁሌም አነሳዋለሁ በሕሊናው ምንም በደል የሌለበት
ግን እውነትን ባለማወቁ የክርስቲያኖች አሳዳጅ የነበረውን ሳውል (ቅዱስ ጳውሎስን)፡፡ በተቃራኒው እውነትን አውቆ ግን ሕሊናውን
በሰላሳ ብር የሸጠውን ይሁዳንም እናስተውል፡፡ እውነትን ለመቀበል እያወቁ እምቢ ያሉትን የአይሁድ ካህናትንም፡፡ ጳውሎስ ስለሕሊናው
ምርጥ የክርስቶስ ምርጥ ሊሆን ተመረጠ እውነት በተገለጠችለት ጊዜ ሕሊናው እውነትን ሊክድ የሚችል አልነበረምና፡፡
አባ አሁንም አላለሁ ሁላችሁም የሕሊናችሁን ንፅሕና እንድትመረምሩ፡፡
በስልጣንና በከፍተኛ ማዕረግ መቀመጥ እንደ አይሁድ ካህናት ክርስቶስን የሚያስክዳችሁ ምቾት አይሁንባችሁ፡፡ ስለ ሕዝብና ስለትውልድ
መጨነቅን ልመዱ፡፡ የድህነትን መንገድ ለማሳየት መነገድ የጠፋበትን ታች ወርዳችሁ ምሩት፡፡ ክርስትናው ወግና ልማድ ብቻ ሆኖ ሕዝብ
በክፉ ኃይል እንደወደቀ አስተውሉ፡፡ ከልዑል እግዚአብሔር ክብር ሕዝብ ለክፉ መንፈስ እንደተገዛም እዩ፡፡ ጠንቋዮችና ደብተሮች ከፍተኛ
ክብር አላቸው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱም ከፍተኛ ስልጣን ላይ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ሲያስፈራሩን ቆይተዋል! ዛሬ ግን ሊቋቋሙት የማችሉትን
እኛም ታጥቀናል፡፡ የዛሬ ዓማት በእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን የነበረው የመምህሩ የማስተማሪያና የፈውስ አገልገሎት መስጫ መድረክ ከነቅዱሳን
ሥዕላቶቹ ድምጥማጡ ሲጠፋ ከጠንቋዩች፣ ቃሊቻዎች፣ ሌሎችም ጣዖት አማላኪዎች እየተሰበሰቡ የሚመጡ የጣዖት ማመለኪያ እቃዎች የሚጣሉባት
አንዲት ትንሽ ክፍል ግን አንዳች አልተነካችም፡፡ ሰይጣን ነብረቱን ምን ያህል እንደሚጠብቅ ብዙዎቻችን አየን፡፡ ዛሬም ድረስ በዚያው
ጊቢ ያቺ ክፍል ብቻዋን አለች፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልፈለጉት መጠን የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው ያለው ፈላስፋው እውነት ነው፡፡ አስደንጋጭም ነው! አንዴ ለማይረባ አእምሮ
ከተጣልን በምን ማሰብ እንችላለን፡፡ ጌታን በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ባሉት ጊዜ የተናገረው አሳዛኝ መልዕክትም በአእምሮዬ
መጣ፡፡ "እኔ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን የማወጣ ከሆነ ልጆቻችሁ በምን ያወጧቸዋል" አለ፡፡ አዎ በጌታ ሥም ማመን
ካልቻልን በምን ክፉውን ልንቋቋመው እንችላለ፡፡
ብዙ ጉዳዩች በአእምሮዬ አሉ እዚሁ ላይ ላቁም ግን ለሁለተኛ ጊዜ እለምንዎታለሁ፡፡
ሥለ ሕሊና ፍርድ ራስዎ በይፋ ይናገሩ፡፡ ስለመምህሩም ስለሌላውም የቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ፡፡ እኛም ስለሕሊናችን አገልጋዮች እንሆናለን፡፡
አምላክም እውነትን እንከተላት ዘንድ እንደ ቅዱስ ጰውሎስ የአይናችንን ቅርፊት ያስወገድልናል! በእውነትም ተጉዘን መንግስቱን እንወርሳለን፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር አእምሮአችንን ይክፈት!
አሜን
የታላቋ ቀን ልጅ መጋቢት 21 2006 ዓ. ም
No comments:
Post a Comment