Saturday, February 1, 2014

ሰዎች በሀይማኖት ለምን ተልያዩ?




ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ ከእኛ ወገን ለአንተ እናት ሆናህ በእሷ በኩል በሥጋ ትዛመደን ዘንድ በመረጥካትና ስለብዙዎች ልቧ (አእምሮዋ) ሐዘንን (ነብዩ እንደተናገራት ፍላጻዎችን) ሁሉ ያስተናግድ ዘንድ ባጸናሀት፣ ቅድስት፣ ንፅህትና ዘላለማዊት ድንግል በሆነች እናትህ ማሪያም ሥም ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
ከዚህ በፊት ከእምነት ጋር በተያያዘ አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለአንባብያን አንሲቼ ነበር፡፡ ዋናው ጥያቄ መንፈስ የሚባል ነገር አለ ወይ? የሚል ነበር፡፡ ከዚሁም ጋር  ሰይጣን የሚባል ነገር አለ ወይ? አኛ ማን ነን? እኔ ራሴ ማን ነኝ? የሚሉ ጥያቄዎችን ከነሙሉ የጥያቄዎቼ መነሻ ነበር ያቀረብኩት፡፡ ይህንን ጥያቄ በኢሜልም የላኩላቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም መልስ ሊሰጠኝ የደፈረ የለም ከአንድ ፈላስፋ በቀር!  በእግዚአብሔር እናምናለን ብላችሁ ከምታስቡት ምን ያህሎቻችሁ የሰይጣንንም መኖር እናውቃለን እንደምትሉ አላውቅም፡፡ እኔ ግን እግዚአብሔርን አምናለሁ ብዬ ከሚያስቡት ግን ሰይጣን የሚባል ነገር የለም ብለው ደረታቸውን ነፍተው ከሚናገሩት ስለነበርኩ አሁን ላይ ያለውን እውቀት ከፈላስፋው ስረዳ በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ የጥንታዊው ፈላስፋ ከእግዚአብሔር ከሆንን ዓለም በሞላው በክፉ እንደተያዘ እናውቃለን የሚለው ንግግር ወደ አእምሮዬ የገባው ያኔ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ አንቢቤው ይሆናለ ግን ምን ዋጋ ነበረው፡፡ አዎ እርግጥ ነው ደግ እንዳለ ሁሉ ክፉ አለ! እግዚአብሔርን እናምናለን የምንል ሰይጣን እንደሌለ የምናምን እግዚአብሔርንም ማመናችን እውነት እንዳልሆነ ልንረዳው ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ዘንድ በሕሊናቸው እንደሚወከል አምናለሁ፡፡ ሕሊናን መሸወድ በፍጹም አይቻልም፡፡ ሆኖም አንዴ ለማይረባ አእምሮ ተላልፈን ከተሰጠን በኋላ ሕሊናችንም ሊነጠቅ እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ከለላ አይኖረንምና አእምሮአችን ሙሉ በሙሉ በክፉው ኃይል ይያዛል፡፡ ያን ጊዜ ማስተዋል የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡ ብዙ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች አእምሮአችን በእርግጠኝነት ትክክል እንደሆኑ ማሰብ ይችላናልና ወደትክክለኛው ነገር ለመመለስ ዕድል የለውም፡፡  
ከመጀመሪያው ሰዎች በአንድ የሰማይ አምላክ የሚያምኑ፣ በተለያዩ ጣዖታት የሚያመልኩ እንዲሁም ምንም እምነት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በእርግጥም የሰው ልጅ አእምሮ አንድ ፈጣሪዬ ብሎ እንዲያምንበት የሚፈልገው ነገር ስላለ ያለ ምንም እምነት ለመኖሩ አጠያያቂ ነው፡፡ አእምሮአችንም እኛ በፈለግንው የሚታዘዝ ሳይሆን በሌላ ኃይል ቁጥጥር ሥር ያለ ነውና፡፡ እኔ አእምሮዬየን እቆጣጠራለሁ የሚል ካለ እንደተሸወደ ልጠቁመው እወዳለሁ፡፡ ይህ ሌላ የጠለቀ ትንታኔ ስለሚያስፈልገው ወደተነሳሁበት የሀይማኖቶች/እምነት መለያየት ልቀጥል፡፡  በአንድ እምነት ሥርም ሆነው ሰዎች የተለያየ የእምነት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ እንደ መጽሐፍ ከመጀመሪያው አዳምና ሔዋን እኩል የእምነት አቅም እንዳልነበራቸው እንረዳለን፡፡ አዳም አምቢ ያለው ሰይጣን ወደሴቲቱ ሄዶ አታሏታልና፡፡ ከዚህ በኋላ ነው አዳም በሴቲቱ የተሸነፈው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሁለት ተቃራኒ መንፈሶች ወደ ሰው ልጆች እንደ ገቡ ፈላስፎች ይናገራሉ፡፡ ቀጥሎ በዚያው ትውልድ በአቤልና በቃየን መካከል ያለ የእምነት ልዩነት በገሀድ ተገልጦ አናየዋለን፡፡ በአንድ እግዚአበሔር እናምናለን የሚሉት ሰዎች ሌሎች ጣዖታትን የሚያመልኩትን በሰይጣን ምሪት እንደሆነ ቢናገሩም እናምነዋለን የሚሉትን እግዚአብሔር ብዙዎች በትክክል ያገኙት አይመስልም፡፡ ብዙም ጊዜ ከጣዖት አምላኪዎቹ የተለየ እምነት ሳይኖራቸው አንዳንዴም ጣዖት ከሚያመልኩት በባሰ ለጣዖታት የተገዙ እግዚአብሔርን አናምናለን በሚል አፋዊ እምነት ብቻ  የሚኖሩ ጥቂት አይደሉም፡፡  
እንደ መጽሐፍ ትልቁ የእግዚአብሔር ተከታይ የሚባለው ሕዝብ የእስራኤል (ያቆብ) ነገድ ቢሆንም፣ ከጥንት ጀምሮ ብዙዎች ሊያውም እስራኤል ከተባለው ሕዝብ በተሻለ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ነገዶች እንደነበሩ እንረዳለን፡፡ ለዚህ ምሳሌ ብንጠቀስ የኛዎቹ (ኢትዮጵያዊ የተባሉት) እንደሆኑ የሚነገርላቸው የሙሴ አማት ዮቶር (ካህን ነበር)፣ ካህኑ መልከጼዴቅ (የክርስቶስ ምሳሌ የሚባለው) እንዲሁም ከሙአባውያን (ከኤሳው ነገድ) ወገን የሆነው ፈላስፋው በለዓም ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እንግዲህ የእነዚህ ሰዎች ነገድ ተብለው በኋላ የመጡት ትዎልድም እግዚአብሔርን ቢያንስ የተወስኑት ያመልኩት እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ አንዳንዶቹም እስራኤል ከሚባለው ሕዝብ በተሻለ መልኩ እንደሚያመልኩ እንረዳለን፡፡ ለዚህም የበለዓም ዘር ተብለው የሚታመንላቸው ሰብዓ ሰገሎች ከእስራኤሎቹ በላቀ ሁኔታ ስለክርስቶስ ማንነትና መቼ እንደሚመጣ ጠንቀቀው የተረዱ መሆናቸውን እንደ ምስክር ልናቀርበው እንችላለን፡፡ በተቃራኒው እስራኤሎቹ ብዙ ጊዜ ከእግዚአብሔር አምልኮ እየወጡ እናያቸዋለን፡፡ ብዙ ተዓምራትን እያሳያቸውና መና ሳይቀር ከሰማይ እያወረደ እየመገባቸው እንኳን በእግዚአብሔር ማመንን አልቻሉም ነበርና፡፡ ይህ የሚያሳየን በምናየውም ነገር እንኳን ማመን እንደማንችል ጭምር ነው፡፡ የአእምሮአችን ጉዳይ በእኛ ቁጥጥር ሥር አደለም ከሚያሰኝ አንዱ መገለጫም ይሆናል፡፡ በትክክል ያወቅናቸውንም ነገሮች ለማሰብ የራሳችን ፍቃድ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በመጽሐፍ የምናነባቸው በሰዎች የተነገሩን ሁሉንም አወቅናቸው እንጂ አስተዋልናቸው ወይም አመንባቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ብዙም ጊዜ አፋችን ያንን ያወቅንውን እየተናገረ አእምሮአችን ሌላ ያልተጻፈ ነገር ያነባል፡፡
ታላቁ ፈላስፋ በእግዚአብሔር የሆነች አንዲት እምነት/ሀይማኖት ብቻ እንዳለች ይናገራል፡፡ በገሀድ ጣዖትና ሌሎች ነገሮችን የሚያምኑትን ትተን በእግዚአበሔር እናምናለን የሚሉ የዛሬዎቹን የሀይማኖት ብዛቶች ስንመለከት ነገሩ እንዴ ነው? ከማለት አልፎ በሕይወታችን የቱ ይሆን ትክክሉ እያልን ውዥምብር ውስጥ እንደከተተን አረዳለሁ፡፡  አሁንም በጥንታዊያኑ የኦሪት ተከተዮችና በክርስትናው መካከል ያለውን ትተን በአንድ ክርስትና በሚባለው ሥር እንደ አሸን በፈሉት የእምነት ብናኞች ባክነናል፡፡ ይህ ሁሉ ግን አሁንም አንዲት እምነት የምትለውን የፈላስፋውን ብሒል ሊቋቋመው የሚችል አይመሰለኝም፡፡ ሁሏም በየፊናዋ ትክክለኛዋ የኔ ናት እያለች ትኖራለች እንጂ፡፡ ይሄው አንዲት እምነት ያለው ፈላስፋ ያቺ እሱ የተናገረላት እምነት ፍቀር፣ ሰላም፣ ወዘተ እያለ የበጎ ነገር ሁሉ ምንጭ እንደሆነች ይናገርላታል፡፡ እንግዲህ ዛሬ እምነት ነን የሚሉት ሁሉ ራሳቸውን ከፈላስፋው መስፈርቶች ጋር ሊመዝኑት ይችላሉ፡፡ የብዙዎችን የዛሬዎቹን የአምነት ጉዳዮች ስንመለከት አጀማመራቸውም አካሂዳቸውም አኔ ከማን አንሳለሁ በሚሉ ግለሰቦች ሀሳብ ተጀምረው ቀስ እያሉ ትልልቅ ጎራዎች ሆነው የጦርነት ያህል በእውንም ጦርነት ሳይቀር ከፍተው የተፋለሙ እየተፋለሙ የሚገኙ ናቸው፡፡ ብዙዎቹም ሠረታዊ የሆነ የፍልስፍና ልዩነት እንዳላቸውና እንደሌላቸው አያውቁትም፡፡ ተከታዮቻቸውም የጅምላ ተጓዥ እንጂ መሠረታዊ ነገሮችን (ፈላስፋው ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች) አይረዱም ለመረዳትም አይፈልጉም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ያሉ ክፍፍሎች ናቸው፡፡ ክርስቶስ አንግዲህ ፈላስፋው አንድ ጌታ ያለው በእሱ የሚያምን ሁሉ በአንዲት እምነት ጥላ ሥር እንዳለ የተናገረለት ሲሆን ብዙዎች ግን የየራሳቸውን ክርስቶስ ነው የሚያምኑት፡፡
ከመጀመሪያው ከእስልምና በፊት ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ሁለት ጎራዎች እንዳሉ እናያለን፡፡ የክርስትናና የአይሁድ ተብለው የተሰየሙ፡፡ ኋላ ደግሞ ክርስትናው ራሱ ዛሬ ካቶሊክና ኦርቶዶክስ ወደምንላቸው ተመነዘረ፡፡ ቀጥሎ የአይሁዳውያኑንና ክርስትናውን ያዋሀደ የመሰለው የእስልምናው እምነት መጣ፡፡ እነዚህ ሁሉ በጥቂት ግለሰቦች ማፈንገጥ ተጀምረው ወደ ትልልቅ የእምነት ጎራዎች እንደተቀየሩ እናስተውል፡፡ እስኪ እነዚህን ሶስት እምነቶች ብቻ እንመልከት፡፡ ሁላችንም ግን ሕሊናችንን ሳንሸሸው በቀጥታ እምነቶቹ እንመራባቸዋለን በሚሉት መጻሕፍት የተጻፉትን እንጋፈጣቸው፡፡  የካቶሊኩና ኦርቶዶክሱ ልዩነታቸውን በአዋጅ ቢከፍሉትም ያንንው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ይከተላሉ፡፡ እስልምናው ደግሞ ቁርዐንን ይከተላሉ፡፡ ቁርዓኑም መጽሐፍ ቅዱሱም ስለክርስቶስ የሚሉት ነገር ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የአንዱ እምነት ተከታይ ሌላውን በጠላትነት ሊያስመለክተው የሚችል አንዳችም ነገር የለም፡፡ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በድንግልና እንደተወለደ፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ ወደ ሰማይ እንዳረገ፣ በኋለኛውም ዘመን ለፍርድ እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱሱም፣ ቁርዐኑም ይናገራሉ፡፡ ልዩነቱ በቁርዐኑ ሞቶ የተነሳው ክርስቶስ ሳይሆን እግዚአብሔር ልጁን ሊሰውረው ሌላ ሰው አይሁዶች እንዲገድሉ አድርጎ ልጁን ከሞት አተረፈው በኋላም ወደ ሰማይ ወሰደው የሚለው ነው፡፡ ወደ እምነቱ ስንመጣ በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ አምላክ (እግዚአብሔር) እንደሆነ ይናገራል በእስልምናው ግን ነብይ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ከመጀመሪያው በክርስትናው አማኞች (ካቶሊክና ኦርቶዶክስ) በውልም ግልጽ ባልሆኑ ልዩነቶች ጥላቻዎች ነግሰው እንደነበር እንጂ ተሳስቷል በሚል አንዱ ስለሌላው በፍቅር ለድህነቱ ሁሉንም ማድረግ ይችላል የሚሉትን አምላክ ስለፍቅር አልተገዳደሩትም ፡፡ ይባስ የሰው ልጆችን እልቂት ያስከተሉ ጦርነቶችን ቀሰቀሱ እንጂ፡፡ በክርስትናውና በእስልምናው መካከል ስናይም በክርስቶስ ስም ምክነያት ምንም ጥላቻ የሚፈጥር ነገር እንደሌለ እንረዳለን፡፡ ክርስቲያኖቹ አምላካቸው እንደሆነ ቢያምኑም ሙስሊሞቹም ነብያችን ነው ብለው ያምናሉና፡፡ ዛሬ ላይ ስናይ ግን በእስልምናው አለም የኢየሰሱ ክርስቶስን ስም መጥራት እጅግ አደገኛ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ እናስተውል በኋለኛው ዘመን መጥቶ ይፈርዳል ተብሎ በቁርዓናቸው የተጻፈላቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ሥም ለመስማት እንኳን ፍቃደኛ ያለመሆናቸውን አስቡ፡፡
ቀጥሎ ወደ ተፈጠሩት የክርስትናው ክፍፍሎች ስናመራ በካቶሊኮችና ዛሬ በጅምላው ፕሮቴስታነት በሚባሉት መካከል የሆነውን የጎራ ልዩነት እናያለን፡፡ ከመጀመሪያው (በነማርቲን ሉተር ጊዜ) የዚያን ያህል ባይሆንም እየቆየ በመጣ የእርስ በእርስ ጥላቻ የሁለቱ እምነቶች ልዩነት ሰፍቶ ፍጹም ተቃራኒ ሆነዋል፡፡ ይህ የፕሮቲስታን እምነት በተመሳሳይ የኦርቶዶክሱንም የሚቃረን ሆኗል፡፡ ካቶሊኮቹና ኦርቶዶክሶቹ የቀዱሳንን ምልጃና ተራዳኢነት ሲያምኑ ፕሮቲስታንቶቹ ግን ኢየሱስ  ብቻ እንጂ ሌላ አያስፈልግም ባይ ናቸው፡፡ በተለይም ደግም ከክርስቶስ እናት በድንግል ማርያም ጋር በተያያዘ ተቃርኖው የበዛ ነው፡፡ ልክ የእስልምናው አማኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥም ሲነሳ እንደሚያስደነበረው የፕሮቴስታንቱም እምነት ተከታይ የክርስቶስ እናት የማርያም ሥም ሲነሳ ይደነበራል፡፡ ያስቆጣዋልም፡፡ አሁን አሁን ይባስ የክርስቶስን እናት በግልጽ የሚሳደቡ የፕሮቲስታንት ተከታይ ሰባኪዎችንም እንሰማለን፡፡ ኢየሱሰ ጌታ ነው እያሉ የሚፎክሩት የእምነቱ ተከታዮች የቱ ኢየሱስ? የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ? ተብለው ሲጠየቁ ሌላ ድንጋጤ ይፈጥርባቸዋል፡፡ በክርስትናው መጽሐፍ ብዙ ኢየሱሶች እንደሚነሱ ተጽፏል፡፡ የክርስትናው ኢየሱስ ግን በእርግጥም በመለኮቱ የእግዚአብሔር ልጅ፣ በስጋ የድንግል ማርያም ልጅ የሆነው ብቻ እንደሆነ እናውቃለን፡፡
በተመሳሰይ በአገራችን ደግሞ የተሀድሶና የድሮ ኦርቶዶክስ በሚል ጎራ የተፈጠሩ ዛሬ የምናያቸው አሉ፡፡ ተሀድሶዎቹ ከፕሮቴስታንትና ከኦርቶዶክስ መሐከል ላይ የቆመ የሚመስል እምነት አራማጅ ናቸው፡፡ በቅርቡ ኢየሱስ ጌታ ነው! እያሉ እንደሚፎክሩት በኦርቶዶክስም ውስጥ ያለ ወላዲተ አምላክ አማላጅነት አለም አይድንም በሚል ፉከራ ምክነያት በብዙዎች ዘንድ ክርክር እንዲነሳ ሆኗል፡፡  እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስም ጌትነት፣ የወላዲተ አምላክም አማላጅነት አውነት ነው፡፡ ግን እነዚህን መፈክሮች ማንሳቱ ለምን ተፈለገ በማንስ መፈክሮቹ ተነሱ ብንል፡፡ ችግሩ የመጣው ከውስጥ በሆነ የእምነት ማጣት በአፍ ራስን ለመሸንገል በሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው እያለ የሚለፈልፍ ሰው በትክክልም በኢየሱስ ጌትነት ከውስጥ ማመን እንዳቃተው እንረዳለን፡፡ ብቻ ለሌሎች ይምሰል ወይም ከሱ ሌላ እምነት የሚከተሉ የመሰለውን ለመቃረን በአፉ ይፎክራል፡፡ በተመሳሳይ ያለ ወላዲተ አምላክ አማላጅነት አለም አይድንም ብለው አብዝተው የሚለፈልፉት ከውስጥ የሆን የወላዲተ አምላክን አማላጅነት መረዳት እንደቃታቸው እናስተውላለን፡፡ ከውስጥ ለአባቷ ፍቀር የሌላት ልጅ አባቷን አስሬ አወድሀለሁ በማለት የውስጥ ማጣቷን ለማካካስ የመታደርገው አይነት ነው፡፡ አባቷን በጣም የምትወደው ግን ሥሙን እንኳን ደጋግማ ከጠራች የሚያልቅባት ስለሚመስላት ትሰስታለች፡፡ በተመሳሳይ ፍቀረኛዋን/ውን አወድሀለሁ/ሻለሁ በማለት የሚያበዛ ነው፡፡  በሳይኮሎጂ ይህ ሕክምና የሚያሻው ችግር ነው፡፡ ትክክለኛውና ከውስጥ የሆነው ሁሉም በመሳሳት ስለሚሆን በቁጠባ ነውና፡፡  የክርስቶስም ጌትነት የእናቱም አማላጅነት በአፍ በሚሆን ልፍለፋ ሳይሆን እጅግ በሚያስጨንቅ ፍልስፍናና ጥበብ ውስጥ የምናስበው ከባድ ጉዳይ ነውና፡፡ ክርስቶስ ጌታ መሆኑን ሁሉም ያውቃል ግን ምን አይነት ጌታ፣ የክርስቶስ እናት ድህነትን የምታሰጥ አማላጅ እንደሆነች እናውቃለን ግን እንዴት፡፡ ክርስቶስ (በባሕሪው አማላክ የሆነ) በሥጋ እንደመጣ (ከእኛ ወገን (ሰው) የሆነችውን እናቱን ባሕሪ እንደተዋደ) ስንረዳ ያኔ ሁሉም ይገባን የሆናል፡፡
እንግዲህ ሀማኖቶች የእኔ ሀሳብ ከአንት ይበልጣል በሚል ፉክክር፣ ያም ፉክክር በሰይጣን አጋዥነት ወደ ገዘፈ ልዩነት አየሰፋ፣ ጎራ በመሆን እንደተፈጠሩ እናምናለን፡፡ ከመጀመሪያው ፈላስፋው ለሐይማኖት ያስቀመጣቸው መስፈርቶች ለአንዳቸውም የሀይማኖት መፈጠር ምልክት አይሆኗቸውም፡፡ ሰላም፣ ፍቅር፣ ትዕግስትና የመሳሰሉት በሐይማኖት በለያየት ዘመን የሉም፡፡ በተቃራኒው ግን ፀብ፣ ክርክር፣ ትዕቢትና አልፎም ጦርነት መገዳደል የመሳሰሉት ግን በእርግጥም በእነዚህ ወቅቶች በዝተዋል፡፡
ለሁሉም ሚስጢራትን ሁሉ የሚገልጽ አምላክ ማስተዋልን ይሰጠን ዘንድ በፊቱ እንንበርከክ፡፡ አቤቱ አባት ሆይ አእምሮአችንን ክፈት!
የታላቋ ቀን ልጅ ጥር 22 2006 ዓ.ም (Son of the great day January 30, 2014)          
   

No comments:

Post a Comment