Saturday, January 11, 2014

ኬሳ ኬሳ አዱሬን ቢነሳ…(ውስጥ ውስጡን ድመትም ነብር ናት) ክፍል 1( በቶሎሳ በቀለ)


ይድረስ ታሪክ ለመታንሻፈፉ እና በብሄር ለማጋጨረት ለምትጠሩ ሁሉ Ethiopian Flag
አባቴ አንድ ነገር ሳይጥማቸው ሲቀር ‹‹ኪሳ ኬሳ አዱሬን ቢኒሳ..›› ይላሉ፡፡ ‹‹ውስጥ ውስጡን ድመትም ነብር ናት..›› ማለት ነው፡፡ ይህ የኦሮሞን አባባል የተጠቀምኩት የኦሮሞ ልጆች ላይ ነብር መስለው ድመት የሆኑ የተገላበጠ ገመና ያላቸው እንደ እባብ ቆዳቸውን እየሸለቀቁ ወደ እሳት የሚገፉት ስንኩል ሰዎች ስላሉ ነው፡፡ ለእነዚህ የታሪክ ዝቃጮች ጥያቄ ማቅረብና እና እውነታውን ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ መጀመሪያ ደረጃ ለጁዋር እና ብጤዎቹ መጠየቅ የምፈልገው….የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ታሪክ አለው ወይ? ኢትዮጵያስ ከኦሮሞ ህዝብ የተነጠለ ታሪክ አላት ወይ? እንደ አለመታደል ሆኖ ጥሩ አስተዳደር ያላገኘው ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ተረግጦ ተበድሎ እኩል እየተበደለ፣ እየሞተ ነው የኖረው፡፡
አሁን ኦህዲድን ከመሰለ አሸርጋጅና ወገኑን በላ ድርጅት ጀምሮ ለመጣው ሁሉ ሲሰግዱ እጅ መንሻ የሚያቀርቡት የኦሮሞን ልጅ ጭዳ አድርገው ነው፡፡ ይሄ ስልጣን ፈላጊ ኦሮሞ የኦሮሞን ልጅ አሳልፎ መስጠት በፊትም የነበረ ነው፡፡ እውነት እንነጋገር ካልን የአኖሌን ጭፍጨፋ እውን ምኒልክ ነው የፈጸመው? የኦሮሞን ልጅ አጥንት ሲበላው የሚታየው ለገዢው አካል አሸርጋጅ ሆኖ የሚያጎበድድ የኦሮሞ ልጅ ነው፡፡ የኦሮሞን ህዝብ የጨፈጨፈው ጎበና ዳጬ ሆኖ ሳለ አንድም ቀን ስትጠሩት ሰምቼ አላውቅም፡፡ ለምን?…
ስላለፈውና ያልሆነውን ሆነ ብሎ በማውራት ለነገም ስቃይን ማስቀመጥ ምን ይሰራል? እውነት እንነጋገር ከተባለ ማንም ጥሩ ጎን ቢኖረውም መጥፎ ጎን እንዳለውም መዘንጋት የለበትም፡፡ ምኒልክ ሰው ነው ሁሉ ነገሩ ጥሩ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እሺ እንዳላችሁት ጎበና ዳጬን በማዘዝ ኦሮሞ ህዝብ ላይ ግፍ ፈጽመዋል ብለን እናስብ፡፡ ግን በስልጣን ዘመናቸው ጥሩም ነገር ማድረጋቸውን አንዘንጋ፡፡
በተጨማሪ የጣሊያንን ወረራ ኃይል ምኒልክ በድል ተወጥተው ባያሸንፉ (የአድዋ ድል..የጥቁር ህዝብ ኩራት) ባይከሰት በጣሊያን ቅኝ ብንገዛ ኖሮ ዛሬ ስምህ ወይም ስማችን ማን ይሆን ነበር? ሮቤርቶ፣ ካርሎስ..ኪኪኪኪ…ይሄ ስምና ማንነት ላይ የሚመጣውን ለውጥ እንተወው፡፡ የኦሮሞ ዋነኛው ስርዓት፣ ባህል፣ እምነት..ዋቄፈታ፣ ዋቄፋና ነው፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ማንነት መገለጫ የሆነው ኢሬቻስ ይደረግ ነበር? የገዳ ስርዓትስ ይኖር ነበር? ቅኝ ግዛት ዋነኛ አላማው እንደዚህ አይነት የማንነት መገለጫዎችን ማጥፋት መሆኑን እንዴት ረሳችሁት፡፡ የመዳ ወላቡስ ታሪክ ይቀጥል ነበር ወይ?
ሌላም ነገር ልጠይቅ ወደድኩ፡፡ ዛሬ ምሁር ለመምሰል አነጋገር የምታሳምሩ ታሪክ መስራት ሲያቅታችሁ ከመቶ አመት በፊት የተፈጸመን ነገር እያነሳን እርስ በእርሳችን እንድንናቆር መንገድ ከምትጠርጉ ለኦሮሞ ህዝብ የሚበጀውን ለምን አትጠቀሙም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምኒልክ ነው ወይስ ወያኔ ነው የኦሮሞ ህዝብ ራስ ምታት? ዛሬ የኦሮሞን ልጅ እየገደለ፣ እያሰቃየ፣ ለስደት እየዳረገ ያለው ገዢው ወያኔን ለምን ታግላችሁ መጣል አትሞክሩም? ይህን ብታደርጉ ነው ለኦሮሞ ልጅ እውነተኛ ተቆርቋሪ የምትሆኑት፡፡ ያለበለዛ ወዲያልኝ ወዲያ ዋጋም የለሽ ብሬን መልሽ እንደተባለው አይነት ናችሁ፡፡ አሁን እየሞትን ባለፈ ታሪክ ላይ የምታላዝኑ… (ሀሬ ዱቴ ኩር ኢንጀጠኒ..) ይላል አባቴ፡፡ የሞተ አህያ ኩርር…አይባልም እንደማለት ነው፡፡
ከደቡብ አፍሪካ ብሎም ከማንዴላ ምን መማር አለብን? ብሔራዊ እርቅ…ያለፈን ይቅር ብሎ በሰላም መኖር ነው የሚበጀው፡፡ የኦሮሞ ህዝበ እሰከዛሬ ያየው እያየ ያለው ሰቆቃ ይበቃዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ኢህአዴግ በስሩ የፈለፈለው ኦህዲድ የሚባል የአሸርጋጆች ቡድን የወገናቸውን ደም መጣጮች ህዝቡን እየሸጡት ነው፡፡ መድረስ ያለብን አሁን በስቃይ ውስጥ ላለው ህዝብ ነው፡፡
በቀጣዩ ክፍል እንገናኝ
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

No comments:

Post a Comment