Monday, January 13, 2014

አባጣለው ገብሬና ጓደኞቹ፦(ጌታቸው ከሰሜን አሜሪካ)



(ጌታቸው ከሰሜን አሜሪካ)
ዓመተ ምህረቱንና ወሩን ለጊዜው አላስታውስውም።ድርጊቱ የተፈጸመ ሰሞን ወሬው በየአቅጣጫው በሰፊው ይወራ ነበር።ጉዳዩ ግን የሀገር ድንበር ጉዳይ ነበር።ቦታው ምዕራብ ጎንደር አርማጭሆ ወረዳ ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ሰበካ(አጥቢያ) ወዲ ከውሊ ፈሸካ ከምትባል ቀበሌ የሱዳን ጦር ካምፕ አደረገ የሚል ወሬ የሰሙ ትውልዳቸው እዛው አርማጭሆና ጠገዴ የሆኑ አራት ሰዎች(ገብሬ ተወልደመድህን፤ድረስ ዓይናለም፤አወቀ ዋናሁንና ሌላ አንድ ሰው) መሬቱ የኢትዮጵያ ነው ።የሱዳን ጦር ለምን እዚህ መጥቶ ሠፈር በሚለው ጉዳይ ተቆጥተው ጦሩን መግጠምና ካምፑን ማቃጠል አለብን የሚል አቋም ላይ ደርሰው ተኩስ ከፈቱ።እንዳሉትም የሱዳንን ጦር ሠራዊት ክፉኛ ጎድተው ካምፑን አቃጥለው ክቡር መስዕዋትነት ከፍለው የሀገራቸውን ድንበር አስከብረው አልፈዋል።ሲባል እንደሰማሁት አባጣለው ገብሬ የተመታው ነብሱ ባልወጣች አንድ የሱዳን ቁስለኛ ጦር ሠራዊት እንደሆነና አባጣለውም የታባትክ እንዲህ ነው የምናደርግ እያለ ሲንጎራደድ እንደሆነ ይነገራል።እነዚህ ትልቅ ታሪክ ሰርተው ያለፉ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ እንዲዘክራቸው ይደረግ እያልኩ ከዚህ ባሻገር ይህ የሰሜን ምዕራብ ጎንደር ወሰን ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር መንግሥት ድንበር ጠባቂ ጦር ሠራዊት መድቦ የሚያስጠብቀው ሳይሆን በአካባቢው በሚኖሩት ተወላጆች የጎበዝ አለቃ እየተሾመ በሕዝብና በሕዝብ የግል ብረት ተጠብቆና ተከብሮ መኖሩ የትናንት ትዝታችን ሲሆን ያን ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው ነገሮች ተገላብጠው እናገኛቸዋለን።

የዛሬዎቹ ገዥዎች በዱር በነበሩበት ወቅት ከሱዳን ለተደረገላቸው ትብብር የኢትዮጵያ ሀብት የሆነውንና ባጥንትና በደም ተከብሮ የኖረውን ለም መሬት ለሱዳን መስጠት ማለት በሕዝብ ላይ ያላቸውን ንቀትና ኢትዮጵያ ጥቂቶች እንዳሻቸው የሚያደርጓት ብቻ መሆኑ ሳይሆን ትናንት ኢትዮጵያ ከመሐዲስቶች (ድርቡሽ) ጋር ስትዋጋ ንጉሧን አጼ ዮሐንስንና ሌሎች ልጆቿን የገበረችበትን መሬት አስልፎ ለጠላት መስጠት ማለት ገዥዎቻችን ምን ያህል ለትውልድ ፤ለሀገርና ለታሪክ የሚያስብ ጭንቅላት ያልፈጠረላቸው እነሱን ብቻ የሚያስቡ አራዊቶች መሆናቸውን እንድንገነዘብ የሚያደርግ ነው።መሬቱ የኢትዮጵያ ሀብት ነው።በመሬቱ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይመክርበት ኢትዮጵያና ሱዳንን የሚያካልለው ድንበር ድንበሩን በሚያውቁ ሰዎችና የታሪክ ተመራማሪ የሆኑ ሰዎች ሳይሳተፉበት ህወሃቶች ደፍርሰው ባደሩ ቁጥር የመሬት ስጦታ ማበርከት ሸክማቸውን የሚያቀልላቸው መስሎ ቢታያቸውም አንዲት ስንዝር መሬትም ብትሆን ለማንም የመስጠት መብቱ በፍጹም የላቸውም።አዎ! ጦሩ ፤ፖሊሱ ፤ ደህንነቱ በእጃቸው እንዳለ እናውቃለን።የአሰብና ከኤርትራ ጋር ደም ያፋሰሰው ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ሌላ ጠብ አጫሪ የሆነ መሰሪ ተንኮል መጎንጎን መታጠፊያውን የተበላሸ ያደርገዋል። እንደ ኃይል የሚመኩበትና ደረታቸውን ያሳበጠው መከላከያውም ሆነ ደህንነቱ ነገ ይናዳሉ።ይህ የማይቀር ነገር ነው።ደርግን ይወድቃል ብሎ ያሰበ አልነበረም ነገር ግን በአፍሪቃ ቀንድ ወደር ያልነበረው ግዙፍ ጦር ፈረሰ።ህወሃትንና ደርግን ለንጥጥር አቅርበን ስንመለከትም በገዳይነታቸው አንድ ቢሆኑም በሀገር ጉዳይ ደርግ ዋዛ አልነበረም። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ደርግ በህዝብ ዘንድ ይሁንታ ነበረው።ህወሃት ከሕዝብ ተነጥሎ ቆሞ በየአመቱ የሀገር ጥፋትን ለምን እንደሚያውጅ በውል ሊመረመረ የሚገባው ጉዳይ ነው።

ህወሃት ለሱዳን የሚሰጠውን መሬት በትክክል ሱዳን ትጠቀምበታለች ብሎ አስቦ እንዳልሆነና ሱዳኖች ግብር እየከፈሉ ለከብት ግጦሽ ይጥቀሙበት የነበረ የኢትዮጵያ መሬት እንጅ የሱዳን ይዞታ አለመሆኑን ያውቃሉ።የሚያውቀ ከሆነ ለምን መሬታችን አሳልፈው ይሰጣሉ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይህ ግልጽ ነው የህዋሃትን አጀንዳ ምንድን ነው ብሎ ማየት በቂ ነው። ሱዳን ያላትን ኃይል በሙሉ የተሰጣትን መሬት ለሚያለሙ ጥበቃ መመደብ አለባት ወይም ህወሃት የራሱን መከላከያ ኃይል መመደብ አለበት።ይህ ካልሆነ ገና ኢትዮጵያ ይገባኛል የምትለው መሬት ከሱዳን ሳይመለስ ሌላ ወሰን ዘላ እንድትገባ ማድረግ አካባቢውን ሰላም ለማሳጣትና ደም ለማፋሰስ ካልሆነ መሬትህ ይወሰድብሃል የተባለውን የአካባቢ ሕዝብ ከማንም በላይ ህወሃት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በውጤቱ ማንም ትርፍ እንደማያገኝና በህወሃት ላይ የተጀመረውን የተቃዋሚ ኃይሎች ሥርነቀል የሥርዓት ለውጥ ትግልም ሊያዘናጋ እንደማይችል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በርግጥ እንደዚህ ላለው ቀን የሚሆኑትን ውድ የሀገር ልጆች አስቀድመው ገድለዋቸዋል፤ አስድደዋቸዋል ወይም በሌላ ምክንያት በዚህ ክፉ ቀን ለሕዝብ እንዳይደርሱ ተደርጓል። ይሁን እንጅ «እሳት ከነበረበት ረመጥ አይጠፋም ይባላልንና» ጀግናው የሽንፋ ሕዝብ ፤የመተማ የቋራና የአዳኝ አገር የጫቆ ሕዝብ ፤የወልቃይት የጠለምት የጠገዴና የአርማጭሆ ጀግና ሕዝብ ዛሬም እንደትናንቱ አባቶቹ የሚከፈለውን ከፍሎ ድንበሩን እንደሚያስከብር እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።እንደዚሁም የሌላው አካባቢ ኢትዮጵያዊ የጥቃቱ ዒላማ የሆነው የራሱን የጎበዝ አለቆች እየመረጠ በመተባበር ድንበሩን ማስከበር ይኖርበታል። በተናጠል እየገጠመ የጥቃቱ ሰለባ መሆን አይገባውም የሚገጥመው ከሱዳን ብቻ ሳይሆን ከህወሃትም ጋር ስለሆነ «አንድነቱን አጠንክሮ መዋጋት አለበት በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊም አቅሙ በሚፈቅደው መጠን ሕዝቡን ማገዝና ከተቻለም እዛው ተገኝቶ የሕዝቡን ሞት መሞት ክብር ስለሆነ ታሪክ ሊሰራ ይገባዋል እዚህ ሆኖ ማቅራራቱ በቂ አይደለም። ህወሃትን በሚፈልገው ቋንቋ ማናገር ስንችል ነው ሀገርና ሕዝብን የምናድነው;» ከባዶ እየተነሱ ሚንስትር ለመሆን መሮጥና ፈርም ከተባለው ላይ እየፈረሙ ታሪክን ማበላሸት  ሳይሆን ለተተኪ ትውልድ ለሀገር ለሕዝብ ማሰብ ይገባል።ያሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር ያለፈውን ጠቅላይ ሚንስትር ውዝፍ ሥራዎች ለመጨረስ ከሆነ ቦታውን ይዞት ያለው ባዶ ቀፎ ከመሆን አይዘልም ። መለስ ሀገርን አጥፍቶ የረጅም ዓመት የቤት ሥራ ጥሎልን ሄዷል።አሁን ያለው ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሌላ ሰው ነው ታሪክ መስራት መቻል ያለበት አሁን ነው።ሥልጣኑን መጠቀም ያለበት በል እያሉ ከኋላው ተቀምጠው ለሚጋልቡት ሳይሆን ለራሱ ፤ለቤተሰቦቹ ለሀገር ለህዝብ በተለይም ለተተኪው ትውልድ አስቦ መሥራት ይኖርበታል። በተለይ ጠቅላይ ሚንስትር  ኃይለማሪያም ደሳለኝ  ሥርዓቱን በማራመድ እንደማንኛውም ተጠያቂ ቢሆንም ጎልተው እንደወጡት የህወሃት ነብሰ ገዳዮች የሚታደን አይመስለኝም እነሱ የደረሱበት ልድረስ ብሎ የሚሮጥ ከሆነ ግን ፍርሃትን እንዳዘለ ውለህ ግባ ሳይባል ከጨዋታው ይወጣል። መመርመር ያለበትም ይህ የመሬት ስጦታ ውል የድሮ ህወሃት አጀንዳ  ኢትዮጵያን ለመበታተንና ወደ መጨረሻም «ታላቋን ትግራይ ትግርኝት ሪፐብሊክ » ለመመሥረት በነበረው ወቅት ስለሆነ ወደ ፊት ከእጁ ያለውን ክብር የሚያሰጥና በሕዝብ ዘንድ እምነት እንዲጣልበት የሚያደርግ ተግባር መፈጸም ያለበት ይመስለኛል። ሕዝቡን ለማጭበርበር ጡረታ ወጥተዋል የተባሉት ዛሬም በቁልፍ ጉዳዮች ላይ እጃቸውን እንደሚያስገቡና ውሳኔ እንደሚሰጡ መዘናጋት የለብንም  ለማንኛውም እነሱም ሆኑ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የህወሃት ገዥዎች በጎ ነገር እንዳይታያቸውና እንዳያስቡ የሚገፋቸው ችግር ብዙ ነው።ለምሳሌ ይህ ዛሬ የተነሳሁበት ሃሳብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት የሆነውን መሬት ለሱዳን አሳልፎ መስጠት የሀገርን ልዓላዊነት የሚነካና የተዳፈረ ተግባር ነው፤ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል እርስ በርሱ እንዲጋጭ አድርገዋል፤ገድለዋል ፤አስረዋል፤አስድደዋል፤አፈናቅለዋል፤የኢትዮጵያዊ ዘግነት መብቱን ገፈዋል፤ሀብት ንብረቱን ዘርፈዋል…ወዘተ ይህ ወንጀል ነው።ይህ የሕሊና እርፈት ይነሳቸዋል በውስጣቸው ሰላም እንዲያጡ ያደርጋቸዋል ይታመሳሉ።በሰላም ጊዜ ከሕዝብ ጋር እንዳይኖሩ የሚያደርግ ተግባር ስለፈጸሙ ከሕዝብ መነጠላቸውን ስለሚያውቁ ሕዝብና ሀገርን በማወክ ሥራ ላይ ብቻ የተጠመዱ ናቸው።ስለዚህ አዲሶችና ወጣቶች ወደ ሥልጣን ገበታው ብቅ ያሉትን በህወሃት ስብስብ ውስጥ ለመታቀፍ የሚያስችል ወንጀል እንዲፈጽሙ ያደርጓቸዋል። ልክ አይደለም ይህ መሆን የለበትም የሚሉትን ደግሞ ደብዛቸው እንዲጠፋ ይደረጋሉ። ጠቅለል አድርገን ስንመለከት የህወሃት አመጣጥና ወደፊትም ግዞው ይህ ነው የሚሆነው። የበሉበትን መሶብ የሚደፉ የእናት ጡት ነካሽ ይሏል ይህ ነው።

የኢትዮጵያ የቦርደር ኮሚቴ(በውጭ የሚንቀሳቀሰውን የሕዝቡን የኢትዮጵያ የቦርደር ጉዳይ ኮሚቴ ማለቴ ነው) በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን መግለጫዎች ፤በራዲዮ የሚደረጉ ቃለ-ምልልሶች ተከታትያለሁ ለገዥው ቡድን የተላከ እንደሚሆንም አምናለሁ።አንዲት የምትጣል ነገር የላትም የኢትዮጵያና የሱዳኑን ድንበርም ከማንም በተሻለ ስለማውቀው የቦርደር ኮሚቴውን ማመስገንና እንዲበራቱ ማድረግና የምናውቀው ማስረጃ ካለን እንድንሰጣቸውና ከጎናቸው እንደንቆም እየጠየቅሁ ገዥው መደብ አሁንም ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ አቋሙን እንዲመረምርና ውሳኔውን እንዲያነሳ ወደ ግጭቱ ሳንገባ መፍትሄ እንዲሰጡበት ማስጠንቀቅ እወዳለሁ።እሳቱ ከተጫረ በኋላ ሰማይ መሬቱን ማየት ፍሬ አይኖረውም። ምናልባት ይህን ስል ይህ ሰው እብድ መሆን አለበት እንደምትሉኝ ይገባኛል። በጣም ጤናማ ሰው ነኝ። ህወሃትና እኔ ስለምንተዋወቅ በገዳዳሙ ምን እያልኳቸው እንደሆነ ግጥም አድርገው ያውቁታል  ለአይን ጤና።

በመጨረሻ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እንጅነር ይልቃል ጌትነት በዋሽንግተን ዲሲ በጠሩት ስብሰባ የታደሙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ ስለድርጅቱ ምንነት ሌሎችም ጉዳዮች ካዳመጡ በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር ሁሉም ጥያቄዎች በተገቢው ተመልሰዋል ብየ አምናለሁ።አንዱና ሁሉም የተቃዋሚ ኃይሎች ሆነ እኛም ልንመልሰው ያልቻልነው ጥያቄ የአንድነት ጥያቄ ነው። ጥያቄው ለእንጅነሩ ቀርቦ ነበር እንጅነሩ ወጣት ነው የሚገርመው ነገር ግን ያለው ፈሪሃ እግዚአብሔርና ትግስቱ ትህትናውና ለወገኖቹ ያለው አክብሮት ምንኛ የላቀ እንደሆነ በአንክሮ ተመልክቸዋለሁ። ስለጥያቄው ሲመልስ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ስለ አንድነት ግንባታ የሄዱበትን ርቀትና ወደፊትም በአንድነት ግንባታ ጉዳይ የድርጅቱን ራእይ በግልጽ አስቀምጦ አንድ ቦንብ የሆነ ጥያቄ ግን ለሁላችንም በተራው ጠይቆናል። ኃይለኛ ጥያቄ ነው። ሰማያዊ ፓርቲ ሆነ ሌሎች የተቃዋሚ ኃይሎች በአፋኙ የህወሃት አምባገነናዊ ሥርዓት እየተዋከቡ ፤እየታሰሩና እየተደበደቡ በዱላ እንደ እባብ ራስ እራሳቸውን እየተቀጠቀጡ አንድነት ለመፍጠር ያንጎላቹ ቢመስሉም አልተኙም እንደማለት ነው።ሁሉም ሥርአቱን እየተጋፈጡ በጋራ ለመስራትና ወደ አንድነት ለመምጣት የሚያደርጉትን ጥረት ገልጾ ነገር ግን እኛ እንዲህ ባለ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በዚህ በውጭው ዓለም ዴሞክራሲ በሰፈነበት አገር በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት ለምን አንድነት የፈጠረ «የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ» አልፈጠራችሁም? የሚል ጥያቄ ነበር ለቤቱ የጠየቀው።«የሽ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ» እንደሚባለው እስኪ በራሳችን ላይ እንፍረድና ከጥቂቶችና በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር ሰላም እንዲፈጠር አንድነት እንዲገነባ የሚያደርጉ አጀንዳዎች ዙሪያ ተነጋግረን እናውቃለን? መቼ? በቴሌ ኮንፈረንስና ፓልቶክ እንደምትሉኝ ገባኝ እሱ አይደለም። በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ሰጥቶ በመቀበል፤ አንተ ትብስ አንቺ በመባባል ኢትዮጵያዊ ባህል በተላበሰ መልኩ ተከባብረን ተመካክረን ሳንፎካከር ትግሬው አማራውን ሳይዘረጥጥ ኦሮሞው ጉራጌውን ሳይነቅፍ ሁሉን አቀፍ መድረክ ፈጥረን ለእኛም ሆነ ለተተኪው ትውልድ ታሪክ ለምን አንሠራም? እንጅነሩ ጥሩ የቤት ሥራ ሰጥቶናል እስቲ ስንቶቻችን እንደጎበዝ ተማሪ የእንጅነሩን ጥያቄ መልሰን እንደምንመጣ እንይ። በተለይ ጋዜጠኞች ፤ኢሳት እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ አክቲቪስቶች በዚህ ዙሪያ ዳሰሳ ብታደርጉ መልካም ነው እላላለሁ።


ኢትዮጵያ ልዓላዊነቷ ተከብሮ ለዘላዓለም ትኑር!!!

ጨርሰን ሳናልቅ ህወሃት የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አያስረክብም!!
Pen(ጌታቸው ከሰሜን አሜሪካ)
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

No comments:

Post a Comment