ከሸንጎ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ባለፉት ሳምንታት እና ጥቂት ወራት ብቻ አሳፋሪ በሆነ መልኩ በአረና ፓርቲ አባላት ላይ ድብደባ እና አሰጸያፊ
ተግባር ተፈጽሟል። ለምሳሌም ባለፈው ሳምንት ማለትም በጥር 16 ቀን 2006 ዓ/ም በኣቶ ኣስገደ ገ/ስላሴ፣ ኣቶ
ኣብርሃ ደስታ፣ አቶ አንዶም ፤ መምህር ፍፁም ግሩም፣ ገዛኢ ንጉሰ እና ሌሎችም የአረና አባላት ላይ በዓዲግራት
ከተማ ድብደባ እና አስጸያፊ የሆነ ተራ የዱርየ ምግባርን የሚያንጸባርቅ ክብረነክ ተግባር ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ይህ የሆነው የአረና አባላት የገዥው ቡድን የማስፈራራት ዘመቻ ሳይበግራቸው ስርአቱ በመፈጽም ላይ ያለውን
ግፍ እና በደል ለትግራይ ህዝብ ለማሰማት የሚያደርጉትን ተጋድሎ ለማጨናገፍ ነው። እጅግ አሳፋሪ የሆነው ጉዳይ
ደግሞ፣ ገዥው ቡድን ለዚህ እኩይ ተግባሩ ህጻናትን በማሰማራት የአረናን አባላት በመከታተል እንዲሰድቡ፣
እንዲደበድቡና ተመሳሳይ አሳፋሪ ተግባር እንዲፈጽሙ ማድረጉ ነው።
ኢትዮጵያዊ ባህላችን ህጻናት ታላቆቻቸውን እንደ ወላጆቻቸው አክብረው እንዲያዩ ያስተምራል። ገዥው ቡድን
ህጻናትን በዚህ አይነቱ እጅግ ዝቅ ያለ አሳፋሪ ምግባር ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረጉ፣ ለአካባቢውም ሆነ ባጠቃላይ
ለኢትዮጵያ ህዝብ ባህል ምን ያህል ግድ የሌለው እንደሆነ ያሳያል። በተጨማሪም ገዥው ቡድን ከርሱ የተለየ ሀሳብ
ያላቸውን ለማኮላሽት ምን ያህል እንደሚጓዝና በአሁኑ ሳአትም ምን ያህል የሚይዘውና የሚጨብጠው እየጠፋበት እንደሆነ
ያመለክታል።
ገዥው ቡድን የትግራይን ህዝብ በቋሚ እስረኛነት አፍኖ ለመያዝ በሚያደርገው መፍጨርጨር ቀደም ባሉ ወራቶችም
በመቀለ፣ በክልተ አውላእሎ ፣በሽረ፣ በማይጨው፣ በተምቤን ዓብይ ዓዲ እና ሌሎችም ከተሞች ህዝባዊ ፖለቲካዊ
ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ እጅግ ስፊ አደናቃፊ ተጋባሮችን ሲያካሂድ እንደነበር ይታወሳል፡፤
ገዥው ቡድን ተቃዋሚውን የማዋከቡን ሩጫ በመላ ሀገሪቱ በስፋት እያካሄደ ሲሆን በቅርቡም በደቡብ የሀገራችን
ክፍል አቶ አለማየሁ ለፌቦ የተባሉ የሲዳማ ጭሬ የአንድነት ፓርቲ አባል የፓርቲያቸውን ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፈው
ሲመለሱ ያለምንም ወንጀል ለእስር እንደዳረጋቸው ይታወሳል።
የሰማያዊ ፓርቲ አባላትም መሰረታዊ መብታቸውን በመጠቀም ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ በሰልፍ ለመግለጽ በሚያደርጉት ሙከራ ተመሳሳይ እንግልት እየገጠማቸው ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሽንጎ) በአረና፣ በአንድነት፣ በሰማያው ፓርቲ እንዲሁም በሌሎች ላይ
በገዥው ቡድን የሚካሄደውን አፈናና የመብት ረገጣ በጥብቅ ያወግዛል። ህጻናትን ለፖለቲካ መሳሪያ መጠቀሚያ ማድረግ
እጅግ ህገወጥ እንደሆነ እየገለጥን ይህ አሳፋሪ ተግባር ባስቸኳይ እንዲቆም ሽንጎ ያሳስባል።
ሁሉም ኢትዮጽያውያን መሰረታዊ መብታችንን፣ ሀገራዊ ጥቅማችንን እና አንድነታችንን ለማስከበር ፍርሀትን አስወግደን የጋራ ትግላችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ሽንጎው አሁንም ያሳሰባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of
various information and content providers. The Website neither
represents nor endorses the accuracy of information or endorses the
contents provided by external sources. All blog posts and comments are
the opinion of the authors.
No comments:
Post a Comment