Saturday, January 18, 2014

ቴዲ አፍሮ የቅኔ ዕንቡጥ – ለእናቱ ልዩ ዓርማ ነው!


ከሥርጉተ ሥላሴ 16.01.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)
“የሰው ልብ መንገዱን ያዘጋጃል እግዚአብሄር፤ ግን አካሄዱን ያቃናለታል“ (ምሳሌ ምዕራፍ 16 ቁጥር 9 )
የሀገሬን ክብር አዝልቀህ – ልታደምቅ ታጥቀህ ተነስተኃል – አንተ የቅኝት ብርቅ፤ ራዕይ — አብነት። እማን ከፍ አድርገህ ልታሸልማተኝ ጌጥ ዕውቅናዋ ፈክቶ ዓለምን ልትመስጥ። ተግተህ ትሠራለህ – አንተ የቅኔ ዕንቡጥ፤ የነፃነት ቃና – የትውልዳችን – ፈርጥ!
ባልባለቀው መንፈሴ – ቴዴ አፍሮ የተስፋዬ ፀሐይ ነው። ማህተም አለበት! teddy afro
ዋና በር … ከሳቢያ ጥረት ምክንያታዊ፤ ከሳቢያ ተኮር ድካምም ምክንያታዊ ተግባራት የድል ዋዜማ ናቸው። ምክንያቱም የችግሩን ምንጭ ከሥሩ የሚያደርቀው በምክንያታዊና መሬት በረገጠ ተግባር ብቻ ጨለማው ነግቶ፤ የምሥራች ለነፃነት የመሸለም ስበታቸው ሆነ አስገዳጅነታቸው ጉልበታም ናቸው። የሚያስቀሩት ፍርፋሪ ስለማይኖርም ዘላቂ ድህነት ያስገኛሉ። የመፍትሄ መንገድ ጠራጊ የችግሩን ሳቢያ ማወቁ ሳይሆን ይልቁንም ምክንያቱን በሚገባ በልቶ ያማያዳግም መለስ ከመስጠቱ ላይ ነው። ምክንያት ተኮር የምርምር ተግባር በሸታውን ያገኛል። ህመሙን ከሥሩም ይነቅላል። ሳቢያ ተኮር እርጃዎች አቅመቢስ በመሆናቸው፤ ዋስትና የማይሰጡ ማስታገሻ ናቸው፤ አዘናጊ ልፈስፍስ ዝልቦ መንገዶች ናቸው!
ምልሰት፣ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008፤ በኢትዮ – አፍሪካዊው የቅኔው ልዑል በብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ሥም በሰዬምኩት ማህበራዊ ድህረ ገጽ፤ እንዲሁም በጸጋዬ ድምጽ ራድዮ ፕሮግራሜ ቃሊቲ ውስጥ ለነበረው ታናሼ „ሥምን መላዕክ ያወጣዋል“ በሚል አንድ መጣጥፍ መጻፌን ብቻ ሳይሆን በድምፄም ማቅረቤን አስታውሳለሁ። ልቤ ውስጥ የገባ የቅኔ ቀንበጥ ነበርና ቴዲ አፍሮ። ስለ ወጣቱ ከያኒ – ገጣሚ – ዜመኛ – ድምጽ ቃና፤ እንዲሁም የአቀራረብ ብቃት- በዛ ጹሑፌ ላይ ሥራዎቹ ተተርጓሚነታቸው (interpretable) እንዲሁም ተዋራራሽነታቸውን በስፋት ነበር የገለጽኩት።
የድርሻዬን ይባልለት – ስለ ይፈልቃል ገና!
ዛሬም ደግሞ ትንሽዬ የግል ዕይታዬን ለማለት ትክሻዬን ለሚወርደው ዱላ አስመችቼ ለመቀበል ቆረጥኩና እንዲህ ልል ነው። በዚህ ፈታኛ ወቅት መቆስቋሻ የሚያስፈልግበት ሳይሆን ገብቶ መርመጥመጥም ይጥማል። ፈተና ተፈልጎ የማይገኝ ከተገኘ ግን አንጥሮ የሚያሳምር ሜሮን ነው። አባቶቻችን ፈተናቸው ሲዘገይ ወይንም ፈተና ቸልም ብሎ ሲረሳቸው ሁለት ሶስት ሱባኤ ይይዛሉ። እኔው የእነሱ ህይውት ኑሮኝ በመንፈሳዊ ዘርፍ ብጣቂ ዘር ባይኖረኝም። በገኃዱ ዓለም ግን እኔም ፈተና ሥልጡን አድርጎ ቀርፆኛል። ተላምጄዋለሁ። ከጋሼ ጸጋዬ ፍቅር መንጭቶ በውሰድኩት የድህረ ገጽ ስያሜ ብርትዬም ታስራ በነበረችበት ውቅት ተግቼ በብዕር ብቻ ሳይሆን በተገኘው አጋጣሜ ሁሉ መፋለሜ፤ እኔን ቢደቁሰኝም፤ ክሱ ሀገር ምድሩን ቢያዳርስም እኔኑ ቢያደቃኝም፤ የወረደው ማዕት …. ግን ኃይልና ብርታት ሰጥቶት ከዛ በኋላ የተከደኑ ብዙ ሲሳዮችን እንድከውን አምላኬ ረዳኝ። ቀን ሲወጣ ታላቋ ኢትዮጵያ ትንቆጠቆጥበታለች። አዎን! እኔ በምኖርበት ሀገር ኢትዮጵያ የምትባል ታላቅ ሀገር ጸጋዬ የሚባል የኢትዮ አፍሪካዊ ፈላስፋ ዕውቅናቸው ሙሉዑ እንዲሆን ሆኗል። የኦነግን ተልዕኮ ለማሳካት ሆነ በቅዱስ ወንጌል ሰባኪ ተብዬ ክስ ተመስርቶብኝ ነበር። ለዛውም ለአንስት ባልተሰጠኝ ጸጋ ብከሰስም አሸነፍኩ። ተመስገን። እድሜ ለሚሹንግ ዩንቨርስቲ ታላቅ ሚዛናዊ ኢትዮጵያዊ ሙሑር። ብዕራቸው ከእሥር አስለቀቀን በጋራ ….. ሰላምም አሰፉን። ምስክርነታቸው አንጀት አርስ ነበርና። አለን ሚዲያዎቼ እና እኔ እንደ አመረብን። ፈቃዱን ለሰጠኝ ለራዲዮ ፕሮግራሙ ቲም የተሰጠው አጥጋቢ ጥሁፍም በእጄ ላይ ይገኛል።
እግዚአብሄር ይመስገን የ21ኛው ምዕተ ዓመት ታላቅ ሥራ የሆነውን የደራሲ አቶ ምስብእክ ወርቁን „ዴርቶ ጋዳን“ ረቂቅ ወጥ ሥራ ጭብጥ ሳስብ፤ የቴዲን በጋሼ ጸጋዬ ዙሪያ የሰራቸውን ድንቅ ጽጌረዳዊ ተግባር በመንፈሴ ደም ሳዘዋውር፤ የመንፈስ ቋሚ ትውፊታችን በዕድሜ ተከታዮቼ እንዲህ ፋፍቶ ሳልሞት ቆሜ በህይወት በማዬቴ እግዜአብሄር ይመስገን። አሜን! የኔ ታናሾችን እግዚአብሄር ያኑልርኝ። ደሜ ቋንቋ ቢኖረው የሚናገረው ቋንቋ ጸጋዬ በሆነ ነበር – ተግባባን?! እኔ ጋሼ ጸጋዬን እማውቀው ኢትዮጵያዊ ሆኖ እናቱን – ሰንደቁ ሲያደርግ ነው። ክብራችንም ነው። ጉልህ የቋንቋ ሊቅም።
አሁን ወደ ተነሳሁበት ወጣቱ የተወቀሰበትን „ጥቁሩን ሰው“ ለእኔ የሰጠኝን ንጹህ ትርጉም ለሌሎች ወገኖቼ ለምን አልሰጣቸውም ብዬ አላዝንም። ውበት እንደ አካባቢው ስለሚተረጎም። እኔ በሚታዬኝ፣ ለእኔ በሚሰማኝ ውስጥ እነሱ ላይኖሩ ይቻላሉ – ለእኔ አርቲስት ቴዲ አፍሮ ሥጦታ ነው። ለትውልዱ በጣምራ ገለጻ አንገት ነው። ባለዜማዎችን ለዘመኑ ሊመራ የሚችል ምልክትም ነው። ይህ ወጣት የከወናቸውን ተግባራት በማስተዋል ሆነን ስናነባቸው አሱም ሆኑ ሥራዎቹም አርማችን ናቸው። ባለመታደል ሆኖ እንጂ። ከዚህ ሌላ እኔ የወጣቶች አደራጅ ስለነበርኩኝ ስሜታቸው በጣም ቅርቤ ነው። „የልጅ ነገር አንዱ ፍሬ አንዱ ጥሬ ሆኖ“ ነው እንጂ በዚህ ዙሪያ መሬት ዬያዘ ሰፊ ጥናት ከወጣቶቹ ጋር ሰርተን ነበር። ከእጄ ቢኖር እንዴት ወርቅ በነበረ። በሌላ በኩልም ወጣትነት ሁላችን ያለፍንበትም ነው።
ለማንኛውም ወጣት አትሁን ማለትም የፈጣሪን ታላቅ ተፈጥሮዊ ዶግማ ሆነ ሥልጣን መጋፋት ይመስለኛል። በዚህ አፍላ ዘመን ስንት ቦታ ይደረሳል። ወጣትነት ሳተናነት ነው ….. በእኔ ስሜት ማዕቀፍ ውስጥ ያለው የነፃነት ትርጉም፤ የማንነቴ ጣዝማ በመሆኑ የውስጤ ፍጹም ገዢ ነው። ነፃነት ማንነት ላለው እኔነቴ አንጎሉም ነውና። ማናቸውም የገኃዱ ዓለምን የኑሮ ስንክሳሮች የማያቸው ሆነ የምመዝናቸው እኔን ከሰጠኝ ብሄራዊ ነፃነት በታች እንጂ በላይ ከቶም ሊሆን አይችልምና። ከዚህ አንጻር ቴዲ አፍሮ ለትውልዱ ጥበብ ነው። አጀንዳዎቹ ኢትዮጵያና ነፃነቷ ስለሆነ – የሥርጉተም።
ስለሆነም „የጥቁሩ ሰው“ ፊልም በሙዚቃ የተቀነባበረ ብቻ ሳይሆን እኔ ሳዬው፤ እውነትም ለመናገር፤ ፊልሙ በዛ ዘመን የተሰራ ነው የመሰለኝ። ማለት ትዕይንቱ ጦርነቱ እዬተካሄደ የተቀረጸ ዓይነት ነው። ጭብጡና የጭብጡ ማዕከላዊ ተልኮዎ በሥርዓተ ተክሊል በፍጹም ሁኔታ በተፈጥሯዊ አኃታዊነት የተጋቡ ናቸው። በጣም የተዋጣለት ታላቅ ተግባር ሆኖ ነው ያዬሁት። ከዚህ ባለፈ ድሉ ሙሴውን – የህዝብ ስለመሆኑም አባወራ ጀግኖቻችን በነቂስ አውጥቶ ነው የተቃኘው ስለሆነ ይህ ወጣት በቀደመው፤ በዛሬው ወይንስ በሚመጣው በዬትኛው ዘመን የተፈጠረ ነው በማለት በልቤ ውስጥ ባለችው ሙዳይ ወስጥ እጅግ መስጥሬ አስቀመጥኩት። መብቴ ነው። እኔ እንደዚህ ላሉ ወጣት ጀግኖቼ አብዝቼ እሳሳላቸዋለሁ፤ ሰብስቤ በማህጸኔ ውስጥ ባስቀምጣቸውም እወዳለሁ፤ ዓለም ቀናተኛ ስለሆነች እንዳትነጠቀኝ ስለምሰጋ
teddy afroየወጣቱን ንጥር ተግባር ብቁ ከሚያደርጉት መሰረታዊ ነገሮች ግጥሞቹ ጥልቅ መሆናቸው ነው። ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ በነብይነት ማያያዣ ፈጥሮ ያወራርሳቸዋል። ጥበብ ማለት ይህ ነው። ግጥምጥሞሽ ያልሆነ። እርግጥ ነው በግልብ ካዬናቸው ጊዜያዊ ደስታ ወይንም የማንደግፈው ከሆነም ጠብ አጫሪነ ስሜትን ቀስቅሶ ሊያበሳጨን ይችላል። አብሶ ከመልዕክቱና ሰብሉ ሊያለማ ከፈለገው ማዕከላዊ ማሳ ካልተነሳን እንደ መደዴ የቃላት ድርደር አድርገን ልንመከተው እንችላለን። የመልዕክቱ ውስጥ ንዑድ መንፈስ ነፃነት ነፃነት ነፃነት፤ ተፈሪነት ተፈሪነት፤ ገናናነት ገናናነት፤ ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊነት – አፍሪካዊነት ነው – የዓለም አብነት ኢትዮጵያ! ይህ ነው ውስጣችነን የወያኔ ሸፍጥ ካላሸፈተው …..
እያንዳንዱን ስንኝ በተን አድርገን በቁሙ ሳናነብ ውስጡን በቅንነትና በአዎንታዊነት ስንፈትሸው ቃሎችን ከስንኙ ሐረግ ነጥለን በመልካቸው ስናይ ደግሞ ቀለማችን አጉልቶ፤ እኛነታችን አብርቶ፤ ፍቅርን እንደ ታቦት ከብክቦ፤ ሩቅ ተጉዞ ሰላምን በናፍቆት ይጠራና ውስጣችን አስተቃቅፎ፤ ነገን በተስፋ ቀይሶ ይመከረናል፤ ያስተምረናል። ይፈትሸናል። ፍላጎታችን ኮትኩቶ የአቅጣጫውን ቅዬሳ ናሙና ከመንፈሳችን ሰርበዬር ውስጥ በሳቢነት ይቀርጸዋል። …..
እንዲሁም „ጥቁሩ ሰው“ በሀገራችን የነበረውን፤ አሁን ያለውን የሥነ ጥብብ እድገት ሥልጣኔም ቁልጭ አድርጎ ያሳዬናል። „ይህ የትውልድ ክፍተት አለበት፤ ወጥ ሥራዎች ተራቆቱ፤ የቀደሙት የሙዚቃ ስንኞች ቃናቸው ከዕውነተኛው ወይንም ከጋህዱ ዓለም ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ነበሩ። መሬት ያያዙ ነበሩ፤ ስለሆነም ወስጥን የመግዛት አቅም – ኃይልና – ስበት ነበራቸው። የዛሬዎቹ ግን ቤታቸው እንኳን አይመታም፤ ሥር አልሰደዱም“ … ወዘተ
… ለሚሉት ዕውነት ለመናገር የአርቲስት ቴዲ አፍሮ የመንፈስ ምርት ጥያቄያቸውን ሁሉ በአግባቡ የመለሰ ይመስለኛል። ደግሜም እላለሁ … እኔ አሁን ለተፈጠሩት ወጣቶች እጅግ ታላቅ አክብሮትና አድናቆት አለኝ። በስለው ነው የተወለዱት ማለት እችላለሁ። መድረክ ሲያገኙ የማዬው ብቃት ከቶውንም ሊለካ የማይችል የመንፈስ ሐሴት ይሰጠኛል። ለዛውም በዚህ ሙጃ ሥርዓት፤ በዘመነ ወያኔ ተወልደውና አድገው … ሞት ያልተዋጀበት አንድም የኢትዮጵያዊነት የመንፈስ ተቋም በሌለበት …. ይህን ጥሰው የወጡ የዘመኑ ጥቁር አንበሶች ናቸው – ለእኔ።
ንጽጽር፤
የብዙ ታዋቂ ዓለምዓቀፍ ባንዶችን ኮነሰርትን አብዝቼ እከታተላለሁ። የወጣቱ የፈጠራ ብቃት እኔ ነኝ ካለ ባንድ ጋር ሊመጥን የሚችል በቂ አቅም እንዳለው ነው ያዬሁበት። የቴዴ ሥራዎች መነሻ እሩቅ አይደለሙ። ከእናቱ ጓዳ፤ ከተጨባጩ ጭብጥ ስለሆነ፤ ስሜትን የመሳብ ችሎታው ብቻ ሳይሆን ስሜትን ተቆጣጥሮ የማቆዬት ጉልበቱም አንቱ ነው። ሁሉን ነገር፣ ሁሉን አካባቢ በቅኑና በትሁት መንፈስ ይዳስሳል። አንዱ የግጥም ዜማ በራሱ አንድ መጸሐፍ ይወጣዋል። ይህ ለኢትዮጵያ የሥነ – ግጥም ሆነ ሙዚቃ ነገ አዲስ አቅጣጫ ነው። ለማግሥትም ብቁ እርሾ!
ሌላው ቅኝቱ ራሱ መሰራቱ፤ ፍሬዘሩ ከውስጡ መፍለቁ፤ ከዚህም በላፈ የስንኙን ፍሰት ሳይጎዳ እንደ ራሱ ውስጠት አድርጎ፤ ጤናቸውን ጠብቆ፣ ሴላቸው ሆነ ደም ሥራቸው ሳይጎዳ፤ ኦርጋናቸው ሳይነደል እንደ ተፍጥሯቸው ስለሚቀርበው ይህ ደግሞ የወጣቱ ልዩ መለያ ጸጋው ነው። /ጀርመኖች አውስጌቦልሼ ታለንት/ ከሰው ዘር የተለዬ መክሊት እንደ ማለት። በዬሙያው እንዲህ ያሉ ሁለት አንጎል ያላቸው ይፈጠራሉና። በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊነት በጠላትነት ተፈርጆ፤ በፖሊሲ ደረጃ ወያኔ ተግቶ እዬሰራ፤ በዘመኑ ተፍጠሮ ግን፤ የወያኔን ኢትዮጵያዊነትን የማፍረስ ፖሊሲ የቀደመ፤ የበለጠ ሥራ ነው። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ረጅም ዓመት ከደከመበት የቴዲ ስንኞች የበለጠ ያፈሩና አርበኞች ናቸው። ለኢትዮጵያዊነትም ዘብ አደርም ናቸው። ሥነ ጥበብ ወተቱ የአድማጭ የሰላ እርምት ነውና ወጣቱ እርማቶችን በጸጋ ተቀብሎ ማስተናገድ ከቻለ አንድ ትውልድ የመፍጠር አቅሙ አንቱ እንደሚሆንም አልጠራጠርም።
የቅኔው ልዑል ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ያን የመሰሉ ሥራዎቹን፤ ትውልድ የማይተካው ያ …. ዕንቁው ጋሼ ወጋዬሁ እሸቱ ነበር የሚተውንለት – የሚያነብለት። መዳህኒተዓለም አባታችን ንጉሥ ዳዊትን „እንደ ልቤ“ አለው ለጋሼ ጸጋዬም እንደ ልቤ ነበረው ጋሼ ወጋዬሁ። ዕድለኛ ነበር። እንደ ውስጡ ሆኖ፣ ከውስጡ የተቀመጠ ለእሱ ጸጋ ብሎ አምላኩ የመረቀለት ጋሼ ወጋዬሁ ነበር። ትውናው እንደ እራሱ ውስጥ አድርጎም ያቀርብለት ነበር። የጋሼ ጸጋዬ ስሜቱ መንትዮሽ በአህትዮሽ እንደ ነበር ይሰማኛል። መቼም እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ በሺ ዘመናት አንድ ጊዜ ወይንም ሁለት ጊዜ ነው የሚከሰተው። ከዚህ አንፃር ውስጡን ከእነተፈጥሮው ማቅረብ መቻሉ ለቴዴ ዕድለኛነቱን ድርብ ያደርገዋል። በስሜቱ የፍልጎት ልብ ውስጥ እሱ እራሱ በመንፈስም በአካልም አለና። ተቀድቶ የማያልቀው ውበቱም ይህ ነው። ወጣቱ ከያኒ የጻፈውን እራሱ ያቀርበዋል …. እራሱ አቀናብሮ እራሱ ያስጌጠዋል። አደራጅቶ፤ ውስጡን የሚገልጽለት ሌላ ሰው ቢያስፈልገው ኖሮ ከባድ ነበር። ግን እድሉና ምርቃቱ ወፍ አወጣቸው። ስለሆነም ተ — ጠ – በ – በ – በ – ት።
የሰማይ የላቀ ስጦታ!
እኔ የእግር ኳስ ፍቅረኛ ነኝ። እጅግ በጣም እግር ኳስን እወዳለሁ። አሁን ዬይድነቃቸው ልጆች ለእፍሪካ ዋንጫ በ2013 እ.ኤአ. ሲታደሙ ሰፊ የሆነ አትኩሮት ነበረኝ። ኢሮ ስፖርት ሀገራችን እንዴት ከፍ እዬደረገ ሲገልጸው እንደ ነበረ ማመን እስኪያቅት ድረስ እጅግ እጅግ ድንቅ ነበር። ያን ጊዜ አጋጣሚው ረድቶ ሀገሬ ኢትዮጵያ ከፍ አለች። ታሪኳ፤ የህዝቧ ባህል፤ ወግ ልምዷ፤ የነፃነት ገድሏ ሁሉ ተዘከረ። ኢትዮጵያን የኢሮ ስፖርት ፕሮግራም አቅራቢዎች ሆኑ አዘጋጆች ውስጣችን አሳምረው ነበር ኪናዊ አድርጎ ያነበቡን – ቀለማም አድርገው ነበር የኳሉን። ለእኔ ፈውስ ነበር። ዳንኩኝ!
መቼም ትውልዱ አዲሱ ማለቴ ነው በብዙ ፈታና ውስጥ ሆኖ፤ ግን ድንቅ ነገር ያሳዬናልና ከዓለም ዋንጫ ዝርዝር ውስጥ ዬኛዎቹ ሲገቡ ደስታዬ ወደር አልበረው። ታዲያ የመጨረሻ ማጣሪያው ከናይጀሪያ ጋር ሲሆን ግን አልተመቸኝም ነበር። አሳምሬ ናይጀሪያዎችን አውቃቸዋለሁና። የሆነ ሆኖ የኔዎቹ ማጣሪያ ሳያልፉ ሲቀሩ ዕንባ አውጥቼ ነበር ያለቀስኩት። የእውነት። እናት ሀገሬ፣ የመንፈስ ተክሊሌ፤ እምዬ ኢትዮጵያ – እንጀራዬ የመላ ዓለምን የእግር ኳስ ጨዋታን አለመገኘቷ አስከፋኝ። ልክ እንደ መጻፍ፤ መጸሐፍ ማንበብ ድንቡልቡሏንም ስለምወድ ብራዚል ላይ እመቤት ኢትዮጵያ ስትደምቅ ናፈቆኝ ግን ሳይሆን ሲቀር በጣም ተጎዳሁ። የኢትዮጵያ ጎል ጠበቂ ገና አልተወለደምና።
እግዚአብሄር ይመስገን … ሁልጊዜም የማምናበት ነገር፤ ኢትዮጵያ አምላክ አላትና ዕንቡጡ ቅኔ አህጉርን ወክሎ በ2014 የዓለም ዋንጫ ብራዚል ላይ መገኘት በራሱ ክብር ነው። የሰማይ የላቀ ሥጦታ ነው። ልዩ ምርቃት ነው። የሥነ ጥበብ ቤተኛ ታዳሚዎች ሁሉ ልንደሰትብት የሚገባው መሪ ድል ነው። ቅኔኛው ቴዲ አፍሮ እንደ አባቶቹ እንደነ የቅኔው ልዑል ብላቴ ጸጋዬ ገ/መድህን መንገድ ተከትሎ፤ የአፍሪካ ነገር መስመሩ ነበርና፤ ፈልጎ የተነሳለት ድንቅ ራዕይ ከሀገሩ አልፎ አህጉሩንም ሊወክል ነው። እግዚአብሄር ደግ አምላክ ነው እንሆ አደረገለትም። ጉዞው አቅጣጫው እጅግ አጓጊ ነው።
ፅኑ ዕይታ!
እናት ሀገር ኢትዮጵያ ስትከብር፣ ስትደምቅ፤ ከፍ ስትል፣ ዜግነት ሲያበራ፣ እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያ አፍሪካን በሥነ ጥበብ ጎራ ዳግም ልትመራ ስትመረጥ፤ ለመልካም ነገር ስትታጭ፤ ልዩ ፍጹም ልዩ ትርጉም ነው – ዕጹብ ድንቅ። ፍካታዊ ገጸ በረከት ነው። አበባዊ ረድኤት ነው። ለዚህ ተግባር ስኬታማነት እንደ ሰው የተገባን እናድርግ እንጂ፤ ትዕዛዙ ከመዳህኒተዓለም አባቴ ስለሆነ ሳንኩን ሁሉ አሸንፎ ሚሊዮን ፈን ያፈራል። አብሶ ጀርመኖች የሥነ – ጥበብ አክባሪና አፍቃሪ በመሆናቸው ለሽልማት ያጩታል። ጠብቁ። ቴዲን የቆዬ ሰው ይዬው። አፍሪካዊ ቪቫ ይሆናል። ዕውቅናውን አሳምረው ይሰጡታል። ሰፊ የሆነ በር ተክፍቶለታል። በሰውኛ ሥልጣን በሩን መዝጋት አይቻልም። „ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል“ ይላል ጎንደሬ ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነውና!
ጀርመን በሥነ ጥበብ ጉዳይ 13ኛው ፕላኔት ነው – ለእኔ። ፍጹም የተለዩ ናቸው። በደንበር – በክልልል – በቀለም በምንም ነገር አይደለም የጥበብን ልዩ ጸጋ የሚለኩት፤ በመንፈስ ቅዱስ ንዑድ ስሜት እንጂ። የሰማይ ጸጋን ለመተርጎም ሆነ ለማመሳጠር ተስጥቷቸዋል። ይህ ቀን እኔ ስመኘው ነበር። አንድ ዝግጅት ለጀርመን ህዝብ ቢኖረው በማለት። የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ከጀርመን አልፎ ዓለም ሊታደምበት እንሆ ፈጣሪ አምላክ ወሰነ። ተመስገን!
እኔ በግሌ በፈጣሪዬ ስለማምን፤ ደግሞም የሥነ ጥብብ ሰውነት ሥጦታው የሰማይ ስለሆነ ጥበቃው ሰማያዊ ነው። በድንግልና ውስጡን ሆኖ ስለሚጫወተው ሥነ ጥበብን ያምርበታልና ሰጪው አጥር ቅጥር ይሆንለታል።
አዎን! ቀኑ እስኪደርስ ድረስ በጥንቃቄ፣ በፆም በጸሎት፣ ከብዙ ነገር ታቅቦ፣ ለዚህ ማዕረግ ካበቃው ከአምላኩ ጋር ቴዴ መሆን እንዳለበት እንደ ታላቅ እህታዊ አስተያየቴን አካፍለዋለሁ፤ ህይወቱ ያላችሁ ደግሞ እንደ ዕምነታችሁ በጸሎት ትደግፉት፣ ትረዱት ዘንድ በትሁት መንፈስ እጠይቃችኋለሁ። ከፀሎት በላይ ጠበቂ የለምና። ከጸሎት በላይ ዘበኛ የለምና። ምክንያቱም ያቺ መከራዋና ፍዳዋ የጠናባት ልዕልት ኢትዮጵያ፣ ልጆቿን አብልታ ማሳደር ያቃታት እናት ሀገር፤ ሚሊዮን የነገ ፍሬዎች ጉርሻ አጥተው በጠኔ የሚረግፉባት አምላኳ አረሳትምና እንሆ ከፍ ሊያደርጋት ማቀዱ ዬምልዓት ዕንባ ካሳ ነው። ለአምላካችንም ለቅዱስ እግዚአብሄር ከእኛ የሚፈልገውን ምስጋናችን ሳናቋርጥ እንግለጽለት። በዚህ ዘመን አንድ ታዊቂ፤ ተደማጭ ለዛውም ወጣት ማፍራት ነገን ያበራልና።
የአይቮሪው ዓለምዓቀፍ ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫወች ዝሆኑ ድሮግባን፤ የዩክራይን ሁለት ወንድማማቹች የጀርመን ዓለም ዓቀፍ ቦክሰኞች ወስጥ ታናሹ ለዩክሬን ፍትኃዊ አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሲገኝ የዓለም ሚዲያ እንዴት ያረብርባል መሰላችሁ፤ የኛ ግን ትዕቢተኛው የሳውዲ መንግሥት የታላቅ ሀገርን ክብር ጠቅጥቆ ልጇቿን እንደ እንሰሳ አስፓልት ላይ እንደዛ ሲያርድ አንድ ለዕንባችን ዕውቅና የሚያሰጥ ታዋቂ፤ ተደማጭ፤ ዓለም ጆሮውን የሰጠው ዋቢ አልነበረንም። ነገ ግን ይኖረናል ….. ለዚህ ፈታናውን ተጋርቶ መረባረብ የግንባር ተልዕኳችን ነው። ጦርነቱ ተክፍቷል በድል ማጠናቀቅ አለብን! ማቄን ጨርቄን የለም! ለተደራጀ መሬት ለያዘ ተግባር እያንዳንዳችን በግል ሁላችንም በጋራ እንትጋ! ኢትዮጵያ ናት ፊት ለፊት ቁማ እሳት ውስጥ እዬተርመጠመጠች ያለችው። በኪነጥበቡ ይህ ዕውቅና ሲመጣ ደግሞ ግንባር መሆን!
በተረፈ ትምክህት ጎርፍ ነው፤ አድማም ጤዛ ነው። በሥነ ጥበብ ላይ ተደራጅቶ ጦርነት መክፈትም ወስጥን መፋቅ ነው። ፍቅር ግን የጸደቀ ፍሬ ነው። ኢትዮጵያዊነት የሚያሳፍር ሳይሆን የሚያኮራ፣ ተለምኖም የማይገኝ ምርጥ ዘርነት ነው። ውስጣችን የነጠረ ወርቅ ነው። ድህነታችን፣ የህዝብ መበደል፣ መንገላታት ደግሞ የሥርዓታት እንጂ እናት አንዱን ልጅ የክት ሌላውን የዘወትር፤ አንዱን አብልታ ሌላውን አስርባ በፍጹም አታውቅም። የወተት ጡት ጋቶቻ ለሁላችንም እኩል ማጥባትን አዘውትረው ይሻሉ …. ህግጋቶቿ ናቸውና። እቅፏም ለሁላችን ሳይዛነፍ በእኩልንት ነው። ማዕዷም እኩል ለሁላችንም ነው። ስለሆነም በእናት ሀገራችን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሁሉ መቆስቆሻ ሳንፈልግ ሁላችንም እኩል መማገድ በእጅጉ ያስፈለገናል። ፈተና መጥቷል – ማለፍን ይጠይቃል_! እናት ኢትዮጵያ የበደለችው አንድም ሰው የለም!
ክወና! …
ኢትዮጵያን የፈጠራት አምላኳ ምንጊዜም ስለማይረሳት እሷን ለማጠቃት የተነሱት ሁሉ የዶግ አመድ ይሆናሉ። በእኛ እድሜ እንኳን ሱማሌ፤ ኤርትራ፤ ግብጽ፤ አሁን ደግሞ ሱዳን ይታመሳሉ። አምላኳ ቀናተኛ ነውና። በ2012 እ.ኣ.አ. የአሳ ግማቱ ከአናቱ እንዲሉ እጬጌውን ከመንበራቸው፤ የጎጥ አፄውንም ደግሞ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ለኑዛዜ ሳያበቃ ነበር ያነሳቸው። ይህ ምርታማ መሬት፤ ለምለም አካባቢ፤ ሃብታምነት የሚባለውም ቢሆን አባታችን ከተከፋ ትል ከሰማይ ሊያዘንብበት ይችላል። እናስተዋል! —- ጉዳቱ ደግሞ የጋራ ነው እንደ ሰው ለምናስበው – ለእኛ።
እንኳንስ በተፈጥሮ ኤኪኖሚዋ ጥገኛ ለሆነ፤ ያልጠመጣጠነ ኤኮኖሚዊ ዕድገት ለሚገርፋት ኢትዮጵያ ቀርቶ የሰማይን ቁጣ እንጃፓን፣ ሱናሜም ማስቆም አልቻሉም። ይልቅ እንደ ሰው አስበን በዛ ቦታ ማን ይኖራል? ህፃናትን፣ አቅመ -ደካሞችን፤ ህሙማን፤ ነፍሰጡር ሴቶችን፤ እንሳሰት ሳይቀሩ ሊታስብላቸው ይገባል። ቀይ ቀበሮ እኔን ይገልጸኛል። ሶፍ ኡመር ዋሻ እኔን ያብራራኛል። ልዩ የሚባሉ አብዛኞቹ ሌላ ዓለም የማይገኙ አዕዋፋት ኢትዮጵያ ብቻ ነው የሚገኙት፤ ሁሉንም የሰማዩ ቁጣ ውስጣችን አብሮ እንዳያጭደው አደብ ገዝተን ወደ ፈጣሪያችን እንመለስ!
… ለሰው አይደለም። ወደ ፈጣሪያችን ቀልባችን መልሰን እራሳችን አዋርደን፤ ይቅርታ አምላካችን እንጠይቅ …. ኢትዮጵያ ሶስት አፄዎቿ ዓለም በቃኝ ብለው ገዳምን የመረጡ ንዑዳን የፈጠረች ቅድስት ሀገር ናት። ዘጠኙ ቅዱሳን ከተፈጠሩባት ሀገር አስበልጠው የመረጧት ሀገር ናት። ነብዩም ለጆቻቸው የተመኩባት ተምሳሌት ሀገር ናት።
የማከብራችሁ ወገኖቼ …. እጅግም የምናፍቃችሁ ደሞቼ … መንጠራራት መልካም ባይሆንም፤ ሰው ባላው ነገር ወይንም በቀጣይ ፍላጎቶቹ ዙሪያ አብዝቶ ሊንጠራራ ወይንም ሊመካ ይችላል። በተማመነበት ጉዳይ። በክርስቶ ወይንም በአላህ ሥልጣን መንጣራራት ግን ዕጣው ትውልድን ያሳርራል – ያርሳልም። ቅጣቱን የሚያቆም ምድራዊ ኃይልም አይኖርም፤ አባ ጳውሎስን አተረፈ ተዋህዶ? ወይንስ ቲፒ.ኤል.ኤፍ ሄሮድስ መለስን ታደገ? ገዳማት ታረሱ …. ቁጣውም ነደደ!
ፍቅር ተንበርክኮ እንሆ ይለምናል። አሁንም ህዝባችን በፍቅር ይጋባል፣ ይዋለዳል፣ አብልጅነት ይናሳል፣ ይጎራበታል፣ ጡት ይጣባል፤ ጓደኝነት ይገጥማል፣ ማህበሩን ዝክሩን አብሮ ይጠጣል፤ ሀዘን ተፍሰኃውን ፈቅዶና ደስ ብሎት ይጋራል፤ ይረዳዳል፤ ይህን የደም ግንኙት መበጠስ አይቻልም … ሰውኛ አይደለምና ….. በቁጭት ምክንያት ምላሽ ለመስጠት ፍላታችን ለማስታጋስ ስንል በምንሰነዝራቸው ቃሎች ከእልህና ከግብታዊነት ጸድተን እንስከን። ማስተማር የሚቻለው የሚወረወረውን ናዳ መልሶ በመልቀቅ ሳይሆን፤ ጨዋነታችን በለገሰን አርምሞ፤ በተደሞ፤ በትግሥትና በሆደ ሰፊነት ወያኔ ያዘጋጀውን ሴራ ማክሸፍ ስንችል ብቻ ይሆናል ብጡልነት። የዚህ ሁሉ ትርምስ ተዋናዩ ወያኔ ነው። ይህ አውሬ ያዘጋጀው መርዝ ወገኖቻችን አልተረዱትም። ዕውነተኛውን ነገር ወስጣችን ፈቅዶ ይቀበል ዘንድ እግዚአብሄር ይርዳን። ትጉኃን ቀጥሉ የሃቅ ምስክር መረጃዎችን በሚዛን ቀልቡን። አትናቁ ወይንም አቅልላችሁ አትዩትት። የተደራጀ ፈተና ነው። ፈተናው የሚረታው ደግሞ በበለጠ በተደራጀ ሥልጡንና ብልህ ተግባር ብቻ ነው።
ቀኑ እዬናፈቀኝ – የሰንደቄ ዜማ …
ህብር ስንኞችህ ማንነት ሊያለማ።
አፍሪካዊነቴ ሊደምቅም – ሊያበራ
በፈጠራ ዓውራ! ….
ዛሬ ለትናንቱ፤ ትናንትም ለነገ – አድዮ አጎመራ፤
ሉሲ ከፍ ትላላች በመንፈስ – በማማ
በፍውሰትህ – ጣዝማ …..።
እናት ታጌጣለች ….. በሞገስህ ግርማ፤
ታሪክ ይዘከራል – በወጣቱ ዓርማ!
ዓለም ይታደማል በመረዋ እማማ!
ህበረ – ቀለማቱ፤ — የቁንጅና ዋና!
አማንህ – ሊያዘመር ….
እሙ – ልትቀምር
የታጠቀ ዕውነት ብቃት ሊመሰክር፤
ያ …. የደግ ታሪክ ገር፤ መቅድምን ሊመራ
የዘማናት ሂደት …. ትውፊት ሊያነባብር
ዋዜማን – ሊያዘመር …. ብቃት አጎመራ!
ማሰሰቢያ።
• ግጥሞቹ 13.01.2014 00.17 (እ.ኤ.አ) ተጻፉ።
• ጎልተው የተጻፉት ፊደላት ጠብቀው እንዲነበቡ የሻትኳቸው ናቸው።
• የግጥሞቹ – ዕርእሶቹ ጎልተው የተጻፉት የተሰመረባቸው ቃሎች ናቸው። ነፃነት ታወጀላቸው ከፈለጉት ቦታ ላይ ሆኑ፤
• ፎቶው ከቴዲ አፍሮ የግል ድህረ ገጹ የተወሰደ ነው።
መፍቻ።
ዋና ሁለቱንም ትርጉም ይዞ ነው የታደመው። ለሁለተኛው ግጥሜ እርእስም ነው።
• ላልቶ ሲነበብ አብይ፣ ኣናት፣ አለቃ፣ መሪ፤ አስተዳደሪ፤ ሰብሳቢ፤ አዛዥ፤ ሙሴ፣ እረኛ፣ ተጠሪ፣ እርእሰ ጉዳይ እንደ ማለት … ሁሎችም እንደ አረፍተ- ነገሩ ፍሰት ይተረጉሙታል። ለእኔ ግጥም ሙሴ የሚለው ግጥሙ ነው።
• ሁለተኛው ጠብቆ ሲነበብ ደግሞ የአሳን ተፈጥሮዊ የኑሮ ልማድን የሚከተል ይሆናል። … የሰው ልጅ በእህልና በመጠጥ ብቻ አይኖርም። ህሊናው መስኖ ይፈልጋል። መስኖው ደግሞ ሥነ ጥበብ ነው። ሥነ ጥበብ ጥሩ ዋናተኛ ነው። ዋናው በውጭ ሳይሆን ውስጥን የሚቀድስ የሚፈውስ፤ የሚጠግን፤ የሚያጽናና፤ የሚያጸና፤ የውበት ውበት፤ የጌጥ ጌጥ ነው። ልዩነት በአንድነት አንድነት በልዩነት አኃቲነት በመፈቃቀድ የሚያበቅል – የሚያጸድቅም ነው … በዚህ ሂደት ህልም ህልም ነው ነገሩ የሚመስለው የዓለም ብቸኛ ፍቅረኛ በሆነው የእግር ኳስ ትንሳኤ የኢትዮጵያ ሥነ – ጥበብ በበትሩ አሳላፊ በውስጥነት ሊዋኝ ነው …. ያ … የዓለም ሚዲያ ሰልፉ፤ ያ … የዓለም ዕውቅ ሰዎች ታዳሚነት ውስተት እኛነት መስፍን ሆኖ ሊሰነቅ፤ እሰቡት ….. ውህድነት። በአንድ ለጋ ሊጋባ …. ይህ የምልዓት መንፈስ በሐሤት ኢትዮጵያን በዕዝነ – ህሊናን ሲዳስሳት … የቅዝፈቱን ቅኔ ዘጉባኤን የዳጎሰ ድምር ነው ዋና ያልኩት ….
• ጣዝማ …. ከተለመደው ውጪ የሚገኝ የተፈጥሮ የማይረጋ ማር። ለጤና እጅግ መዳህኒት የሆነ። አብዛኛውን ጊዜ የሚገኘው በቆላማ የሀገራችን ቦታዎች ነው። ቀለሙም ትንሽ ደመቅ ያለ ነው።
• አድዮ ማንም ሀገር ብሄራዊ አበባ የለውም። ኢትዮጵያ ግን አላት። መንገድ ጠራጊዋ የተስፋ አበባ አድዮ የአዲስ ዓመት ዋዜማ! የሰንደቅዓላማችን ማዕከላዊ ቀለም ከዚህ ተፈጥሮ ጋር የተሳሰረ ይመስለኛል – በኪዳን። በ5ኛው መጸሐፌ ላይ „በፊደል“ የልጆች የግጥም መድብል የተሰራበት ነው፤ እንደዚህ ለዬት ያሉ ተፈጥሯችነን ከፊደል ላይ ዘርዘር አድርጌ ጽፌዋለሁ። በነገራችን ላይ የፊደል የፊት ሽፋን ከዓለም የሚለዬን፤ እንደ ውስጣችን የተፈጠረው ድንቁ የፊደል ገበታችን ሲሆን ከሌሎቹ መጸሐፍቶቼ በበለጠ በነጮች ተወዳጅም የሆነው እሱ ነው። ይወዱታል … በጣም። ቋንቋው አማርኛ ግን ተማረኩለት … ሌላ ቀን በዚህ ዙሪያ እመጣላሁ … አሁን ደግሞ የአፈሙዙ አቅጣጫ በእሱ ዙሪያ ስለሆነ ….
መንፈሶቼ – ታዳሚዎቼ! የፍቅር ማዕድ በመከባባር አብሮ አቆዬን ፤ለተሰጠኝ በቂ ጊዜ ምስጋናዬን በቅኑ ውስጠት – እንሆ!
ፈጣሪ አምላካችን የተበተነን ልቦናን ስበስቦ፤ እናታችን ከፍ ትል ዘንድ የጀመረውን ይጨርስ።
ልብ ይስጠን – ለሁላችን! የምንችለበትም ጽናትም! አሜን
ጨረስኩ — ንጹህ አዬርም አገኘሁ – ዱላውን የምችልበት!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

No comments:

Post a Comment