ግርማ ካሳ
Muziky68@yahoo.com
በፌስቡክ የሚጽፋቸውን እየሰበሰቡ አንዳንድ ድህረ ገጾች ያስነብቡናል። በመቀሌ ነዉ የሚኖረዉ። ወጣት ነዉ።
አብርሃ ደስታ ይባላል። የሚያምንበትን ከመናገርና ከመጻፍ ወደ ኋላ አይልም። በቅርቡ ከጻፋቸው አስተያየቶች አንዱ፣
ልቤን ማረከው። እኔም በዚያ ላይ ጨመር ለማድረግ ፈለኩ።
«ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል ናቸው ብለን ከተነሳን ሁሉንም ብሄራቸውን ግምት ዉስጥ
ሳናስገባ (ምክንያቱም ሁሉም እኩል ናቸው ብለናልና) በኢትዮጵያዊነታቸው እንመዝናቸው። ለማንኛውም ጉዳይ (ለስራ፣
ለስልጣን …) በትምህርት ደረጃቸው ወይ ብቃታቸው ወይ ሌላ፣ ለሁሉም በእኩል ሊያገለግል በሚችል መስፈርት
እንመዝናቸው። ሁላችን እኩል ከሆንን፣ አንድ ሰው ለመመዘን ጉራጌነቱን፣ ኦሮሞነቱን፣ ትግራዋይነቱን፣ አማራነቱን፣
ዓፋርነቱን፣ ሶማሌነቱን፣ ጋምቤላነቱን … ማስታወስ አያስፈልገንም። ማንነቱ የራሱ ነው። በኢትዮጵያዊነቱ መመዘን
መቻል በቂ ነው።» ነበር ያለው ወጣቱ።
«አቶ መለስ ታመዋል፣ ሞተዋል» እየተባለ በሚወራበት ወቅት፣ ማን ሊተካቸው እንደሚችል፣ ከሕወሃት/ኢሕአዴጎች
ጋር ቅርበት ካለው አንድ ወዳጄ ጋር የተነጋገርኩትን ላካፍላችሁ። «ላለፉት ሃያ አመታት ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበረዉ
ትግሬ ስለነበረ አሁን ከሌላ ብሄር ብሄረሰብ መሆን አለበት» አለኝ። «ይሄማ አይሆንም። መስፈርቱ መሆን ያለበት፣
ዘር ሳይሆን ብቃት ነዉ» አልኩኝ። ትግሬም ቢሆኑ፣ አቶ አርከበ እቁባይ፣ መለስን ቢተኩ መልካም ሊሆን እንደሚችል
ገለጽኩ ። «ለምን ?» ቢባል፣ አዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩ ጊዜ መልካም የሰሩ ተወዳጅ ስለነበሩ። መቼም አቶ
አርከበ እቁባይን፣ በሌሎች ነገሮች ሊወቀሱ ቢችሉም፣ አዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩ ጊዜ «ጥሩ አልሰሩም ነበር»
የሚሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብዙ ይኖራሉ ብዬ አላስብም። ታዲያ በተግባር መልካም ያደረገ ሰው፣ ከአንድ ዘር
ስለሆነ አገር እንዳይመራ ለምን ይከለከላል ? ሰው መመዘን ያለበት በዘሩ ሳይሆን በስራዉ መሆን የለበትም ወይ ?
እርግጥ ነዉ ሕወሃት/ኢሕአዴጎች ዘረኛ በመሆናቸው ፣ ጠዋትና ማታ የሚለፍፉት የዘር ፖለቲካን በመሆኑ፣ እኛንም
በመጠኑም ቢሆን በክለዉናል። እኛም እንደነርሱ «ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ …» መባባል እየለመድን ነዉ። «ለሃያ አመት
ትግሬ ገዝቶ፣ እንዴት ከአሁን በኋላ ትግሬ ይገዛል ? » የምንልም አለን። መልካም ከሰራ፣ ሕዝብን ካከበረ፣
ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ፣ ሳይሰርቅ፣ ሳያጭበረብር በሕዝብ ከተመረጠ፣ ኢትዮጵያዊ እስከሆነ ድረስ ማንም
ለምን መቶ አመት አይገዛም !!!! ዘሩ ምን እንደሆነ በማይታወቀዉ በመንግስቱ ኃይለማሪያም ዘመንና
በትግሬዉ/ኤርትራዊዉ መለስ ዜናዊ ዘመን ፣ የሕዝቡ ጥያቄ ዳቦና መብት ነበር። በወላይታዉ ሃይለማሪያምም ዘመን
አሁንም ጥያቄዉ ዳቦና መብት ነዉ። የገዚዎች ዘር ቢለዋወጥም፣ የሕዝቡ ጥያቄ አልተለወጠም። የኢትዮጵያ ሕዝብ
ፍላጎትና ጥያቄ «ማን ነው ስልጣን ላይ ያለው ? » የሚል ሳይሆን «ስልጣን ላይ ያለው ምን እየሰራ ነዉ ? »
የሚል ነዉ።
ገዢዎቻችን ሁሉንም ነገር የሚያሰሉትንና የሚያሰቡት በዘር ሂሳብ ስለሆነ፣ በብቃት ሳይሆን በዘር ላይ ተመስርተዉ
የስልጣን ድልድል አደረጉ። አቶ ኃይለማርያምን ጠ/ሚኒስቴር፣ ሌሎች ዘሮችን ለማስደሰት ደግሞ፣ ከሕገ መንግስቱ
ዉጭ፣ በርካታ ጠቅላይ ሚኒስቴሮች መደቡ። አንዱን ለአማራ፣ አንዱን ለትግሬ፣ አንዱን ለኦሮሞ ሰጡ። የካቢኔ ድልድልም
ሲደረግ፣ ክርክሩ «የኔ ዘር ብዙ አላገኘም.. ወዘተረፈ» የሚል ነበር። ብቃት ሳይኖራቸው ከአንድ ዘር በመሆናቸዉ
ብቻ ሃላፊነት እየተሰጣቸው፣ ሕዝብን በስራቸው የሚበድሉ በዙ።
ዜጎች በመታወቂያቸው ላይ፣ ወደዱም ጠሉም ዘራቸውን መጻፍ አለባቸው። ኦሮሞ ወይ ትግሬ ወይ አማራ ካላሉ
መታወቂያ አያገኙም። ኢትዮጵያ ኤምባሲ ባሉ ፎርሞች ላይ ዘር መጠቀስ አለበት። እኔ በዘሬ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቴ
ነዉ መታወቅ የምፈልገዉ፤ ዘሬ ኢትዮጵያዊነት ነዉ» የሚል ካለ አንዳች የዜግኘት መብት አይሰጠዉም። እንድ ዉጭ አገር
ሰው ነዉ የሚቆጠረው። ከዘር ዉጭ አሁን ምን አለ ከዚህ የኋላ ቀር ጎጣዊ አመለካከት ነጻ ብንወጣ ? ምን አለ
አብርሃ ደስታ እንዳለው፣ በስራችን ብንመዘን ?
በነገራችን ላይ አብርሃ ደስታ፣ በቅርቡ ከአንድነት ጋር ለመዋሃድ ጥያቄ ያቀረበዉ የአራና ትግራይ አመራር
አባል ነዉ። ከጥቂት አመታት በፊት ደግሞ፣ የቀድሞ የአራና ሊቀመንበር ፣ የተከበሩ አቶ አስራት ገብሩ የተናገሩት
ግሩም አባባልም ነበር። ከአምስት ሺሆች በላይ በተሰበሰቡበት የመቀሌ ስብሰባ፣ አንድ ጥያቄ በአንድ የሕወሃት ካድሬ
ተጠየቁ። «እንዴት ከትግራይ ጠላቶች ጋር ትሰራላችሁ ? » የሚል። አሳፋሪ፣ ዘረኛ ጥያቄ !!!! የአቶ ገብሩ
መልስ ቀጥተኛና ግልጽ ነበር። «ማንም ኢትዮጵያዊ ለማንም ጠላት አይደለም። ትግራይ የትግሬዎች ብቻ ሳይሆን
የአማራዉ፣ የኦሮሞው የሁሉም ናት፡፡ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ ሳትሆን የትግሬዉ የጉራጌዉ የሁሉም ናት። ማንም
ኢትዮጵያዊ በየትኛዉም የአገሪቷ ግዛት የመኖር መብት አለው» የሚል የሚያረካ መልስ ነበር የመለሱት።
ከቀድሞ የአረና አመራር አቶ ገብሩ፣ ከአሁኑ ደግሞ አቶ አብርሃ ደስታ አባባሎች የምንማረው ፣ የሰለጠነ
የኢትዮጵያዊነትን ፖለቲካ ነዉ። ሕወሃት/ኢሕአዴግ የሚያራምደው የዘር ፖለቲካ ምን ያህል የከሰረ መሆኑን በግልጽ
ያጋለጠ ነዉ። አረናዎች፣ በትግራይ እንደነበሩት ጀግኖቻችን (ራስ አሉላ፣ አጼ ዮሐንስ ) የኢትዮጵያዊነት
አርበኞች፣ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ቀዳሚ ሆነው የተሰለፉ መሆናቸዉን እያስመሰከሩ ነዉ።
እዚህ ላይ አንድ ነገር አንርሳ። ይህ አሁን በሕወሃት/ኢሕአዴግ አማካኝነት በአገራችን ላይ የተዘረጋዉ ፣
በዘር ላይ የተመሰረተው፣ የኋላ ቀር ፖለቲካ፣ ይህ አሁን ዜጎችን ትግሬ፣ አማራ ብሎ የመለየትና የመከፋፈል አባዜ፣
መሰረቱ ትግራይ አይደለም። በአንድ በኩል ከሞስኮ፣ ከማርክሲስቶች፣ ከነስታሊን ኮርጀዉ፣ እነ ዋለልኝ መኮንን
ያመጡት፣ አንድ ወቅት ኢሕአፓዎችም ሲያራግቡት የነበረዉ፣ አጉልና እንግዳ ፍልስፍና ሲሆን፣ በሌላ በኩል አንዳንድ
ክርስቲያን ተብዬ፣ ጸረ-ወንጌልና ጸረ-ፍቅር የሆኑ ሚሲዮናዉያን (በተለይም በምእራብ ኢትዮጵያ)፣ የላካቸው
መንግስት ኢትዮጵያን ግኝ ለመግዛት እንዲመቸው ሆን ብለው፣ ሕዝቡን ለመከፋፈል የረጩት መርዝ ነዉ። እነ መለስና
ስብሃት ነጋም ከዚያ ወስደው ነዉ፣ በትግራይና በተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ላይ መርዘኛና ዘረኛ ስርዓትን የጫኑት። እንጂ
መሰረቱ ከትግራይ የሆነው ኢትዮጵያዊነት ነው !!!!!
ቃሊቲ እሥር ቤት የነበሩ ጊዜ ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ስለትግሬዎች የጻፉት አንድ ጽሁፍ ነበር። አንድ
የቀድሞ ተማሪያቸው፣ ደርግ እንደወደቀ ትግራይ ሄዶ የታዘበዉንና ያካፈላቸዉን ነበር የጻፉት። ሕወሃት በአደባባይ፣
የሕወሃት እንጂ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ እንዳይውለበለብ አግዶ ነበር። «ኢትዮጵያዊነት»
እንደ ሐጢያት ይቆጠር ነበር። ኢትዮጵያዊነት ወደዚያ ተጥሎ፣ ዋናዉን ስፍራ የያዘዉ «ትግሬነት፣ ኦሮሞነት፣
ጉራጌነት..» ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ በአደባባይ ቢከለከልም፣ በቤቱ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ይሰቅል ነበር።
«ምንም እንኳን ሕወሃት ቢያስፈራራንም ኢትዮጵያን ከልባችን የሚወስዳት የለም። የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ልባችን
ዉስጥ ናት። ቤታችን ዉስጥ ናት» እያሉ ፣ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ከማንም በበለጠ እንጂ ባልተናነሰ መልኩ
ያንጸባርቁ ነበር። በርግጥ ትግራይ ዉስጥ ከጥንት ጀምሮ፣ የነበረዉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጠፍቶ ወይንም መንምኖ
አያውቅም፤ እንደዉም የበለጠ ጠነከረ እንጂ።
ለማጠቃለል አንድ ነጥብ ልጨመር። አገራችን ዉስጥ ያሉ የተለያዩ ቋንቋዎች ፣ የተለያዩ ባህሎች ኢትዮጵያዊነት
ናቸው። የኢትዮጵያ የተለያዩ ጅማቶች ናቸው። አፋን ኦሮሞ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ እንዲስፋፋ ማድረግ ኢትዮጵያዊነትን
ማጠናከር ነዉ። እናቴ ጅጅጋ ተወልዳ ሃረር ያደገች ናት። ሶማሌኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ እኩል ትናገራለች።
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አማርኛ ያስተማሩኝ አንድ መምህር ነበሩ። ጉራጌኛ፣ ትግሪኛ፣ አፋን ኦሮሞና አማርኛ
አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር። ሲዳማዎች በብዛት በሚኖሩባት ይርጋለም ከተማ፣ ከወላይታ ቤተሰቦች ነዉ የተወለደችው።
በደርግ ጊዜ አስመራ መካነ ሕይወት ሆስፒታል ለብዙ አመታት ሰርታለች። ሲዳምኛ፣ ወላይተኛ፣ አማርኛና ትግሪኛ
ትናገራለች። አያስደስተም። ቋንቋ ጠቃሚ ነዉ። ቋንቋ መግባቢያ ነዉ። ብዙ ቋንቋ ባወቅን ቁጥር እነጠቀማለን እንጂ
አንጎዳም። ቋንቋ የልዩነት ምክንያት ሊሆን አይችልም።
ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ስል «የብሄረሰቦች ቋንቋ ይደጉ፣ የብሄረሰቦች ባህል ይስፋፋና ይዳብር» ማለቴ ነዉ።
«አፋን ኦሮሞ ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ …. የኦሮሞዎች ፣ ትግሬዎች ፣ ጉራጌዎች ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዲ ኢትዮጵያዊ
ቋንቋዎች፤ የኢትዮጵያ ሃብቶች ናቸው» ማለቴ ነዉ። እንደ አንድ ሕዝብ ተያይዘን፣ የተለያዩ ቋንቋዎቻችንና፣
ባህሎቻችን እናዳብራለን። የኢትዮጵያ ዉበቷ ብሄረሰቦቿ ናቸውና !!!!!!!
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of
various information and content providers. The Website neither
represents nor endorses the accuracy of information or endorses the
contents provided by external sources. All blog posts and comments are
the opinion of the authors.
No comments:
Post a Comment