ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ የነሳሳኝ በቅርቡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅዳሜ ህዳር 28/2003 ዓ.ም ‘’በመዲናዋ ሚስጥራዊ የወሲብ ገበያ ደርቷል፣
የትላልቅ ድርጅቶች ጸሃፊዎች፣ ሞዴሎችና ተዋናዮች አሉበት። ድንግልና በ10 ሺብር የሚያሻሽጡ ደላሎች ሞልተዋል
የከተማዋ ቱባ ባለሃብቶች ‘’የአገልግሎቱ’’ ተጠቃሚዎች ናቸው’’ በሚል ርእስ ያቀረበው ዘገባ ነው።
ከዚህ ቀደም ባለ ጊዜ (1995) አዲስ አበባ
ውስጥ የሴተኛ አዳሪዎችን ሕይወት ለመለወጥ በብርቱ ይታገል ከነበረ አንድ ድርጅት ጋር የበጎ ፈቃድ
አገልጋይ/ሰራተኛ ሆኜ ለጥቂት ጊዜ ሰርቻለሁ። በዛ ቆይታዬ ከሰማጛቸው ነገሮች ውስጥ የሴተኛ አዳሪነት ስራ ላይ
የተሰማሩት እህቶቻችን ‘’ታክሲ’’ ብለው የሚጠሯቸው ‘’ባሎች’’ እንዳሏቸው ነው። እነዚህ ባል ተብዬዎች ሴቶቹ ማታ
ወንድ ቆመው ሲጠብቁ በማቋየት እና በመሸኘት ሲመለሱም በመቀበል ስራም ያገለግላሉ። ባጭሩ ሚስት አከራይቶ አዳሪዎች
ልንላቸው እንችላላን። እነዚህ ሰዎች ኑሮ ከብዷቸው ሊሆን ይችላል የማህበረሰባችንን ‘’ በእናት አገር እና በሚስት
የለም ዋዛ!’’ የሚባልለትን እና ብዙዎች የውጭ ጸሃፍት ጭምር ይሄንንው ተመልክተው የዘገቡለትን ማንነታችን እንኳን
የጣሱት። ረሃብ ህሊናን ያስታል። ይሁንና ማንም ጤነኛ ወንድ ሚስቱን ቀርቶ ያሽኮረመማትን ሴት እንኳን አከራይቶ
ገንዘብ ማግኘት አይፈልግም። ያውም ኢትዮጵያዊ?!
ከረምረም
ብሎ (1999) አዲስ አበባ ይኑቨርስቲ ይማር የነበረ በድንገት የተዋወቅሁት በጣም ግሩም ሰው አንድ ያልጠበቅኩት
ነገር አወጋኝ። በጫወታችን መሃከል ላነሳሁት የተሳሳተ አስተያት እርማት እንዳደረግ ጫን ብሎ ነበር የተናገረኝ።
‘’የማተውቀው ነገር አለ እዚህ ግቢ ከሌሊቱ ለስድስት ሰአት አስር ወይም አምስት ጉዳይ ብትመጣ አጅግ በርካታ
መኪናዎች ቆመው ታያለህ’’ አለኝ። ለምን አልኩት? ‘’ልክ የትምህርት ሰአት እንዳበቃ የከተማው ወንዶች ለወሲብ
የወሰዷቸውን ሴት ተማሪዎቻችንን የግቢው በር ከመዘጋቱ በፊት ሊመልሱ’’ አለኝ ፍርጥም ብሎ። እውነቱን ለመናገር ክው
ብዬ ነው የቀረሁት። በታላቁ አዲስ አበባ ይኑቨርስቲ የሚማሩ፣ ቤተሰቦቻቸው እና አገራቸው ትልቅ ተስፋ የጣሉባቸው፣
አጅግ ብዙ ህዝቧ በማሃይምነት በሚንገላታባት ሀገር የእውቀት አብነት የሆኑ እና የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና
ፖለቲካዊ ገጽታ ይቀይራሉ ብለን የምንጠብቃቸው እህቶቻችን በዚህ ነገር ሲወቀሱ መስማት አስደንጋጭ ነበር። በጣም
መደንገጤን ያየው ልጅ ግን ንግግሩን በዚህ ብቻ አላበቃም። ይብስ ብሎ ሌላ ጉድ ጨመረልኝ። ‘’ይሄነው የገረመህ?
የነዚህ ሴቶች የወንድ ጓደኞች ደግሞ ሴቶቹ ሲመለሱ ከግቢው በር ላይ ሆነው በመጠበቀ ይወስዷቸዋል’’ አለኝና እርፍ
አለው። ልክ ይሄን ጊዜ ከላይ ያልኳችሁ የመዲናችን ሴተኛ አዳሪዎች እና የባል ተብዬዎቹ ‘’ታክሲዎች’’ ህይወት ትዝ
አለኝ።
ግን
እነዚህን ከጾታ በቀር በማህበረሰባችን ውስጥ እጅግ የተራራቀ ግምት የሚሰጣቸውን ምሁራን እና ሴተኛ አዳሪዎች፣
የነርሱም ባል ተብዬ ሚስት አከራይቶ አዳሪዎች ምን አንድ አይነት አደረጋቸው? ይህ ሰፊጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።
ሆኖም የራሴን መላምቶች ለማቅረብ ልሞክር። መቼም ሁላችንም እንደምንስማማው ድህነት የዚህ ሁሉ ጉድ ምንጭ እንደሚሆን
ጥርጥር ባይኖረውም እየተፈጠረ ያለው ነገር ግን ከዚህ ዘለል ያለነው። ሴቶቹ የወሲብ ንግድ ውስጥ ገንዘብ ለማግኘት
ገቡ ብለን ብናስብ ሚስትን ወይም ፍቅረኛን ለወሲብ አከራይቶ ገንዘብ መካፈል ግን ከደህነት በላይ የስብእና ድህነት
ነው። አልፎ አልፎ እንደሚሰማው ከሆነ ደግሞ የሞጃ ልጆች የምንላቸውም እዚሁ ጉድ ውስጥ አሉበት። በዚህ ጉዳይ ላይ
የስነአእምሮ እና የሳይኮሎጂ ምሁራኑ የሚሉትን ቢሉበት ጥሩ ሳይሆን አይቀርም። ያገሬ አርሶ አደርና በየከተማውም
ያሉ ቁጥረ ብዙ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ወላጆቻችን
በሃይማኖት የታረቁ፣ በስነምግባር የታነጹ እና ባህላዊ መስተጋብራቸው ያልተፋለሰ በመሆኑ ምን ድሃ ቢሆኑና በችግር
ቢማቅቁ እንኳ ባል ሚስቱን አከራይቶ ገንዘብ ሲቀበል እና ቤቱን ሲያስተዳድር ማየት ቀርቶ ማሰብ እንኳን በጭራሽ
የሚታለም እይሆንም። እዚህጋ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር አለ። የማህረበረሰባችን ወንዶች አከራይም ተከራይም
መሆናቸው መስተዋል አለበት። እስካሁን እንዳልኩት የሴቶቹ ‘’ፍቅረኞች’’/ ‘’ታክሲ ባሎች’’ ‘’ሚስቶቻቸውን’’
ያከራያሉ። ገንዘብ አለን የሚሉ ሌሎች ወንዶች ደግሞ ይከራያሉ። ሴቶቻችን ተማሩም አልተማሩም የወሲብ ንግዱ ሁነኛ
የሽያጭ ‘’እቃዎች’’ ሆነው ተገኙ ማለት ነው። ስለዚህ ለችግሩ የመጀመሪያ ረድፍ ተሰላፊ የሚሆነው የስነምግባር
መፋለስ እና ምናልባትም የባእድ ባህል ወረራ መሆኑ አይቀሬ ነው።ከዚህም ለጥቆ ያልተመጣጠነ የኑሮ ዘይቤ (
Extravagance) ለዚህ የተማሪዎችና ከሴተኛ አዳሪነት ሌላ ገቢኖሯቸው ሳለ በወሲብ ንግዱ ለሚሳተፉ ሴቶችም
ይሁን ወንዶች ምክኒያት ሁኖ ሊጠቀስ ይችላል ባይነኝ። ምክኒያቱም አንዳንዶቹ ከሚያገኙት ተመጣጣኝ ገቢ በላይ
ላልተገባ ነገር ሁሉ ያለልክ ማውጣት ከመፈለጋቸውና በጣም የተደላደለ ኑሮ በአጭር አቋረጭ አመቻችተው መገኘትም
መፈለጋቸው ይህን መሰል ነውር ሳይጸየፉ ለመፈጸም ብርታት ሊሆናቸውም ሊያስገድዳቸውም ይችላል።
በሁለተኛ
ደረጃ ላስቀምጠው የምፈልገው ነገር ቢኖር የሴቶቻችን በተለይም ‘’ተማሩ’’ የምንላቸው ሴቶች ለራሳቸው ክብር
አለመስጠት ይሆናል። ባገራችን ’ዲግሪ አላቸው’’ የተባሉ በርካታ ወጣት ሴሴቶች ከያዙት ሞያ ይልቅ በተፈጥሮ
ያገኙትን ቁንጅና እጅግ ትልቁን ቦታ አስይዘውት ማየት እና በእርሱም ምክኒያት የሚያገኙት ጥቅም የተሻለ እንደሆነ
ማመናቸው አሁን አሁን አነጋጋሪ የማይሆን ደረጃ እየደረሰ ያለ ይመስለኛል። ይህንንው ማንነታቸውን ተጠቅመው በብርሃን
ፍጥነት ‘’ሲለወጡም’’ ይታያሉ። በጣም ባጭር ጊዜ ባለቤት፣ ባለመኪና፣ ባለብዙ ገንዘብ ሁነው አብረዋቸው ትምህርት
ከጨረሱ በርካታ ወንዶች እና ስርአት ጠብቀው ከሚኖሩ ሴት ጓደኞቻቸው የተለየ ኑሮ ሲመሩ ማየት የተለመደ ነው።
እንዲህ ያለው ድር ወጥ የሆነው ማንነታቸው ያስገኘላቸውን ጥቅም ከመኮነን ይልቅ ክብር ሲያጎናጽፋቸው መገኘቱ ደግሞ
የህዝባችንን የስነምግባር ሚዛን ብልሹነት ከማሳየቱ ሌላ ሌሎችን ወደዚህ የወረደ ማንነት ገፋፊ ሁኗል። እንዲህ ስል
በየመስሪያቤቱ ለቅጥር ከሚቀርቡ መመዘኛዎች እንዱ የወሲብ ጥያቄን መመለስ እንደሆነ የሚቆጥሩ ነውረኛ ወንዶችን
ሳልዘነጋ እንደሆነ ይታወቅልኝ። ቅጥ ያጡ የመዝናናት ሱሶች እና ተሽቀርቃሪነቶችም ለዚሁ የወሲብ ነጋዴነት የሁለተኛ
ደረጃ ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች ሴቶቻችን እንደገንዘብ ማግኛና አዝናኝ ማፈላላጊያ እንዲጠቀሙበት በማድረግ ስብእናን
በርካሽነት አስቀያሪ አባዜም ሳይሆን አልቀረም።
ቤተሰቦችም
ለዚህ አሉታዊ ድርጊት የማይናቅ ድርሻ አላቸው። አንዳንድ ወላጆች እና ታላላቅ እህቶች/ወንድሞች ሴቶችን በዚህ
አስነዋሪ ድርጊት እንዲሳተፉ ይገፋፋሉ። ‘’ ቁንጅናሽን ተጠቀሚበት! እንቺስ ሴት አይደለሽ እነዴ? ከጓደኞችሽ በምን
ታንሻለሽ? ወዘተረፈ በማለት የሚያነሳሱ እና ይህን ካልፈጸሙም አማራሪ ተጽእኖ የሚያደርጉም በርካቶች አሉ። ከዚሁ
ጋር የጓደኛ ተጽእኖም አብሮ ሊነሳ ይችላል።
ይህን
ሁሉ ስል ግን እውነተኛውን ሴቶቻችንን ለወሲብ ንግድ አሰማሪ ድህነት ልዘነጋው አልችልም።ለምሳሌ በይኑቨርስቲ
ተመድበው ከሚማሩ በርካታ ሴት እህቶቻችን ውስጥ ብዙዎቹ የተለያየ አኮኖሚያዊ ችግሮች እና አሱም የሚያስከትላቸው
ተጽእኖዎች ተጋፋጮች ናቸው። በየዶረሚተሪዎቻቸው (የማደሪያ ክፍሎች) ያሉ ሴት አቻዎቻቸው ተኳኩለው እና አጊጠው
ሲታዩ እነርሱ ግን በየወሩ ለሚያስተናግዱት የሴት ወጋቸውና ለንጽህናቸው መጠበቂያ የሚሆን ሞዴስና ሳሙና መግዢያ
እንኳ ይቸገራሉ። ይህ በጣም አሸማቃቂ ሊሆን እንደሚችል ሁሉም ሰው መረዳት ይኖርበታል። በዚህ ስፍራ ‘ ወፍ
እንዳገሩ ይጮሃል እና ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም’’ አይነት ብሂሎች አይሰሩም። ምክኒያት ቢባል
የዶርሚተሪ ኑሮው የጋርዮሽ ነው። ቤቴ ገበና ከልካዬ የሚባል ነገር የለም። እነዚህ እህቶቻችን በዚህና ሌሎች
ተደራራቢ ችግሮች ተገፍተው ወዳልተፈለገው አቅጣጫ ቢያመሩ ወቀሳውን የምንወስደው እኛም አብረን መሆኑን ግን መዘንጋት
አልፈልግም። ከተለያየ ቦታ የሚመጡና ዘመድ አዝማድ የሌላቸው ብዙ ወንዶችም ይሁኑ ሴቶች በትምህርትቤት ቆይታቸው
በርካታ አሰቃቂ ችግሮች እንደሚያሳለፉ ማሰብም ሁኔታውንም ለማቃለልም የተቻለንን ነገር ማድረግም የወሲብ ንግዱን
ልናስቆም የምንችልበት አንድ አማራጭ ተደርጎም መውሰድ ጥሩ ሊሆን ይችላል ባይ ነኝ።
ችግሩን
እንዲህ ካልን መፍትሄውንም ብንጠቋቆም መልካም ነውና አንድ ሁለት ልበል። የህዝባችንን የስነምግባር ደረጃ ሊቃኙት
እና ልክ ሊያበጁለት ከሚችሉት ዋንኛ መሳሪያዎች አንዱ ሃይማኖት ነው። የሃይማኖት ተቋማቶቻችን ላለፉት ትውልዶች
ግብረገብነት በማሰተማር እና የማህበረሰቡን የስነምግባር ሚዛን በማውጣት ለአንዳንድ ድር ወጥነቶችም ማህበራዊ
ውግዘትን እንደቅጣት በመጠቀም ድንበሩን ሲያስከብሩት ኑረዋል። እነዚህ ተቋማት ‘’በመንግስታዊ
የባህል አብዮተኞች’’ ሰበብ ስራቸው መስተጓጉሉ እና እነርሱም ከተልእኳቸው መዘናጋተቸው አሁን ላላው ወረርሽኝ
ተጋላጭ አድርጎናልና ተገቢ ሚናቸውን መልሰው እንዲጫወቱ ላሳስብ እወዳለሁ። ከዚሁጋር እንደ እድር፣ እቁብ እና
የመሳሰሉት ማህበራዊ ተቋማት ለዚህ አስነዋሪ ነገር ትኩረት በመስጠት ውግዘት እና ቅጣት ቢጥሉ ተደማጭ ነታቸው
ከፍተኛ ነው። ግን መረጃ ሊኖራቸው ይገባልና አሁን ስራውን የጀመራችሁት ሚዲያዎች በዚህረገድ አስተዋጽኦዋችሁ ከፍተኛ
ነው።
የትምህርትቤት አስተዳዳሪዎችና የተማሪዎች የወላጅ ኮሚቴዎች በጥምረት ችግሩን ተወያይተው የጋራ መፍትሄም ሊያመነጩ እና እርሱንም ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል።
የሃገሪቱ
ህግ በዚህ ችግር አንጻር ተጠንቶ ምናልባት የዚህን ነውረኛ ተግባር ተሳታፊዎች እና አቀናባሪዎች በማጋለጥ ህዝብ
እንዲያውቃችው ቢደረግ የሚፈጥረው ነገር ሌሎችም እንዲያድቡ ማድረጉ አይቀርምና በዚህም አቅጣጫ መሄድ ጥሩ ሊሆን
ይችላል።
ከነዚህ
ሌላ መንግስታችን ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ በሚገባው ነገር ላይ እንኳ እጁን በማስገባት አደብ ቢያስገዛልን ጎንበስ
ብለን ምስጋና እናቀርብለት ይሆናል። እጅግ አስደንጋጭ ዜና ቢሆንም አዲስ አበባችን እና ሌሎች ከተሞቻችን ቀስ በቀስ
እየተላመዱት ያለ አደገኛ ነገር ነው። ሆዳሞቹ ባለሃብቶቻችን አብዛኞቹ ሳይደክሙ በሃገሪቱ በተንሰራፋው ሙስና
ዘርፈውን ባካበቱት ሃብት የበደሉን አንሶ ባዶው ጭንቅላታቸው ቅንዘረኝነታቸውን እየመራ በሀገር እና በህዝብላይ
የሚፈጽሙት ነውረኝነት እንዲሁ መንሰራፈቱ ‘’አሳዛኝ ነው’’ የሚል ቃል አይገልጸውም። አሳ ካናቱ ይገማል እንዲሉ
የመንግስቱ ባለስልጣናትም በዚሁ ቅሌት እየተከሰሱ ስለሆነ ጉዱ ገና ብዙ ነው። በዚህም ህግን በጣሰ አገር እና ባህል
አሰዳቢ ጉዳይ ውስጥ የወሲብ ደላሎች ሳይቀር የሚሳተፉበትን ድርጊት መንግስት ሳየውቅ ወይስ የጉዳዩ ባለቤቶች
እራሳቸው ተሳታፊዎች ሆነው እርምጃ የማወስደው? አሊያም አይመለከተውም!
http://sodere.com
No comments:
Post a Comment