Tuesday, December 10, 2013

ተቃዋሚ ስለሆንን ብቻ በጅምላ መኮነኑ ምን ይረባናል?



 
ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ ከእኛ ወገን ለአንተ እናት ሆናህ በእሷ በኩል በሥጋ ትዛመደን ዘንድ በመረጥካትና ስለብዙዎች ልቧ (አእምሮዋ) ሐዘንን (ነብዩ እንደተናገራት ፍላጻዎችን) ሁሉ ያስተግድ ዘንድ ባጸናሀት፣ ቅድስት፣ ንፅህትና ዘላለማዊት ድንግል በሆነች እናትህ ማሪያም ሥም ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
ሰሞኑን በወገኖቻችን ላይ በሳውዲ አረቢያ እየተፈጸመ ባለው አረመኔያዊ ድርጊት ሳቢያ ብዙዎች ለወገን ተቆርቋሪነታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ይህ ከበጎ ጎኑ የሚታይ አገራዊ ስሜትንም የሚያጠናክር ነው፡፡ ሆኖም ግን ብዙዎቻችን ለመፍትሄ የሚሆኑ ሀሳቦችን፣ ስልቶቸህን ከመጠቆም ይልቅ በድፍኑ የገዥው ፓርቲ ላይ ውርጅብኝ እናወርዳለን፡፡ በእርግጥም የገዥው ፓርቲ ቀዳሚ ተጠያቂ እንሚሆን አምናለሁ፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ሁላችንንም ከተጠያቂነት የሚያድን ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ምክነያቱም ብዙዎች እንዳሉት ይህ ውርደት ዛሬ የጀመረ ሳይሆን ሥር የሰደደና ከውርደት ለመውጣትም ክፉ እድል ሆኖብን ችግርን እመቢ የሚል ዜጋና መሪ ማጣታችን ነው፡፡ በአጋታሚ ወደ ወራዳ አገራት የተሰደዱ ዜጎቻችን ሰሞኑን የምንሰማውን አይነት መከራ ደረሰባቸው እንጂ ወደ የትኛውም አገር መሰደድ ክብር ሳይሆን ውርደት ነው፡፡ መሠረታዊ ምክነያቱ ከአገር ይልቅ ሌሎችን መናፈቅ ነውና፡፡ በስደት ያሉትም ይባስ ሌሎች እንዲሰደዱ ከኢትዮጵያ ሲዖልም ቢሆን ይሻላል የሚያስብል ማበረታቻን ይሰጣሉ እንጂ በአገር መኖርን የመሰለ ክብር እንደሌለ አገር ቤት ላለው አይመክሩም፡፡ አገር ቤት ያለው ዋሊያ ታዲያ ውጭውን ቢናፍቅ ምን ይገረርማል፡፡ አገርን ለኑሮ ምቹ ማድረግ፣ ዜጎችን በስነ ልቦና በአገር የመኖርንና የመስራትን ያህል የመሰለ ክብር እንደሌለ ማሳወቅና የአገርን ፍቅር ማሳደግ፣ ለዜጎች ዋስትና መሆን ከፍተኛው ድርሻ የመንግስት ቢሆንም እያንዳንዳችንን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ ሲጀምር መንግስተ ማለት የቤተመንግስት ጣሪያና ግድግዳ ወይም ግቢ ሳይሆን በመሪነት ቦታ ላይ በየመዋቅሩ ያሉ የግለሰቦች ስብስብ ነው፡፡ ይህ መዋቅር ብቃት ያላቸውን ግለሰቦች መያዝ አለመያዝም ቢሆን ግለሰቦች የምናደርገው አስተዋጽዖ እንጂ የግዑዙ መዋቅር ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግስትን የሚሰማ ጆሮ ካለው በዚህ በዚህ ምክነያት ልክ አይደለህም ማለት ትክክለኛ ትችትም ጠቋሚም ነው፡፡ የእኛ ነገር ግን በአብዛኛው ስታዘበው እርስ በእርስ ለመቃወም የሚደረገው ሽኩቻ እጅጉን ይበልጣል፡፡ ምን ጥሩ ሀሳብ ቢሆን መንግስት ተብዬ ባለስልጣኖቻችንም ከሌላው አመስግነው ለመቀበል ፍቃደኛ አይደሉም እነዲሁም ምን ጥሩ ቢሰራ ገዥው መንግስት የሚሰራው በተቃዋሚ ተብዬዎች ዘንድ አይወደስም፡፡ እንግድህ ለመልካም ነገር የተዘጋ አእምሮ እንዴት ውርደታችንን የሚበቀሉ ሀሰቦችና ስልቶችን እንደሚያመጣ አላውቅም፡፡ አእምሮአችን ሌላውን ለመኮነን ብቻ ባሪያ ሆኖ ሳለ ውርደትን የመበቀል አቅም ከየት ያመጣል፡፡
ሰሞኑን አንድ "ግልጽ ደብዳቤ" በሚል ለዶ/ር ቴዎድሮስ የተጻፈውን መልዕክት ሳነብ ተመሳሳይ አቅም የማጣታችን ነገር ተሰማኝ፡፡ በእኔ እምነት የየትኛውንም ፓርቲ፣ ዘር (ጎሳ) ወይም ሌላ ቡድን ሊወክሉ ይችላሉ፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ቡድኖች ወይም ፓርቲዎች አልፎም ብሔረሰቦች የተለያየ ሀሳብና ችሎታ ያላቸው የግለሰቦች ስብስብ እንጂ እንደ ተባለው የፋብሪካ ውጤቶች ይመስል አንድ ናቸው ብሎ መፈረጁ ልክ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ መርዘኛ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ተቃዋሚዎች ውስጥም አሉ፡፡ ጥሩ ሰዎች በኢሕአዴግም በተቃዋሚሆችም አሉ፡፡ እያንዳንዳችን ከራሳችን ብንነሳ ራሳችንን ከክፉው እስከ ጥሩ ባለው መካከል እንገኛለን፡፡ ምንም ከማይረባው እስከ ስል አእምሮ ያለው ነን፡፡ ወሳኙ በአንድ ቡድን ውስጥ የበላይ ሆኖ የሚገኙት የትኞቹ ናቸው ነው፡፡
አካፋን አካፋ ዶማንም ዶማ ማለት ይገባልና ኢሕአዴግ ውስጥ ያለው ስብስብ የሰላ አእምሮ ያለው በበላይነት የሚመራው አይደለም፡፡ አልፎ አልፎ ግን ድንቅ የተባሉ ግለሰቦች መኖራቸውን ልናምን ይገባል፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ ከእነዚህ ጥቂት የኢሕዴግ ድንቅ ባለስልጣን አንዱ መሆናቸውን ደግሞ ሳንወድም ቢሆን ከሚሰሩት ሥራ ልናምነው የሚገባ ነው፡፡ እኚህ ሰው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በነበሩበት ወቅትም በኢትዮጵያ ብቸኛው በሚኒስቴርነት ማዕረግና ስልጣን የአገለገሉ የሚኒስቴር መ/ቤታቸውንም ያስመሰገኑ፣ አልፎ ተርፎም አለም አቀፍ አድናቆትን ያገኙ ሰው ናቸው፡፡ ይህን ሁሉ ደግሞ በቲፎዞ ያገኙት አድናቆት ሳይሆን በተግባር በተገለጠ የሥራቸው ውጤት ነው፡፡ በተመሳሳይ አሁን ያሉበትን ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ያሉ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ የሰውዬውን ብቃት በትክክልም የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርነት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት ሲቀየሩ ነገሮች ይበላሹባቸዋል ብለን ነበር፡፡ ግን ሰውዬው አሁንም ብቃታቸውን እያሳዩ ነው፡፡  እኚህ ሰው ጋር ታች ያለው የሕዝብ ችግር ሕመም ነው፡፡  ቢሮክራሲ የሚባል ነገር እሳቸው ሰፈር ሥሙም አይጠራ፡፡ ለትንሹም ለትልቁም ቢሮአቸው ክፍት ነው፡፡ ዋናው ነገር ማንም ያምጣው ማን የጉዳዩ መክበድ ነው፡፡ በመሆኑም ታች ያለው የህዝብ ችግር ሳይቀር ጆሮአቸው የመድረስ እድል አለው፡፡ ሌላ ቀርቶ አብረዋቸው የሚሰሩ ሰዎችን ሁሉ ነው እየቀየሩ ያሉት፡፡ የሥራ ባልደረቦቻቸው በፍቅር ይታዘዟቸዋል እንጂ ስለማይፈሯቸው የሕዝብን ችግር ያደርሷቸዋል፡፡ ይህ በእውነት መታደል ነው! ከጥቂቶቻችን በስተቀር ይህ አይነት ተሰጥዖ የለንም፡፡
ሆኖም ግን ዶ/ር ቴዎድሮስ የኢሕዴግ አባል ናቸው፤ ከዚያም በላይ ብዙዎች በመልካም የማያዩት የሕወሐት አባል፡፡ የክፉው ዘመን በአመጣብን አስተሳሰብ ደግሞ "ትግሬ" ብለን የሰየምንው ብሔረሰብ አባል ናቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ አልፈውም "የኤርትራዊ ደም" በሚል ይታማሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን ሰውዬውን ለመቃወም አንዳችም መሠረት ያለቸው አይደሉም፡፡ በእነዚህ ሁሉ አባሎች ውስጥ ክፉ እነዳለ ጥሩ ይኖራል፡፡ ወራዳ አስተሳሰብ ያለው እነዳለ ብስልና በክብር ማማ የሚያስቀምጥ አስተሳሰብ አለ፡፡ ይህ ለሁሉም ፓርቲ፣ ብሔረሰብ፣ ቡድን ተበዬ ሁሉ የሚሰራ ነው፡፡ አኝህ ሰው የመልካም ነገሮችን የሚወክለውን ባሕሪና ችሎታ አላቸው ከተባለ ደግሞ መልካም የሆኑበትን ማድነቅና አረአያነታቸውን መከተል ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከተልባ ጋር የተገኘሽ ስናፍጭ አብረሽ ተወቀጭ አይነት ትችት አይመጥንም፤ አያንጽም፤ ራስን ትዝብት ውስጥ ከመክተት ውጭ፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ "ትግሬ" ብለን ያልነው ብሔረሰብ አባል ስለሆኑ አገር መምራት የለባቸውም፡፡ በፊት ሌላው የዚሁ የተባለው ብሔረሰብ አባል የሆኑ ስለመሩ አሁን ደግሞ ሌላ ይምራ አይነት አመለካከት በታላቋ ልጅ ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ አገር በወረፋና በኮታ በግድ የለሾች እንድትመራ እያሰብን ውርደትን መበቀል ዘበት ነው፡፡ ቴዎድሮስ በራሳቸው እቅድ "ትግሬ" ከተባለው ብሔረሰብ አልተወለዱም፡፡ በራሳቸው እቅድ "ኤርትራዊ ደም" አልተቀበሉም፡፡ እርግጥ ወደውና ፈቅደው ኢሕአዴግ ሆነው ይሆናል፡፡ በዚህ ሁሉ ግን ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያጎድል ተፈጥሮአዊ ሥሜት የላቸውም፡፡ ሁሉንም በአንድ ለማየት አቅም አላሳጣቸውም፡፡ "ኦሮሞ" ነኝ ከሚለው ባለስልጣን "ትግሬ" የተባሉት ቴዎድሮስ "ኦሮም" ላልንው ሕዝብ ውለውለታል፡፡ "አማራ" ነኝ ከሚለው ባለስልጣን "ትግሬ" የተባሉት ቴዎድሮስ "አማራ" ላልንው ሕዝብ ውለውለታል፡፡ ለሌላውም እንደዚያው፡፡ በአጋጣሚ ሕወሀት በመሆናቸው በብዛት "ትግሬ" ባልነው ሕዝብ የሚኖራቸው ተሳትፎ ስለሚጨምር ካልሆነ በኢሕአዴግነታቸው (በሚኒስቴርነታቸው) "ትግሬ" ለተባለው ሕዝብ ከሌላው የተለየ ምንም ያደረጉለት ነገር እንደሌለ አምናለሁ፡፡ እኚህ ሰው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ወክለው ሚኒስቴር ሆነው ያገለግላሉ እንጂ እንደሌሎች ከጎጥና መንደር ባላለፈ አመለካከት የወረዱ አይደሉም፡፡ ሕዝብም ማንነታቸውን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እንዲህ ያሉ ሰው ኢትዮጵያን ቢመሯት ምን ያንሳቸዋል፡፡ ኢሕአዴ በሚያላዝንበት ለፈለገው ነገር የሚጠቀምበት ሕገ-መንግስት በሚሉት ግርግር አሁን አገሪቱን እመራለሁ ብለው የሚያስቡት ጠ/ሚኒስቴር ተብዬው ቦታ ቴውድሮስ ወይም ሌላ ብቃት ያለው ቢሾም ለአገር ምንኛ ጥሩ በሆነ፡፡ እድል ሆኖብን ይሄው ሌላላ የእውር ድንብር ጉዞ እንጓዛለን፡፡
ቴዎድሮስ ሰሞኑን ከስደት ለተመለሱት ወገኖቻችን ያደረጉትን እንክብካቤና አለሁላችሁ ባይነትን እስኪ ማን አደረገው? እስኪ አስቡት ቀድሞ የውጭ ጉዳይ የነበሩት ሰው ቢሆኑ ይሄንን ያደርጋሉ ብላችሁ ታስባለችሁ? እርግጥ ሟቹ ጠ/ሚኒስቴር እንደ መጨረሻ ዘመናቸው የሕዝብ አሳቢነት በሕይወት ቢኖሩ በዚህ ወቅት ከስደት ተመላሾቹን ለማጽናናት መታየታቸው አይቀርም ነበር፡፡ የአሁኑ ጠ/ሚኒሰቴር ተብዬው ለዜጎች አለሁላችሁ አለማለታቸው ቴዎድሮስ ምን ውስጥ ሆነው ነው ተጠያቂ የሚሆኑት፡፡ ሲሆን አኮ አገሪቷን የሚመሯት ኃ/ማርያም እንደመሆነቸው ኃላፊነታቸውን አውቀው ዜጎችን ለማጽናናት ቀዳሚ መሆን ነበረባቸው፡፡ ቴዎድሮስ እንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነታቸው በውጭ ያሉ ዜጎች ስለሚመለከታቸው ከዚያም በላይ ሰውዬው ለዜጎችና ለአገር ያላቸው አሳቢነትና ክብር የበኩላቸውን እየለፉ ይገኛሉ፡፡ መቼም ከዚህ አልፈው ኃ/ማርያምን አንም እስኪ የአገርና የዜጎች ጉዳይ ይሰማህ ማለት ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ያም ቢሆን ጊዜ ከማባከን ውጭ ትርፍ የለውም፡፡
ኢትዮጵያዊ (ለወገን፣ ለዜጎችና አገር ክብር) ባለስልጣኖቻችንን እንንከባከብ፡፡ ብዙዎቻችን ለመተቸት እንችል ይሆናል፡፡ ግን እኔ ብሆን ይሄን ይሄን አደርግ ነበር የሚል ጠቋሚ ሀሳብ የለንም፡፡ ብዙዎቻችንም ኢሕዴግ በመረዘን የዘረኝነት መርዝ ተነድፈን ከእኛ ሰፈር ካልሆነ ሌላው ብቃት ያለው አይደለም፡፡ "አማራው" በአማርኛ፣ "ኦሮሞው" በኦሮምኛ ሌላውም እንዲሁ በየቋንቋውና በየቀበሌው እያሰበ እንዴት ነው ትልቋን የብዙዎች መኖሪያ የሆነችውን ኢትዮጵያን የሚመራው፡፡ አንዳነዶቹማ ከነጭርሱም ኢትዮጵያው አይደለንም እስከማለት አእምሮአቸው ነጥፏል፡፡ እንዲህ ኢትዮጵያዊነትንና ሌሎች ዜጎቿን የሚጠላ ዜጋ በየትኛው መስፈርት የኢትዮጵያ መሪ ሊሆን የሚችለው፡፡ እስኪ በዚያውም አገራችን ማን ማን ሰው እንዳላት እርስ በእርስ መረጃ ለመሰጣጠት ይረዳናል፡፡ ከሸነሸናቸው ብሔረሰቦች ከእያንዳንዱ እከሌ ብቁ ነው የምትሉትን ጠቁሙ፡፡ ከተቃዋሚም ይሁን ከገዥ ተብዬው ፓርቲ፡፡ አኔ ቴዎድሮስን ለመጠቆም አላፍርም፡፡ በአዴን ከተባለው ስብስብ ተፈራ ዋልዋ በቃኝ ብለዋል እንጂ በኢትዮጵያዊነታቸውና በአስተሳሰባቸው የሚያሳፍሩ አልነበሩም፡፡ ብዙዎቻችን እኝህን ሰው የምናውቃቸው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ አሁን በፓርቲው ውስጥ ከቀሩት ግን ጥራ ብባል ይከብደኛል፡፡ ኦሕዴድ ተብዬው እንኳን ጠ/ሚኒስቴር ኦሮሚያ የተባለውን ክልል ለመወከል አቅም ያለው የለውም፡፡ ሁሉም በየቀበሌው የሚያስብ፤ ብዙዎችም ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያዊ ዜጎችን የሚጠላ ኦነግ ከተባለው ፓርቲ ተብዬ የመጣ የውርስ ልክፍት አለባቸው፡፡ 
የታላቋ ቀን ልጅ ዘር ከነጭርሱም መስፈርቱ አይደለም፡፡ ፓርቲም ብዙ አይገደውም፡፡ ኢትዮጵያዊነት፣ የአገርና የዜጎች ክብርን የሚረዳ መሪ ግን ይናፍቀዋል፡፡ ማንንም በዘሩና በተከተለው ፓርቲ ሊኮንን አይፈልግም፡፡ የምርጦቹ ስብስብ (ፓርቲ በሉት ቡድን) እሰከ ሚመጣ ድረስ ከሁሉም ወገን ለይቶ ግለሰቦችን ይተቻል፣ ያደንቃል፡፡ ምኞቱም የሚያደንቃቸው ግለሰቦች በአንድ ስብስብም ይሁን በተለያ የስብስብ ስለአንዲት አገራቸው ጉዳይ አንድ እንዲሆኑ ነው፡፡ የፓርቲ መለያየታችን በተቃዋሚነት ብቻ ሳይሆን ለአገር ጉዳይ በተበረከቱ መልካም ሥራዎች የምንቃወማቸውንም ለወደድንላቸው ሥራ መድነቅና ማመስገን አገርንና ዜጎችን ማክበር ነው፡፡ ከጭፍን ጥላቻ ውስጥ ብርሀናዊ ራዕይ ሊኖረን አይችልም፡፡ የተጠላውን ስናወግዝ፣ የተወደደውን ስናወድስ በትክክልም አእምሮአችን ክፉንና ደጉን የመለየት አቅሙ እንዲጎለብት እያደረግንው ስለሆነ እኛም በተራችን በኃላፊነት ቦታ ስንቀመጥ ሁሉንም በእኩል አይን የማየት እድል፣ ጥሩን በጥሩነቱ የመተቀም እድል፣ መጥፎውንም በመጥፎነቱ የማስወገድ አቅም ይኖረናል፡፡   
ልዑል አባት ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ የምናስተውልበትን አእምሮ ስጠን! አሜን!
የታላቋ ቀን ልጅ ሕዳር 26ኛው ቀን 2006 ዓ.ም (Son of the great day 5th of December 2013)

   
       

No comments:

Post a Comment