Monday, December 30, 2013

አይ አበሻ! አበሻና ልመና፤ ሁለት (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

ልመና ሳይሰርቁና ሳይቀሙ የሌላውን ሰው ንብረት ፈልቅቆ ለመውሰድ የተፈጠረ ዘዴ ነው፤አንዳንዴ ትልቅ ነገርን ሲመኙ ትንሽ ነገር መስጠት የልመናውን በር መክፈቻ ይሆናል፤ እነዚህ የልመና ስጦታዎች ስሞች አሉአቸው፤ እጅ መንሻ፣ ወይም መታያ ይባላሉ፤ የጌቶችን ፊት ለማየት፣ ወይም ጌቶችን እጅ ለመንሣት፣ ሲፈቀድም እግር ለመሳም የሚቀርብ ስጦታ ነው፤ ያለው ሰንጋ ወይም ሙክት ይሰጣል፤ ሴቶች ፈትል ወይም ስፌት ይሰጣሉ፤ ይህ እንግዲህ ትንሽ ሰጥቶ ብዙ የመቀበያ የልመና ዘዴ ነው፤ በዘመናችን በተለይም በከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉቦ፣ ሙስና፣ ንቅዘት የሚባሉ ክፉ ስሞች ለክፉ ተግባር ተሰጥተዋል፤ ልመናን ከዚህ ርካሽ፣ መናኛና ወራዳ ተግባር ጋር እንዳናዛምደው፤ ልመና የተራቀቀ ማኅበራዊ ዝቅጠት ነው፤ ሙስና የወራዳና የስግብግብ ግለሰቦች ጸረ-ሕዝብ ሌብነት ነው፤ ልመና ማኅበረሰቡ ሥራን ችላ ብሎ የሚሰማራበት ነው፤ ሙስና ጥቂቶች ሰዎች የማኅበረሰቡን አጥንት እየጋጡ በዱለትና በቁንጣን ነፍሳቸውን፣ አእምሮአቸውን፣ በመጨረሻም አካላቸውን የሚያጡበት ሥልጣንና ሀብትን አምላካቸው ያደረጉ ሰዎች የማይጠግብ ወይም የማይሞላ የወንጀል ተግባር ነው፡፡Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
ማማለድም አለ፤ በቀጥታ መለመን የሚፈራ ወይም የሚያፍር ሲሆን የሚለምንለትን የሚለምንበት ዘዴ ነው፤ ስለዚህም አማላጅ ማለት አስለማኝ ወይም የለማኝ ወኪል ማለት ይሆናል፡፡
ልመና በሰው ላይ ልዩ ጠባይን ያሳድራል፤ አጥንት እንደሌለው ነገር ልፍስፍስ፣ ስብርብር፣ እያሉ መቅለስለስና መለማመጥ የልመና ጥበቦች ናቸው፤ በነዚህ ጥበቦች ያልሠለጠነ ልመናው ሊሳካለት አይችልም፡፡
አበሻ ከልመና ውጭ በሰማይም ሆነ በመሬት የሚያገኘው ምንም ነገር የለም፤ አስተዳደር በልመና ነው፣ ገበያም አንኳን በልመና ነው፤ የሎተሪ ቲኬት የሚሸጡትን ልብ ብላችሁ አስተውሉአቸው፤ ሴት በልመና ነው፤ በእኔ ዕድሜ አበሻ ሆኖ የማይለምን ንጉሥ፣ ፕሬዚደንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትር፣ ሹም አላየሁም፤ ብዙ ጊዜ በተዋረድ ያለውን ለማኝነታቸውን አናስተውለውም፤ ተራው ሠራተኛ የቀጥታ አለቃው ለማኝ ነው፤ ቀጥታ አለቃው ደግሞ የመምሪያ ኃላፊው ለማኝ ነው፤ የመምሪያ ኃላፊው ለዲሬክተሩ፣ ዲሬክተሩ ለሚኒስትሩ፣ ሚኒስትሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከበላዩ ላለው ለማኝ እየሆነ በመሰላሉ ላይ ይንጠለጠላል፤ እንዳየነው ልመናቸውን የሚሰማቸው ሲጠፋ ከመሰላሉ ይወድቃሉ፡፡
በታላላቆቹ ለማኞችና ጭርንቁስ ለብሰው በየመንገዱ በሚታዩት ለማኞች መሀከል ያለው ልዩነት አፍአዊ ብቻ ነው፤ ታላላቆቹ ለማኞች የሚለምኑት በሕዝብ ስም ነው፤ ትንንሾቹ ለማኞች የሚለምኑት ለየራሳቸው ነው፤ ትልልቆቹ ለማኞች የሚለምኑት በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በዱባይ፣ በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ … ፎቅ ቤቶች ለመሥራትና ምርጥ መኪናዎችን ለመግዛት ነው፤ ተራ ለማኞቹ ግን የዕለት እንጀራቸውን ብቻ የሚሹ ናቸው፤ ስለዚህም የታላላቆቹ የልመና ከረጢት ሰፊና የማይሞላ ከመሆኑ ሌላ አንድ ሰው የሚሸከመው አይደለም፤ ደሀው ለማኝ ከዕለት ጉርሱ በላይ መሸከም አይችልም፡፡
ልብ ብሎ ላስተዋለ ከመንግሥት ጀምሮ ወደታች እስከደሀው ድረስ ለተመለከተ የማይለምን አበሻ የት ያገኛል? መንግሥት የሚባለው ድርጅት በልመና እንደሚኖር የታወቀ ነው፤ የናጠጠው የአበሻ ሀብታም ለማኝ መሆኑን ብዙዎቻችን የምናውቅ አይመስለኝም፤ ሀብታሙም አበሻ የለየለት ለማኝ ነው! ለመሆኑ ስታስቡት በለማኞች አገር ሳይለምኑ ሀብታም ለመሆን እንዴት ይቻላል? አንድ ቀን በጠዋት ተነሥቼ የኤንሪኮ ቡና ቤት እስቲከፈት በእግሬ ስዘዋወር አንድ ሰው ከውስጥ ነጠላ ለብሶ፣ ካፖርት ደርቦ ባርኔጣ አድርጎ ከታክሲ ሲወርድ አይቼው የት እንደማውቀው ሳንሰላስል ትንሽ ቆይቶ ጭርንቁስ ለብሶ ከዘራውን እየተመረኮዘ ብቅ አለ! ማን እንደሆነ አወቅሁት!
እንደአበሻ ሀብታም ለማኝ አለ እንዴ! ከባንክ ብድር ለማግኘት፣ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት፣ ካስወጣ በኋላ ግብር ለማስገመት፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት፣ ግብር ለመክፈል ለምኖና እጅ ስሞ ነው፤ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የአበሻ መሥሪያ ቤቶች ሁሉ በአበሻ ላይ ልመናን የዘለዓለም ባህል አድርጎ ለመጫን በተካኑ ሰዎች የሚመሩ ናቸው፤ መንግሥት የሚባለውም ሆነ ሀብታሙ፣ ደሀውም ሆነ ተማሪው የሚለምኑት ቸግሮአቸው ይመስላችኋል? አስቡበት! ግን አንድ ነገር አትርሱ፤ በአበሻ የልመና ሥርዓት የሚለምን ሁሉ ያስለምናል፤ አበሻ የሚወዳት አዙሪት!ሲለምን ያጣውን ክብር ሲያስለምን መልሶ የሚያገኘው ይመስለዋል፤ አይ አበሻ!
አበሻ ልመናን ወደተራቀቀ ጥበብ አድርሶታል፤ በግጥም፣ በጮሌ አፍ፣ ድምጽን በማቅጠን፣ አንገትን በማቅለስለስና አጥንት የሌለው በመምሰል፣ ‹አግኝቶ ከማጣት ያድናችሁ፤ … አዱኛ ጠፊ ነው፣ መልክ ረጋፊ ነው፤ ዓለም አላፊ ነው፤ ቀኑ አይጨልምባችሁ፤ …፤› እያለ ሲለምን የሰውን ልብ ለማራራት ብቻ አይደለም፤ ስውር ማስፈራራትም አለበት፤ የድሬ ዳዋ ለማኞች ትንሽ ለየት ይላሉ፤ አንዱ ጠጋ አለኝና ‹አንድ መቶ ብር ስጠኝ!› አለኝ!
‹አንኳኩ ይከፈትላችኋል›፤ የተባለውን አበሻ የተገነዘበው ‹ለምኑ ታገኛላችሁ፤› በሚል ትርጉም ነው፤ ማንኳኳት ትንሽ ጉልበትም፣ ትንሽ ወኔም ያስፈልገዋል፤ አበሻ ጎመን በጤና ብሎ ጉልበቱንም፣ ወኔውንም የሚቆጥብለትን ልመና ይመርጣል፤ ያላቸው ቢሰጡ ሰጡ፤ ባይሰጡ የሚጎዱት እነሱ ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት አይገቡ!

 https://ecadforum.com/Amharic/archives/10528/

No comments:

Post a Comment