Monday, December 16, 2013

ይቁረጥ – በዳዊት ዳባ


ዳዊት ዳባ
1998 በቅድስት ባይልልኝ ተደርሶና  ተዘጋጅቶ ለእይታ የቀረበው ህይወት እንደዋዛ ድራማ ላእይታ ከቀረበ ሀያ አንድ አመት ሆነው። ቅድስት በዚህ ስራዋ በየአረብ አገሩ ለስራ የሚላኩ ዜጎች በይበልጥም የሴት እህቶቻችን ሂወት ምን ያህል በመከራና ስቃይ የተሞላ እንደሆነ እንደወረደና መታየት በሚገባው መንግድ አሳይታናለች። ይህንን ፊልም በጊዜው ሁላችንም ተመልክተን ጉድ ብለናል። ለረጅም ጊዜ ዋና መወያያችንም ነበር።  መንግስት ነን ያሉት ለቀጣይ ሀያ ምናምን አመታት በየአረብ አገራቱ ወንድምና እህቶቻችንን በገፍ ሲልኩ በነዚህ አገራት የሚጠብቃቸውን ፍዳ አናውቅም ነበር ሊሉ አይችሉም። ይህ ፊልም የችግሩን መነሻ ጊዜ አመላካችም ነው።
በቀጠሉት አመታት በመከራ ብዛት አይምሯቸው ታውኮ ወይ ያካል ጉዳተኛ ሆነው ያለረፍት ከመስራትና በተለያዩ መንገዶች ክብር የሆነ ሂወታቸውን አጥተው   እሬሳቸው ወደ አገር  የተመለሱ ወገኖቻችን ከመብዛታቸው ብዛት አሁን አሁን በትናንሿ መንደር ደረጃ ብዙም ማሰብ ሳይፈልግ ሁሉም ዜጋ በስም እየጠራ በቁጥር የሚያስቀምጠው ሆኗል። እረ እንደውም በዘምድ አዝማድ መሀል። አንድ ወይ ከዛም በላይ ሉሁላችንም ተዳርሷል።  እንትና እኮ አረብ ሀገር ሄዳ ከዛ ያሳዝናል ብለን የምናወራው አንጀት የሚያኮማትር ሀዘናችን ከሆነ ውሎ አደረ ። ዛሬ የእንባሲ ሰዎቻችው አይምሯቸው ታውኮና ለዘላለሙ እንዳይድኑ በሽተኛ ሆነው የሚመለሱትን ሳይጨምሩ በሳምንት ከስድስት እስከአስር እሬሳ ወደ አገር እንልክ ነበር እያሉን ነው። በእርግጥ ይህን መነገርም አያሻንም እናውቅ ነበር።
ከአገር ቤት ወደ አደጉት አገራት የሚበሩ አይሮፕላኖች የኛዎቹን ጨምሮ በማደጎ ስም የሚቸበቸቡ ኢትዬጵያዊ ህጻናት ወና ደንበኞቻቸው ናቸው።  በተመሳሳይ ጦርነት ላይ ያለች አገር እስክትመስል ከየአረቡ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ በረራዎች እሬሳና ህሙማምን  በገፍ ማመላለስ ከጀመሩ ሀያዎቹን አመታት አስቆጥረዋል። በየአረብ አገራቱ ተጎጂ ስለሆኑ ዜጎቻችን ስናወራ የምናወራው ስለ አምስት ሞቶ ሺ ተጎጂዎች ወይ ስለ አንድ ሚሎዮን ተጎጂ ዜጎች አይደለም። ስለ ብዙ ሚሊዮን ተጎጂ ዜጎች ነው?። በተመሳሳይ  የምናወራው ዛሬ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ እየሆነ ስላለው ብቻ አይደለም ሀያ ሶስት አመት ስላስቆጠረ የዜጎቻችን መከራና አገራዊ ችግር ነው።
እነዚህ ብዙ ሚሊዮን ሰቆቃ የተፈፀመባቸው ዜጎች የበዙት ህጋዊ በሚባለው መንገድ ወደየ አረብ አገራቱ የተላኩ ናቸው። ህጋዊ የሚባለው መንገድ የትኞቹንም ተጎጂዎች እስከዛሬ አልታደገም። ህጋዊ መሆን አለመሆን  ምንም አይነት ልዩነትም አልነበረውም።  ልዩነቱ ፍዳውን ጉዞ ላይ መጀመር ወይ በሚመች አይሮፕላን ቶሎ ቦታው ደርሶ  የመከራውን ሂወት መጀመር ብቻ ነው። ወገኖቻችን እዛ ሲደርሱ ህጋዊ የሚያሰኛቸው ወረቀታቸው ባሰሪዎቻቸው እጅ ስለሚሆን ህገወጥ ብቻ ሳይሆን ያሰሪዎቻቸው ባርያ ነበር የሚሆኑት።  ላለመገደል፤ ላለመደፈር ሰቆቃ እንዳይፈፀምባቸው፤ ጉልበታቸው ያለአግባብ እንዳይበዘበዝ፤ የለፉበትን ሀቃቸውን እንዲይከለከሉ ህጋዊ ወረቀቱም ሆነ ወያኔዎች ተዋዋልን ወይ ስምምነት አደረግን ሲሉት የነበረው ቅራቅንቦ ምንም አልፈየደም።
ይህንን መካድም አይቻልም። አለም ሁሉ ያየውን ያለማቀፋ ሜድያዎችን ሽፋን ካገኙት ውስጥ የጋዳፊ ልጅ ሚስት ወ/ሮ ሀኒባል እህታችን ሸዋዬ ሞላ ላይ ያን ሁሉ ሰቆቃ የፈፀመችባት  ወረቀት ስለሌላት አይደለም። ወይስ ቤሩት ውስጥ ባደባባይ እየደበደቡና ኡ ኡ አድኑኝ፤ የወገን ያለህ እያለች አፍነው የወሰዷትና ጩህቷን አለም ስላየው ወስደው ከገደሏት በሗላ እሯሳን ገደለች ብለው የተፈፀማባትን ግፍ ያዳፈኑት አለም ደቻሳስ እሷም ህገወጥ ስደተኛ ስለነበረች ነበር ወይ?። በጭራሽ። እንዲሁ በየበረሀው የሰውነት ክፍሎቻቸውን የተሰረቁት ወገኖቻችን ህገ ወጥ ስለሆኑ ወይስ ተቆርቋሪ ስለሌላቸውና ውድ የሆነ የሰውነት ክፍላቸውን ስለተፈለገ።
አለም ባልሰለጠነበት ዘመን ሰዎች ያለፍላጎታቸው ባርያ ተደርገው ያድሩ ነበር። እጅግ ዘግናኝ ኢሰባዊ ድርጊት ይፈፀምባቸው እንደነበር አውቃለው። በጊዜው ባሮቹ ሲሸጡ ዋጋ ስላላቸውም ይሆናል  ዋና አላማው በሂወት እንዲኖሩና ስራ በነፃ እንዲሰሩ ነበር። ወያኔዎች  በየአረብ አገራቱ የምትልኳቸው ወገኖቼ ጉዳይ የሚመስለው “እስኪያብዱ ወይ እስኪሞቱ ባሰኛችሁ መንገድ አሟጣችሁ ተጠቀሙባቸው ነው።  ሰቆቃ ፈፅሙባቸው ነው። ሌላ ሙሉ ጉልበት ያለው ይላካል ትቀይሯቸዋላችሁ ነው።”   ይህን እንድል ያደረገኝ በየትኛውም ባርያ ማሳደር ህጋዊ በነበረበት ዘመን  ወይ በየትኛው የባርያ ስርአት የነበረበት አገር  ባርያ የተደረጉ የሰው ልጆች ሰቆቃና ስቃይ ስጋቸው መቋቋም እያቃተው በዚህ ብዛት(ሬሾ) ይሞቱ እንደነበር ወይ  ሰቆቃውን መሸከም እያቃተቸው ያብዱ እንደነበር ስለማላውቅ ነው። “ምን እያደረጓቸው ነው?” “ምን አይነት ማሰቃያ ነው የሚጠቀሙት?” የሚለው ጥያቄ ሁሌም የብዙ ተቆረቀቋሪ  ዜጎችና የኔም መልስ ያላገኘ እንቆቅልሽ ከሆነ ከረመ።
የሚያሳዝነው ግን የበዛው ኢትዮጵያዊ ሀዘኑና መጠቃቱ በየቤቱ እየገባ እያለም ባገር የመጣ(አገራዊ ችግር) አድርጎ በቶሎ አላየውም።  ችግር የሆነው በአገሪቷ ውስጥ ባለው አፈና ግዙፍነት  (አፈናውን በጭራሽ በጭራሽ አሳንሰን አንዳናየው)    ተጎጂዎቹ የሱ እህት፤ የነሱ ሰፈር ልጅ፤ ያአክስቷ ልጅ እንደሆነች እንጂ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በተመሳሳይ ስለባ እየሆኑ ያሉበት ስር የሰደደ አገራዊ ችግር አድርጎ አለማየቱ ነው።
ሁለተኛው ምክንያት ወደየአረብ አገራቱ የተገፉው ህዝብ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ነው። ስለ አረብ አገራት ስናወራ የምናወራው ስለህዝብ ነው። ክፉ ሰዎች ያሉትን ያህል ደግና ጥሩ ሰዎች ደግሞ አሉበት። በአገሮቹ መሀከልም የሰማይና የምድር ያህል ልዩነትም አለ። እድለኛ ሆነው እነዚህ ደጋጎች ጋር ተቀጥረው መስራት የቻሉት ወይ ሰቆቃ የማይበዛበት  አገራት ውስጥ የሄዱት ጉዳተኛ የመሆን እድላቸው ያነሰ ስለሆነ የተወሰኑት አምሮባቸው ገንዘብም ይዘው ወደአገር ቤት ይመጣሉ። ጎጆ ይቀይሳሉ፤ ቆርቆሮም ይቀይራሉ። ህዝብ ይህንንም አይቷል ሰምቷልም ስለዚህም ይህንንም አዳምሮ ነው ችግሩን ሲያይ የነበረው።
ሶስተኛው ምክንያት ሰቆቃውን መሸከም አቅቷት እስከመጨረሻው ያንቀላፋችው  ወይ አይምሮውን የሳተውን ጨምር ሁሉም በሂወት እስከነበሩና እስከቻሉበት ጊዜ የገኟትን ወደቤተሰቦቻቸው መወርወራቸውን አላቆሙም። ብዙዎቹ በደም፤ በላባቸው፤ በሰውነታችውና በሂወታቸው ዋጋ ይከፍሉ ነበር እንጂ አኗኗራቸው የገንዘብ ወጪ አልነበረበትም። እጃቸው የገባችውን ሁሉ ነው ሲልኩ የነበሩት። መንግስትን ያፀናው የበዛው ከውጪ ይገባል የሚባለው ገንዘብ በዚህ መንገድ ወደ ወደ አገር ሲፈስ የነበረ ነው። በተጨማሪ መናገር ምንም ላይፈይዱ ቤተሰብ ማሳሰብ ነው ብሎ በደላቸውን መደበቅም አለበት። ድቅድቅ ባለ አፈና ውስጥ ለምንኖር ህዝቦች በነዚህና ይህን በመሰሉ ሊሎች ምክንያቶች ተጨማምረውበት ህዝብ የችግሩን ስፋት፤ የጉዳቱን ደረጃና አገራዊ ውርደት መሆኑን ለማወቅ ጊዜ ቢወስድበት አያስገርምም።
በአግባቡ ያልተረዳነው ግን የችግሩን ደረጃና ስፋት ብቻም አልነበረም ። ከዛሬ ሀያ ሁለት አመት በፊት የመጀመርያዋ አይምሮ ህመምተኛ፤ የመጀመርያው እሬሳ  ሲገባ ጀምሮ መንግስት ያውቅ  እንደነበረም ነው።  የምናወራው የውስጥ ሱሪያችንን ቀለም ለማወቅ ስለሚሰሩ ዘረኛ ውላጆች ነው። በአሀዝ ማስቀመጥ በሚችሉበት ደረጃ አንድ ብሎ ሲጀምር ጀምሮ ያውቁ ነበር ። እኛ ግን ችግሩን በየግሉ ወስደን የልጆቻችን እሬሳ ሲልኩልን ተቀብለን አልቅሰን እንቀብራለን። አብደው ሲመጡ ዜጋው ተቀብሎ በግሉ ለማዳን መከራውን ያያል።
ሌላው አይደለም የበዛው ህዝብ ስር የሰደደ ችግር መሆኑን የሚያውቀውና ተቆርቋሪነቱን ሲያሳይ የነበረውም ወገን ውስጥም ብዙ ቁጥር ያለው  ዋና መሆን ይገባው የነበረውን መንግስት ተብዬው እዚህ አገራዊ ውርደት ውስጥ ያለውን ድርሻና ሀላፊነት  አውጥቶ ነው ችግሩን ሲያይ የነበረው። ዛሬም ድረስ ይህ ዳተኛ አመለካከት አለ።  ዛሬም በሳውዲ በወገኖቹ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ሰቆቃ እያየም ይሄ ፖለቲካ  አይደለም  ወይ መንግስትን አታስገቡበት የሚሉ ተላላዎች ብዙ ናቸው። ይህንን አይነት አመለካከት ህዝብ ውስጥ እንዲቀጥል የስራ ድርሻቸው የሆኑ ጊንጦችም አሉ። ወዲያም አደረግነው ወዲህ ግን መሪዎቻችን ዘረኛ ውላጅ ወያኔዎች ባይሆኑ ኖሮ ዛሬ በሳውዲዎች ወገኖቻችን ላይ የተሰራው ወንጀል አይፈፀምም ነበር። ሲጀመር ተቆርቋሪ መንግስት ባለበት፤ ለዛውም ሀያ ሶስት አመት መግዛት የቻለና መንግስቱን ያፀና መንግስት ባለበት አገር ዜጎቹ እራሳቸውን እዚህ አይነት ችግር ውስጥ ማግኘት አልነበረባቸውም። አንዴ ከገቡም ዘረኛ ውላጅ ወያኔዎች ባይሆኑ ስልጣን ላይ ያሉት በጣም፤ በጣም፤ በጣም በቀላሉ ይህን ግፍና ውርደት ማስቀረት ይቻል ነበር። ሰውዲ አረቢያ ውስጥ የሆነው በቀላሉ በርግጠኛነት  መከላከል ይቻል የነበረ ችግር ነው። የሰማነው አይነት ዎይታ በሌለበትና በሰከነ ሁኔታ በቀላሉ ወደ አገራቸው መመለስ ሲቻል ነው እነዚህ ጉዶች ቁጭ ብለው ሲያዩ የከረሙት። ዛሬ  የህዝብ ጩህትና ውግዘቱ ሲበዛ ተንደፋድፈውና አተረማምሰውት ይባስ ብለው ችግሩን ፎቶ መነሻና መታያ አድርገው ከውነውታል።
“ይቁረጥ!። ማንሿከክ አላውቅ ወይ በተፈጥሮዬ ማሽንክነት የለብኝም። ይቁረጥ ብያለው። ያለበለዚያ እኔ እቆርጥልሀለው”። ከረጅም ጊዜ በፊት ካየሁት ድራማ ሁሌም የማስታውሰው ትወና ነው።
ዛሬ በአለም ያሉ የደሀ ይሁን የሀብታም፤ አንባገነናዊ ይሁኑ ዲሞክራሲያዊ፤ አፍሪካዊ ይሁኑ ኢሲያዊ፤ ትናንት ነፃ የወጡም ይሁን የኛ አይነት የጠገበ ታሪክ ያላቸው አገራት የየትኛዎቹም አይነት መንግስታት ህዝበቸው በሌላ አገር መንግስታትና ህዝብ በዚህ ደረጃ ሰቆቃ እንዲፈፀምበት አይፈቅዱም። ሲፈፅም ማየትም የሚያስደስታቸው አይደሉም። ለሀያ ሶስት አመት አይደለም ለአንድ ቀንም የዜጎቻቸውን ያለ አግባብ መበደል አይተው ዝም የሚሉም በጭራሽ አንዳቸውም አይደሉም። በአሁኑ ጊዜ በአለም ላይ ያሉ መንግስታት በሙሉ የሚመሩት ህዝብ እራሱን የዚህ አይነት ችግር ውስጥ እንዳይገባ ያቅማቸውን የሚቻላቸውን ሁሉ የሚያደርጉ  ናቸው። ለማድረግ ቁርጠኛነቱና ፍላጎቱም ያላቸው ናቸው። ስለዚህም ይቁረጥ ብያለው።
ዛሬ በኛ ላይ እየሆነ ያለው ወገንታዊ የሆነ መንግስት ስለሌን ብቻ ነው። የምንሰማውን የወገን መገደል፤ መደፈር፤ ይውጡልን መባል መንጓጠጥ፤ ማበድ በአጠቃላይ በየአረብ አገራቱ በወገናችን ላይ የደረሰውን ሰቆቃ ሁሉ  ማስቀረት የሚቻልበት አንድ ሚሊዮን ቀላል የሆኑ መንገዶች ባሉበት የሚፈፅም ነው። ምን ያደርጋል የኛዎቹ መሪዎች ጋር ፍላጎቱ የለማ። ወገንታዊነት ሸቀጥ አይደለም። እሱቅ የማይሸጥ ሆነ። ስለዚህም ለምን? እኛ ኢትዮጵያዊያን ላይ ብሎ ለሚጠይቅ በቂ ከበቂ በላይ አጥጋቢ የሆነ ምክንያት ያለው ችግር ነው። ወደፊትም የሚገዙን ወያኔዎች እስከሆኑ የዚህ አይነት አገራዊ ውርደትና የዜጎች መጎዳት የሚቀጥል ነው።
ችግሩ ላይ የዜጎች ግንዛቤና’ የመንግስት አያያዝ እላይ ባየንበት ጠቅለል ያለ ሁኔታ ላይ እያለ ነው ኢሳት አገልግሎቱን የጀመረው። ኢሳት በዋናነት ህዝብን ስለችግሩ በማሳወቅ ከፍ ያለ ሚና ተጫውቷል። ላለፉት ሶስት አመት ተኩል ህዝብ ማወቅ መብቱ የሆነውን እውነት ይነግረው ጀመረ። የመንግሰት ደርሻ፤ ግዴለሽነትና ዜጎቹን ለመታደግ አለመፈለግ ያጋለጥ ገባ።  ወያኔዎች አያሳደዱና እያዋከቡ እነዚህ የመከራ አገር የከተታቸው ጋዜጠኞች እቦታው ሆነው የመከራውን ብዛት እውነቱን የማጋለጥ የጀግና ስራቸውን ቀጠሉበት፤ ወገንታዊ ሜዲያዎች ይህ የዜጎች ሰቆቃና መከራ ዋና አምዳቸው ሆነ። ምሁራን ፀሀፍት እንዲሁ በውጪም በአገር ውስጥም ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ወገንታዊ የሆኑ ዜጎች ባገኙት አጋጣሚ ይናገሩበት ይፅፉበት ጀመረ። ችግሩ ሊደበቅ ከሚችለው ደረጃ አልፎ የውጪ ሜዲያዎች ሽፋን ማግኘት ጀመረ። እንደምናያው ተንተክትኮ ተንተክትኮ መገንፈል ጀመራል። እዚህ ላይ ያለማቀፉ የሴቶች ማህበር ያደረገው ያላሰለሰ ጥረት  እጅጉኑ የሚያስመሰግናቸው ነው።
ወያኔዎች ይህን አገራዊ ውርደት የችግሩን መጠንና የተጎጂ ዜጎችን ሰቆቃ ግዝፈትና በነሱ ምክንያት ይህ መከራ አንደመጣብን ህዝቡ ማወቁ እየጨመረ መሄዱን ሲገነዘቡ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ በሟቹ መለስ ዜናዊ የተደረሰ ‘ያዞ እንባ” የተሰኘ ድራማ መፍትሄ ነው ብለው መተወን ጀመሩ። ከሀያ ሁለት አመት በሗላ  መሆኑ ነው።ክንቅልፍ እንደባነነ ህፃን በገፍ ለመካራ ሂወት ስላጋዟችውና ስላሰደዷቸው ዜጎቻችን እንደማያውቁ ሆነው እንደ አዲስ ሊነግሩን ጀመሩ።  መፍትሄ ፈላጊዎች ችግሩ ላይ ተረቃቂዎች ሆነው ለመታየ እላይ እታች አሉ። ተሰብስበው አልቅሰው ሊያስምኑን ሁሉ ሞክረዋል። ይህ መራወጥ የገባው ድራማውን “ከአዞ እንባ” ወድ “ሀይሌ እንባ”  ቀይሮ ቁጭ ብሎ አየው።   መፍትሄ ብለው የሞከሩት ድራማ ያስገኘው ውጤት ህዝብ የበለጠ ስለችግሩ እንዲያውቅና መታየት በሚገባው መንገድ የገዘፈ ሀገራዊ ችግር አድርጎ እንዲያየው ማድረግ መቻሉ ብቻ ነው። አሁን ለረጅም ጊዜ ችላ ከመባሉ ብዛት ችግሩ ነቀርሳ ሆኗል። ለገዥዎቻችን መፍትሄውም ከጃቸው ወጥቷል። ህዝብ ብሄራዊ ውርደትና በያንዳንዱ ዜጋ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት አድርጎ ወስዶታል። ለወያኔዎችና ደጋፊዎቻቸው የቀራቸውና ማምለጫው መንገድ በጊዜ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ መሸሽ ብቻ ነው እላለው።
ይህ ፅሁፍ ለፕሮፌሰር ተኮላ ሀጎስ  ባደባባይ የተሰጠ መልስም  ተደርጎ ይወሰደልኝ። ጊዜው አንዳንድ መያዝን ይሻል።  የሚቀናቀን ካልመጠ ተመችተውኝ ቀድሜ ይዣቸዋለው።   ወደፊትም በፃፉ ቁጥር መልስ እሰጣለው። የበዛው አንባቢ ዘረኝነት ፃያፍ የሰውን ልጅ ፍረድና አመለካከት ምን ያህል እንደሚያዛባ ያውቃል። ዘረኝነትን ግን እስከ ቦርቃቃ አፉ፤ አስከ ስድስት እግሩ፤ አስከ ጥፍራም እጆቹና እስከ ተንጨባረረ ፀጉሩ አውሬውን ማየት ከፈለጋችሁ የኚህን እውቅ ፕሮፌሰር ፅሁፎች አንብቡ። በቅርቡ አቦጊዳ ላይ የወጣላቸው ፅሁፋቸው አውሬውን በደንብ ልታዩበት የምትችሉበት ነው።

Pen

Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

No comments:

Post a Comment