Wednesday, December 11, 2013

ለምን ህወሓት/ኢሕአዴግ ያሸንፋል?



አማኑኤል ዘሰላም
በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት የነበረውን ሁላችንም የምናስታወሰው ነው። ያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፁን ለቅንጅት ቢሰጥም፣ ህወሓት/ኢሕአዴግ የሕዝቡን ድምፅ ነጥቆ እስከአሁን ድረስ በኃይልና በጡንቻ እየገዛ ነው። በሥልጣን ላይ ለመቆየት በቀዳሚነት አገዛዙ የወሰዳቸው አምስት እርምጃዎች ነበሩ። እነርሱም ...
የቅንጅት አመራሮችን ማስወገድ (እንዲታሰሩ፣ እንዲሰደዱ በማድረግ)፤ ቅንጅትን መከፋፈል፣ ሕዝቡን ተስፋ ማስቆረጥ፣ ሌላ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳያንሰራራ ማፈን እና ኢኮኖሚውን እንደመቆጣጠራቸው በጥቅም በጉያቸው የሚያስገቧቸውን ማብዛት።
አገዛዙ እነዚህን የክፋት ስትራቴጂዎች ይዞ ሲንቀሳቀስ፣ በተቃዋሚ ወገን ያሉት ግን፣ የአገዛዙን ተንኮል ለማምከን፣ ተመጣጣኝ ሥራ ሰርተዋል ማለት አይቻልም።
"ተባበሩ ወይንም ተሰባበሩ" የሚባል አባባል አለ። ትብብር መልካምና ወሳኝ ነው። "መተባበር ያስፈልጋል" ተብሎ ግን የማይሆንና የማይሰራ ትብብር ውስጥ መግባት ግን ችግር አለው። ገዢውን ፓርቲ በተለያዩ ምክንያቶች ስለሚቃወሙ ብቻ፣ ደርጅቶች አንድ ላይ መሰባሰብና መቀናጀት የለባቸውም። የቅንጅቱ ወይም ትብብሩ መስፈርት "ኢሕአዴግን መቃወም" ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው። ነገር ግን ትብብር/ቅንጅት የሚፈጥሩ ድርጅቶች፣ በፖለቲካ አቋሞቻቸውና ፕሮግራሞቻቸው የተቀራረቡ፣ አብረው ሊሰሩ የሚችሉ መሆን አለባቸው። በፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸው መሰረታዊ ልዩነቶች እያሉ፣ የሚደረግ ትብብር፣ በሂደት መፍረሱ አይቀርም።
ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ደርጅቶች አሉ። አብዛኞቹ ሀገር አቀፍ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አንድን ጎሣ ብቻ ያቀፉ ናቸው። በጎሣ ድርጅቶችና በሀገር አቀፍ ደርጅቶች መካከል በጋራ ሊሰሩ የሚችሉ ሥራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ ድርጅቶች ሊቀናጁ አይችሉም። ለምን? መሰረታዊ የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነቶች አሏቸውና። (የጎሣ ድርጅቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ መደራጅት ጥቅሙ ገብቷቸው፣ የአቋም መሸጋሸግ እስካላደረጉ ድረስ)
ከጎሣ ድርጅቶች ውጭ፣ በርካታ ተመሳሳይነት ያላቸው ሀገር አቀፍ ደርጅቶች እንዳሉ ይታወቃል። ለምሳሌ መኢአድ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ እና ኢዴፓ፣ አራቱም ቅንጅት የነበሩ፣ ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ያላቸው ድርጅቶች ናቸው። አራቱም በሀገሪቱ ያለው በዘር ላይ የተመሰረተ ከፋፋይና ዘረኛ ፌዴራል አወቃቀር መቀየር አለበት ብለው ያምናሉ። አራቱም ለሁሉም ዜጎቿና ብሔረሰቦች እኩል የሆነች አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ይፈልጋሉ። አራቱም ኢትዮጵያ የባህር በር ሊኖራት እንደሚገባ በማስረገጥ፣ የአልጀርሱን ስምምነት ይቃወማሉ። አራቱም አሁን ባለው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና የመሬት ጥያቄ ዙሪያም ተመሳሳይ አቋም አላቸው። በአጭሩ አራቱም ቀድሞ በሕዝብ ትልቅ ድጋፍ አግኝቶ የነበረውን የቅንጅት ማኒፌስቶን ይቀበላሉ።
እንደዚያም ሆኖ ግን እነዚህ ድርጅቶች፣ አብረው እንደገና መቀናጀት እስከአሁን አልቻሉም። ይሄ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ዴሞክራሲን ለተጠማው ወገናችን በጣም አሳዛኝ ሲሆን፣ ለአገዛዙና ለአምባገነኖች ደግሞ በጣም ያስደሰተ ድርጊት ነው። ይሄ በአስቸኳይ መቀየር ያለበት ይመስለኛል።
በአቶ ልደቱ አያሌው ይመራ የነበረው ኢዴፓ፣ ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ ብዙም አላውቅም። በምርጫ 2002 ኢዴፓዎች፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ከኢሕአዴግ ጎን በመሰለፍ፣ ከሌሎች ተቃዋሚዎች የተለዩ እንደሆኑ ለማሳየት ሞክረው ነበር። ነገር ግን ያ አካሄዳቸው ብዙ ውጤት ያመጣላቸው አይመስለኝም። ይሄን በሚገባ እነርሱ እራሳቸው የተረዱ ይመስለኛል።
አንዳንዶቻችን ደግሞ መረጃ ሳንይዝ፣ በኢዴፓ አመራሮች ላይ ስንዘነዝራቸው የነበሩ በርካታ ክሶችም ጠቃሚ አልነበሩም። ይህ፣ ከኢሕአዴግ ጋር ደምሮ፣ ኢዴፓዎችን የማጥቃት ዘመቻ፣ ኢዴፓ ወደ ኢሕአዴግ እንዲጠጋ በማድረጉ አንጻር አስተዋጽዖ ያደረገ ይመስለኛል። እኛ ነን ወደዚያ የገፋናቸው። ህወሓት/ኢሕአዴጎች ብልጥ ናቸውና፣ ሆን ብለው ለኢዴፓ ነገሮችን በማመቻቸት፣ በደስታ አስተናገዷቸው። በዚህም መልክ ኢዴፓን ኒውትራላይዝድ የማድረግ ዓላማቸው ከሞላ ጎደል ተሳካ።
እንግዲህ ኢዴፓዎችና እኛ ብዙ ተባብለናል። ብዙ ስህተቶች ሰርተናል። ነገር ግን ወቅቱ ትብብርን ይጠይቃል። "ያለፉትን ቁርሾዎች ወደ ጎን በመተው፣ በፖለቲካ ፕሮግራም ከሚመሳሰሏቸው ጋር ኢዴፓ አብሮ መስራት መጀመር ይገባዋል" እያልኩ ሌሎቻችን ደግሞ ኢዴፓን ለመቀበል እንድንዘጋጅ እጠይቃለሁ። ለምን ህወሓት/ኢሕአዴግ ያሸንፋል?
ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ስንመጣ ይሄን እላለሁ። የሰማያዊ ፓርቲ፣ አዲስ ፓርቲ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ የገነነ ፓርቲ ለመሆን ችሏል። በተለይም የአመራር አባላቱ ድፍረትና ቆራጥነት በውጭ ሀገር ብዙ ደጋፊዎችን አፍርቶላቸዋል። ለዚህ በወጣቶች ለሚመራ ድርጅት፣ እኔም በግለሰብ ደረጃ ትልቅ አድናቆት አለኝ።
ነገር ግን ሰማያዊዎች አንድ ማስተካከል ያላባቸው ጉዳይ አለ። ከሌሎች ድርጅቶ ጋር የመስራት ፍላጎት ብዙም ያላቸው አይመስልም። በትብብርና በአንድነት ማመን ይኖርባቸዋል። ለጊዜው ትልቅ የሆኑ ቢመስላቸው፣ አይሳሳቱ፤ ለብቻቸው ብዙ ርቀው እንደማይሄዱ ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ። ይህ የ"ብቻህን ተጓዝ" አቋማቸውን ትተው፣ ከሌሎች፣ በፖለቲካ ፕሮግራም ከሚመሳሰሏቸው ጋር አብሮ መስራት መጀመር ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ደግሞ በውጭ ካሉ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች መጠበቅ አለባቸው። በሀገር ቤት ካሉ ወንድሞቻቸው ጋር በጋራ በመሆን ትግሉን ከሀገር ቤት መምራት አለባቸው እንጂ ውጭ ባሉ መመራት የለባቸውም።
ወደ መኢአድና የአንድነት ፓርቲ ስመጣ ደግሞ፣ ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን እያየሁ መሆኔን መግለጽ እወዳለሁ። ለዚህም አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። አቶ አበባው መሃሪ ጌታነህ ይባላሉ። የአንጋፋው የመኢአድ ሊቀመንበር ናቸው። በቅርቡ ኤስ.ቢ.ሲ ከተባለ ራዲዮ ጣቢያ ጋር አጭር ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር። "ከአንድነት ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ በንግግር ላይ መሆናችሁ ይነገራል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው። ከሆነስ ከውህደቱ ምን ፋይዳ ይገኛል ይላሉ?" ተብለው ሲጠየቁ፤ አቶ መሃሪ የሚከተለውን ነበር የመለሱት።
"ሂደቱ እውነት ነው። ተጀምሯል። የሁለቱ ፓርቲዎች ፍላጎት ያሳዩበት ሁኔታ ነው ያለው። በእውነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሚያመች ሁኔታ ይሄ ድርድር ይጠናቀቃል። የኢትዮጵያን ሕዝብ የድል ባለቤት ወይንም የመብቱ ባለቤት ያደርጋል ብለን እናስባለን። ይሄ ውህደት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ "ወይ ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ" የሚል ነው። ሕዝቡ የትብብርን ግፊት እያደረገ ነው። "አንድ ላይ ሆናችሁ ይሄን ክፉ መንግሥት መገርሰስ አለባችሁ። አንድ ላይ ካልሆናችሁ ለውጥ ማምጣት ያስቸግራል" እያለ ሕዝቡ ግፊት እያደረገ ነው ያለው። ይሄንን የሕዝቡን ፍላጎት ምክንያት በማድረግ እየተደራደርን ነው"
(የአቶ መሃሪን ቃለምልልስ ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)
መኢአድ በሀገሪቷ ክልሎች ሁሉ መረብ ያለው፣ ከአንጋፋውና ተወዳጁ ፕሮፌሠር አስራት ወልደየስ ጊዜ ጀምሮ፣ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለዜጎቿ መብት የታገለ አንጋፋ ድርጅት ነው። እልም ያለ የሀገራችን ገጠሪቷ ክፍል ብትሄዱ በዚያ መኢአድ አለ።
የአንድነት ፓርቲ በበኩሉ፣ በቅርቡ በደሴ፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ አርባ ምንጭ፣ ባህር ዳር፣ ፍቼ፣ ባሌ ሮቢ፣ ጂንካ፣ አዳማ፣ ወላይታ ሶዳ፣ ... በመሳሰሉ የሀገሪቷ ክፍሎች፣ ባደረገው የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት እንቅስቃሴ በግልጽ እንዳሳየው፣ በጣም ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር ያለው፣ ሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ ሀገር በስፋትና በብዛት ደጋፊዎችን ያፈራ፣ በሳል ደርጅት ነው።
የመኢአድ እና የአንድነት መቀራረብ ወቅታዊ፣ ትግሉን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬድ፣ በማያሻማ መልኩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚቀየር መልካም ዜና ነው። ይሄ፣ ሕዝቡ እነርሱ የሚሉትን ብቻ በፍርሃት አሜን ብሎ እንዲቀበልና አማራጭ እንዳይኖረው የሚፈልጉ ህወሓት/ኢሕአዴጎችን የሚያስከፋ ነው። እንግዲህ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ፣ ይህ አይነቱ፣ አገዛዙን ከመስደብና ከመርገም ያለፈ ነገር፤ ድርጅታዊ ጥንካሬን በሕዝቡ ዘንድ የሚያጎለብት፣ የሕዝቡን አመኔታና ድፍረት የሚያሳድግ፣ በሳል የፖለቲካ ሥራ መሰራት አለበት።
መኢአድ ከጥቂት ወራት በፊት አዲስ አመራር አባላትን መርጧል። የአንድነት ፓርቲም፣ በቅርቡ በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባዔ፣ አዳዲስ ወጣቶችን በብዛት ያካተተ አመርሮችን ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል። ከአዳዲስ አመራሮች ጋር፣ የመኢአድና የአንድነት መቀናጀት እውን ይሆናል የሚል ትልቅ ተስፋ አለኝ። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊም የመኢአድ እና የአንድነት አመራር አባላትን እያደረጉት ባለው ውይይት "በርቱበት፣ ቀጥሉበት፤ ለሕዝቡም መልካም ዜና አሰሙት" እላለሁ።
እግዚአብሔር ያክብርልኝ!
አማኑኤል ዘሰላም

 www.ethiopiazare.com

No comments:

Post a Comment