Wednesday, December 11, 2013

New Interview with Teddy Afro [Enqu Magazine]

New Interview with Teddy Afro [Enqu Magazine]

(እንቁ መጽሔት) ተወዳጁን ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁንን በዚህ የመጽሔታችን ልዩ ዕትም፤ የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን 100ኛ የሙት ዓመት… በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለመከበሩን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄዎች አቅርበንለታል። ቴዲም በምላሹ “በማንኛውም ሁኔታ ጥሩ የሠራን ሰው ማመስገን፣ ማክበር ጠቃሚ ባህል መሆኑን ተረድተን፤ በዚህ በኩል እስከዛሬ ያለውን ስሕተት ማረም አለብን” ብሏል። ሌሎች መሰል ሐሰብ አስተያቶችንም ሰንዝሯል። ሁሉንም ከቃለ-ምልልሱ ዝርዝር ይዘት ያገኙታል። መልካም ቆይታ!
ዕንቁ፡- የዳግማዊ ዐፄ ምንሊክ 100ኛ የሙት ዓመት በብሔራዊ ደረጃ አለመከበሩን እንዴት አየኸው?
ቴድዎሮስ፡- በቅድሚያ ከአከባበሩ አግባብነት ተነስተን ለይተን ልናስቀምጠው የሚገባ ነጥብ መኖር አለበት። ይከበራል የሚባለው ቀን የሞቱበት ይሁን፤ ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመበት ወይስ ምኒሊክ በሠሯቸው አገራዊ ቁም ነገሮች ላይ ያአተኮረ ይሁን የሚለው ሀሳብ እራሱን የቻለ ውይይት የሚፈልግ ነው። እንዲህም ሆኖ ግን በግሌ የምኒልክ ማንነትም ይሁን ለኢትዮጵያ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በብሔራዊ ደረጃ አለመከበሩ ያሳስበኛል።
ዕንቁ፡- በአንተ ግንዛቤ ከኢትዮጵያ ባሻገር ባለው ዓለም ብሔራዊ ኩራት የሆኑ ሰዎች ስለምንድነው የሚታሰቡት? አያይዘህም ምኒልክን በማክበር ሊገኝ ይችላል ብለህ የምታምንበትን ብሔራዊ ጥቅም ብትገልጽልን?
ቴድዎሮስ፡- ግለሰቦች እንዲታወሱ የሚደረግበትም ምክንያት፤ መሻሻልና መደገም ያለባቸው ጥሩ ታሪኮች ወደ አዲሱ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ስለሚፈለግ ነው። እነዛ ብሔራዊ ኩራት መሆን የቻሉ ሰዎች ሲታሰቡ ወይም የመልካም ስምና ተግባራቸው ማስታወሻ ዝግጅት ተደርጎ ክብራቸው እንዲገለጥ ሲደረግ፤ ሌሎች መልካም የሚሠሩ ሰዎችን ማፍራት የሚያስችል መነሣሣትን ይፈጥራል። በመሆኑም ነው ክብረ በዓሎች በታላላቅ ግለሰቦች ስም እየተሰየሙ፣ የእነሱም መልካምነት እየታሰበ የሚወሱበት አንድ ብሔራዊ ዝግጅት የሚከናወንበት ሥርዓት የሚያስፈልገው።
ዕንቁ፡- ዳግማዊ ምኒልክ ስለዛሬይቱ ኢትዮጵያ መፈጠር ሲሉ የገቡበትን ጦርነት እንዴት ነው የምትመለከተው?
ቴዎድሮስ፡- ምንጊዜም ሰዎች የሚበጃቸውን ነገር እስኪገነዘቡት ድረስ ያለመግባባቱ መጠን ይሰፋል። ያም ግጭት ሊፈጥር ይችላል። ይህም ደግሞ በእኛ ሀገር ሁኔታ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሆነም ነው። እንዲህም ሆኖ ግን ለምሳሌ ምኒልክ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ዘምተው ንጉሥ ጦናን ማረኩ። ከማረኳቸውም በኋላ እግራቸውን እያጠቡ ‹‹የእኛ አንድ አለመሆን፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት አለመመሥረታችን፤ የጋራ ለሚሆነው ጠላታችን ጥቃት አሳልፎ የሚሰጠን አደገኛ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በዚህ ምክንያት ነው ወደ አንተ ጦር ያዘመትኩት እንጂ ሥልጣንህን ለመቀማትና በአንተ ላይ ለመግነን… ፈልጌ አይደለም። ማእከላዊ መንግሥታችንን ማጠናከሩ ግን ሁላችንንም የሚጠቅመን ነው። አገራችንን፣ በሕላችንን፣ ታሪካችንን፣ ቋንቋችንን ጠብቀንና ድንበራችንን አስከብረን ለመኖር ይረዳናል›› ነበር ያሏቸው።
ለምንጊዜውም ነገሮችን በቀና ማየትና የጎደለውን ሞልቶ፣ ያለውን ጥሩ ነገር እንዳለ ይዞ መሄዱ፤ ለተሻለ ሀገራዊ ርምጃ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህን የመሰለው አካሄድ ደግሞ በሌሎች አገሮች አልተሠራበትም የሚል ቅንጣት ዕምነትም የለኝም። ወቅቱ በረዳቸው መጠን የነበረውን የአንድነት ክፍተት ሞልተውና አመጣጥነው ማእከላዊ መንግሥቱን ከነበረው የግንዛቤ ማነስ ሁሉ… ቀድመው፤ በተቻለ መጠን በትህትና ዝቅ ብለው እግር በማጠብ ጭምር የነበረውን መጥፎ ሁኔታ መልክ ለማስያዝ ደክመዋል። ዛሬ ያለው ኢትዮጰያዊም ከተለያየ የኢትዮጵያ ብሔሮች ምንጭ ፈልቆ ይኸው በአንድነት ‹‹ኢትዮጵያዊያን ነን›› ለማለት ችሏል። ስለዚህ የምኒልክ ስም ብሔራዊ አክብሮት ማግኘት የሚገባው፣ በሕልውናችንም ላይ ከፍተኛ የሆነ ሚና ያለው፣ የተባበታተነውን ሰብስበው ያቆዩ በመሆናቸው ነው።
ዕንቁ፡- “በዐፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የተጀመሩት ሥልጣኔን የመከተል ጉዞዎች እንደጅምራቸው ቀጥለው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ያደጉትን ሀገራት ጎራ ለመቀላቀል በቻለች ነበር” በማለት የሚቆጩ ወገኖች አሉ። አንተስ ምን ትላለህ?
ቴዎድሮስ፡- ያንን የሥልጣኔ ጅምር ከነበረው የኋላቀርነት ሁኔታ ጋር ሲመለከቱት ለመቀበል በጣም ከባድ ነበር። ለምሣሌ ‹‹ ስልክ ማነጋገር የሰይጣን ተግባር ነው…›› በማለት የተቃውሞ ሃሳባቸውን የሚሰነዝሩ ሰዎች ነበሩ። እንደዚህ ያለውን አመለካከት እና አስተሳሰብ አሸንፎ ለመሄድ ምኒልክ ብዙ ደክመዋል። ከዚህ ተነስተን የመሄዱ ጉዳይ በእሳቸው ተነሳሽነትና አስተማሪነት የተጀመረ ቢሆንም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በስልጣን ዘመናቸው ትምህርትን በማስፋፋት የተወሰነ ደረጃ ለማስኬድ መሞከራቸው የስልጣኔ ምንጩ ትምህርት መሆኑን ያገናዘበ ቀጣይ እርምጃ ነው ለማለት ያስደፍራል።
ዕንቁ፡- አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ባለታሪክ የሆኑ አርዓያዎቻቸውን ያለማክበራቸው ችግር ከምን የመነጨ ነው?
ቴዎድሮስ፡- የችግሩን ምንጭ አጠር አድርጎ ለመግለጽ ያስቸግራል። ነገር ግን ምንግዜም ቢሆን ለጥሩም ይሁን ለመጥፎው ድርጊት፤ መንግሥትም በመንግሥትነቱ፣ ሕዝቡም በሕዝብነቱ የየራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንዲያም ሆኖ ለሀገርና ለወገን የሠራን ሰው ማክበር ጠቃሚ ባሕል ነው። ምንግዜም ቢሆን ጥሩ ተምሳሌት በማይኖረው ማኅበረሰብ ውስጥ ጥሩ የሚሰራ ዜጋ ለማፍራት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ በማንኛውም ሁኔታ ጥሩ የሠራን ሰው ማመስገን፣ ማክበር ጠቃሚ ባህል መሆኑን ተረድተን፤ በዚህ በኩል እስከዛሬ ያለውን ስሕተት ማረም አለብን። ጥሩን ነገር ማየትና ማክበር መቻል፤ ጥሩ ነገር በራስ ውስጥ እንዲሰርጽ መፍቀድ ማለት ስለሆነ፤ ከሞቱት ሰዎች ሕይወት ያለው ሥራቸዉን ወስዶ መራመድ የሚገባን ይመስለኛል።
ዕንቁ፡- እስቲ “ምኒልክ ተወልዶ…” ስለሚባልበት ምክንያት የሚሰማህን ግለጽልን?
ቴድዎሮስ፡- አዎ ‹‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፣ ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ›› ተብሏል። ለእኔ ዕንቁላሉ የምዕራባውያንን ባሕልና ቋንቋ፣ በመውሰድ የራስን ባህል እና ማንነት ለማስጣል የተሞከረውን ሀሳብ ይወክላል።ዕንቁላሉ ውስጥ ተደብቆ የመጣው የተገዥነት አስኳል ሌላው ምስጢር ነው። የዚህ ጥቅስ ወርቁ በራሱ ባለብዙ ትርጉም ነው። ምኒልክ በራስ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ፍልስፍና… የመመራት አስተሳሰብ እንዳይጠፋ ያደረጉትን አስተዋፆም ደርቦ ይገልፃል።
ዕንቁ፡- “የምኒልክ ታላቅነት መከበር የነበረበት በኢትዮጵያ ብቻ አልነበረም። በአፍሪካም ደረጃም ነው እንጂ” የሚሉ ወገኖች አሉ። ለዚህም አባባላቸው አስረጅ የሚያደረጉት የዓድዋን ድልና የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎውን ነው። የአንተ እስተያየትስ?
ቴዎድሮስ፡- በስፋት እንደሚታወቀው የዓደዋ ድል፤ ለመላው አፍሪካውያን ወንድሞቻችን…. ነጻ መውጣት ታላቅ የሞራል ስንቅ መሆን የቻለ ነው። የኢትዮጵያ አርበኞች ትግል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው የመሰከረ ነው። ነገር ግን ይህን ታሪክ አፍሪካዊ በዓል አሳክለን ከማክበራችን በፊት ትርጉሙን ባገናዘበ መልኩ ኢትዮጵያዊ በዓል አክሎስ ይከበራል ወይ የሚለዉን ጥያቄ በቅድሚያ ለራሳችን መመለስ ያለብን ይመስለኛል።
ዕንቁ፡- ከዚሁ ወቅታዊነት ያለው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ይኖረዋል የሚል ግምት አለንና … “ጥቁር ሰው ” የተሰኘውን ዜማ ለመሥራት ምን አነሣሣህ?
ቴዎድሮስ፡- አንድ ሰው ከፍላጎቱ፣ በውስጡ ከሚፈጠረው ስሜትና ከተፈጥሮአዊ ዝንባሌው በመነሳት ሥራዎችን ይሠራል። አንድ ሰው ማንን ይመስላል? ቢባል፤ እናቱንም አባቱንም ከመምሰሉ በላይ አነጋገሩን ይመስላል እንደሚባለው እኔም የምጫወተው ሙዚቃ የምናገረውን ይመስላል ማለት ነው። ከምንምና ከመቼውም ጊዜ በላይ ለእነዚያ ታሪክ የሠሩ ሰዎች አክብሮት መጠስት ተገቢ ነው የሚል ስሜት በውስጤ ይመላለስ ስለነበር፤ ያንን ስሜት ለመግለፅ ስል የሠራሁት ሙዚቃ ነው።
ለምሣሌ የምኒልክ ተግባር ዛሬ ያለንበትን ሀገር መዋቅር የሠራ በመሆኑ፤ የተዘፈነው ዘፈን ለክብራቸው ቢያንስ እንጂ የሚበዛ ሊሆን አይችልም። እንዲህም ሆኖ መቼም የሰው ልጆች አመለከካከት እና ስሜት የተለያየ ስለሆነ ዳግማዊ ሚኒልክ ያበላሹት ተግባር አለ ብለን የምናምን ወገኖች ካለን እንኳ የተበላሸውን ነገር ለማስተካከል በተበላሸ መንገድ መሄድ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። በተበላሸው መንገድ የሚኬድ ከሆነ ምንጊዜም በዚህ ምድር ላይ ዕዳ ተከፍሎ ሊያልቅ አይችልም።ዕዳ ተከፍሎ የሚያልቀው በፍቅር ብቻ ነው። ጥቁር ሰውንም የፈጠረው ‹‹ፍቅር ያሸንፋል›› የሚለው መንፈስ ነው። ። በዳህላክም ላይ የምናየው ይሄንኑ ነው። ስለዚህ ዕዳ የመሰረዝ ጉዳይ ከአበዳሪ አገሮች የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከእየራሳችንም ህሊና የሚጠበቅ ተግባር ነዉ።
ዕንቁ፡- የምኒልክ የመሪነት ጥንካሬ ከራሳቸው ብቻም ሳይሆን ከዕተጌ ጣይቱም አጋርነት የሚመነጭ ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብት ላይ ሠፍሮ ይነበባል። አንተስ ስለጣይቱ ምን ትላለህ?
ቴዎድሮስ፡- ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ሴት አለች እንደሚባለው የምኒልክ ጥንካሬ የጣይቱም ነው። ከዚህም በዘለለ ልናየው ስንሞክር የጣይቱ ሚና ሲመዘን አንደኛ የምኒልክን የልብ ሥፋት የምንረዳበት ነው። በጊዜው እንደማንኛውም ኋላቀር አስተሳሰብ ለሴቶች ከሚሰጠው ግምት አንፃር ምኒልክ ሚስታቸውን በነበሩበት ደረጃ ኃላፊነት የሰጡ፣ ምክራቸውንም ለመቀበል የማያመነቱ ሰው ሆነው እናገኛቸዋለን። ዛሬ ስለሴቶች ጥንካሬ ለማወራት፤ ጣይቱ በጣም ጥሩ ምሣሌ ናቸው። ይሄ የጣይቱ ብልሀት፣ የጣይቱ መንፈሳዊ ጥንካሬ፣ የአመለካከት ሥፋትና ጥልቀት… ምኒልክን ‹‹ዕምዬ›› እስከማሰኘትና አልፎ ተርፎም በዓድዋ ጀግንነታቸው ጎልቶ እንዲዋጣ የወኔ ኃይል እስከመሆን ደረጃ የዘለቀ ነው። የሁለቱ የመቻቻልና የመደማመጥ መጠን በራሱ፤ በተለይ አሁን አሁን… ለሚስተዋለውና ‹‹የሴቶች የበታችነት፣ የወንዶች የበላይነት…›› ለሚባለው አጀንዳ ጥሩ ማጣቀሻ ነው። ከዚህም ባሸገር ጣይቱ በብዙ መመዘኛ ትልቅ ሥራ የሠሩ ሴት ናቸው።
ዕንቁ፡- ምኒልክን በተመለከተ እንደ ሙዚቃው ሁሉ ፊልም ሠርቶ ሕያው ሥራዎቻቸውን ማክበር አይቻልም?
ቴድዎሮስ፡- አንተ ያላከበርከውን ሌላው ሊያከብርልህ አይችልም። አፍሪካዊያን ወገኖቻችን የእኛን አባቶችና አያቶች ዋጋ ያውቃሉ። እኛ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ገና ጭቅጭቃችንን አልጨረስንም። ስለዚህ በፊልምም ሆነ በሙዜቃ መደገፎ ጠቃሚነቱ በአያጠያይቅም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እኛ በታሪካችን ላይ ያለንን ግንዛቤ የማስፋት ደረጃና ጥልቀቱ በቂ ሆኖ መገኘቱ ላይ ነው።
ዕንቁ፡- የምኒልክ ማንነት በብሔራዊ ደረጃ መከበር ይገበዋል… ከመባሉ አኳያ ለወጣቱ ትውልድ የምታስተላልፈው መልዕክት ይኖርሃል?
ቴዎድሮስ፡- ቅንነት ከሌለ ጥሩ ነገር ማየት እንደማይቻል አውቆ። ታሪኩንም በቅንነት ስሜት መመርመር ይኖርበታል። የባለታሪክ ሰዎችን ጥሩ ነገር መውሰድና ጥሩ ያልሆነ ነገራቸውን ደግሞ እንዳይደገም ለማረም መትጋት ከኛ ከወጣቱች ይጠበቃል። ትልቁና ቁልፍ ነገር የማንነትን መሠረታዊ ጥያቄ ከመገንዘብ ይመነጫል። ሕይወትም የሚጀምረው ራስን ከመሆን ነው። ሰው ራሱን ሲያክል ሌላ ብዙ ነገር ማድረግ ይቻለዋል።… ስለዚህ የነገር ሁሎ ምንጭ ፍቅር ስለሆነ ከፍቅር የሚጀምረውን ህይወት በፍቅር ለመጨረስ ቅንነት ያስፈልጋል። አመጣጡን ያዬ አካሄዱን ያዉቃልው ምክኒያቱም ታሪኩን እየዞረ የማያይ ተጋዥ የኋላ መመልከቻ መስታወት የሌለው መኪናን ይመስላልና።

sodere

No comments:

Post a Comment