Wednesday, December 18, 2013

ቴዲ Vs ምኒልክ፡ ስለ ጥቁር ሰው ወይንስ ስለ ጥቁር ገበያ? – ከታምራት ነገራ (ጋዜጠኛ)


ቴዲ አፍሮ ዳግማዊ ምኒልክን አስመልክቶ ለዕንቁ መጽሄት የሰጠውን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ ሱናሚ ሊባል የሚቻል ንትርክ ስለ ቴዲ እና ስለ ዳግማዊ ምኒሊክ በሶሻል ሚዲያ ተናፍአል፡፡ ሰሞኑ ደግሞ የዳግመዊ ምኒልክ ያረፉበት መቶኛ ዓመት የሚታሰብበት መሆኑ ለሱናሚው ትልቅ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡
ቴዲ አፍሮ ጥቁር ሰው ከሚለው አልበሙ ወዲህ ስለዳግማዊ ምኒልክ በተለያዩ ቦታዎች ተናግሯል፡፡ እኔን ግን ከቴዲ አፍሮም ፣ ከዳግማዊ ምኒሊክም፣ ከጥቁር ሰው አልበምም በእጅጉ የሳበኝ የዳግማዊ ምኒልክ ተዋስዖ (Discourse) ነው፡፡ በተለይም ተዋስዖው እየተካሄደ ያለበት ገበያ በእጅጉ ስቦኛል፡፡ አንድን ተዋስዖ ስናስተውል የተዋስዖውን በርካታ ክፍሎች ለያይተን ልናይ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የአንድን ተዋስዖ ይዘት የሚያጠና ሰው በተዋስዖው ውስጥ ጎልተው በተደጋጋሚ የሚታዩ ሐሳቦች፣ ቃላት፣ እና ዝንባሌዎች ያጠናል፡፡ በተያያዥነትም በተዋስዖው ዙሪያ ወሳኝ የሚባሉትን መልዕክት አስተላላፊ ምርቶች ለምሳሌ ዘፈኖች፣ ፊልሞች፣ አልበሞች፣ መጽሐፍትን፣ መፈክሮች፣ እና ፖስተሮች ሊያጠና ይችላል፡፡ በተዋስዖው ዙሪያ ያሉ ተዋናዮች ላይ ማተኮር የሚፈልግ ሰው ደግሞ ተዋስዖውን የሚያንቀሳቅሱትን የሐሳብ አመንጭ እና አከፋፋይ ጋዜጠኞች፤መጽሄቶች፤ ፀሐፍት፤ ምሁራን ፤አርቲስቶች ዙሪያ ጥናቱን ያተኩረል፡፡ ልክ እንደዚሁ አንድ ሰው አንድ ተዋስዖ የሚካሄድበትን ገበያ አተኩሮ ማየት ይችላል፡፡
Teddy afro minilik
ገበያ የሚለውን ቃል የምጠቀመው በተዋስዖው ውስጥ ያለውን ትርፍ ወይንም ኪሳራ ብቻ ለማሳየት ሳይሆን ተዋዖውን በሚያካሂዱት ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ቡድኖች እና ሐሳቦች መካከል የሚደረገውን ግብይት የሚካሄድበትን ሥርዓት (System) ለማመላከት ነው፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ ወቅታዊው፣ ትልቁ፣ እና እውነተኛው ጥያቄ ቴዲ፣ ጃዋር፣ በቀለ፣ ጫልቱ፣ እና አብደላ ስለ ዳግማዊ ምኒልክ ምን አለ? ምን አለች? ምን አሉ? አይደለም፡፡ ስለ ዳግማዊ ምኒልክ በክፉም ኾነ በደጉ መናገር እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ እንዴት ሱናሚ ማስነሳሳት ቻለ ? ስለ ዳግማዊ ምኒልክ እገሌ ገለመሌ ቢል ስለለምን ይኼን ያህል ያወዛግበናል? ይኼ ለእኔ ትልቁ እና ዋነኛው ጥያቄ ነው፡፡ ሱቅ በደረቴዎች የዳግማዊ ምኒልክ አድናቂዎችም ኾኑ ተቺዎች ስለ ዳግማዊ ምኒልክ የሚያስደስታቸውን፣ የሚያምኑበትን፣ እንደውም ሕይወታቸውን እስከሚሰጡለት ድረስ የሚያምኑትን ነገር እየተናገሩ፣ እያደረጉ እንደኾነ ሊወተውቱን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በዳግማዊ ምኒሊክ አድናቂዎችም ሆነ አውጋዦች መካከል በሚደረገው ምልልስ ከመሳተፍ በመጠኑም ራቅ እና ከፍ ብለን ለማየት ከሞከርን ግን የዳግማዊ ምኒልክን አድናቂዎችም ኾነ ተቺዎችን የሚያስተዳድረውን ገበያ ለማየት እንችላለን፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ ደጋፊዎችም ኾነ ተቺዎች በዳግማዊ ምኒልክ ተዋስዖ ዙሪያ ያላቸውን ሐሳብ በተገኘው አጋጣሚ እና ሥፍራ ከማስተላለፋቸው አልፈው በዳግማዊ ምኒልክ ዙሪያ አለኝ የሚሉትን ዕውቀት እና ግንዛቤ እንዴት እንደ ጨበጡት፣ ማን እንደሰጣቸው፣ ከየት እንዳገኙት፣ እና እንዴት እንደ ቀረበላቸው የሚኖራቸው ግንዛቤ እጅግ ውሱን ነው፡፡ አንድ ባለሱቅ በሱቁ ውስጥ ስላለው እቃ እና ዋጋ መጠነኛ ግንዛቤ ይኖረዋል ሊኖረውም ይገባል፡፡
ከዛ ባለፈ ግን አገሪቷን ወይንም ዓለምን ስለሚያንቀሳቅሰው የገበያ ሥርዓት፣ የገበያ መርህ፣ የገበያ ተቋማት፣ እና የገበያ ሕግጋት ኃይል ያለው ግንዛቤ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ጩኸት፣ ትርምስ፣ምሥጢር፣ ግርግር፣ ፍርሀት… ዳግማዊ ምኒልክ እና ሥርወ መንግሥታቸው በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ካላቸው ሰፊ ተጽዕኖ ተነስተን ከተወያየን እስከ ዛሬ አይደለም ገና ለሚቀጥሉት ብዙ መቶ ዓመታት የማንግባባቸው በርካታ ነጥቦች ይኖራሉ፡፡ ለእኔ አሳሳቢው ጉዳይ ስለዳግማዊ ምኒልክ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ሙሉ ስምምነት ላይ መድረስ አይደለም፡፡ አሳሳቢው ጉዳይ ለምን በውይይቱ መካከል ስክነት፣ እርጋታ፣ ዕውቀት፣ እና እውነት ጠፍተው በሥፍራቸው ጩኸት፣ ትርምስ፣ እና ድንቁር እንደ ምን ነገሡ ነው፡፡ እንደ እኔ እምነት በዳግማዊ ምኒልክ ዙሪያ የሚደረገው ተዋስዖ ከስክነት ትርምስ እንዲበዛው፣ በምክንያት ከሚናገሩ ሰዎች ጯኂዎች መድረክ እንዲያገኙ፣ አዋቂዎች ከአላዋቂዎች እንዳይለዩ፣ እውነት የያዙ ፈርተው ሐሰተኞች እንዲዳፈሩ ነገር ዓለሙ በአጠቃላይ ትርምስ እንዲበዛበት ሆን ተብሎ እተደረገ ነው፡፡
minilikበዚህ አጋጣሚ ርዕሰ ጉዳዩ የምኒልክ ተዋስዖ ስለኾነ እንደ ምሳሌ ልጠቀመው ብዬ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ስላለው ማንኛውም ተዋስዖ በእርጋታ፣ በአመክንዮ እና በዕውቀት መናገር አይቻልም፡፡ ይህ ትርምስ የተፈጠረው ደግሞ በአብዛኛው ኾን ተብሎ በተገነባ የተዋስዖ ገበያ ሥርዓት እንጂ ዝም ብሎ በአጋጣሚ ከሰማይ ዱብ ያለ ክስተት አይደለም፡፡ የዳግማዊ ምኒልክን ተዋስዖ በምናየው እጅግ አጨቃጫቂ በኾነ መልኩ በመላው አገሪቷ እንዲተዋወቅ የተማሪዎች ንቅናቄ እና የሕወሃት መንግሥት ዋነኛውን ሚና ተጫውቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዳግማዊ ምኒልክ ዙሪያም ኾነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ዙሪያ የምንሰማቸውን በርካታ ሀሳቦች ጥንስሳቸው በ1966ቱ የተማሪዎች ንቅናቄ ነው፡፡ በተማሪዎች የተነሱትን አንዳንድ ሐሳቦች ለምሳሌ መሬት ላራሹ የደርግ መንግሥት በከፊል ተግባራዊ ተደጓል፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል እና ሌሎች መሰል ሐሳቦችን ግን እንኳን ሊተገብር መኖራቸውንም እንኳ በአግባቡ ሳይናገር ዘመኑን ጨረሰ፡፡ በ1983ዓ.ም ሕወሃት ሥልጣን እንደያዘም ሻዕቢያን እና ኦነግን በግራ እና በቀኝ አስከትሎ በተማሪዎች ንቅናቄ የተጠነሰሱ በርካታ ሐሳቦችን በመላው አገሪቷ አወጃቸው፡፡ የፈለገውን ሕግ አደረገ ያልፈለገውን ችላ አለ፡፡ ሌዋታን፤ የገበያው ጌታ ማንኛውም መንግሥት በሚያስተዳድረው አገር ላይ በሚካሄደው ተዋስዖ ላይ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር የታደለ ማንም ግለሰብ እና ቡድን ደግሞ በኢትዮጵያ ተዋስዖ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ በእጅጉ ኃያል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ኋይት ኃውስን ለመቆናጠጥ እድል የቀናው ፓርቲ በአሜሪካ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ተዋስዖውን ሊያነቃንቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሜሪካንን የሚገዛው ፓርቲ በአሜሪካ ተዋስዖ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ፓርቲ በኢትዮጵያ ተዋስዖ ላይ ከሚኖረው ተጽዕኖ ጋር ሲነጻፀር አቅሙ እጅጉን ውሱን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፓርቲ ዋይት ኃውስን ያዘ ማለት ኮንግረስ በእጁ ነው ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ በፖሊሲ እና በጀት መሰል ጉዳዮች ላይ ያለው ተጽዕኖ ይወሰናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ተዋስዖን በመቅረጽ፣ በማዳበር፣ እና በማከፋፈል ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ሚዲያ፣ የሕትመት ቤቶች፣ እና መሰል ተቋማት በዋይት ኃውስ እጅ ውስጥ አይደሉም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንድ ቡድን በድንገት ተነስቶ ወዲያውኑ የአገሪቷን ተዋስዖ ወደ ፈቀደው ርዕዮተ ዓለም (Ideological) ዝንባሌ መንዳት እንዳይችል የሚያደርጉት ዘልማዶች እና ሕግጋቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካን ዶላር እና ሳንቲሞች ላይ የሕያው ፕሬዝዳንት ምሥል እንዳይቀረጽ ህግ አለ፡፡ ይህ ሕግ እንደ አሁኑ በይፋ ሕግ ሆኖ ከመጽደቁ በፊት የሕያው ፕሬዝዳንት ምሥል በዶላር ላይ እንዳይቀረጽ ያልተጻፈ ስምምነት ነበር፡፡ የኛ ብር መልኩ ስንቴ ተለዋወጠ? እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ማንበብ እና መፃፍን የመሰለ ዝቅተኛው የተዋስዖ መሳተፊያ ክህሎት ጭራሹኑ በሌለበት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ገደብ የሌለው ሥልጣን በእጁ ላይ የወደቀ ቡድን በአገሪቷ ተዋስዖ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ልክ የለውም፡፡
በዚህ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚኖረው ጉልበትም የተዋስዖውን ይዘት ከመቆጣጠርም አልፎ ተዋስዖው የሚካሄድበትን ገበያ ሕግጋት እንደ ፈለገው መቆጣጠር እንዲችል አቅም ይሰጠዋል፡፡ ሕወሃት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በዳግማዊ ምኒልክ ዙሪያ የለኮሰውን ተዋስዖ ለአጃንዳ አጠር ሎሌዎች በሊዝ አኮናትሮ ገበያውን በጌታነት ከላይ ሆኖ እየዘወረው ነው፡፡ በአንድ አገር የተዋስዖ ገበያ ላይ እጅግ ተፈላጊው ግብ እውነትን ማግኘት ነው፡፡ እውነት በአንድ ጉዳይ ላይ የሚኖረንን የመረጃ ትክክለኝነት እና ሐሰትነት ላይ ብቻ የተገደበ ግንዛቤ አለመኾንኑ፤ በተዋስዖ ትንታኔ ውስጥ በአብዛኛው እውነት ስንል ከመረጃው ትክክለኝነት እና ስህተትነት ባሻገር ያሉ ሐሳቦችንም ይዳስሳል፡፡ በተዋስዖ ትንታኔ ውስጥ እውነት የተዋስዖው ተሳታፊዎች በመረጃው ላይ የሚኖረቸውን ትርጓሜ፤ በትርጓሜው ላይ ያላቸውንም ስምነት ሊያካትት ይችላል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ዘመቱ የሚለውን አረፍተ ነገር እንውሰድ፡፡ ይህኑ አረፍተ ነገር አንድ የዳግማዊ ምኒልክ ነገር ሲነሳ ሆዱን ባር ባር የሚለው ወዳጃችን ብድግ ብሎ ዘመቻው ከእግዚአብሄር ለኢትዮጵያ የተሰጠ ቅዱስ ስጦታ ነው ብሎ ይህንኑ አረፍተ ነገር ሊተረጉመው ይችላል፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ ነገር ሲነሳ የሚያንገሸግሸው ሌላኛው ወዳጃችን ደግሞ ብድግ ይልና ዘመቻው የተካሄደው ዳግማዊ ምኒልክ አያቶቼን እንዲያጠፏቸው በሰይጣን ስለታዘዙ ነው ብሎ ትርጓሜውን ይሰጠናል፡፡ እነዚህም ሆኑ ሌሎች በርካታ ትርጓሜዎች በዳግማዊ ምኒልክ ተዋስዖ ዙሪያ ይኖራሉ፡፡ እያንዳንዱ ቡድን የራሱን ትርጓሜ ይዞ ወደ ገበያው ይመጣል፡፡ ትርጓሜ ሊሸጥ፣ ትርጓሜ ሊገዛ፡፡ ሕወሃት ግን ገበያው ውስጥ ትርጓሜ ይዞ ከመቅረብ የተዋስዖ ቸርቻሪነት ከወጣ ሰነበተ፡፡
tedy afro new
እጅግ የሚያዋጣው የገበያውን ሥርዐት እና መዋቅር መቆጣጠር እንደ ሆነ ስለገባው ችርቻሮውን ለጉልቶች ሰጥቶ ኪራይ ይሰበስባል፡፡ ሕወሃት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የተዋስዖ ገበያ በነጻ ገበያ መርህ እንዲመራ ፈጽሞ አይፈልግም፡፡ ይልቁኑ የተዋስዖው ገበያ የሚያስተዳደረው ሻጭንም ሆነ ሸማችን በሚያደናብረው የጥቁር ገበያ መርህ ነው፡፡ በነጻ ገበያ መርኾዎች የሚንቀሳቀስ የተዋስዖ ገበያማ እውነትን ያገኛታል፡፡ እውነትን ያገኛት እርሱ ደግሞ አርነት ይወጣል፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በገበያው ካሉን እልፍ አዕላፍ የምኒሊክ ትርጓሜዎች በተደጋጋሚ ጮክ ብለው የሚሰሙት ሁለቱ ጽንፈኞች ብቻ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የተዋስዖ ገበያ የሚመራበት ሥርዐት የገበያው ተሳታፊዎች ወደግራም ሄዱ ወደቀኝ ወደ አንድ ትርጓሜ እንዲሰባሰቡ፤ በዚያ ትርጓሜ ዙሪያም አዲስ እውነት ቀርጸው የጋራ አገር እንዲገነቡ የሚፈልግ የገበያ ሥርዓት አይደለም፡፡ ሕወሀት ምን ዐይነት ሚዲያ፤ በምን ያህል መጠን እንደሚኖር ይወስናል፡፡ ያለማንም ሀይ ባይነት የትምህርት ሥርዐቱን ወደ ፈለገው የትርጓሜ አቅጣጫ ያሳልጣል፡፡ የአደባባዮች፣ የመንገዶች፣ የሀውልቶች፣ አስፈላጊ ከኾነ ደግሞ የከተሞችን ስም እርሱ ወደፈለገው የተዋስዖ ትርክት እንዲያፈገፍጉ በማድረግ ገበያውን እንዳፈተተው ያቆማል፣ ይበትንማል፡፡ የብሔራዊ መዝሙር፣ የባንዲራ፣ የብሔር ብሔረሰብ ክብረበዓላት ይቀርጻል፣ ያውጃል፣ ይበጅታል፣ ያስፈጽማል፡፡ የአየር በአየር ነጋዴዎች ለጥቂት ደቂቃ አገሪቷ ውስጥ ያሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከፓርቲው ገለልተኛ ቢሆኑ፤ ነፃ ሚዲያ በብዛት እና በጥራት ቢስፋፋ፤ የትምህርት ሥርዓቱ የሚቀረጸው አሁን ከሚታየው ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በተለየ መልኩ ቢኾን ኖሮ ምን አይነት የተዋስዖ ገበያ በኢትዮጵያ እንደሚኖር ለመገመት አያዳግትም ፡፡ በምናባዊቷ ኢትዮጵያም እንኳን ስለዳግማዊ ምኒልክም ኾነ ስለጨለንቆ ሙሉ በሙሉ አንስማማም፡፡ ነገር ግን ውይይቱን የሚያስተናብሩት የጥቁሩ ገበያ የአየር በአየር ነጋዴዎች ፤ ውይይቱንም የሚመሩት ለጥቁር ገበያው የተመረቱ አልበሞች፣ መጽሐፎች፣ ድግሶች እና ሰልፎች አይሆኑም፤ የውይይቱ ይዘትም ልክ 1983 ዓ.ም እንደ ነበረው እጅ እጅ አይልም ነበር፡፡ ያልጨረቱ ሀልዮቶች፣ ያልነፈሰባቸው ትችቶች፣ አዳዲስ ዘርፎች በየጊዜው እየበቀሉ እያደጉ ስለዳግማዊ ምኒሊክም ሆነ ስለ ኢትዮጵያ የሚደመጡት ትንታኔዎች እና ትርጓሜዎች ለተዋስዖው ሞገስ ይሆኑት ነበር፡፡ የገበያው የበላይ ጠባቂ ሕወሃት እጅጉን የሚጠነቀቀው ስምምነት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በየትኛውም ተዋስዖ ላይ የሰከኑ አስታራቂዎችን ሳይሆን ስምምነት ላይ ለመድረስ ይቅር እና ለመደማመጥ የማይችሉትን ያበረታታል፡፡
በዚህ ድቅድቅ ጭለማ ውስጥም ሁሉም በእውር ድንብር ይተራመሳል፡፡ ጥቂት ትንሽ ሻል ያሉ አራዶች በየጥጋጥጋቸው ርዕስ እና ትርጓሜ እየመረጡ ቢጫ ሰው ፣ ሰማያዊ ዶሮ፣ ሲያዴ ፈረስት፣ እና ሚያዚያ 9 ምናምን የሚል የአየር በአየር ቡቲክ ይከፍታሉ፡፡ ከዚህም ከዚያም የለቃቀሙትን የትርጓሜ ሰልባጅ አዲስ ልብስ አስመስለው ይሸጣሉ፡፡ እነዚህ የአየር በአየር ነጋዴዎችም የገበያውን ሕግ አይቀይሩም፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም የገበያው መሰረታዊ ሕግ ከተቀየረ ሕልውናቸው አደጋ ላይ እንደሚኾን ስለሚገነዘቡ ከጥቁር ገበያነት ወደ ነጻ ገበያነት እንዲለወጥም አይፈልጉም፡፡ ገበያውን እንዴት አድርጌ ነው የምጠቀልለው ብለው ሁሉ የሚገዛው ትርጓሜ ለማምጣትም አፈልጉም፡፡ የአየር በአየር ነጋዴዎች ናቸው እና ቶሎ ቶሎ ከግርግሩ አትርፈው ሽል እና ሽብልል ከማለት ውጪ ገበያውን ሙሉ ለሙሉ ለመማረክ ወገቡም የላቸውም፡፡ To be fair ለሕወሀት ሳይሆን ለእውነት ‘ፌር’ ለመሆን የኢትዮጵያ ተዋስዖ ገበያ የጥቁር ገበያን መርህ መከተል የጀመረው ግንቦት 20/1983 አይደለም፡፡ ከሕወሀትም በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የትርጓሜ ገበያው በገዢው ቡድን ተፅዕኖ መሆኑ አይካድም፡፡ የወቅቱ ትክክለኛ መረዳት ተዋስዖው የጥቁር ገበያ ሥርዐት መኾኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ እንዴት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ትርጓሜዎች በሰላም ሊንሸራሸሩ የሚችሉት ? በእርጋታ እና በስክነት የሚንቀሳቀስ የተዋስዖ ገበያ ሥርዐት መመስረቻ ቁልፎቹ ምንድን ናቸው ? በባህሎቻችን እና በቋንቋችን ውስጥ ምን ያህል ሀብት ምን ያህል ድህነትስ አለ ? አሁንም ስለጥቁር ሰው ማሰብ ይፈልጋሉ ? I don’t .
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

No comments:

Post a Comment