Monday, December 16, 2013

ሰመጉ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ዉስጥ ወያኔ የዜጎችን ሰብአዊ መብት መርገጡን አጋለጠ


የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዉስጥ ባካሄደው ጥናት ባለፈዉ አመት ከክልሉ አማራ ናችሁ ተብለዉ በተባረሩ በብዙ ሺዎች በሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የክልሉ ባለስልጣኖችና የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች የሰብአዊ መብት ጥሰት እና አካላዊ ጉዳት ማድረሳቸዉን አረጋገጠ። በክልኩ በተለያዩ ዞንና ወረዳዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ቁጥራቸው ከ10 ሺህ በላይ የሚገመቱ ዜጐች ለረዥም አመታት ይኖሩበት ከነበረው አካባቢያቸው የዚህ ክልል “ተወላጆች አይደላችሁም” በማለት በሀይልና በግዳጅ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከመጋቢት 15/2005 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰደዱ መደረጋቸውን ተቋሙ አውስቷል፡፡
የሰመጉ የጥናት ቡድን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡለን እየተባለ በሚጠራዉ ወረዳ ባካሄደዉ ጥናት ህፃናትና ሴቶች እንዲሁም አቅመ ደካማዎች በቂ ምግብና ህክምና ባለማግኘታቸው በከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀው እንደነበር አረጋግጦ የጉዳዩን ስፋትና ተፈናቃዩች በአሁኑ ግዜ የሚገኙበትን አጠቃላይ ሁኔታ ለማጣራት መቻሉንም ገልጿል።ተፈናቃዮቹ አሁን የሚገኙበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው ያለው የጥናቱ ሪፖርቱ፤ በአንዳድ አካባቢዎች ለምሳሌ በካማሼ ዞን ተፈናቃዮቹ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ የተደረገ ቢሆንም ከተመለሱ በኃላ ንብረታቸው በመወሰዱና በመጥፋቱ ለመቋቋምና ወደ ነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ለመመለስ አልቻሉም ። በተለይ ተፈናቃዮቹ ለእርሻ ግብዓት የሚሆኑ እንደ ዘር ፣ማዳበሪያ የመሳሰሉትን ለመግዛት ወይም ብድርም ለመውሰድ በሞከሩባቸዉ አማራ በመሆናቸዉ ብቻ አድሎ እንደተደረገባቸዉ ለማወቅ ተችሏል።
በጥናቱ ወቅት ተፈናቃዮቹ ለሰመጉ እንዳስረዱት የደረሰባቸውን ከፍተኛ በደልና እንግልት በተለያዩ የሀገር ውስጥ ጋዜጦችና የውጭ ሚዲያ በመናገራቸው ምክንያት እስራት ዛቻና ክትትል እየተፈፀመባቸው እንደሆነና በከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ተፋናቃዮቹ ለረዥም አመታት ያፈሩትን ንብረትና የእርሻ መሬታቸውን በአካባቢው ባለስልጣናትና በሌሎች ብሔረሰብ አባላት መነጠቃቸውን፣ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶቻቸውን እንዳያዙበት መደረጋቸውን፣ መታወቂያ ካርድ እንዳያወጡ መከልከላቸውንና፣ ልጆቻችው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው እንዳይማሩ መደረጉን ተናግረዉ “የዚህ ክልል ተወላጅ አይደላችሁም” እየተባሉ ዛቻ፣ ድብደባ፣ ንብረት ነጠቃና ለእሰራት ጭምር እንደተጋለጡ የተፈናቃይ ተወካዮች ለሰመጉ በፃፉት ማመልከቻ ተናግረዋል።
የባሩዳ ቀበሌ ተፈናቃዮች “ በአካባቢው አስተዳደር አካላትና በሌሎች የክልሉ ብሄረሰብ አባላት የተነጠቁትን የተለያዩ ንብረቶች ተመላሽ አለመደረጉን ፣በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ብሄረሰቦች እየተለዩ ማስፈራሪያና ድብደባ እየተፈፀመባቸው መሆኑ፣ ምንም አይነት እገዛና ማቋቋሚያ አለመደረጉ፣ የእርሻ ግብዓትን እንደ ዘር ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችን “እናንነተ የዚህ (ብሄር) አባላት ናችሁ” በማለት እየተከለከሉ ነገር ግን ለሌሎች እየተሰጠ እንደሚገኝና በፌዴራል መንግስት አማካኝነት ቢመለሱም የዞንና የቀበሌ አስተዳደር አካላት “እናንተ ከዚህ ክልል ውጪ ናችሁ” በማለት ልዩ ልዩ አድልዎና መገለል እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ ለሰመጉ አመልክተዋል፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ለረዥም አመታት ይኖሩበት ከነበረው ቦታ “ የዚህ አካባቢ ሰዎች አይደላችሁም” በማለት ከተፈናቀሉ በኋላ ወደ ነበሩበት ቦታ ይመለሱ እንጂ ምንም አይነት እገዛ ከመንግስት እንዳልተደረገላቸውና ይባስ ብሎም እንግልትና የተለያዩ አስተዳደራዊ በደሎች እየተፈፀመባቸው እንዳለ ዘጋቢያችን ሪፖርቱን ተከትሎ ባደረገው ማጣራት ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል።

 https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/12/16/232-13/

No comments:

Post a Comment