Friday, December 6, 2013

ለስደት የዳረጉን ኢኮኖሚያዊ ማሳያዎች Economic indicators that force Ethiopians to leave their country


ሰንደቅ ጋዜጣ ሪፖርተር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከህገወጥ ስደት ጋር በተያያዘ ከሚነሱት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንባር ቀደሙን ቦታ እየያዙ ነው። በቅርቡ በሳዑዲ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የደረሰው አስከፊ ጉዳት ደግሞ ጉዳዩ የበለጠ መነጋገሪያ አጀንዳ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜጎች ለምን ለከፋና ለመረረ ስደት ይደረጋሉ የሚለው ጉዳይ ሲነሳ በዋነኝነት የሚታየው የፖለቲካው እንዲሁም የኢኮኖሚው ጉዳይ ነው። ከኢኮኖሚ አኳያ ለዜጎች ስደት የሚጠቀሱ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በተለይ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ለችግሩ መባባስ አይነተኛ ምክንያት ይሆናሉ ተብለው በዋነኝነት የሚጠቀሱት አንኳር ጉዳዮ እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።
በገቢ መጠን መተዳደር አለመቻል የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ጤናማነት ከሚለካባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው ዜጎች በገቢያቸወ መጠን መተዳደር የሚያስችል መሆኑ ነው። ኢኮኖሚው ጤናማ ከሆነ ዜጎች ሰርተው እንደየአቅማቸው ህይወታቸውን መምራት ይችላሉ። ይሁንና አንዱ ኢኮኖሚ በተለይ በግሽበት ክፉኛ የተጠቃበት ሁኔታ ካለ ዜጎች የሚያገኙት ገቢ ቢያድግ እንኳን በዚያው መጠን ለኑሮ የሚያወጡት ወጪ (consumer coast of living) በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ስለሚሄድ ኑሯቸው ፈተና ውስጥ ይወድቃል። ግሽበቱ ለእለት ኑሮ የሚያወጡትን ወጪ ስለሚያንረው በቁጠባ ወደ ኢንቬስትመንት የመቀየር እድሉን በማቀጨጭ የዜጎችን ተስፋ ያጨልማል። ሁኔታው እየተባባሰ ሲሄድም ቁጠባ ይቅርና የእለት ኑሮን እንኳን መሸፈን እየከበደ ይሄዳል። በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሀገሪቱ ባለፉት ስምንትና ዘጠኝ ዓመት ሀገሪቱ በከፍተኛ የግሽበት አዙሪት ውስጥ (Inflationary cycle) አልፋለች። ባለፉት አመታት በተመዘገበው የዋጋ ግሽበት እስከ 60 በመቶ ድረስ የደረሰበት ሁኔታ ነበር። ይህን ያህል የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ደረጃ ጣሪያ ሲነካ ምን ያህል የዜጎችን ኑሮ በተለይም የደመወዝተኛውን ህይወት እንደጎዳው መገመት አያስቸግርም። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፖርት ባለሙያዎች ማህበር በ2000 እትሙ እ.ኤ.አ ከ1974 እስከ 1990 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ዝቅተኛ የዋጋ ግሽበት መጠን (Low rates of inflation) ከተመዘገበባቸው ሀገራት መካከል አንዷ እንደነበረች ይገልጻል። ከዚያ በኋላ በተለይ ከድርጅቱ ጋር በተያያዘ የእህል አቅርቦት መጠን አነስተኛ መሆን በደርግ ዘመን የምግብ ፍጆታ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መናሩን ሪፖርቱ ያመለክታል። ሆኖም የዝናቡ ሁኔታ መሻሻሉ በሂደት ዋጋ እንዲወርድ ቢያደርገውም ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ስልጣኑን ሲረከብ በነበረው የመንግስት ለውጥ ሂደት የዋጋ ግሽበቱ መናሩን ያመለክታል። ዋጋ ንረቱ የእርስ በእርስ ጦርነቱ እየበረታ ከሄደበት ወቅት ጀምሮ ኢህአዴግ ስልጣኑን ማረጋጋት እስከቻለበት ወቅት ድረስ በየዓመቱ የ20 ከመቶ ለውጥ በማሳየት የመጨመር አዝማሚያን ሲያሳይ ቆይቷል። በወቅቱ ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው የሀገሪቱ የኤክስፖርት መጠን መቀነስ፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረት መከሰቱና ይህንንም ተከትሎ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጫናን በማሳደሩ ነው። ይህ እንጭጭ የነበረውን ኢኮኖሚ ክፉኛ ከመጎዳት ባሻገር የዜጎችም የኑሮ አቅም ክፉኛ ተፈታትኗል። ኢህአዴግ ከዚያ በኋላ በወሰደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋሟት በተሰጠው ምክር መሰረት ብር ከዶላር አንጻር አንድ ዶላር በአምስት ብር ሂሳብ እንዲመነዘር ማድረጉ በራሱ የገቢ ሸቀጦችን ዋጋ በማናር ግሽበት ከፍ እያለ እንዲሄድ ማድረጉ አልቀረም። ይህ የብርን የምንዛሪ መጠን በአዋጅ ዝቅ የማድረጉ ሂደት ባለፉት አመታትም ሲሰራበት የቆየ ሲሆን ይህ እርምጃ በግሽበት ተመንዝሮ በዜጎች ህይወት ላይ ሲያደርሰው የነበረው ተጽዕኖ ቀላል አልነበረም። ይህ የግሽበት መጠን በተለይ ከፍላጎትና አቅርቦ አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ የበለጠ እየተባባሰ የሄደው ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ከዚህ ወቅት ጀምሮ የግሽበት መጠን ክፉኛ እያሻቀበ ሄዶ እስከ 67 በመቶ እስከመመዝገብ ደርሷል። ከአረብ አብዮት ጋር በተያያዘ ስጋት ያደረበት መንግስትም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን ቢያውቅም በተለያዩ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመን በማስቀመጥ ሁኔታውን በተወሰነ ደረጃ ለመቆጣጠር ሞክሯል፡፡ ሆኖም ዘላቂ መፍትሄን ማምጣት አልተቻለም። የዋጋ ንረቱ ክፈኛ እየናረ መሄድ ዜጎች ስራ ይዘውም ቢሆን እንኳን ስራቸውን በመጣል ወደ ሌላ ሀገር እንዲኮበልሉ አድርጓቸዋል። በርካቶች በየመሥሪያቤቶቻቸው የአመት ፈቃድና የህመም ጊዜ ፈቃድ በመውሰድ ስራቸውን ጥለው ለተሻለ ገቢ ወደ ተለያዩ ሀገራት በስደት ሄደዋል። ጉዳዩ የደመወዝ መብዛትና የማነሱ ጉዳይ ሳይሆን አንድ ዜጋ በሚያገኘው የገቢ መጠን መተዳደር አለመቻሉ ነው። በዚሁ ዙሪያ ከሰሞኑ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ሰዎች ይሄንኑ ሀሳብ ያንፀባርቃሉ። በርካታ ሴትና ወንድ ወጣቶች ከሜክሲኮ ወደ አፍሪካ ህብረት በሚወስደው የሱዳን ኤምባሲ በር ላይ ተኮልኩለዋል። አንዳንዶቹ ገና በመጀመሪያ ጊዜ ሱዳን ለመሄድ የተዘጋጁ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ደርሰው የተመለሱና ድጋሚ ለመሄድ ሌላ የጉዞ እንቅስቃሴ የጀመሩ ናቸው። ካነጋገርናቸው መካከል አንዱ የሆነው አብዱራህማን ከድር ቀደም ሲል በሰበታ አካባቢ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥሮ የሰራ ነበር። በጊዜው እስከ 2200 ብር ይከፈለው የነበረ ቢሆንም በሚከፈለው የገንዘብ መጠን ግን ቤቱን መምራት ስላልቻለ ስራውን ጥሎ ወደሱዳን ለመሄድ ተገዷል፡፤ በዚያም በአንድ ጣውላ ፋብሪካ ውስጥ የሚያገኘው ወርሃዊ ገቢ የእለት ኑሮውን ከመሸፈን አልፎ እንዲቆጠብ አስችሎታል። ሆኖም ጋላባት በተባለ ቦታ ፓስፖርቱ ስለጠፋበት አንዳንድ የጉዞ ዶክመንቶችን ለማስተካከል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል። አብዱራህማን በኢትዮጵያ ባደረገው ቆይታ የኑሮ ውድነቱ ቀደም ሲል የቆጠበውን ገንዘብ ክፉኛ ሰላመናመነበት ብዙም መቆየቱን አልመረጠም። ብዙዎች በሱዳን ኢምባሲ አካባቢ ተኮልኩለው ያገኘናቸው ወጣቶች የሀገሪቱ የኑሮ ውድነት ሥራ ቢቀጠሩም እንኳን በሚያገኙት ወርሃዊ ገቢ የተሻለ ህይወትን መምራት እንዳልቻሉ ይገልፃሉ። ይህ ጠቅለል ብሎ ሲታይ ዜጎች ምንም ይሁን ምን የሚያገኙት የገቢ መጠን ኑራቸውን መምራተ ካላስቻላቸው ሀገራቸውን ጥለው ለመሄድ ሌላን ሀገር ማማተራቸው አይቀርም። ይህ በተጨባጭ እየታየ ያለ እውነታ ነው። ይህንን ችግር የበለጠ እያባባሰ ያለው የሀገሪቱ የግሽበት መጠን ነው። ግሽበቱ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ደረጃ እንደወረደ እየተገለጠ ቢሆንም ግሽበት ቀነሰ ማለት ግን ዋጋ ወረደ ባለመሆኑ ዛሬም ቢሆን የኑሮው ውድነት እንዳለ ነው። በፍጥነት ያደገው የህዝብ ቁጥር የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ በሚያመነጨው የሀብት መጠን ብቻ ሳይሆን በሚያስተናግደው የህዝብ ቁጥር መጠንም ይወሰናል። ሀገራት ምንም ያህል የኢኮኖሚያቸው አቅም ቢያድግ የህዝባቸውን ቁጥር ካላቸው የኢኮኖሚ አቅም ጋር እያመጣጠኑ መሄድ ካልቻሉ እድገቱ የዜሮ ድምር ውጤት ሆኖ ይቀራል፡፡ የአንድ ሀገር የህዝብ ቁጥር ከኢኮኖሚው ጋር ብቻ ሳይሆን ካለው የቆዳ ስፋትም ጋር ጭምር የተመጣጠነ መሆን እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ከኢኮኖሚውም ሆነ ከሀገር የቆዳ ስፋት ጋር መመጣጠን ያልቻለ የህዝብ ቁጥር በልማት ፣ በሥራ እድል፣ በምግብ እህል አቅርቦት፣ በትምህርት፣ በጤና እና በመሳሰሉት መሰረታዊ ፍላጎቶች ያለው ተደራሽነት እጅግ ውስን ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ አሳሳቢ ነው ማለት ይቻላል። በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በፍጥነት እያደገ የመጣውን የህዝብ ቁጥር ለመመጠን ባለፉት 22 ዓመታት የሰልጣን ቆይታ ጊዜው የሄደበት መንገድ ያን ያህል ውጤታማ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የስነህዝብ ጉዳዮች ዳየሬክቶሬት ዳይሬክተር የኢትዮጵያ የስነህዝብ ሁኔታ በተመለከተ የሚለቃቸው መረጃዎች ኢህአዴግ በስልጣን በቆየባቸው ዓመታት በዚህ ዙሪያ የሰራው ውጤታማነቱን የሚያሳይ አይደለም። ይህም የህዝብ ቁጥር ባለፉት 22 ዓመታት በምን ያህል መጠን እንዳደገ ብቻ ማየቱ በራሱ በቂ ማስረጃ ይሆናል።
በሀገሪቱ በየአስር ዓመቱ አንድ ጊዜ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ተካሄዶ ለህዝብ ይፋ ይሆናል። የህዝብ ቁጥር ፍጥነቱን (population growth rate) መሰረት በማድረግ ደግሞ የትበያ ሥራ ይከናወናል። ይህንን ሥራ እንዲያከናውን ኃላፊነት የተሰጠው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ነው። በተለያዩ ጊዜያት በተደረገው የህዝብ ቆጠራ በ1977 ዓ.ም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 42 ሚሊዮን ነበር። ይህ የህዝብ ቁጥር በወቅቱ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ስለነበረች የኤርትራን ህዝብ ጭምር የሚያካትት ነው። ይህ ቁጥር ከ10 ዓመታት በኋላ ማለትም በ1987 ዓ.ም ወደ 53.5 ሚሊዮን አድጓል። ኢህአዴግ ደርግን በመጣል ሀገሪቱን የተቆጣጠረው በ1983 በመሆኑ ደርግ ስልጣን ላይ በነበረበት የመጨረሻዎቹ ዓመታት የህዝቡ አጠቃላይ ቁጥር ከ50 ሚሊዮን በታች እንደነበር መገመት አያስቸግርም። ከዚያም ከ10 ዓመታት በኋላ ማለትም በ2000 ይፋ በተደረገው የህዝብ ቁጥር ስታትስቲክስ 53.5 ሚሊዮን የነበረው የህዝብ ቁጥር ወደ 73.8 አሻቅቦ ተገኘ። የህዝብ ቆጠራው ይፋ ከሆነ ወደ ሰባት ዓመታት አካባቢ ተቆጥሯል። በቀጣይ ቆጠራው የሚካሄደውና ይፋ የሚሆነው ምንአልባትም ከሶስት ዓመታት በኋላ ነው። ሆኖም የህዝብ ቁጥር እድገቱን መሰረት በማድረግ እየተሰጡ ያሉ ትንበያዎች በአሁኑ ሰዓት ያለውን አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ከ85 እስከ 90 ሚሊዮን ያደርሱታል። ይህ ሲታይ ሀገሪቱ በታሪኳ እንደ ሀገር ከቆመችበት ወቅት ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመን ድረስ ከ50 ሚሊዮን በታች የነበረው የህዝቧ ቁጥር በኢህአዴግ የ22 ዓመታት ቆይታ በእጥፍ ማደጉን የሚያሳይ ነው። በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ40 ሚሊዮን ውስጥ ወደ 90 ሚሊዮን ተተኩሷል። ይህ እንግዲህ ቀደም ሲል ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ወቅት ቆጠራው የኤርትራን ህዝብ ጭምር ያካትት እንደነበር ሳይዘነጋ ነው። ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ግን ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ስላልሆነች ይህ ቁጥር በዚህ ደረጃ የተመዘገበው ኤርትራን በመቀነስ ነው። ይህ ሲታይ የኢህአዴግ መንግስት የሥነህዝብ ፖሊሲን ያወጣ ቢሆንም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በዚህ ዙሪያ መስራት የሚገባውን መሥራት አለመቻሉን ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ከናይጄሪያና ከግብፅ ቀጥሎ በህዝብ ቁጥር ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ግብፅን በማለፍ በአፍሪካ በህዝብ ቁጥር ብዛት ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ይህ ፍጥነት ከቀጠለ በቀጣዮቹ አንድና ሁለት አስርት ዓመታት ይህ ቁጥር የት ሊደርስ እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። አሁን ባለፈው የህዝብ ቁጥር ፍጥነት የህዝቡ ቁጥር በየዓመቱ 2.9 በመቶ እየጨመረ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የህዝብ ቁጥር የኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ዳቦ ተካፋይ ነው። ሥራ ይፈልጋል፣ መኖሪያ ቤት ያስፈልገዋል፣ ምግብ የህክምና አገልግሎትንና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ፍላጎቶች ይጠይቃል። መንግስት ከህዝቡ ቁጥር እድገት መጠን በላይ ኢኮኖሚውን ማሳደግ ካልቻለ እድገቱ ከስታትስቲክስ ፍጆታ የሚያልፍ አይሆንም። ዜጎች በአሁኑ ሰዓት በገፍ ወደተለያዩ ሀገራት በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ እንዲሰደዱ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ውስጥም አንዱ ይህ የህዝብ ቁጥር እድገት ያመጣው ጣጣ ነው። ያለው የሥራ እድልና የስራ ፈላጊው መጠን ፈፅሞ አይገናኝም። ለአንድ የሥራ እድል ከመቶ እስከ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ይወዳደራሉ። የኢኮኖሚው እድገት የህዝቡን ቁጥር እድገት አልመጠነም። አንድ የኢኮኖሚ እድገት ከሚፈተንባቸው ፈተናዎች መካከል አንዱ ለዜጎች ምን ያህል የሥራ እድልን መፍጠር ችሏል የሚለው ነው። መንግስት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ “ቅጥር አትጠብቁ” በማለት ኃላፊነቱን ከራሱ እያሸሸ ነው። ዜጎች በአንፃሩ የተሻለ ገቢና ሥራ ፍለጋ በየትኛውም መንገድ ሀገር ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል። የኢኮኖሚ እድገቱ ካለው የህዝብ ቁጥር አኳያ ሲታይ ስለማይመጣጠን ከማቃመስ ያለፈ በግለሰቦች ኪስ ቢመነዘር የሚችል ለውጥን አላመጣም። ለዚያም ይመስላል የመንግስት የኢኮኖሚ እድገት መረጃዎች በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ የሚታየው። በቂ የሥራ መፈጠር ያልቻለው የኢንዱስትሪው ዘርፍ እስከዛሬ ባለው ኋላቀር የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ዜጎች ከስራ እድል ብዙም የሚጨነቁበት ሁኔታ አልነበረመም። ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ በገጠር የሚኖርና ህይወቱም ከግብርና ጋር የተያያዘ በመሆኑ በመንግስት ላይ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጥያቄን የሚያነሳበት ወይም ቀየውን ጥሎ የሚሰደደው ድርቅ ሲከሰት ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሯል። የገጠሩ ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ለእርሻ በሚውሉ መሬቶች ላይም ጫናን እየፈጠረ ነው። ገበሬው ልጅ ሲወልድ ለልጁ የሚያከፋፍለው ቀደም ሲል የነበረውን የመሬት ይዞታ ነው። ይህም በጊዜ ሂደት መሬት በምርታማነት ደረጃ ለማንም የማይጠቅም ብጥስጣሽ መሬት እያደረገው ነው። አብዛኛው ወጣት የገበሬ ልጅም ከግብርናው የአስተራረስ ዘዴ ኋላቀርነትና ከግብርናው ውጤት አልባነት ጋር በተያያዘ መኖሪያ ቀየውን እየጣለ ወደ ከተማ ለመግባት ተገዷል። የከተማ ነዋሪነት በግብርና ውጪ ያለ የሥራ እድል ማግኘትን ይጠይቃል። ይህም ኢንዱስትሪውንና አገልግሎቱን የሚመለከት ይሆናል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ ያለው የኢንዱስትሪውም ሆነ የአገልግሎቱ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ከገጠር ወደ ከተማ እየፈለሰ ያለውን የሰው ኃይል መሸከም አይችልም። ይህ አለመሆኑ ደግሞ አብዛኛው የገጠር ወጣት ከገጠር ወደ ከተማ ከዚያም ወደ ሌሎች ሀገራት ለመፍለስ ተገዷል። ጉዟቸውን ወደ ሱዳን ለማድረግ የተዘጋጁ ወጣቶች ባነጋገርንበት ወቅት ብዙዎች በሱዳን በነበሩበት ወቅት ተቀጥረው ይሰሩ የነበረው በተለያዩ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ነው። ኢህአዴግ ረዥም ዓመታት በግብርናው ላይ ብቻ ጊዜውን በማጥፋት መቆየቱ የሥራ እድል መፍጠር የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን በግሉም ሆነ በራሱ በመንግስት እንደይፈጥር አድርጎታል።

No comments:

Post a Comment