ከጥበቡ ተቀኘ
የሃገራችንን የሙዚቃ ስራ ድሮ በሽክላ ኋላ ላይ በካሴት አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሲዲ ታትሞ ገበያ ላይ
ሲቀርብ እንገዛና ከማዳመጥና ከማጣጣም አልፈን እንደ ቅርስ በየቤታችን የምንወዳቸውን ዘፋኞች ስራ እናስቀምጥ
ነበር:: ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የለመድናቸው የሙዚቃ ቤት ስሞችም ነበሩን ታንጎ ፣ አምባሰል ፣ ሶልኩኩ
፣ ኤሌክትራ ፣ ዜድ… አድራሻችን ከመርካቶ ዝቅ ብሎ፣ ከአውቶቡስ ተራ አጠገብ ፣ አንዋር መስጊድ ፊት ለፊት…
ግጥም ይልማ ገብረአብ ፣ ዜማ አበበ መለሰ ፣ ከመድረክ የቀረጸው ከድር ጭቅሳ… የሚሉ ጽሁፎች በየካሴትና ሲዲው ላይ
ይታይ እንደነበር ካስታወስኩኝ በኋላ ወደ ዛሬ ዋናው ጉዳዬ እገባለሁ::
ኣሁን በተለይ ያለፉትን ሶስትና አራት አመታት ትላልቅ የማስታወቅያ ባነሮች ላይ የዘፋኙ ፎቶ አጠገብ በጣም
በትልቁ ሜታ ቢራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ፣ በደሌ ቢራ፣ ባቲ ቢራ፣ ሐረር ቢራ… የሚል ማስታወቅያ ማየት የተለመደ
ነገር ሆኗል::በጣም የሚገርመው ደግሞ ዘፈኖቹን ልንሰማ ሲዲውን ስንገዛው ከሲዲው ጀርባ ይሄንኑ የቢራ ማስታወቅያ
ቤታችን ይዘነው እንመጣለን:: እኔ ይሄንን ካየሁ በኋላ ለልጆቼማ ኑ በቢራ ተደሰቱ የሚል ማስታወቅያ ያለበት ሲዲ
ይዤ ላለመግባት ወስኜ መግዛቱንም ትቼዋለሁ:: ሙዚቃው በሙዚቃ ቤት ብቻ ሳይሆን በቢራ ፋብሪካዎች ስፖንሰርነት
እየወጣ እንደሆነም በሰፊው ማየት ይቻላል:: ለመሆኑ ሙዚቃው ካለ ቢራ ማስታወቅያ መሰራት አይችልም? ዘፋኞቹስ
ለልጆች እና ለሚያድጉ ወጣት ጎረምሶች የወደፊት እጣ እንዳይናጋ ወይ እንዳይበላሽ በመቆርቆር ይሄ የሚያስነውር
አካሄድ አይሆነንም ፣ አይበጀንም አይሉም እንዴ? ነፍሱን ይማርና ተፈራ ካሳ ለህዝብ ትምህርቱን በዘፈን እንዲ
ነግሮን አልፏል:
በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ
በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ
መጠን አትለፉ ትቃጠላላችሁ
ለነገሩ ቴዲ አፍሮ ወዶ ከፈረመና ከሰራ በኋላ እኔ አልፈልግም ፣ ይሄንን ጉዳይ እቃወማለሁ ፣ እንደውም
እከሳለሁ ብሎ ቡራ ከረዩ አብዝቶ እንደነበር ይታወቃል ግን የፈጠረው ምንም ነገር እንደሌለ መገንዘብ ችያለሁ::
ይልቁንስ አሁን ከቅርብ ቀን በፊት ልጆች የኔን ፎቶ ከቢራ ጋር እንዲያዩት አልፈልግም ፣ ለወጣቶች ጥሩ አርአያ
መሆን እፈልጋለሁ ሲል የነበረው እራሱ ቴዲ ለቢራ ፋብሪካ ፈረመ የሚል ዜና አንብቤ ወይ ስብ እና እያልኩ ነበር::
ዘሪቱ ከበደ በዚህ ከቢራ ፋብሪካ ስፖንሰርነት ጋር በተያያዘ ጉዳይ በጣም ጠንካራና የምትመሰገን ሴት ዘፋኝ
እንደሆነች አስመስክራለች::
ግን ይሄ ሁሉ የሞራል ድቀትና አደገኛ ግድየሌሽነት በሃገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለይ በዘፋኞቻችን
ላይ እንዴት ሊመጣ ቻለ? ኪነጥበባውያንስ ነፍሳቸው ምን ያህል ብትደነድን ነው ይሄንን ኑ በቢራ ተደሰቱ የሚል
መአት ሲዲያቸው ላይ ለጥፈው ግዙን የሚሉት? መጠጥን ማስተዋወቅ ከስነ ጥበብና ትውልድን ከማስተማር ጋር ምን
አያያዘው? ከሰፊው ህዝብ በፊት እንዲህ አይነት አካሄድ ለአገር ጥሩ እንዳልሆነ የሙዚቃ ሰዎቻችን እንዴት ማወቅ
ተሳናቸው?
አቤት ጥያቄዎቼ ብዛታቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ ነገር መጻፍ አስቤያለሁ ያልኩት ወዳጄ ‘አንተ እኮ በጣም
የምትገርም እውነቱን አልቀበልም ብለህ ዝም ብለህ የምትንገላወድ ምስኪን ፍጡር ነህ:: እዚ አገር ዘፋኙ እንዴት
ሞራሉና ስብእናው ወርደ ትለኛለህ? የዚ አገር ዘፋኝ አይደለም እንዴ እየዘመረ አምባገነኑን መለስ ዜናዊን ነቢይ ነው
ሲለን የነበረው? የዚ አገር ዘፋኝ አይደል እንዴ የማያቀውን ታሪክ አዋቂ ነኝ እያለ የሚዘላብደው? የዚ አገር
ዘፋኝ አይደል እንዴ በመሃይምነቱ ዘሎ ፓርቲዎች አስታርቃለሁ የሚለን? የዚ አገር ዘፋኝ ሲጀመር ምን አይነት ሞራል
እና ስብእና አለው እና ነው አሁን ሞራሉ ወደቀ ምናምን እያልክ የምትቀባጥረው? የበውቀቱ ስዩም እና የሌሎች ታላላቅ
ደራስያን መጽሃፍ ምረቃ ላይ የማይገኙ ዘፋኞችና የኪነጥበብ ሰዎች አይደሉም እንዴ በሚኒስትሩ በረከት ስምኦን
መጽሃፍ ምረቃ ምሽት እንግዳ ከበር ከመቀበል አንስቶ እስከ ዝግጅቱን መምራትና ማድመቅ ሲያሽቃብጡ የነበሩት? የዚ
አገር ዘፋኝ እና የኪነጥበብ ሰዎች ያለ ምንም እውቀት የሚሰብኩን ሁሉ ስለ አባይ፣ ስለ ህዳሴ፣ ስለ ትራንስፎርሜሽን
እና ስላለው የሃገሪቷ እድገት አይደለም እንዴ? የህዝብ መበደል፣ የኑሮ መወደድ፣ የህዝብ በህግ ጉዳይ ያላግባብ
መንገላታት መቼ ተሰምቷቸው ያቃል እና ነው ዛሬ ሞራላቸው ወደቀ የምትለኝ? ‘ ብሎ በቁታ እየገነፈለ ተወኝ አለኝ::
ወድያው ደግሞ “ግን ደሞ” ብሎ ጀመረ “ግን ደሞ አንዳንድ በጣት የሚቆጠሩ ነፍሳቸውን ጊዜያቸውንና ሁለመናቸውን
ለኪነ ጥበብ የሰዉ እንዳሉም የማላቅ አልምሰልህ እኔ እነዛን ጥቂቶችን እጅግ በጣም አከብራቸዋለሁ” ብሎኝ ሌላ ጨዋታ
አውግተን ተለያየን:: እኔም ብዙ ማሰብ ጀምሬ አውጥቼና አውርጄ…..
እውነትም ከዘፋኞች ሞራል ዝቅጠት ጀርባ የሚታይ ወይ አላዋቂነት ፣ ወይ ጥቅም እስካገኘሁ ምናገባኝ ማለት ፣ ወይ ደግሞ ትልቅ ድንቁርና አለ በሚለው ተስማማሁ:: እንደዚህ ያልኩበት ምክንያት ምንድነው? ነጥቦቼንም በዚህ መልኩ አስቀመጥኩ
እውነትም ከዘፋኞች ሞራል ዝቅጠት ጀርባ የሚታይ ወይ አላዋቂነት ፣ ወይ ጥቅም እስካገኘሁ ምናገባኝ ማለት ፣ ወይ ደግሞ ትልቅ ድንቁርና አለ በሚለው ተስማማሁ:: እንደዚህ ያልኩበት ምክንያት ምንድነው? ነጥቦቼንም በዚህ መልኩ አስቀመጥኩ
- ኮፒ ራይቱ አላሰራ አለን፣ ተቸግረናል፣ በጣም ተቸገርን፣ እየተዘረፍን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መፍትሄ ይፈልግልን በማለት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ጋር ስብሰባ ሲያደርጉ አምሽተው ተቸግረናል እየተዘረፍን ነው ባሉበት አፋቸው ዝግጅቱ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በስጦታ መልክ የወርቅ ብእር እንደሰጡዋቸው ሳስታውስ፣
- ባደባባይ ሰው እንዲገደል ያደረገ መሪ ሲሞት ከተከበረው ብሄራዊ ቲያትር እስከ ቤተመንግስት ምነው ተለየኸን መስከረም ሳይጠባ የሚለውን ዘፈን እየዘፈኑ ነጠላ አደግድገው (ለቅርብ ዘመዶቻቸው የማያደርጉትን) እያለቀሱ መሄዳቸውን ሳስብ፣
- ከእንግዲህ ሻማ ለልደት ነው እያሉ የማያቁትን የኢንጅነሪንግ ሙያ እየተጨማለቁበት ሳይ ከአንድ ግድብ ምረቃ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ችግር እንደማይኖር ማብራሪያና ዲስኩር የሰጡትን ሳስበው፣
- ታላቅ የኦርቶዶክስ አማኝ ነኝ በማለት የማያቁትን የቤተ ክርስቲያንን ህግና ቀኖና ባልተከተለ መልኩ በድፍረት መዝሙር ዘምረው ማሪያም ማርያም የሚል ነጠላ ዜማ በለቀቁ ማግስት ዳንኪራና አስረሽ ምቺው ማድረጋቸውን ሳስበው፣
- እንኳን ሌላ ሰው ያላግባብ ታሰረ ሊሉ እራሳቸው ያላግባብ ታስረው ያለ ወንጀሌ ነው የታሰርኩት በጣም ተበድያለሁ ለማለት ድፍረትና ብቃት የሌላቸው እንደሆኑ ሳስበው፣
- ዘፈን እምቢ ሲላቸውና ከገበያ ሲወጡ በመሃይምነት እንዲሁም በከባድ ድፍረት ጌታ ጠርቶኝ ነው ብለው ለሃይማኖትም ለህዝብም ክብር ሳይሰጡ የስብከትንና የዝማሬን ተአምራዊ ጥበብ ምንም ሳይማሩ የፕሮተስታንት ዘማሪ ሲሆኑ ሳይ፣
- እከሌ ሮጦ ሲያሸንፍ ሲዘፍኑ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሲዘፍኑ ለአባይ ግድብ ሲዘፍኑ ሳውዲ ለሞቱት ሲዘፍኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሞቱ ሲዘፍኑ ጥበብን ከውስጣዊ ስሜታቸው ሳይሆን ከጊዜውና ከሰሞኑ ወሬ ጋር ሊወስዷት ሲፈልጉ ዜና የሚመስል ዘፈን አቅርበው ስሰማ፣
- በመሃይምነትና በድንቁርና ታውረው ያልሰሩበትንና ያልለፉበትን የሌላ ሰው ዘፈንና ዜማ ከአገር ውስጥም ከውጭም ወስደው በማስረጃ ሲቀርብባቸው ይቅርታ በስህተት ባለማወቅ ነው እንደማለት ይህንን ፕሮግራም ይሰራ የነበረውን ለምን ይዋሻል ራዲዮ እስከማዘጋት መድረሳቸውን ስሰማና ሳይ፣
እነዚህንና ሌሎች ብዙ ያልዘረዘርኳቸውን ነጥቦች ካየን የኢትዮጵያ ኪነጥበብ በተለይ ሙዚቃ ከባለሙያ የእውቀት
ማነስ ችግር የተነሳ ወርዶ በዚህ ባለንበት ዘመን እንኳን ራሱን መደገፍ እንዳቃተው ግልጽ ይሆንልናል:: ግን
ዘፋኞቻችንና የኪነጥበብ ሰዎች ይህንን ችግር በጣም በሰለጠነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ እራሳቸውን አዋርደው ያለቢራ
ፋብሪካዎች ማስታወቅያ ካሴታቸውን ማሳተም ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን በግልጽ የተናገሩ አይመስለኝም:: እንደውም
ጥሩ ነገር በመስራት ያለብን ችግር ሊቀረፍ ይችላል ብለው ከማሰብ ከባለስልጣን ጋር፣ ከካድሬ ጋር፣ ከባለሃብት ጋር
በመሞዳሞድ ሊያልፉ ያሰቡ ይመስለኛል:: ይህ ደግሞ በጣም አስነዋሪና ከኪነጥበብ ሰው ሳይሆን ከአየር በአየር ነጋዴ
የሚመነጭ ተራ ውርደትና ስግብግብነት ነው::
ጊዜውን በውል ባላስታውሰውም በዚህ ሶስት አራት አመት ውስጥ የኢህአዴግ ባለስልጣኖች ያሳተሙትን የህዳሴ ዋዜማ የተሰኝውን DVD አባዝቶ በህገ ወጥ መንገድ ሲሽጥ የተያዘ ሰው 15 አመት እንደተፈረደበት ሰምተን ማንም እየተነሳ የድምጻዊያኖቻችንን ካሴት እና ሲዲ ለዘመናት በህገ ወጥ መንገድ ሲሸጥ ምንም አለመደረጉ ከዘፋኞቻችን በላይ እኔን ለምን እንዳስቆጨኝ አላውቅም::
ጊዜውን በውል ባላስታውሰውም በዚህ ሶስት አራት አመት ውስጥ የኢህአዴግ ባለስልጣኖች ያሳተሙትን የህዳሴ ዋዜማ የተሰኝውን DVD አባዝቶ በህገ ወጥ መንገድ ሲሽጥ የተያዘ ሰው 15 አመት እንደተፈረደበት ሰምተን ማንም እየተነሳ የድምጻዊያኖቻችንን ካሴት እና ሲዲ ለዘመናት በህገ ወጥ መንገድ ሲሸጥ ምንም አለመደረጉ ከዘፋኞቻችን በላይ እኔን ለምን እንዳስቆጨኝ አላውቅም::
የራሳቸውን መብት ሳያስጠብቁና ኮፒ ራይታቸውን ታግለው ሳያስከብሩ ዘፋኞቻችን ለኛና ለመጪው ትውልድ ያስባሉ
ማለት ዘበት ነው ግን ቢሆንም ካለባቸው ችግር ለመውጣት የጀመሩት መንገድ ትክክል እንዳልሆነና ነገ ሁላችንም
በልጆቻችን ፊት ሊያሳቅቀን የሚችል የሞራል ዝቅጠት መሆኑን ሳልጠቁም አላልፍም:: አርአያ የሚለው ቃል ለነገ
ከማሰብና ለመጪው ትውልድ ከመጠንቀቅ ጋር አብሮ የሚሄድ ትርጉም ያለው ትልቅ ቃል ነው:: ይሄ ቃል ተረስቶ ወይ
ደግሞ የሰው ስም ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ካለኝ ስጋት ይቺን ጽፌያለሁ ደህና ሁኑ::
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of
various information and content providers. The Website neither
represents nor endorses the accuracy of information or endorses the
contents provided by external sources. All blog posts and comments are
the opinion of the authors.
No comments:
Post a Comment