Monday, December 16, 2013

ሀገራዊ ትንሳኤ ያስፈልገናል



አስራት አብርሃም (በዕንቁ መፅሔት ወጥቶ የነበረ)
የራሳችን መንግስት ያሳድደናል፤ እዚያ በሌሎች ሀገራት መንግስታት ህገ ወጥ ስደተኞች ተብለን እንሳደዳለን፤ እዚህ የእኛ የራሳችን ፖሊሶች ይደበድቡናል፤ ያስሩራል፤ እዚያ የሌሎች ሀገሮች ፖሊሶች ይመቱናል፤ ያስሩናል፤ ይገድሉናልም። ይህ ሁሉ ለምን ሊሆን ቻለ?

ኢትዮጵያዊ ግን ለምን እንደዚህ ተቅበዝባዥ እና ማንም የሚያሳሰድደው ህዝብ ሊሆን ቻለ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። እዚህ የራሳችን መንግስት ያሳድደናል፤ እዚያ በሌሎች ሀገራት መንግስታት ህገ ወጥ ስደተኞች ተብለን እንሳደዳለን፤ እዚህ የእኛ የራሳችን ፖሊሶች ይደበድቡናል፤ ያስሩራል፤ እዚያ የሌሎች ሀገሮች ፖሊሶች ይመቱናል፤ ያስሩናል፤ ይገድሉናልም። ይህ ሁሉ ለምን ሊሆን ቻለ? ሲባል፤ አንድም ለዜጎቹ የሚቆረቆር፣ ለሀገሩ ክብር የሚጨነቅ መንግስት ስለሌለን ነው። አንድም ደግሞ ድሆች ስለሆን ነው፤ እንዲህ እየተናቅንና እየተዋረድን ያለነው። ኢትዮጵያውያን ቆነጃጅት የዓረብ እድፍ እንዲያጥቡ፣ እጅግ ዝቅተኛ የሆነውን ስራ ሁሉ ተዋርደው እና ከሰብአዊ ፍጡር ውጭ ሆነው እንዲሰሩ እየተደረጉ ያሉት ድህነታችን ፍፅም ቅጥ ያጣ በመሆኑ ነው።

በሌላ በእኩል ሶስት ሺህ ዓመታት የሚዘልቅ፣ የመንግስትነት ስርዓት አለን የምንለው ህዝብ ነን። ገናና የሆነ የነፃነት ታሪክ የነበረን ህዝብ ነን፤ እንዴት ዛሬ ከሁሉም ጭራ ሆነን እንዲህ በውርደት አረንቋ ውስጥ ልንገኝ ቻልን?! ከሁሉም በፊት ጠንከራ ስርዓተ መንግስት የነበረን እንዴት ዛሬ እኛ በህግ የምንቆጣጠረው፣ ሰብአዊና የዜግነታዊ ክብራችንን የሚጠብቅልን መንግስት ሳይኖረን ቀረ?! ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው። አባቶቻችን ያ ሁሉ ዘመን ምን ሲሰሩ ነው ጊዜያቸውን ያሳለፉት?! እንዳለው አንዱ ፀሐፊ ምን ስንሰራ ነው ያ ሁሉ ዘመን የፈጀነው?! ብሎ መጠየቅና መልሱ በጥልቀት መመርመርም ተገቢ ነው።

የዛሬው ኢትዮጵያዊ የካሌብ፣ የሮምሃይ ልጅ አይደለም እንዴ! የዛሬው ኢትዮጵያዊ እነ ቴዎድሮስ፣ እነ ዮሐንስ፣ እነ ሚኒልክ፣ እነ ኃይለስላሴ የመሳሳሉ ጀግኖችና ገናና መሪዎች ከነበረው ህዝብ ፅኑ ህዝብ አብራክ የተገኘ አይደለም እንዴ! ዛሬ እንደምን በዚህ ውርድት ውስጥ ሊገኝ ቻለ! እንሰሳት እንኳ የራሳችውን ምግብ ይሰብስባሉ፤ የራሳቸው መኖርያ አላቸው። ኢትትዮጵያዊ ምን ሆኖ ነው እንዲህ በየሀገሩ ተቅበዝባዥ እና ተሳዳጅ ሆኖ የተገኘው! ለረጅም ዘመን የነበረው የነፃነት ታሪኩ፣ ያ ኩራቱ፣ ያ ኃያልና የማይደፈር ያደርገው የነበረው ብልሀቱ ዛሬ ምን ወሰደው?!
ኢትዮጵያውያን ከዚህ ዓይነቱ ውርደት የሚያወጣን ሀገራዊ ትንሳኤ ያስፈልገናል። ኢትዮጵያዊ ክብር ከሞት የሚነሳበት፤ መንግስታዊ ስልጣንና ሀላፊነት በህግና በስርዓት የሚሆንበትና በህዝብ መልካም ፍቃድ የሚተሳርበት፤ በሀገሪቱ ሁሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሰላም የሚሰፍንበት እና አዱኛ ሞልቶ የሚፈስበት ዘመን ይመጣ ዘንድ በእርግጥም ትንሳኤ ያስፈልገናል። እንደ ህዝብ እንደ ሀገር ሁላችንም በነጻነትና በሞራል ከፍታ ቀና የምንልበት ሀገራዊ ትንሳኤ ያስፈልገናል። በእርግጥ በኢትዮጵያችን ያሉት ችግሮች እጅግ በጣም ፈርጀ ብዙ ናቸው። ከእነዚህ ችግሮች የመውጫ በር ለማበጀት በቅድሚያ የሚከተሉትን የመፍትሄ አቅጣጫዎች በተግባር ላይ ማዋልና ለተግባራዊነታቸውም መንቀሳቀስ ይኖርብናል፤
1. ፖለቲካዊ ለውጥ ማምጣት:-
አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት የመሰረተው ስርዓት ለዜጎቹ ድህንነትና ለሀገር ክብር ብዙም ደንታ የሌለው ነው። ይሄ ስርዓት በተባበረ ሰላማዊ ትግል መቀየርና በህዝብ ወደ ሚመረጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማሸጋገር የሚያስፈግ ነው። የስርዓት ለውጥ ሳይመጣ አሁን በሀገሪቱ ላይ ሰፍኖ ያለውን ፈርጀ ብዙ ችግር መፍታት የሚቻል ነገር አይደለም። የፖለቲካ መስተጋብሩ ሲቀየር ነው የኢኮኖሚ መስተጋብሩም ነው አብሮ የሚቀየረው። ስለዚህ የመንግስት ለውጥ እንዲመጣ በሚቻለው መንገድ ሁሉ መታገል ለነገ ይደር የማይባልና ሁሉም ዜጋ በተለይ ደግሞ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆኖ መሄጃ አጥቶ እየተቸገረ ያለው ወጣቱ ትውልድ በአንድነት ሆኖ ወደ ትግሉ መቀላቀልና የነቃ ተሳትፎ ማደረግ የግድ የሚለው ነው። የዚች ሀገር ችግር ዋነኛ ምንጭ ስርዓቱ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሄ ስርዓት ለሩብ ክፍለ ዘመን በሚጠጋ ዕድሜ ሁሉ አይተነው ያመጣልን ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ከአሁን በኋላም ቢሆን ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሀገር እየተመራ፣ የፖለቲካ ነፃነት መስፈን፣ የሰብአዊ መብት መከበር፤ ነፃ ሚዲያ፣ ነፃ ፍርድ ቤት በአጠቃላይ ገለልተኛ የሆኑ የመንግስትና የግል ተቋማት የሚታሰቡ አይደሉም። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ እንዲኖረን ከተፈለገ ይሄ ስርዓት መቀየር አለበት።
2. የህዝብ ቁጥር ምጣኔ መቆጣጠር :-
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሌላኛው ችግር የህዝቡ ቁጥር ዕድገት ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር ሊመጣጠን ያለመቻሉ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ የምትቀመጥ፤ ከዘጠና ሚልዮን በላይ ዜጎች ያሉባት ሀገር ነች። የኢኮኖሚ ሁኔታዋና እድገቷ ሲታይ ግን እጅግ በጣም ወደ ኋላ ከቀሩ ሀገሮች ተርታ የምትመደብ፤ በየዓመቱ ዜጎቿ በረሃብ ጠኔ የሚሰቃዩባት፤ ከምዕራባውያን የእህል እርዳታ መላቀቅ ያልቻለች ሀገር ነች። ለዚህ ችግር መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም የህዝቡ የውልደት እድገት ከኢኮኖሚው እድገት ጋር ሊመጣጠን ያለመቻሉ ዋነኛው ነው። ለዚህም እንደ መፍትሄ መወሰድ ያለበት ጠንካራ የሆነ የቤተሰብ ምጣኔ ህግ አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ለምሳሌ ቻይና እንዳደረገችው በሚወለዱ ህፃናት ብዛት ላይ የህግ ገደብ ማስቀመጥ ይቻላል። አንድ ቤተሰብ ከሁለት ወይም ከሶስት ልጆች በላይ እንዳይወልድ ህግ ማውጣት እና በሁሉም የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ማድርግ ያስፈልጋል። በእርግጥ እንዲህ ያለውን እያንዳንዱን ቤት የሚነካ ከባድ ጉዳይ ተግባራዊ ማድረግ ሊያስቸግር ይችላል። ስለሆነም ህግ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት ከህዝብ ጋር መወያየትና መግባባት፤ አዎንታዊና አሉታዊ ጎኑ ነፃ በሆኑ ምሁራና በእውቀት ተቋማት መጠናት ይኖርበታል።
ማህበረሰባችን ለልጅ ያለው አመለካከት ሲበዛ በጣም የተዛባ ነው። ልጅ የሀብትና የዕድል ምንጭ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። በትግርኛ አንድ አባባል አለ “አንድ ልጅ ያለው እንደሌለው፤ ሁለት ልጆች ያሉት ደግሞ አንድ ልጅ እንዳለው ይቆጠራል።” የሚል ነው። ልጅ የሚበላው አያጣም በዕድሉ ነው የሚያድገው ወይም የራሱን እድል ይዞ ነው የሚወለድው የሚል አነጋገርም በማህበረሰባችን ውስጥ በብዛት የሚንፀባረቅ ነው። በእርግጥ ይሄ ነገር በእድል፣ በምትሀትና በተአምራት ከሚያምን ባህላዊ የሆነ ማህበረሰብ የሚጠበቅ ነገር ነው። ባህላችንንም፣ ሃይማኖታችንንም አንድ ቤተሰብ ብዙ ልጆች እንዲኖሩት የሚያበረታቱ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ሃይማኖት ወይም ብሄር ታሳቢ ያደረጉ ብዙ ነን ለማለት ታስቦ ያለገደብ የመውለድ ነገርም አለ። ነገር ግን “ብዙ ተባዙ ምድርን ሙላት” ተብሎ የተነገረው የዓለም ህዝብ በጣም ትንሽ በነበረበት ዘመን ነው፤ አሁን ዓለም በህዝብ ብዛት ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቷል። በተለይ በእኛ ሀገር በየመንደሩ እየተፈለፈሉ ያሉት ህፃናት ነገ ስራና ቤት ይቅርና የእግር መርገጫም ለማግኘታቸው እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻለም። ስለዚህ ይሄ ከኢኮኖሚው ጋር ያልተመጣጠነ ውልደት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ ብዙ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት አንድ መላ ሊበጅለት ነው የሚገባው።
የህዝቡ ቁጥር እድገትና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ሊመጣጠንና ሊመጋገብ ካልቻለ ሄዶ ሄዶ አንድ ቀን ሊፈነዳ የሚችል ችግር ማስከተሉ አይቀርም። በሌላ በእኩል ካየነው ደግሞ የተመጣጠነ የህዝብ ቁጥር ሲኖር ዜጎች ጥራት ያለው ህይወት እንዲኖሩ፣ ጥራት ያለው ትምህርትና እውቀት እንዲያገኙ፣ ህክምናና ሌሎች አገልግሎቶች በአግባቡ እንዲዳረስ ማድረግ ይቻላል። የህዝብ ምጣኔው በአግባቡ መቆጣጠር ስንችል የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትም እንደዚሁ በአግባቡ መቆጣጣር እንችላልን። ስለዚህ የህዝብ እድገት ምጣኔ ቁጥጥር እንዲኖረው ማድርግና በአዋጅ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን መረባረብ ያስፈልጋል ማለት ነው።
3. የስራ ባህላችንን እና የጊዜ አጠቃቀማችን ማሻሻል:-
ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያውን ጠንካራ የስራ ባህል ካላቸው ህዝቦች ጋር ስንነፃፀር እጅግ በጣም ደካማ ሊባል የሚችል ነው። በውጭ ሀገር ሄደን ጥንክረን እንሰራ እንደሆነ እንጂ በሀገራችን ያለን የስራ ተነሳሽነትና ታታሪነት ያን ያህል አይደለም። በዚህ ላይ ስራ የመናቅ ነገርም አለ። ወደ ውጭ ሄደን የምንሰራውን ስራ እዚህ በሀገራችን ለመስራት ብዙም ዝግጁ አይደለንም። እንደእኔ እምነት ከሆነ ተገቢውን ክፍያ እስከተከፈለን ድረስ ማንኛውም ዓይነት ስራ ለመስራት የትም ቦታ ቢሆን ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። በተለይ በሀገራችን ውስጥ ብንሰራ ችግር የለውም። በዚህ በእኛ ሀገር ያለው ተቀጣሪ ሰራተኛ በተለይ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ሰዓት እና ቀን እየቆረ የሚያለምጥ ይበዛል። መሆን የነበረበት ግን ስራውን ላይ ነው የበለጠ ማትኮር የነበረበት። እድሜ ለቻይኖች የስራ ባህላችን ምን ያህል ዝቅተኛና እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን አሳይተውናል። ስለዚህ በውጭ ሀገር ሄደን ከምንዋረድ እዚህ በሀገራችን ሰርተን መኖር፤ እንዲያልፍልንም ጠንክረን መስራት ይገባናል።
የጊዜ አጠቃቀማችንማ እጅግ በጣም አስቂኝም አሳፋሪም ነው። በሀገራችን ጊዜ ማለት ገንዘብ፣ ጊዜ ማለት ዕድል መሆኑ የተገለፀለት ሰው በጣም ጥቂት ነው። አንዳንዶቹ በግጥምም በዝርውም ደህና አድርገው እንደገለፁት ጊዜ እዚህ ሀገር ሞልቶ የተትረፈረፈበት ነው። ቀጠሮ እንኳ ስንሰጣጥ ነገ እንገናኝ ወይም ሳምንት እንገናኝ ነው የምንባባለው። ሆድ ግን እንደዚህ አይደለም፤ ቀጠሮ አክባሪ ነው፤ በሰዓቱ ልክ ነው ምግብ የሚጠይቅህ፤ ሌላውም ነገር እንደዚያ ነው። ስለዚህ አንዱ ማድረግ ያለብን መሰረታዊ ነገር የጊዜ አጠቃቀማችንን በተገቢው ሁኔታ ማሻሻል ነው።
4. እንደ ህዝብ በሁሉም ነገር ራስን መቻል:-
አንዱ ቁልፍ ችግራችን በብዙ ነገር ላይ ጥገኛ መሆናችን ላይ ነው። ከእንጀራ በስተቀር ጥገኛ ያልሆንበት ነገር አይገኝም። አንድ ሰው በተለይ በከተማ የሚኖር ወስደን ብናየው ከገላው በስተቀር ምንም ኢትዮጵያዊ ነው የሚያስብለው ነገር የለውም። የለበሳቸው ልብሶች አንድ ባንድ ቢታዩ ሸሚዙ የቱርክ፣ ጃኬቱ የቻይና፣ ሱሬው የህንድ፤ ጫማው የኢጣሊያ፣ ካልሲውም እንደዚሁ የሌላ የውጭ ሀገር ነው የሚሆነው። እነዚህ ሀገሮች ንብረታችንን መልስ እና ገንዘብህን ውሰድ ቢሉት ያ ሰው እርቃኑ ነው የሚቀረው። ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ግን እንደዚያ አልነበርንም። ልብሳችን የራሳችን እዚህ ሀገር የተሰራ፤ ጦሩና ጋሻችን እዚህ ሀገር የተሰራ ሁሉም ነገራችን እዚህ ሀገር የተሰራ ነበር። ታላቁ ንጉስ አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ለማድረግ ሲያስቡ ይህን ራስን በራስ የመቻል ባሀል መሰረት ባደረገ መልኩ ነበር። መድፍና መሳርያ ላኩልኝ አላሉም፤ መድፍ እና ጥይት ሊሰሩ የሚችሉ ባለሞያዎች ላኩልኝ ነው ያሉት። ያ ትልቅ እድል ተሰናከለ፤ አልተሳካም። ነገር ግን ከእርሳቸው በኋላ የመጡ ነገስታት ይሄን መንገድ ቢከተሉ ኖሮ አሁን በምንገኝበት አረንቋ ውስጥ አንገባም ነበር። በአፄ ሚኒልክ ጊዜ ተመልሰው ወደ ግዛቲቱ እንዲቀላቀሉ በተደረጉት የደቡብ፣ የምስራቅና የምዕራብ አከባቢዎች ብዙ ሀብት እንዲገኝ ምክንያት ስለሆኑ በዚያ ሀብት የተፈለገውን ነገር ሁሉ የጦር መሳርያምው ሌላውም ከውጭ ማስመጣት ተጀመረ። ቀስ በቀስ እኛ የውጭ ርካሽ እቃ ማራገፊያ ሆንን፤ ለማይረባ ብልጭልጭ ነገር ሁሉ በወርቃችን፣ በቡናችን እና በሌሎች ውድ ነገሮቻችን ሁሉ መለውጥ ጀመርን። በዚህም ምክንያት በሂደት ጥገኛ ሆን ቀረን። እስኪ አስቡት ለዘጠና ሚልዮን የሚሆን ህዝብ ልብስ እዚሁ በሀገራችን ማምረት ብንችል! ምን ያህል የስራ እድል እንደሚፈጠር፤ ምን ያህል የውጭ ምንዛሬ እንደምናድን አስቡት! ለቤት የሚያስፈልጉን ቁሳቁሶች ሁሉ እዚህ ሀገር ማምረት ብንችል ስንት ነገር በቀነሰልን! ለወደብና ለማጓጓዣ የምናውጣው ገንዘብምን ያሀል ነው! የሚባክነው የሀገር ሀብትና ጊዜ ቀላል ነገር ነው እንዴ።
ሌላው ቀርቶ ፖሊስ እኛ የሚደበድብን እኮ ከከሌላ ሀገር በውጭ ምንዛሬ በተገዛ ዱላ ነው። ዱላ እንኳ መስራት አቅረቶን ነው! ጥርስ መጎርጎሪያ እስቲክኒ ሳይቀር ከውጭ እናስመጣለን! በመርፌ አቅም እንኳ ከውጭ ነው የምናስመጣው፤ “መርፌ ትሰራለህ?!” የሚለው ግጥም የማን ነበረ! ኢትዮጵያዊ ባህላችን ስራን የሚያናንቅ፤ ወሬንና አውደዳይነትን ነው። በድሮ ጊዜማ አርሶ ጥሮ ግሮ ከመኖር ይልቅ የአንዱን ባላባት አሽከር ሆኖ ማገልገልን የሚያኮራ ስራ ነበር። ይሄ ለዘመናት የዘለቀው ኋላቀር አስተሳሰብ አስተኝቶን ኖረ፤ በመጨረሻ በዚሁ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ዓይናችን ገልጠን ብንመለከት እንስቶቻን የዓረብ መጫወቻ፤ የዘመናዊ ባርነት ሰለባ ሆነው ነው ያገኘናቸው። ኢትዮጵያዊ በህግ ወጥ ደላች ኩላሊቱ እየተዘረፈ ወደ ባህር እየተጣለ፤ የአሳ ነባሪ ሲሳይ እየሆነ ያለው፤ ሬሳው በየአሸዋው እየተቀበረ ያለው በምን ምክንያት ነው ብሎ መጠየቅና ስለመፍትሄው በደንብ ማሳብ የሚያስፈልገው ነው።
5. ብቁ ሞያና እውቀት ያለን ዜጎች ሆኖ መገኘትያለው ህዝብ መሆን:-
ወደ ውጭ በተለይ ወደ አረብ ሀገራት የምንልካቸው ወይም በራሳቸው መንገድ የሚሄዱ ዜጎች አብዛኞቹ ምንም ዓይነት ሞያ ወይም ስልጠና ያልወሰዱ ናቸው። አይደለም ለውጭ ዜጎች እዚህ በከተማ ለሚኖረው ህብረተሰብም የሚመጥን የቤት ሰራተኝነት ሞያ የሌላቸው በጣም ይበዛሉ። አንዳንድ ጊዜ ዘመናዊ ሽንት ቤት እንኳ በአግባቡ መጠየቅ የማይችሉ የቤት ሰራተኞች ሁሉ የሚሄዱበት ጊዜ አለ፤ እንዴት ነው እንዲህ ሆነው የሄዱ ዜጎች መብታቸውን ማስከበርና ተገቢውን ስራ መስራት የሚችሉት! እንደ ሀገርም እኮ ውርደት የሚያስከትል ነው። ቢያንስ መሰረታዊ የሆነ ሞያ፣ እውቀትና ቋንቋ እንዲኖራቸው ተደርጎ ቢላኩ እኮ ለራሳቸውም፣ በሀገርም ጥሩ በሆነ ነበር። እዚህ በሀገራችንስ ቢሆን ዘጠና ሚልዮን የሚሆን ህዝብ ይዘን ከቻይናና ከሌሎች ሀገሮች በውድ ዋጋ ያውም በውጭ ምንዛሬ እየከፈልን ባለሞያ መቅጠር ነበረብን እንዴ! የራሳቸን የሆኑ ብቁ ባለሞያዎች ቢኖሩን እኮ እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች እዚህ ድረስ መጥተው አይሰሩም ነበር። እንዲያውም የእኛ ባለሞያዎች በሌሎች ሀገሮችም ጭምር በደህና ዋጋ ተቀጥረው በሰሩ ነበር። ራሳቸውን ጠቅመው ሀገራቸውም በጠቀሙ ነበር። ስለዚህ እንደመንግስትም፣ እንደሀገርም ያለንን ዜጋ በቻልነው መንገድ ሁሉ በሁሉም የሞያ መስኮች በቂ ሞያና ክህሎት እንዲኖረው ለማድረግ መረባረብ ነው የሚያስፈልገው።
6. እንደ ህዝብ በጋራ ማሰብ እና መንቀሳቀስ:-
በአጋጣሚም ይሁን በዕድል የተለያዩ ቋንቋዎች የምንናገር፤ የተለያየ እምነትና ባሀል ያለን ህዝቦች ሆነን አንድ ህዝብ ሆነን በአንድ ሀገር ጥላ ስር ነው የምንገኘው። ብዙ የማይመቹን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ነገር ግን ከመለያየትና እርስ በእርስ ከመጣላት በጋራ ቁጭ ብለን መመካከርና ያሉትን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉበትን የጋራ አቅጣጫ አስቀምጦ የተሻለ የጋራ ሀገር እንዲኖረን መስራትና መታገል ነው ያለብን። በአንድ ሀገር የሚኖሩ ህዝቦች በአንድ ቤት ውሰጥ እንደሚኖሩ ቤተሰቦች ናቸው። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ መግባባት ከሌለ፤ አንዱ ላንዱ የማይቆረቆር ከሆነ ያ ቤተሰብ ቤተሰብ አይሆንም፤ ያ ቤትም ጤነኛ ቤት ሊሆን አይችልም። ስለዚህ እንደ ሀገር መነጋገርና የጋራ መግባባት መፍጠር የግድ ያስፈልገናል።
እንደ ህዝብም የጋራ ራዕይ እና ግብ ሊኖረን ይገባል። ያን ራዕይና ግብ ለማሳከትም በአንድነት መንቀሳቀስና መተባባር አለብን። በዚህ መልኩ ከሄድን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ትልቅ ለውጥ አምጥተን አሁን ካለንበት የውርደት አሮንቋ ልንወጣ እንችላለን። የዛሬ አምሳ ዓመት የተመሰረተችው እስራኤል ምን ደረጃ ላይ እንዳለች እንመልከት! አንድ ከሆን፣ ከተባበርን እና ከተግባባን የፈለግነውን ዓይነት ህዝብ ለመሆን ምንም ሊያቀሞን የሚችል ኃይል ሊኖር አይችልም።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

(በዕንቁ መፅሔት ወጥቶ የነበረ)

No comments:

Post a Comment